Saturday, 30 March 2013 15:32

.....ተፈጥሮ አዳልታለችን?.

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(4 votes)

“ተፈጥሮ አዳልታለችን?” የሚለው አባባል የአቶ ስምረት አበበ ነው፡፡ አቶ ስምረት ሀሳባቸውን ሲገልጹ... ኧረ ለመሆኑ ...ወንዶች እስከስንት እድሜያቸው ድረስ ነው ልጅ ማስወለድ የሚችሉት? አሁን በቅርቡ በወጣ አንድ ድህረ ገጽ አንድ እድሜያቸው ከዘጠና አመት በላይ የሆኑ ሰው ልጅ ወለድኩኝ ብለው መደሰታቸውን ይገልጻል፡፡ እኔን የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ይኼውም የወንዶችና የሴቶች የልጅ መውለጃ እድሜ ይህንን ያህል መራራቁ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሴቶች ቢበዛ ሀምሳ አመት ድረስ መውለድ የሚችሉ ሲሆን አሱውም ከጤና አንጻር በእናትየውም ሆነ በልጁ ላይ ብዙ ጣጣ ያለው ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ግዜ ለእራሴ ምን እላለሁ መሰላችሁ? ተፈጥሮ አዳልታለች እንዴ? አሁን እኔ ማንሳት የምፈልገው ሁለት ጥያቄ ነው፡፡ 1/ ለመሆኑ ወንዶች ከሀምሳ አመት በሁዋላ እስከ ዘጠናው ወይንም እስከመቶው አመታቸው ድረስ መውለድ የሚችሉት ተፈጥሮ ምን እገዛ ብታደርግላቸው ነው? 2/ ሴቶች የመውለጃ እድሜያቸው ከወንዶች ከግማሽ በላይ ያህል መቀነሱ በምን ምክንያት ነው? ብለዋል አቶ ሰመረ በደብዳቤያቸው፡፡

ካነሳነው ርእስ ጋር ተያይዞ የደረሰን ሌላው መልእክት ተከታዩን ሀሳብ ያስነብባል፡፡ ...ለመሆኑ፣ “ወንዶች የመውለጃ እድሜያቸው እስከመቶ አመት ድረስ ነው” ሲባል፣ እድሜያቸው ከፍ ካለ በሁዋላ የሚወልዱዋቸው ልጆች ጤናማነት ምን ያህል አስተማማኝነት ይኖረዋል? የሚል ነው፡፡ የሴቶችና የወንዶች ልጅ የመውለጃ እድሜ ልዩነቱ በምን ምክንያት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዲያብራሩልን ዶ/ር ሙሁዲን አብዶን ለዚህ እትም ጋብዘናል፡፡ ዶ/ር ሙሁዲን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ኮሌጅ እና በሀያት ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ተማሪዎች መምህር ናቸው፡፡ ኢሶግ፡ የወንዶችና የሴቶች ልጅ የመውለጃ እድሜ መለያየቱ በምን ምክንያት ነው? ዶ/ር ሙሁዲን፡ በሴትና በወንድ መካከል ያለውን የተፈጥሮ ልዩነትን ስንመለከት ከየትኛውም አካል ወይንም የህይወት መስመር በተለየ የስነተዋልዶ አካል የማይመሳሰል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ሴትን ሴት የሚያሰኘው ነገር ወንድጋ የለም፡፡ ወንድንም ወንድ የሚያሰኘው ነገር ሴትጋ የለም፡፡ ሌሎችን የሰውነት አንሎች ብንመለከት ...እጅ ...እግር...ሳንባ...ኩላሊት... ወዘተ... ወንዶችም ሴቶችም በአንድ አይነት ሁኔታ ያሉአቸው ሲሆን በስነተዋልዶ አካል ግን ...ሴቶች ማህጸን ሲኖራቸው ወንዶች ግን የላቸውም፡፡ ወንዶች እና ሴቶች የብልት አፈጣጠራቸው የተለያየ ነው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው የስነተዋልዶ ተፈጥሮአዊ አካል ይኖራቸዋል፡፡ ልክ በዚሁ መልክ ሴት ልጅ የመውለጃ እድሜዋ በአጭሩ የሚቋጭ ሲሆን የወንዶች ግን ረዘም ያለ ጊዜን እና እድልን የሚሰጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የሴት ልጅ የመውለጃ እድሜ የሚጀምረው ከ15-20ዎቹ ሲሆን ማብቂያው 50/አመት ነው፡፡ የወንዶች ልጅ የመውለጃ የእድሜ ክልል ግን ከሴቶች ወደ ሶስት እጥፍ ከፍ ብሎ ...ከ30-70ዎቹ የእድሜ ክልል እና ከዚያም በላይ ይደርሳል፡፡

ስለዚህም ሴቶች በጣም አጭር የሆነ የመውለጃ ጊዜ ሲኖራቸው ወንዶች ግን በጣም እረጅም የሆነ የመውለጃ ጊዜ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ኢሶግ፡ የሴቶች ልጅ የመውለጃ እድሜ ከወንዶች ልጅ የመውለጃ እድሜ ጋር መራራቁ በምን ምክንያት ነው? ዶ/ር ሙሁዲን፡ Reproductive physiology የሚባሉት ሂደቶች ሆርሞን ወይንም ንጥረ ነገሮች በወንድና በሴት የመራቢያ አካላት ውስጥ የሚያሳዩት የተለያየ ኡደትና እነዚያ ኡደቶች በመጨረሻው የመቆም ወይንም የማረጥ ጊዜው ሜኖፖዝ በሴቶች ላይ ፈጣን ሲሆን በወንዶች ላይ ግን አንድሮፖዝ ዘግይቶ የሚመጣ መሆኑ ነው፡፡ በወንዶች ላይ የሆርሞን መቆም እጅግ በጣም አዝጋሚ መሆን ብቻ ሳይሆን የሚከሰቱት ክስተቶችም እንደሴቶች በአካላዊና አእምሮአዊ ወይንም ስነአእምሮአዊ ወይንም የመራቢያ ኡደትን አሳሳቢ ባልሆነ መልኩ ቀስ በቀስ እየቀነሰ የሚሄድ እና ወንዶች እንደሴቶች ከዚህ በሁዋላ የሚባል ገደብ በሌለው መልኩ ልጅ የማስወለድ እድሉ አንዱ ከሌላወ በተለያየ መልኩ ከፍና ዝቅ ባለ እድሜም ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ የሴቶች የመራቢያ እድሜ ሲታይ ማንኛዋም ሴት ብትሆን ከሀምሳ አመት በሁዋላ መውለድ የማትችል ስትሆን ወንዱ ግን ከዚህ በሁዋላ ማስወለድ አይችልም የሚባል ቁርጥ ያለ የእድሜ ገደብ ሳይኖረው እስከ መቶ አመት እድሜም ሊቀጥል ይችላሉ፡፡ ኢሶግ፡ ንጥረ ነገሮቹ ልዩነታቸው ምንድነው? ዶ/ር ሙሁዲን፡ ሴቶች... Fecundity የሚባል ሳይንሳዊ ቃል አለ፡፡ የዚህ ቃል ትርጉምም አንዲት ሴት የወር አበባ አይታ ከዚያም እንድታረግዝና ልጅ ወልዳ እንድታቅፍ የመቻልዋ ሂደት ነው፡፡ አንዲት ሴት ልጅ ወልዳ ማቀፍ የምትችልበት ተፈጥሮአዊ አካሄድ ከእድሜ ጋር በጣም የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከእድሜ ጋር የሚያቆራኝበት ምክንያት (ovary) ወይንም የሴት እንቁላል ማፍሪያ የሆነው አካል ከሚያመርታቸው ንጥረ ነገሮች ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ሴት ልጅ የእንቁላል ማፍሪያዋ በሚያረጅበት ጊዜ እንቁላል የማፍራት አቅሙ በጊዜ ሂደት እየቀነሰ ይመጣል፡፡

ይህም ሂደት የሚጀምረው አንዲት ሴት እድሜዋ 30/ አመት ሲሆን ጀምሮ ነው፡፡ ቀስ በቀስም እንደእድሜው ከፍታ ማለትም የሴቷ እድሜ ...35/... 40.... 45/... እየሆነ ሲቀጥል የእንቁላል ማፍራት መጠኑ ጥራቱ የመሳሰለው ሁሉ እየወረደ ይመጣና ወደሀምሳው ስትደርስ ጭራሹንም የመቋረጥ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ሜኖፖዝ ከሚባለው ክልል የገባች ሲሆን በምንም ምክንያት ልጅ መውለድ አትችልም፡፡ አንዲት ሴት እጅግ ተመራጭ የሆነው የመውለጃ እድሜዋ ከ24-29/አመት ድረስ ነው፡፡ አንዲት ሴት በሃያዎች የእድሜ ክልልዋ ማህጸንዋ በተዋጣ መልኩ እንቁላል የማፍራት ተግባሩን የሚያከናውንበት ሲሆን እድሜዋ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግን በተለይም ሀምሳ አመት ገደማ ስትደርስ የወር አበባ ስለሚቋረጥ ማርገዝ ...ልጅ የመውለድ አቅም ...ሙሉ በሙሉ ይጠፋል፡፡ ወንዶች ... በወንዶች በኩል androgen እና testosterone የሚባሉ ሆርሞኖች በወንዶች የመራቢያ አካል ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱ ሲሆን እነዚህ ሆርሞኖች መፈጠራቸውን የሚቀንሱት እጅግ አዝጋሚ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡የእነዚህ ሆርሞኖች መኖር ስፐርምን የመራቢያ ሕዋሶችን ብቃት ባለው መንገድ ማምረት የሚያስችል ሲሆን ይህም ከእድሜ ጋር የተያያዘ... ነገር ግን እንደሴቶቹ አጭር ቁርጥ ያለ የጊዜ ተመን የሌለው ነው፡፡

የሴቶች የተዋጣለት የመውለጃ እድሜ ሀያ አምስት አመት ሲሆን የወንዶቹ ግን ሰላሳ አምስት አመት ነው፡፡ በእርግጥ ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹ ከተጠቀሰው እድሜያቸው በፊት ልጅ አይወልዱም ማለት አይደለም፡፡ ይህ የተዋጣለት የመውለጃ ጊዜ የሚባለው ከማህበራዊ ፣ስነልቡናዊ የሆርሞኖች ተግባር አንጻር ተመዝኖ በምሁራን የተረጋገጠ ወቅት ነው፡፡ ወንዶች ልጅ ለማስወለድ የሚያበቃቸው ተፈጥሮአዊ አቅም በሰላሳ አምስት አመት እድሜያቸው ጀምሮ እድሜያቸው በጨመረ ቁጥር እየቀነሰ እየቀነሰ ይሄድና ወደሰባዎቹ ክልል ሲገባ ንጥረ ነገሩ መመረቱን ሊያቆም ይችላል፡፡ ነገር ግን ከሰባዎቹ የእድሜ ክልል በሁዋላ ማስወለድ አይችሉም የሚል መደምደሚያ ሳይኖር አንዳንድ ወንዶች እስከ ዘጠና ከዚያም በላይ ባለው እድሜያቸው ልጅ ማስወለድ ይችላሉ፡፡ የወንዶች እድሜ በጨመረ ቁጥር የሚመረተው እስፐርም ጥራትና መጠን ቀስ በቀስ የመቀነስ ሂደቱ ከአንዱ ወንድ የሌላው ሊለይ ስለሚችልም ወንዶች እንደ ሴቶቹ ቁርጥ ባለ የእድሜ ክልል ልጅ ማስወለዳቸው አይቋረጥም፡፡

ይህ የእድሜ ክልል በተለያየ ህመም ምክንያት የሚከሰተውን ልጅ የማስወለድ ችግር አይመለከትም፡፡ ኢሶግ፡ ወንዶች እስከዘጠና አመት ድረስ ማስወለድ ይችላሉ ሲባል የሚወለደው ልጅ ጤንነት ምን ይመስላል? ዶ/ር ሙሁዲን፡ በእርግጥ በሚወለዱ ልጆች ጤንነት ላይ የሚከሰተው ችግር በወንዶቹ ሳይሆን በሴቶች በኩል እድሜ በጨመረ ቁጥር እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ሴቶች እድሜያቸው ከ40/ዎቹ በላይ በሆነ ጊዜ የሚወልዱወቸው ልጆች የአፈጣጠር ችግር ልጆቹ ከተወለዱ በሁዋላም የአእምሮ ዘገምተኛ የአካል ችግር ያለባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወደ ወንዶቹ ስንመለስ ግን ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ምንም እንኩዋን የእስፐርም ጥራትና ብቃት እየቀነሰ ይመጣል ቢባልም እንደሴቶቹ እድሜያቸው ከጨመረ በሁዋላ ...ማለትም በሰባ ወይንም በዘጠና ከዚያም በላይ በሆነ ጊዜ ልጅ ቢያስወልዱ በልጁ ላይ ምንም የሚከሰት የጤና ችግር የለም፡፡ ይቀጥላል

Read 9591 times