Monday, 25 March 2013 11:13

ቺንዋ አቼቤ አረፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከአፍሪካ ታላቅ ደራሲዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው ናይጄርያዊው ቺንዋ አቼቤ በ82 ዓመቱ ትናንት በአሜሪካዋ ማሳቹሴትስ ከተማ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ አልበርት ቺኒዋ ሉሞጉ አቼቤ ከልቦለድ ስራዎቹ ባሻገር በገጣሚነትና በሃያሲነቱ የሚታወቅ ፕሮፌሰር ነበር፡፡

በ1960ዎቹ ስላለፈበት የቢያፍራ ጦርነት ትውስታዎችና የህይወት መታሰቢያ ታሪኩን “There Was a Country: A Personal History of Biafra” በሚል ርእስ ለመጨረሻ ጊዜ አምና ለንባብ አብቅቷል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ አሳታሚ ኩባንያ ፔንጊውንስ ሞቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ደራሲውን “እጅግ ምርጥ ችሎታ ያለው ፀሃፊ እና የአፍሪካ ታላቅ የስነፅሁፍ ሰብእና” ሲል አሞካሽቶታል፡፡ በአገሩ በናይጄርያና በአለማቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው አቼቤ በልቦለድ ስራዎቹ በአፍሪካዊነት፤ በብሄርተኝነት፤ በፀረ ቅኝ ግዛት ጭብጦች ዙሪያ በመፃፍ ይታወቅ በነበር፡፡

ቺንዋ አቼቤ ስነፅሁፍ በመላው አህጉሪቱ እንዲስፋፋ፣ በተማሪዎች ዘንድ የልቦለድ ባህል እንዲፈጠርና ከፍተኛ የስነፅሁፍ እድገት እንዲቀጣጠል በተጫወተው ፈርቀዳጅ ሚና ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ በአሜሪካ ኮሌጆች ሲያስተምር ቆይቶ እኤአ በ1958 በፃፈው ‹ቲንግስ ፎል አፓርት› በተባለ የልቦለድ መፅሃፉ ከፍተኛ ዓለማቀፍ ዝና አትርፍዋል፡፡ መጽሐፉ በመላው ዓለም በ50 የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ 12 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሽጥዋል፡፡

የልቦለድ መፅሃፉ በበርካታ የአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች እንደ መማርያ መፅሃፍ ሊያገለግልም በቅቷል፡፡ አቼቤ የናይጄርያ የመንግስታትንና የባለስልጣናትን ድክመት በመተቸት እንዲሁም ሙስናን በይፋ በማጋለጥ፤ እንዲሁም በተለያዩ የህትመት ውጤቶች መጣጥፎችን በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡ አቼቤ ከ20 በላይ መፅሃፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን ከፃፋቸው ልቦለዶች መካከል ‹ኖ ሎንገር አት ኢዝ›፤ ‹አሮው ኦፍ ጎድ›፤ ‹ኤማን ኦፍ ዘ ፒፕል›፤ እና ‹አንትሂልስ ኦፍ ሳቫና› የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡

Read 3169 times Last modified on Monday, 25 March 2013 15:21