Saturday, 23 March 2013 15:00

ጊዜው የማጅራት ገትር በሽታ የሚስፋፋበት ወቅት ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ አማካኝነት የመተላለፍ ባህርይ ያለው የማጅራት ገትር በሽታ፤ መጨባበጥን በመሳሰሉ ንኪኪዎችም ይተላለፋል፡፡ የማጅራት ገትር በሽታ ያለበት ሰው በሚስልበትና በሚያስነጥስበት ጊዜ አፉን መሸፈን፣ እጁን በውሃና በሳሙና መታጠብ ይኖርበታል፡፡ ጉሮሮን የሚከረክርና የሚያም ስሜት ሲኖር በሃኪም መታየት እንዲሁም ራስን ከከፍተኛ ፀሐይና ከነፋሻማ አየር መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሞቃትና ነፋሻ የአየር ሁኔታ የበሽታውን ስርጭት ያባብሳል በሽታው በወረርሽኝ መልክ በተለያዩ ቦታዎች ተከስቷል የጉሮሮ መድረቅና መሰነጣጠቅን ለመከላከል ፈሳሽ ይውሰዱ የህመሙ ምልክቶች ሲታዩ በፍጥነት ወደ ህክምና ይሂዱ በአዋሳ ከተማ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው የ26 ዓመቷ ወጣት፤ ከሦስት ወራት በኋላ የሠርግ በዓሏ እንዴት እንደሚደምቅ እያሰበች ስትዘጋጅ ነበር፡፡ የወዳጅ ዘመዶቿ መልካም ምኞት አልተለያትም፡፡ በግል ድርጅት ውስጥ በፀሐፊነት ለ3 ዓመታት ስትሰራ የቆየችው ወጣት፣ በስራ ባልደረቦቿ ዘንድ ተወዳጅ ነበረች - በትሁት ባህርይዋ፡፡ ከሠራተኞች ጋር በቀላሉ ተግባብታና ተስማምታ በፍቅር መስራት ትችልበታለች፡፡

ለነገ ለከነገ ወዲያ እያለች ሥራ ማጓተት አታውቅም፡፡ በየሰበቡ ከሥራ የመቅረት ወይም የማርፈድ ልምድ የላትም፡፡ ለዚህም ነው፤ አንድ ቀን እንደወትሮ ከስራ መግቢያ ሰአት ቀድማ አለመገኘቷ፣ ለብዙዎች አስገራሚ የሆነባቸው፡፡ ያን እለት ጤና አልተሰማትም፡፡ ቢሆንም ከስራ ለመቅረት አልፈለገችም፡፡ ድንገት የጀመራት የህመም ስሜት እየበረታባት ቢመጣም እጅ አልሰጠችም፡፡ ከከባድ የራስ ምታት ጋር፤ የማቅለሽለሽ ስሜት ይረብሻታል፡፡ ሄድ መጣ እያለ ያስመልሳታል፡፡ ቢሆንም ጨክኖ ከአልጋ አልጣላትም ነበር፡፡ ሰውነቷን የሚቆረጣጥማት ስሜት እየጠነከረ፣ የሰውነቷ ትኩሳት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ፣ ማጅራቷ አካባቢ የሚጨመድዳት ህመምም እየባሰባት ሲመጣ ግን ከአልጋ መነሳት አቃታት፡፡

የምትበላው ምግብ ስለማይረጋላት አቅሟ በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ በህመሟ የተጨነቁ ቤተሰቦቿ ወደ ሆስፒታል ይዘዋት ሄዱ፡፡ የበሽታ ወረርሽኝ ተከስቷል የሚል ወሬ ይናፈስ ስለነበር ቤተሰቦቿ መጨነቃቸው አይገርምም፡፡ የሆስፒታሉ የምርመራ ውጤት ደግሞ አስደነገጣቸው - ህመሟ የማኔንጃይትስ (የማጅራት ገትር) በሽታ ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻለኛል በሚል ወደ ሃኪም ቤት በፍጥነት ባለመሄዷ በሽታው እጅግ እንደጐዳት ምርመራውን ያደረጉላት የህክምና ባለሙያዎች ለቤተሰቦቿ ነግረዋቸዋል፡፡ መድሃኒት እንድትጀምር የተደረገው ወዲያውኑ ነበር፡፡ የሰናይት የጤንነት ሁኔታ ግን አልተሻሻለም፡፡

ለሰዓታት ራሷን ስታ ትቆይና እንደመንቃት ስትል በላብ ትዘፈቃለች፡፡ ትኩሳቷ እንደ እሳት ይፋጃል፡፡ በማንኪያ አፏ ላይ እየተደረገላት የምትውጠው ውሃ ካልወጣሁ እያለ ይተናነቃታል፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ ስቃይዋን ለማስታገስና ጤናዋን ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ተስፋዋ እንደተመናመነ ሲረዱም ወደቤቷ ወስደው እንዲያስታምሟት ለቤተሰቦቿ ነግረው ከሃኪም ቤቱ አስወጧት፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ህይወቷ አለፈ፡፡ ለሰርጓ ስትዘጋጅ የቆየችውና በባህሪዋ ተወዳጅ የነበረችው ወጣት በጥቂት ቀናት ህመም ስትሞት በእጅጉ ያዘኑ የአካባቢዋ ነዋሪዎች፤ ህመሟ የማጅራት ገትር እንደሆነ ሲሰሙ ደግሞ ተረበሹ፡፡

በሽታውን የሚከላከል ክትባት ለማግኘት ይራወጡ ገቡ፡፡ ክትባቱ በቅድሚያ ለዩንቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለጤና ባለሙያዎችና ለት/ቤቶች እንዲዳረስ ቢደረግም፤ የኋላ ኋላ ነዋሪዎቹም ተከትበዋል፡፡ ከወር በፊት በደቡብ ክልል በተለይ በአርባምንጭ አካባቢ መቶ ሰዎች በማጅራት ገትር በሽታ መጠቃታቸው ከተነገረ ወዲህ፤ ወደ ሌሎች በርካታ ቦታዎችም ተዛምቶ በሸበዲኖ እና በአዋሳ አካባቢዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ወረርሽኝ እስከመሆን ደረጃ ደርሷል፡፡ በርካታ ሰዎችንም ለሞት እንዲሁም በርካቶችን ለአካልና ለአዕምሮ ጉዳት ዳርጓል፡፡ የማጅራት ገትር በሽታ የአንጐልና የህብለሰረሰር ሽፋን የሆነውና ስስ አካል (Meninges) በማጥቃት ከፍተኛ ስቃይና ጉዳትን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው፡፡

በሽታው በዓይን ሊታዩ በማይችሉ ተህዋሲያን (በባክቴሪያ) የሚፈጠር ሲሆን፣ ከ2 እስከ 30 አመት እድሜ የሆናቸው ሰዎች ለበሽታው በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በምድር ወገብ አካባቢ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ባሉት አገራት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚሰተው የማጅራት ገትር በሽታ፣ በአንድ መንደር በሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ከአምስት በበለጡ ሰዎች ላይ ከታየ በወረርሽኝ መልኩ ተከስቷል ይባላል፡፡ ካለፈው ወር መግቢያ ጀምሮ በአርባምንጭና በአዋሳ አካባቢዎች በወረርሽኝ መልክ ስለተከሰተም ነው፤ ክትባት መሰጠት ያስፈለገው፡፡ በሽታው በባክቴሪያ እንጂ በአየር ሁኔታ ሳቢያ የሚከሰት ባይሆንም፤ ሞቃታማ፣ ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ለበሽታው መዛመት አመቺ ነው፡፡ በፀሐያማና ሞቃት የአየር ፀባይ ሳቢያ የጉሮሮ ክፍሎች ሲደርቁና ሲሰነጣጠቁ፤ የበሽታው አምጪ ተህዋሲያን በቀላሉ ወደ ሰውነታችን ገብተው የመባዛት እድል ያገኛሉ፡፡

ለብዙ ሰዓታት በከፍተኛ ፀሐይና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ውስጥ ከመቆየት መቆጠብ በሽታውን ለመከላከል ይረዳል፡፡ የማጅራት ገትር በሽታ (ማኔንጃይትስ) በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል፡፡ ከስያሜዎቹ መካከል፣ ማጅራት ቆልምም፣ የጋንጃ በሽታና ሞኝ ባገኝ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በአዲስ ህይወት ሆስፒታል፣ የውስጥ ደዌ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ዳዊት አማረ ስለማጅራት ገትር በሽታ ሲናገሩ፣ በፍጥነት ህክምና ካልተገኘ በሽታው ለሞት ይዳርጋል፤ አልያም የተለያዩ የጭንቅላት ክፍሎችን በማጥቃት ሊጠገኑ የማይችሉ ጉዳቶችን ያስከትላል ብለዋል፡፡

የጆሮ አለመስማት፣ የዓይን አለማየትና የአካል አለመታዘዝ ችግር ሊከሰት ይችላል በማለትም ምሳሌዎችን ጠቅሰዋል፡፡ የማጅራት ገትር በሽታ የተለያዩ ምልክቶች እንዳሉት የሚናገሩት ዶ/ር ዳዊት፣ ትኩሳትና ሰውነትን የመቆረጣጠም ስሜት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ ማስመለስ፣ የጀርባ ህመም፣ የማጅራት አካባቢ ህመም፣ የመዛል ስሜት እንዲሁም ራስን መሳት ዋነኞቹ ምልክቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ምልክቶች የታዩበትን ህመምተኛ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ነው ትልቁ ቁምነገር፡፡ ህመምተኞች አፋጣኝ ህክምና ካገኙ 96 በመቶ ያህሉ የመዳን እድል እንዳላቸው ዶ/ር ዳዊት ገልፀዋል፡፡ ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ አማካኝነት የመተላለፍ ባህርይ ያለው የማጅራት ገትር በሽታ፤ መጨባበጥን በመሳሰሉ ንኪኪዎችም ይተላለፋል፡፡

የማጅራት ገትር በሽታ ያለበት ሰው በሚስልበትና በሚያስነጥስበት ጊዜ አፉን መሸፈን፣ እጁን በውሃና በሳሙና መታጠብ ይኖርበታል፡፡ ጉሮሮን የሚከረክርና የሚያም ስሜት ሲኖር በሃኪም መታየት እንዲሁም ራስን ከከፍተኛ ፀሐይና ከነፋሻማ አየር መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች እንደሆኑ ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል የተባለውን የማጅራት ገትር በሽታ አስመልክቶ ፈጣንና ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ቢቆጠብም፤ በቅርቡ ጠቅለል ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በሽታው በአገሪቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ምን ያህል ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና እንደሞቱ መግለጫው አይዘረዝርም፡፡ ነገር ግን በሽታው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች መከሰቱንና የህሙማኑ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በሽታው ተከሰተ በተባለባቸው አካባቢዎች ላይ በተደረገ ርብርብ የበሽታው ስርጭት መቀነሱንና እንዳይዛመት እየተከላከለ መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ምናልባት የበሽታው ስርጭት እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ በሚልም የምርመራ፣ የህክምናና የክትባት ግብአቶችን እንዳዘጋጀ አመልክቷል፡፡ ለሞቃታማና ለደረቅ የአየር ፀባይ በብዛት አለመጋለጥ፤ የጉሮሮ መሰነጣጠቅና መድረቅ ሲያጋጥምም ጉሮሮን በፈሳሽ ማርጠብ፣ መጉመጥመጥና በቂ ፈሳሽ መውሰድ በሽታውን ለመከላከል እንደሚረዳ ሚኒስቴሩ መክሯል፡፡ ስለ በሽታውና ስለ ታማሚዎች ቁጥርም ሰሞኑን ዝርዝር መረጃ እሰጣለሁ ብሏል፡፡

Read 8080 times