Print this page
Saturday, 30 March 2013 14:33

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(7 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ - ፲፩

ዛሬ ደግሞ ቦስተን ነኝ፡፡ በዚህ ከተማ የሚገኙ ዘመዶቼን ለመጠየቅ ካረፍኹበት የጓደኛዬ ቤት ወጥተን ባቡር ወደምንሳፈርበት ፌርማታ ጉዞ ጀምረናል፡፡ ለአየሩ ቈሪርነት (ቅዝቃዜ) መግለጫ አጥቼለታለኹ፡፡ እኔ የማውቀው ቅዝቃዜ (ብርድ) ሲያንቀጠቅጥ ነው፡፡ ይህኛው የአየር ኹኔታ ግን መተንፈስ እስኪሳነኝ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ አንዘፈዘፈኝ፡፡ ስነጋገር የምስበው ቀዝቃዛ አየር ወደ ውስጤ ገብቶ ከሆዴ ጀምሮ እስከ ጀርባዬ ስለተሰማኝ መነጋገር አቁሜ አፌን አፍኛለኹ፡፡ እጄን ከቅዝቃዜው ማስጣል ስላልቻልኹ የጣቶቼ መገጣጠሚያዎች እያየኋቸው መጥቆር ጀምረዋል፡፡ ጓደኛዬ የእጅ ጓንት እንዳጠልቅ ስላልመከረችኝ አሳዝኛታለኹ፡፡ የራሷን አውልቃ ልትሰጠኝ ብትጎተጉተኝም በጄ ሳልላት የሩጫ ያህል አረማመዴን አፍጥኜ መጓዜን ቀጥያለኹ፡፡

እንዳኮረፈ ሰው ተለጉሜ ታሕተ ምድር ወዳለው የባቡር መሳፈሪያ የሚወስደንን ደረጃ መውረድ ስንጀምር ቅዝቃዜው ትንሽ መቀነስ ጀመረ፡፡ ጓደኛዬ አርፍደናል በሚል ስጋት ባቡሩ እንዳያመልጠን ርምጃዋን ጨምራ ወደ ትኬት መቁረጫው ትጣደፋለች፡፡ እርሷ ቋሚ ተጠቃሚ ስለኾነች ለአንድ ወር ያህል በየትኛውም ባቡርና አውቶብስ ለመጠቀም የሚያስችል ትኬት አላት፡፡ ለእኔ የሚኾን ትኬት ለመቁረጥ ጥቂት ደቂቃዎችን ወሰደብን፡፡ ይለፉን አቋርጠን ገና ባቡሩ ጋራ ሳንደርስ ወደፊት የሚምዘገዘገውን የባቡሩን የኋለኛ ክፍል አየኹት - ባቡሩ አምልጦናል፡፡ መውረጃችንን ነግረናቸው ሊጠብቁን ለቀጠርኋቸው ዘመዶቼ ደውዬ ማርፈዳችንን መንገር እንዳለብኝ ጓደኛዬ በጠቆመችኝ መሠረት ደወልኹ፡፡

የሚቀበሉን ሰዎች ከቤታቸው ወደ ፌርማታው ለመድረስ የሚወስድባቸውን ሰዓት አስልተው አስቀድመው ወጥተዋል፡፡ ላስጠብቃቸው መኾኑን ስረዳ በቸልተኝነቴ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ፤ በሰዓቱ ተሰናድቼ ያልተገኘኹት እኔ ብቻ ነበርኹና፡፡ ጓደኛዬ አሜሪካ የገባችው በቅርብ ነው፡፡ በአንድ ትልቅ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከአሜሪካኖቹጋ የጥናትና ምርምር ሥር ስለምትሠራ እነሱኑ ኾናለች፡፡ አሜሪካኖቹ ለነገሮች የሚሰጡት ትኩረትና ጥንቃቄ አስቀድሞ በነገሩ ላይ ማቀድንና ባቀዱት መሠረት መመራትን ይጨምራል፡፡ ይህም አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ጀምሮ ሲያስደምመኝ የነበረ ተግባራቸው ነው፡፡ ለእነርሱ እንደዋዛ ወይም በአጋጣሚ የሚታለፍ ምንም ነገር የለም፡፡ ከአዲስ አበባ ከመነሣቴ በፊት እያንዳንዱ ዝርዝር መርሐ ግብር በጊዜ፣ በቀንና በቦታ ተለይቶ፤ ሰነድ ተዘጋጅቶለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተደርጎልኝ ነበር የተሸኘኹት፡፡

ዋሽንግተን ዲሲም ስደርስ ከአውሮፕላኑ መውጫ በር ላይ የተቀበሉኝ በጎ ፈቃደኞች ለቡድን መሪዎቹ ካስረከቡኝ በኋላ እንደ መጽሐፍ ተጠርዞ የተሰጠኝ ሰነድ÷ እግሬ ምድረ አሜሪካን ከረገጠበት ፕሮግራሙን አጠናቅቄ እስከምመለስበት ድረስ ከጠዋት እስከ ማታ የማከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት በደቂቃ ሳይቀር ተብራርቶ የተገለጸበት ነበር፡፡ ለሁለት ቀናት ‹‹ኸሪኬን ሳንዲ›› የሚል ስያሜ በተሰጠው ማዕበል የተቀላቀለበት አደገኛ አውሎ ነፋስ ከተስተጓጎለብን በቀር ቀሪው መርሐ ግብር አንዲት ደቂቃ ሳትዛነፍ በተሰጠን ዕቅድ መሠረት መፈጸሙ ደንቆኛል፡፡ ገለጻ ሲያደርጉም ‹‹ይህ ቀላል ነገር ነው፤ ሊታወቅ ይችላል›› በሚል ንቀው የሚተዉት ነገር የለም፡፡ እያንዳንዷ ነገር ከማብራሪያ ጋራ ትቀርባለች፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በተለይ ከአፍሪካ የሄድነው ጋዜጠኞች ላረፈድንባቸው ጥቂት ደቂቃዎችና ላሳየነው ቸልተኝነት ከቡድን መሪዎቹ ቆፍጠን ያለ ተግሣጽ ደርሶብናል፡፡

ከተግሣጹ በኋላ ማንኛችንም ለማርፈድ አልደፈንርም፡፡ ከተግሣጹ በላይ ግን ጆን እና ካረን የተባሉ ከስቴት ዲፓርትመንት የተመደቡልን ቡድን መሪዎች ለአንድ ወር ያህል አንድም ቀን ሳያዛንፉ እየቀደሙ ቁርስ ቦታ መገኘታቸው የተግባር አርኣያነት ያለው ነበር፡፡ በሰዓቱ ተነሥቶ ቁርስ ቦታ ለማይገኘው ባለመመገቡ የሚያዝንለት ወይም እስኪመገብ የሚጠብቀው የለም፡፡ ከተጻፈለት ሰዓት ሁለት ደቂቃ አሳልፎ ፌርማታ ጋራ የሚደርስ ሰው ምንም ነገር አያገኝም፡፡ በአውቶብሱ መነሻ የመጨረሻ ሰዓት ላይ መድረስም የጠዋት ገለጻ ለማድረግ ውስጥ ቆሞ ለሚጠብቀው የጆን ፊት ይዳርጋል፡፡ ከጆን ዐይነ መዓት ለመዳንና ከጊዜው በፊት ለመገኘት ባሳየነው ትጋት ሰዓት በማክበር የሚችለን ጠፍቶ ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ባለመታከት ማብራሪያ የሚሰጠው ጆን ሁሉም ነገር በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት መከናወኑን ከማረጋገጡ በፊት ፈገግታ አይታይበትም ነበር፡፡ በመጨረሻው ቀን ከፕሮግራሙ ስላገኘነው ጥቅም አስተያየት እንድንሰጥ ስንጠየቅ፣ ‹‹ከዚህም በኋላ ጠዋት፣ ጠዋት አየው የነበረውን የጆንን ኮስታራ ፊት እያስታወስኹ ሁሌም በጠዋት እነሣለኹ፤›› ማለቴ ጆን ፈገግ እንዲል አድርጎት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ የሄድኩበት መርሐ ግብር አልቆ በግል ጉብኝቴ ከሐበሻዋ ጓደኛዬ ጋራ ስገናኝ ግን የጆንን ‹ቀስቃሽ ፊት› ዘንግቼ አረፈድኹና ባቡር አመለጠኝ፡፡ ገና ከአዲስ አበባ ሳልነሣ ቦስተን ስደርስ ስለማከናውናቸው ነገሮች ጠይቃኝ ዕቅድ ላወጣችው ጓደኛዬ በዕቅዷ መሠረት ስላልተጓዝኹ ባቡር አምልጦን ቀጣዩ እስኪመጣ ቁጭ ብለን ለመጠበቅ ተገደን ነበር፡፡ በቆይታችን እነጆን ባስለመዱኝ የጊዜ አጠቃቀም ራሴን ለመግራት የደረስኹበትን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ስለ አሜሪካውያን አስቀድሞ ማቀድ ተጨዋወትን፡፡ በመሀል መምጫና መሄጃው የማይዛነፈው ባቡር በመድረሱ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፡፡

‹‹ቀደም ሲል እሠራበት በነበረው መሥሪያ ቤት ትሠራ የነበረች አንዲት አሜሪካዊት ጓደኛዬ ልመጣ ነው ብላ ኢ-ሜይል አድርጋልኛለች፤›› አለችኝ ፕሮግራም ሲያሲዙ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ እየነገረችኝ፡፡ አሜሪካዊት ጓደኛዋ ቀጠሮውን ያስያዘቻት ከስድስት ወር በፊት አስቀድማ ነው፤ ቀኑና ሰዓቱን በዝርዝር ለይታ ስታበቃ የት መገናኘት እንደሚችሉ እንድትነግራትና በዛን ጊዜ ነጻ መኾኗን እንድታሳውቃት ነበር ኢ - ሜይል የጻፈችላት፡፡ ዛሬ ላይ ኾነን ስለነገው ስንጠይቃት ‹‹የነገውን እግዜር ያውቃል›› ስትል መልስ ትሰጠን የነበረችውን እናቴን አስታወስኋት፡፡ ታዲያ ለእናቴ ስልክ ደውዬ የስድስት ወር ቀጠሮ አስቀድሞ ስለመያዝ የምትለውን መስማት አማረኝ፡፡ ብቻ በጥንቃቄና በዕቅድ መመራታቸውን ወድጄዋለሁ፡፡ ለነገሩ በኢ - ሜይል አይላላኩት እንጂ ‹‹ለሐምሌ አቦ እንገናኝ›› ሲሉ የዓመት ቀጠሮ የሚይዙ የአገር ቤት ሰዎች አሉ አይደል፡፡

************** እኔና ጓደኛዬ ከባቡር ስንወርድ የተቀበሉን ዘመዶቼ ወደሚኖሩበት አፓርትመንት ወስደው ለምሳ ግብዣ ካዘጋጁት የባህል ማዕድ ተሳትፈን የቡና ላይ ወግ ይዘናል፡፡ ቡናውን የምታፈላልን ደግሞ በዕድሜዋ አረጋዊ የኾነችውና የልጅ ልጅ ልጅ ያየችዋ የሐረሯ የአባቴ አክስት ወ/ሮ አበቡ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያውን በርከት ብለው በሚኖሩበት አካባቢ ነጠላቸውን አጣፍተውና ጋቢያቸውን ደርበው ቤተ ክርስቲያን ሲስሙ፣ በመኖሪያ ሕንጻዎች፣ በሬስቶራንቶችና በገበያ ቦታዎች ሲዘዋወሩ ካየኋቸው አረጋውያን እንደ አንዷ አድርጌ ቆጠርኳት፡፡ እንደ ጥጥ የነጣው ፀጉሯ አንቱታዋን ባያስደፍርም እኔ ግን ባለኝ የዝምድና ቅርበት ‹በአንቺ› ነው የምጠራት፡፡ ወ/ሮ አበቡ ቦስተን ከገባች ሰባት ዓመት ኾኗታል፡፡ ሦስቱም ልጆቿ እዚያው አሜሪካ ናቸው፡፡ ሁለቱ ሴቶች በአንድ ሕንጻ ላይ በየራሳቸው ቤት ይኖራሉ፡፡ ወንድ ልጇና የልጅ ልጆቿ ደግሞ ከነልጆቻቸው በሌላ ከተማ ናቸው፡፡

ወ/ሮ አበቡ÷ አገሩን ከመላመዷ የተነሣ በተለያየ መንገድ ከኢትዮጵያ የሚመጡ አረጋውያንን ማላመድ መጀመሯን ነገረችን፡፡ የወለዱ ልጆቻቸውን ለማረስ፣ ለሠርግ ወይም በተለያየ ምክንያት በሚደረግላቸው ጥሪ አሜሪካ ደርሰው የቀሩ ጓደኞችን አፍርታለች፡፡ አሜሪካ ገብተው ባልንጀራ ካደረገቻቸው በኋላ ተመልሰው ሲሄዱ ግን ትቀናለች፡፡ የትውልድ አገሯ ሐረር ይናፍቃታል፡፡ ጠዋት ተነሥታ የቆላችው ቡና ሲወቀጥ ሰምተው ‹‹እንደምን አደርሽ›› እያሉ የሚከቧት ቡና አጣጭ ጎረቤቶቿ ትዝ እያሏት የብሶት እንባ አውጥታ ታለቅሳለች፡፡ ልጆቿን ወደ አገሬ ሸኙኝ እያለች ትወተውታለች፡፡ ‹‹አሜሪካ ለአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አዛውንቶች ተመራጭ አይደለችም፤›› አለችኝ ጓደኛዬ፡፡ እርሷም ከዓመት በፊት እናቷ እንዲጎበኟት አምጥታቸው ነበር፡፡ ከአምስት ወር በላይ ግን ሊቆዩሏት አልፈቀዱም፡፡ እንዲያውም ወጣ ብለው ካፈሯቸው የዕድሜ እኩዮቻቸው ባገኙት መረጃ ‹‹ፓስፖርቴን አምጪ›› ሲሉ አሥቀዋታል፡፡ ወላጆቻቸው ጥለዋቸው እንዲሄዱ የማይፈልጉ ልጆች ፓስፖርት ይደብቃሉ ስለሚባል÷ ‹‹አልሸኝም ካልሽኝ ሰውም ቢሆን ለምኜ ይሸኙኛል፤ ፓስፖርቴን ግን አምጪ›› ማለታቸው ነበር፡፡

ይህን የሰማችው የወ/ሮ አበቡ ልጅ÷ ‹‹እሷም [ወ/ሮ አበቡ] እንዲህ ታስቸግረን ነበር፤ ደብቀንባት ነው እንጂ›› አለችን፡፡ ወ/ሮ አበቡ ጉልበቷ ብዙም ባለመድከሙ የቤት ውስጥ ሥራ ስትሠራ ጊዜው ይሄድላታል፤ በቅዝቃዜው ምክንያት ወደ መናፈሻ ቦታ ወጥታ ከጓደኞቿ ጋር ስለማትጫወት ቴሌቭዥኑ ሲሰለቻት ቀኑን ሙሉ ከመስኮቱ ላይ ተተክላ ከተማውን ስትቃኝ እንደምትውል ከብሶት ጋር አጫወተችን፡፡አገሯ፣ መንደሯ፣ ዕድሯ፣ ዘመዶቿ፣ ዛፍ ቅጠሉ እንደልብ ከቦታ ቦታ ማለቱ ሁሉን ስታስበው እንደሚናፍቃት የስንት ዘመዶቿን እና ጓደኞቿን መርዶ በሰው አገር መስማቷን እየነገረችን እንባዋን ዘረገፈችው፡፡ ‹‹አሁንማ አገሬ እገባለሁ›› ስትል ዛተች፡፡ ሁሉም ልጆቿ አሜሪካ ስለሚኖሩ እርሷ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ምን ትሠራለች በማለት ከሚያከላክሏት ልጆቿ መካከል አንዷ ነገሩን በቀልድ መልክ ወስዳው÷ ‹‹አሁን አንቺን ስላየች ነው፤›› አለችኝ፡፡

ወደ ጓደኛዬ ዞራም ‹‹አንቺም ቅድም እናቴ ትታኝ ሄደች አልሻት፤ እንግዲህ ሰሞኑን መቀመጫም የለን›› ስትል ስጋቷን እየሣቀች አካፈለችን፡፡ የአባቴ አክስት አሜሪካኖቹ ለአዛውንቶች በሚያደርጉት ክብካቤ ሳትደለል ልቧ ያለው ወደ አገሯ መመለስ ላይ ስለመኾኑ በሰበብ የወጣው ብሶቷ አሳብቆባታል፡፡ ለተደረገልን ግብዣ አመስግነን ስንወጣ ወ/ሮ አበቡ እንባዋን እየጠራረገች ልትሸኘን ተከትላን ወጣች፡፡ አሳንሰሩጋ እንደቆምን ጋቢ የተከናነቡ አዛውንት አገኘን፡፡ ስድስት ዓመት የሚኾናትን የልጅ ልጃቸውን አስከትለው ልጃቸውን አስቀድመው ቆመዋል፡፡ ወ/ሮ አበቡ ባልንጀራዋን አግኝታለችና ትከሻ ለትከሻ እየተሳሳመች ሰላምታ ተለዋወጠች፡፡ ‹‹ጓደኛዬን ተዋወቁ ስትልም›› አስተዋወቀችን፡፡

************ ባቡሩ በመጣንበት መንገድ እየመለሰን ነው፡፡ እኔና ጓደኛዬ ስለ አዛውንቶቹ የጀመርነውን ወሬ አልገታንም፡፡ አሜሪካኖቹ ለዜጎቻቸው በሚያደርጉት ጥንቃቄ የምትደነቀው ጓደኛዬ÷ ኢትዮጵያውያን አዛውንቶች ለአገሩ ያን ያህል የኾኑት በአገራቸው የተሳሰሩበትን ማኅበራዊ ኑሮ ስለማያገኙት ነው፡፡ ኾኖም አሜሪካኖቹ ለዜጎቻቸው ከሚያደርጉት ጥንቃቄ አንዱ ለአረጋውያን የሚሰጡት ክብካቤና ክብር መኾኑን አጠንክራ ነገረችኝ፡፡ ‹‹አሜሪካ በወጣትነት ጊዜ የበላችውን ጉልበት የምትክሰው በእርጅና ጊዜ ነው፤›› ትላለች፡፡ የአረጋውያንን መብት በሚመለከተው ጠንካራ ሕግ መሠረት÷ አሜሪካ የተለያዩ በርካታ የአረጋውያን መከባከቢያና መጦሪያ ማእከል እንዳላት፣ እንደ ፍላጎትና አቅማቸው ለጥቂት ሰዎች በቤታቸው ውስጥ የክብካቤ አገልግሎት ወደሚሰጡ ግለሰቦች ቤትና አገልግሎቱን በቤታቸው እንዲያገኙ ባለሞያ የሚቀጠርላቸው አሉ፡፡

ከመዝነኛ ስፍራ እስከ ሕክምና፤ ከትራንስፖርት አገልግሎት እስከ ገበያ ቦታ ለአረጋውያኑ እንዲመች ተደርጎ በጥንቃቄ ተሠርቶላቸዋል፡፡ በአንድ የስፖርት ማእከል ውስጥ ዕድሜያቸው የገፉ ሴቶች እጅግ በጣም ተሸብሽቦ የተንጠለጠለ ቆዳቸውን ለእይታ አጋልጠው፣ በዋና ልብስ ውኃ ውስጥ ቀላል ስፖርት ሲሠሩ ተመልክቼ ከረጅም ሽንሽን ቀሚስና ከእጅጌ ሙሉ ሹራብ ውጭ ዐይቻት የማላውቀውን አያቴን አስታወስኹ፡፡ ጓደኛዬ በአዛውንቶች መከባከቢያ ማእከል ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አረጋውያን አለማየቷን የገለጸችልኝ በጥያቄ መልክ ነበር፤ ምክንያቱ ከኢትዮጵያውያን የኑሮ ዘይቤና ቤተሰባዊ ትስስር አንጻር አልያም በልጆቻቸው ፈቃድ አለመስጠት ምክንያት ሊኾን ይችላል በሚል፡፡ብቻ ኢትዮጵያም እንደ አሜሪካ ለአዛውንቶቿ መጨነቅ የምትጀምርበትን ቀን ትናፍቃለች፡፡ እስከዚያው ግን ስደተኛ ልጆቻውን ተከትለው የሚሰደዱት አረጋውያን በሰው አገር መብትም ቢኾን የጥቅሙ ትሩፋት ቢደርሳቸው እንደማትጠላ አጫወተችኝ፡፡

************* አሜሪካኖቹ ለአረጋውያኑ ብቻ ሳይኾን ለመላው ዜጎቻቸው ምን ያህል እንደሚጨነቁ ለመታዘብ አገራቸውን በረገጥኹ በማግሥቱ ነበር ዕድሉ የተፈጠረልኝ፡፡ ከዋሽንግተን ቀጥሎ በመኪና ወደ ኒውዮርክ እንደምናመራ የተያዘው ፕሮግራም በ‹‹ኸሪኬን ሳንዲ›› ምክንያት ሊታጠፍ እንደሚችል ስጋት እንዳለ ሰፊ ገለጻ ተደረገልን፡፡ ለሰባት ቀናት በዋሽንግተን ከሰነበትን በኋላ ቀድሞ እንደተገመተው ፕሮግራሙ ታጥፎ ለሁለት ቀናት ሆቴሉ ውስጥ እንድንቀመጥ ተደረገ፡፡ በርግጥ ማዕበሉ ያደርሳል ተብሎ የተገመተውና በተጨባጭ ያደረሰው አደጋ ባይመጣጠንም በአደጋው ወቅትና ከአደጋው በኋላ ያለውን እንቅስቃሴ በቴሌቭዥን እንደተከታተልኹት በግልጽ የደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ ፡፡ ሆቴል ውስጥ መታፈኑ ብዙም ስላልተዋጠልኝ አንድ አራት ሰው አነሣስቼ በሆቴሉ አቅራቢያም ቢኾን ተዘዋውረን እንመለስ በሚል ወጣ ብለን ብዙም ሳንርቅ ትንሽ ነፋስ መጥቶ ጥላችንን ያወዛውዘው ገባ፡፡ በነፋሱ ኀይል እየተሣሣቅን ነፋሱን ለመከላከል ስንሞክር አካባቢውን በፓትሮል ሲቆጣጠሩ የነበሩ ፖሊሶች ከየት መጡ ሳንል ከመኪናው ላይ ወርደው ስለ አደጋው ስጋት መስማት አለመስማታችን ጠየቁን፡፡

ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዳይከናወን መታወጁን፣ ሥራ ዝግ መኾኑንና የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን በትጋት አስረድተው ለደኅንነታችን እጅግ በተጨነቀ ስሜት የምንሄድበትን ደግመው ጠየቁን፡፡ ‹‹እኛስ ቅርብ ነን፤ ይብላኝ ለእናንተ›› ስል በሆዴ ታዘብኋቸው፡፡ በተመከርነው መሠረት ምክሩን ተቀብለን ምልስ አልን፡፡ ዳግመኛ ዝም ብሎ መቀመጡ አልኾን ቢለኝ ደፋር ሐበሻ ወዳጅ እንዳለኝ ብዬ ወዳጅ ጓደኞቼ ጋራ መደወል ጀመርኹ፡፡ ስልክ እየደወልኹ ‹‹ኧረ ባካችኁ ከተማውን አሳዩኝ፤›› እያልኹ አግባባኹ፡፡ አንዲቷ ጓደኛዬ እንድትመጣልኝ ሳባብል ‹‹እንደምንም ብለሽ ብትመጪኮ እዚህ ሆቴል እንዴት ፈጣን የኾነ ነጻ ኢንተርኔት አለ መሰለሽ›› አልኋት፡፡ ከጣራ በላይ እየሣቀች፣ ‹‹እስኪ አንቺ እንደምንም ብለሽ ነይ፤ እዚህም እንዴት ፈጣን የኾነ ነጻ ኢንተርኔት ታገኛለሽ መሰለሽ›› በማለት ሽምቅቅ አደረገችኝ፡፡ አገሬ በማውቀው የኢንተርኔት ችግር ማባበሌ ስሕተት ነበር፡፡ ለማንኛውም ዐዋጁ ተነሥቶ ታክሲ ሥራ እስኪጀምር የሚመጣልኝ ማግኘት አልቻልኹም፡፡ ዐዋጁ ከተነሣም በኋላ ለመንቀሳቀስ የደፈረ ባላገኝም በመጨረሻ አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ ተገኘና ሆቴል መጥቶ ይዞኝ ወጣ፡፡ የጎዳናዎቹ ጸጥ ረጭ ማለት ከቀናት በፊት ያየኋትን ከተማ ሌላ አስመስሏታል፡፡ የሰው ዘር በመንገዱ ላይ አይታይም፡፡

ጋዜጠኛ ወዳጄ እግረኛ ስለነበር ታክሲ ካገኘን የዕድላችንን እንሞክር አልያም የአንደኛው ጓደኛችን ቤት ቅርብ ስለኾነ በእግራችን እንሄዳለን ብሎኝ መንገድ ስንጀምር አንድ ታክሲ አገኘን፡፡ አሽከርካሪው ሐበሻ ነበር፡፡ ሥራ እንዲጀምሩ መፈቀዱን ነግሮን አሳፈረን፡፡ በየመንገዱ የፖሊስ መኪናና አምቡላንስ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡ ሬዲዮ የያዙ ፖሊሶች መኪናዎቻቸው አጠገብ ቆመው ግራ ቀኝ ያማትራሉ፡፡ ከጥቂት ቅዝቃዜና መጠነኛ ነፋስ በቀር የከፋ የአደጋ ስጋት አልታይ ስላለኝ ስጋታቸውን ከቅንጦት ነበር የቆጠርኹት፡፡ ስለአደጋው እየተነገረ ያለው ቅድመ ማስጠንቀቂያ በድሬዳዋ ከተማ በ‹‹ድንገተኛ ጎርፍ›› በደረሰው መጥለቅለቅ ያለቀውን ሕዝብ አስታወሰኝ፡፡ ይህኔኮ ትክክለኛ የአደጋ ትንበያና ትንታኔ ቢኖር ጎርፉም ‹‹ደራሽ ወይም ድንገተኛ›› ሳይኾን ተገቢው ስም ተሰጥቶት፣ መምጫው ታውቆ ነዋሪው ከአካባቢው እንዲወጣ ይደረግ ነበር ስል አሰብኹ፡፡ እንዲያ ቢኾን ኖሮ እኔም የአሜሪካ መንግሥትን ጭንቀት እንደማካበድ አልቆጥረውም ነበር፡፡ በድንገት መጣ የተባለው የድሬዳዋ ጎርፍ ያለከልካይ ሰዎችን ጠራርጎ በወሰደ ማግሥት ከጎርፉ የተረፈው የቤተሰቡን አስከሬን ፍለጋ በቁፋሮ ሲተጋ፣ ጎርፍ የተፋው የሰው አካል ከአሸዋ ውስጥ እየተለቀመ ሲወጣ፣ ከተማዋ በሐዘን ማቅ ተውጣ በልቅሶ ዋይታ ስትታመስ በቦታው ነበርኹ፡፡

ኬንያ ጠረፍ በኮረንጋት ደሴት በሚገኙት ዳሰነች እና ኛንጋቶ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ ኢትዮጵያውያኑን ‹‹ድንገተኛው የኦሞ ጎርፍ›› እየጠራረገ ወደ ኬንያው ቱርካና ሐይቅ ይዟቸው በመሄዱ አፈር ለማልበስ እንኳን አስክሬናቸውን ሳያገኙ የቀሩት ቤተሰቦቻቸው ‹‹ያው አዞ በልቷቸው ይኾናል›› ሲሉ መልስ የሰጡኝ ሟች ቤተሰቦቻቸውን ቁጥር የማያውቁ፣ ድንገተኛ ጎርፍ በድጋሚ ቢመጣ ማን እንደሚያስጥላቸው ባለማወቃቸው ግራ የተጋቡ አርብቶ አደሮችን የተመለከትኩ የዐይን ምስክር ነኝና በኒውዮርክ ያጋጥማል የተባለን አደጋ አስቀድሞ በማወቅ በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ የሚጎተጉቱ ገዢዎችን ስመለከት ቅንጦት ቢመስለኝ ምኑ ያስገርማል? ይህን ትዝብቴን የነገርኋቸው ጋዜጠኛ ወዳጆቼ፣ ‹‹እንዲህም ተጨንቀው በኾነላቸው›› አሉኝ፡፡ በእንዲህ ያለ አደጋ የሚደርሰው ጉዳት መንግሥት ለዜጎቹ የማይጠነቀቅ ቸልተኛ አድርጎ ስለሚያስቆጥረው በምርጫ ውድድር ለተቃራኒ ወገን መቀስቀሻ ዐይነተኛ አጀንዳ ኾኖ ሊቀርብበትና መጠቀሚያ ሊኾንበት ይችላል፡፡ ስለዚህ ‹‹ድንገተኛ ጎርፍ›› በሚል ከንፈር መጦ ማለፍ በአሜሪካ የሚታሰብ አይኾንም፡፡

አንዱ ጓደኛዬ አሜሪካኖቹ ለዜጎቻቸው የሚያደርጉትን የጥንቃቄ መጠን ሲያስረዳኝ በእጁ የያዘው ቀዝቃዛ ቢራ ጠርሙስ የለበሰውን መያዣ እያሳየኝ ነበር፡፡ ‹‹እኔን የሚያገርመኝ ለዜጎች የሚያደርጉት ትልቁ ጥንቃቄ አይደለም፡፡ ቢራ የምንጠጣበት ጠርሙስ ቅዝቃዜ ወደ እጃችን እንዳይሄድ ጠርሙሱን የምንይዝበት ትንሽዬ ስፖንጅ ይሠሩለታል፡፡ ትኩስ ነገር ስንጠጣ እንዳያቃጥለን ደግሞ ካርቶን ያበጁለታል፡፡›› እንዲህ የሚያዘጋጁት ነጋዴዎቹ ቢኾኑም ተጠቃሚው ጉዳት ቢደርስበት የሚጠይቅበት፣ ለአፈጻጸም የማያስቸግር ሕግ ስላላቸው ነጋዴው አስቀድሞ ለደንበኛው ይጠነቀቃል፡፡ አሜሪካን አገር ምንም ምልክት ካልተለጠፈበት መስተዋት ጋራ ተጋጭቶ ካሳ ስለተከፈለው ወዳጁ ላጫወተኝ ወዳጄ፣ በአዲስ አበባ ምንም ምልክት ባለመለጠፉ ምክንያት መንገድ መስሎት የተጋጨው ሰው የተሰበረውን መስታወት እንዲያሠራ መደረጉን ነገርኹት፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4139 times