Monday, 07 November 2011 13:24

ወደ ራስ መመለስ፤ ወደ ሀገር መመለስ ነው

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

አዲስ እይታ ሲመጣ ተቀብሎ ከማገናዘብ ውጭ ምንም አማራጭ የለኝም፡ በተለይ ደግሞ ይህ እይታ ከዚህ በፊት ግራ የሚያጋቡ የተበሰጣጠሩ የአስተሳሰብ እንቆቆልሾችን በሙሉ የሚፈታ ከሆነ አለመቀበል ያስቸግራል፡፡ ...ስለ “ሀገር” ሁላችንም ሁሌ እናወራለን፡አገሬን እንላለን፣ አገሬ ገብቼ፣ ሀገሬን አይቼ፣ ለሀገሬ ሰርቼ፣ ሀገሬን አሳድጌ፣ የሀገሬን ባህል ለአለም አስተዋውቄ፣ የሀገሬን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጌ፣ ሀገሬን ከወራሪ ጠላት መክቼ፣ ለሀገራቸው ደማቸውን አፍስሰው… አጥንታቸውን ከስክሰው፣ የሀገሬ ልጆች፣ የሀገሬ ታሪክ፣ ሀገሬ… ሀገሬ… ሀገሬ…፡፡

ያገኘሁት አዲስ እይታ “ሀገር ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ የተለየ መልስ ነው፡፡ ሀገር ያልሆነውን ነገር “ነው” በማለት መሞጋገሱ መሸነጋገሉ ያመጣው ውጤት በነዋሪዎቹ ሰዎች ላይ ተንፀባርቆ ይታያል፡፡ …ሀገሩን የሚወድ ሰው ሀገሩን ጥሎ ለስደት አይሄድም፡፡ …ሀገሩን የሚወድ ወደ ሀገሩ ይመለሳል እንጂ ከሀገሩ አይሰደድም፡ሀገሩን የሚወድ ራሱን የሚወድ ነው፡፡ ወደ ራስ መመለስ ወደ ሀገር መመለስ ነው፡፡ ሀገሩን ማሳደግ የሚፈልግ ሀገሩን በሙስና አይገድልም፡፡ ሀገሩን ሳያውቃት ቀርቶ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ሀገር ራሱ ነው፡፡
እናም እኔ የተረዳሁት፤ ሁላችንም በአንድ ቃል “ሀገር” እያልን የምንጠራው ነገር ለእያንዳንዳችን የሚሰጠን ትርጉም የተለያየ መሆኑን ነው፡፡ ስለ ባለ ሦስት ፊደሉ ቃል “ሀገር” ያለን እውቀት በጣም የተለያየ ነው፡፡ ቃሉ ከተለያየ እውቀታችን ወይንም እውነታችን ጋር ያለውን ቁርኝት ሳይሆን… ቅራኔውን ነው በሀገር ስም ስንጠራ የቆየነው፡ ይህ አገር የሚለው ቃል ትርጉም ከፈተታ… እንቆቅልሻችን እና ምናልባትም እንቆቅልሽነታችን ከተቋጠረበት ግራ መጋባት ይፈታል፡፡ አሊያም ይቆረጣል፡፡ ይህም የእኔ እምነት ነው፡፡
የምናወራውን ቃል ማንነት ከምንነቱ ነጣጥለን መገንዘብ ግዴታ ይሆናል፡፡ ተጨባጩን ነገር ከግላዊ ስሜት እና እምነታችን ጋር አንድ እንደሆነ አድርጐ ባለመግባባት ተግባብቶ መቀጠሉን ማለቴ ነው፡፡
ሀገር በራሱ (In itself) ያለው ፍቺ የመልከአ ምድር ጥርቅም ነው፡፡ የወንዝ የተራራ የሜዳ እና የሸለቆ… እና በመልክአ ምድሩ ላይ በቅለው የሚገኙ ነገሮች የሚሰጡት ጥርቅም ውጤት ነው፡፡ ይህ በራሱ እንደራሱ ያለው ፍቺ ነው፡፡ …ግን በራሱ እንደራሱ ያለው የትርጉም ማንነት እኛ እያንዳንዳችንን ሰዎች የማይመለከተን ከሆነ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ …የማርስ ፕላኔትን እንደ ሀገር የማንቆጥራት ምንም የጥቅምም ሆነ የስሜት ቁርኝት ከማንነቷ ጋር ስለማንጋራ ይመስለኛል፡፡ (ከመሰለኝ ደግሞ…)
“ኢትዮጵያ” ብለን ከምንጠራው የመሬት አንድ ውስን ገፅታ ጋር የጥቅም ግንኙነት አለን፡ የጥቅም ግንኙነት የፈለገው ያህል በውሸት ልንጀቡነው ብንጥርም ቀጥታ ነው፡፡ እኛ ከመሬቷ ላይ ተጠቃሚ መሬቷ ደግሞ እኛን ጠቃሚ ናት፡ ግን ለዘለቄታ እንድትሆነኝ መንከባከብ ግን አለብኝ የሀገሬን መሬት ከወራሪ ጠላት መከላከል፤ የራሴን የመኖሪያ፣ የመጠቀሚያ መሬት መከላከል ነው፡፡ ጠላትም ማለት በጥቅሜ ላይ የመጣ ነው፡በግልፅ ርቀት ሊፈተሽ የሚችል እውነት የተናገርኩ መሰለኝ!
ጥቅም ለጋራ ቢመስልም ወደ አንድ ሰው ደረጃ ሲወርድ ጥቅም የግለሰብ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገር የጋራ ሊሆን አይችልም፡፡ የመጨረሻው መስመር የእኔና የቦታው ግንኙነት ነው፡፡ ከሀገር ይበልጥ ቤቴ ይቀርበኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ሴቶች በፊት ሚስቴ፡፡ ከሀገሬ ልጆች በፊት የራሴ ልጆች… ወዘተ፡፡
አፄ ምኒሊክ የተናገሩት ንግግር ከሌሎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች የበለጠ ይመስጠኛል፡፡ ውስጤ እንዲያድር እና እውነትነቱ እንዲጠነክር ሆኗል፡፡ “ኢትዮጵያ ሀገርህ ሚስትህ ናት… ልጅህ ናት… ሀይማኖትህ ናት…”… ንጉሱ የፈጠሩት ቁርኝት ወደ ግለሰብ ደረጃ በመውረዱ ምክንያት፤ ሀገሩ እና ዜጋው የጠበቀ ግኝኙነት አላቸው ብሎ እንዲሰማው ያስገድደዋል፡፡ እኔ ላልኖርኩበት ዘመን እና ጦርነት እንኳን በዚህ የበሰለ ንግግራቸው እንዲመለከተኝ እና እንድሳተፍ ሆኛለሁ፡፡
እኔ የምወዳቸው ነገሮች ሁሉ ሀገሬን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ሀገሬን ቦታው ከሚፈጥርብኝ ስሜት መመልከት አልችልም፡፡ ሀገሬ ላይ የምወዳቸው ነገሮች ከማዳምጠው ሙዚቃ፣ ከምቀርባቸው ሰዎች፣ ካጋጠሙኝ ትዝታዎች፣ እንዲገጥሙኝ ከምፈልጋቸው ተስፋዎች… ነጥዬ ልገነዘበው አልፈልግም፡፡ አልችልምም፡፡ አንዳንዴ፤ መጥፎዎቹ ትዝታዎች ከጥሩዎቹ ጋር በቅርብ ርቀት እና ሁኔታ በመበየዳቸው፣ መጥፎውን ነገር እንደ ጥሩ አድርጌ ማስታወሴ አይቀርም፡፡ ስህተቱን ከጥሩው ቀይጦ እንዲቀመጥ እና የደም ዑደት ውስጥ በጊዜ አስገብቶ እንደመደባለቅ፡ …ስለዚህ በዚሁ እይታ የተለያዩ ሰዎች ላይ የተፈጠረው የሀገር ስሜት፣ እውቀት፣ እና እውነታ… በጣም የተለያየ ይሆናል፡፡
ስለ አንድ ሀገር እያወራን የምንኖረው ግን የተለያየ ሊሆንብን ይችላል፡፡ ለማሳደግ፣ ለመግለፅ የምንሞክረው ሀገር በእውነታው ላይ ያለውን አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከ11-15 ፐርሰንት ለማሳደግ በሚሞክሩት ሀገር የምንመራው ህዝቦች እየኖርንበት ያለው አይደለም፡፡ እኛ ተርበናል ስንል “ደርቃችሁ ይሆናል እንጂ አልተራባችሁም” የሚል አለመግባባት የተፈጠረው፤ በዚህ ምክንያት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
…እይታዬን ታዋቂ ግለሰቦች ላይ መሞከር አለብኝ፡፡ ስህተት ብሰራም በግለሰቦች አመራረጤ ላይ እንጂ በእይታዬ ምክንያት አለመሆኑን ልመንበት፡፡
ሼክ አላሙዲ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ስሜት እኔ ወይንም በዚህ ዘመን ላይ ያለ አንድ ወጣት ካለው ስሜት በጣም የተለየ መሆኑ አይቀርም፡ …ሼክ አላሙዲ ሀገራቸውን ለመርዳት ሲመጡ የሚረዱዋት ሀገር ስሜት እና ትዝታ… የዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ፣ የነሚኒሊክ ወስናቸው፣ የነመሀሙድ አህመድ… ዘፈንን አብሮ ያካተተ ነው፡ የሀገራቸው ስሜት ወይንም ሀገር የሚለው ፅንሰ ሀሳብ የሚወዷቸውን በመጠበቅ የሚጠሉዋቸውን የሀገሪቱን ገፅታ በመዋጋት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ጥያቄ ልጠይቅ፡- የሚወዷቸው ነገሮች ከትዝታቸው ላይ ቢጠፉ ሀገሪቱን መውደዳቸውን ይቀጥላሉ?… ዘፋኞቹ እና ዘፈናቸው ድንገት ቢደመሰስ ሀገር ተደመሰሰ ማለት ነው፤ ለባለ ትዝታው፡፡ …ከቦታው ጋር ያለው ቁርኝት የግለሰቡን መንፈስ ይቀርፀዋል፡፡ …ለጋሽ አቤሴሎም ይደጐ ኢትዮጵያ ማለት… አትሌቲክስ እና ጀግኖቿ ናቸው፡ የሀገር ዳር ድንበር የሚያስከብሩ ጀግኖች ጦር እና ጐራዴ የያዙ ሳይሆኑ ማራቶን፣ አስር ሺ፣ አምስት ሺ፣ ሜትር ሮጠው ወርቅ የሚያጠልቁ ናቸው፡፡ …ለጋሼ አቤሴሎም የአትሌቲክስ ድል ባይኖር ሀገር የለም፡፡ የጋሽ አቤሴሎም ሀገር አትኖርም፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ለማስተዳደር የሞከሩት ሀገር፣ የኢህአዴግ መንግስት እያስተዳደረ ካለው ቦታ ጋር አንድ ቢሆንም፤ ሀገሩ ግን የተለያየ ነው፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር በኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ተሰምቶ የማይታወቅ እድገት ለማስመዝገብ የሚሞክር ሲሆን፤ የአፄ ቴዎድሮስ ሀገር ኢትዮጵያ የምትባል ቦታን አንድ ለማድረግ በጉልበት የሚሞክር ነው፡፡ …የገብረክርስቶስ “ሀገሬ” የሚለው እምነቱ በግጥም አለም ላይ እንጂ በእውነታው ላይ የለም፡፡ የገብረ ክርስቶስ ሀገር በስደት የናፍቆት ትዝታ ጊዜ ብቻ ነብስ የምትዘራ ናት፡፡
ሀገር የሚፈጠረው ግለሰቡ ከቦታው ጋር ባለው ቁርኝት በሚፈጠር ስሜት፣ ምኞት፣ ራዕይ ትዝታ አማካኝነት ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የሚታያቸውን ሀገር፣ አፄ ሚኒሊክ አይታያቸውም፡፡ የጊዜና የቦታ… የአስተሳሰብ ልዩነት ሀገርን ይለውጣሉ፡፡
“ሀገር” የሚለው ጥቅል መንፈስ ሦስት አውታራዊ ቦታ (three D.space time) እና የእኔ የአእምሮ ትውውቅ መሀል የሚመሰረት ነው፡፡ እኔ ከሌለሁ ቦታው አይኖርም፤ የሀገር ፍቅር ስሜትም ግን አይወለድም፡፡ …እኔ ተወልጄ በቦታው ላይ እየኖርኩም ስለቦታው ያለኝ የትርጉም ፍቺ ከተለወጠ… ሀገሬ ተለውጦብኛል፡ድሮ ይፈጠርብኝ የነበረው ስሜት ከጠፋ ሀገሬ ጠፍቶብኛል፡፡ አዲስ ሀገር ያስፈልገኛል፡፡ አዲስ እይታ፡፡
ሀገር የሚለው ቃል በሶስት ፊደል ተጠቅልሎ ቢቀመጥም ሲነበብ የሚፈጥረው መረዳት ከላይ የተጠቀሱትን ቁርኝት (Association) ሁሉ ይወክላል፡፡ አብሮ አደጎቼ በሙሉ በስደት ርቀው በሄዱበት የአደግኩበት ሰፈር አልተሰደደም ለማለት አልችልም፡፡ ቃሉ በፊደል ሲፃፍ የሚፈጥርልን የቁርኝት መንፈስ የቃሉ ፊደል ቢለወጥ ቁርኝቱ ይላላል ወይንስ ይጠነክራል?… ወይንስ ምንም ለውጥ አይኖረውም? የሚል ጥያቄ በድንገት ተፈጠረብኝ፡፡
ለምሳሌ፡- “ሀገር” የሚለውን ቃል “ኋገር” ብዬ ብፅፈው፤ ስሜቱ የተለያየ ነው የሚሆነው፡፡ የምናውቀው የሀገር ስሜት መሆኑ ይለወጣል?
“ኢትዮጵያ” ብለን ስንፅፈው አሊያም ተፅፎ ስናነበው… የአበሻ ቀሚስ የለበሰች ደርባባ እመቤት አደይ አበባ መሀል ተቀምጣ በአይነ ህሊና እንደሚሳልብን አልጠራጠርም፡፡ እንደምንወዳት፣ እንደምንሳሳላት… አያጠያይቅም፡፡ …ኢትዮጵያ፤ የሚለው ቃል፤ እና እቺ ባለ ጥበብ ሴት… አንድ ቁርኝት እንዳላቸው ተቀብለናል፡፡ የተቀበልነው ተዋህዶናል፡፡ ሰአሊዎች በስዕላቸው፣ ገጣሚዎች በስንኛቸው… የሴቲቱ ምስል እና “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል ትርጉም ሲያስተሳስሩ ነው የኖሩት፡፡ …የሀገርን ትዝታ ከአመት በዓል ምግቦች እና መንፈስ ጋር ስናቆራኝ እንደኖርነው ማለቴ ነው፡፡
ስዕሉ ላይ አንድ አጭር ቀሚስ ያደረገች፣ ሊፒስቲክ የተቀባች፣ መንገድ ዳር ቆማ ሴትነቷን የምትሸጥ የሴተኛ አዳሪ ስዕል ስንመለከት፤ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ትዝ እንደማይለን ግልፅ ነው፡፡ እናቱ ሴተኛ አዳሪ የሆነች እና እናቱን እንደ መኖር ምክንያቱ የሚቆጥር ልጅ ግን የሴተኛ አዳሪዋን ምስል “ኢትዮጵያ” ብሎ ከሀገሩ ሊያስተሳስር ይችላል፡፡ ሀገርን አሰደብክ ተብሎ በንጉሱ ዘመን ቢሆን በአደባባይ ላንድሮቨር መኪና ላይ ቆሞ በገመድ ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡
እሺ ቃሉ፡- “ኢትዮጵያ” ዒትዮጵያ ተብሎ ቢፃፍስ… ከሀገሩ ጋር ያለን ቁርኝት ይላላል፡ “እግዚአብሔር” “ዕግዚዓብሔር” ተብሎ ቢፃፍ የዚህ ሀገር አምላክ መሆኑ ይቀየራል?… ወይንስ የተለያየ አገር ሰማይ ላይ የሚያዝ የተለየ አምላክ ይሆናል? ፊደል እንኳን ሲቀየር ቃሉ ትርጉም ያጣ የሚመስለን ሆነን ሳለ ባህሉ ወይንም አስተሳሰቡ ሲቀየር ሀገሩ እንዴት አንድ ሊመስለን ይችላል?
ሀገርም እንደዚሁ አይነት ቁርኝት (Association) ነው፡፡ ቁርኝቱ ከአንድ ሰው እና በአንድ ቦታ ላይ የሚፈጠር ነው፡፡ ቦታው ከሰውየው ጋር እንደሚፈጥረው የቁርኝት ትርጉም፣ ሀገር የሚባለው ፅንሰ ሀሳብ ይፈጠራል፡ የተለያየ የምርጫ አቅጣጫ፤ እውቀት እና የእድገት ደረጃ፣ እንደዚሁም አካባቢ ላይ ያሉ የተነጣጠሉ ግለሰቦች አንድ አይነት የሀገር ስሜት ግንዛቤ እና አረዳድ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ዘበትም ሆኖ አንድ ሀገር በአንድ መንፈስ ለመግለፅ እና ለመፍጠር ሲሞክር ቆይቷል፡አንዱ መንግስት የሚወርደው እና ሌላው በቦታው የሚተካው ሀገርን አልጠቀምክም በሚል ነው፡ ሀገር የግለሰቡ እይታ እና ትርጉም ቢሆንም እስካሁን የሁሉንም ግለሰብ ትርጉም ከቦታው ጋር በምክንያታዊ እይታ፤ ምርጫ፣ ነፃነት፣ እውቀት ሊያስተሳስር የቻለ የመንግስት አይን የለም፡፡ …እኔም ሀገሬ ላይ ሌሎቹም በሀገራቸው ላይ መኖራቸውን ቀጥለዋል፣ ይቀጥላሉ፡፡ በአንድ ሀገር ላይ እየኖርን እንደሆነ ለማስመሰል በእየመልከአ ምድሩ/ወንዙ፣ ተራራው፣ አለቱ እየተማማልን… እየተሸነጋገልን እንኖራለን፡፡ ሀገሩ ላይ ሁልጊዜ ረሀብ እና ድንቁርና ጠፍቶ የማያውቅ ሰው… የሀገሩን ፍቅር ስሜት ከረሀብ እና ድንቁርናው መኖር ጋር ቢያስተሳስር አይገርምምያስተሳሰረውን ነገር ካጣ አገሬን አጣሁ ማለቱ ያሰጋል፡፡ …ሀገሩን ለማጣትማ ነው በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰደደው፡፡ …ግን ተሰዶም ሀገሩ ይናፍቀዋል፡፡ ግጥም ይጽፋል… መቼ ነው ሀገሬ ተመልሼ የምገባው ይላል፡፡ …መልሶ ሞልቶለት ወደ ሀገሩ ሲገባ እሱ ራሱ ሌላ ሀገር ይዞ ወይንም ሆኖ ነው፡፡ …የሱ ኢትዮጵያ እና የሌላው፣ ለመግባባት “የዲያስፖራ” አስተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል፡ሀገር የግለሰብ እውነት እንጂ የህዝብ እምነት አይደለችም፡፡

 

Read 3235 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:28