Print this page
Saturday, 06 April 2013 13:55

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(14 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ - ፲፪

ኦክቶበር 31 ቀን 2012 ዓ.ም ጠዋት፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ 23ኛው ጎዳና ላይ ወደሚገኘው ስቴት ዲፓርትመንት ለመግባት ከ130 ጋዜጠኞች ጋራ ተሰልፌአለኹ፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት እያሉ በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ለመካፈል ወደ ቢሯቸው ባመራኁባቸው ቀናት በሁለት የመተላለፊያ በሮች የሚደረገውን ጥብቅ የደኅንነት ፍተሻ በማስታወስ ይኼኛው የባሰ ሊኾን እንደሚችል ገምትኹ፡፡ ጊዜው የቁርስ ሰዓት ነው፡፡ ከሰልፉ ርዝማኔ የተነሣ ግን እስከ ምሳ ሰዓት ተራ እንደማይደርሰኝ ርግጠኛ ኾኜ ዐረፍ ብዬ የምጠብቅበት ቦታ ፍለጋ ማማተር ጀመርኹ፡፡ ጋዜጠኞቹ የስቴት ዲፓርትመንቱን ሕንጻ ከጀርባቸው እየተዉ የማስታወሻ ፎቶ ይነሣሉ፡፡ ወደ ሕንጻው ይዞ ለመግባት የተፈቀዱና ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶች ዝርዝር አስቀድሞ በጹሑፍ ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ ሳቢያ የደኅንነት ፍተሻው ተቀላጥፎ ይኹን ፍተሻው በዘመናዊ መሣሪያ በመታገዙ ሳላውቀው ሰልፉ በፍጥነት ተቃልሎ ተራዬ ደረሰኝ፡፡ ጥቁር በጥቁር ለብሰው የታጠቁት ባለግርማ ሞገስ ጠባቂዎች አኳኋን ያስፈራል፡፡

ፍተሻውን በቀላሉ አልፌ ወደ ውስጥ ዘለቅኹ፡፡ የቀድሞዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን (በወቅቱ በሓላፊነታቸው ላይ ነበሩ) ይገኙበታል ወደተባለው ወደ ሕንጻው ውስጠኛው ክፍል አመራን፡፡ የውጭውን ቅዝቃዜ ለመቋቋም የደረብናቸውን ካፖርቶች በክብር ተቀብለው መስቀያ ላይ በማንጠልጠል በምትኩ ከፈገግታ ጋራ መረከቢያ ቁጥር ከሚሰጡት ሠራተኞች አንዷ ካፖርቴን ልትቀበለኝ ቀረበች፡፡ በአገሬ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ከመግባቴ በፊት÷ ለሴቶች ወደተዘጋጀው ፍተሻ ክፍል ተወስጄ ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ተበርብሬ፣ ቦርሳዬም እስኪበቃት ተራግፋ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ፍተሻ በኋላ ቁጥር የተሰጠኝ ይዠው እንዳልገባ ለተከለከልኹት የከንፈር ቻፕስቲክ ብቻ ነበር፡፡ ታዲያ ያን አስታወስኹና አሁን በሰው አገር ባገኘሁት ከበሬታ እየተደነቅኹ በፈገግታ ተሞልታ ለቀረበችኝ ሠራተኛ ካፖርቴን አውልቄ ሰጠኋት፡፡

የቡድን መሪዎቻችን የዓለም አገሮች ሰንደቅ ዓላማ አምሮ በተሰቀለበት ኮሪዶር በኩል አሳልፈውን ቁርስ ወደተዘጋጀበት ቦታ መሩን፤ ግብዣው ሲጠናቀቅም ወደ ትልቁ አዳራሽ ገብተን በስቴት ዲፓርትመንት የትምህርትና ባህል ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አን ስቶክ የእንኳን ደኅና መጣችኹ አቀባበል ተደረገልን፡፡ በተያዘው ፕሮግራም መሠረት ስለ አሜሪካ የጋዜጠኝነት ኹናቴና ስለ 2012 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውይይት እንድናደርግ ተጋበዝን፡፡ ለውይይቱ አሜሪካ ውስጥ አሉ የተባሉት አንጋፋ ጋዜጠኞች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተጋብዘዋል፡፡ ከእነርሱም አንጋፋውና ታዋቂው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ቦብ ውድዋርድ አንዱ ነበር፡፡ ቦብ ከ80 የዓለም አገሮች ለተውጣጣነው ጋዜጠኞች የተናገረባቸው ጭብጦች ስለ ምርምራ ጋዜጠኝነት እና በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በሚዘገብበት ወቅት ስለሚያጋጥመው ችግር ነበር፡፡ ቦብ ውድዋርድ የሚናገረውን ከማዳመጥ ጋራ የተሠየመበት መድረክ የስቴት ዲፓርትመንቱ ሕንጻ አዳራሽ መኾኑንም እያሰብኹ ነበር፡፡

ተናጋሪው ብቻ ሳይኾን መድረኩን የሚያስተባብሩትና ውይይቱን የሚመሩት የጋዜጠኝነት ልምድ ያላቸው ነበሩ፡፡ ተናጋሪው በገዢዎቹ ጣሪያ ሥር ተቀምጦ የአሜሪካን የሚዲያ ነጻነት አደነቀ፤ አጨቃጫቂና አንገብጋቢ ጉዳዮች ሲዘገቡም ጋዜጠኛው የሚያጋጥመውን ችግር እየዘረዘረ የእነ ኦባማን ስም በግልጽ እየጠቀሰ ተቸ፡፡ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋራ በተያያዘ ለሚቀርቡት ጥያቄዎችም በልበ ሙሉነት አስተያየቱን ሰጠ፡፡ እኔም ትንፋሼን ዋጥ አድርጌ፣ በድንጋጤ ተመስጬ ዕድሜ ጠገቡን ጋዜጠኛ ቦብን ከልቤ አዳመጥኹት፡፡ በምናቤ በስቴት ዲፓርትመንት ቦታ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ በቦብ ፈንታ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ተካኋቸው፡፡ በመንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቀውና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጣሪያ ሥር፣ የዓለም ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት መሪውንና ሥርዐቱን ሲተች፣ ዓለም የሚደነቅበትን የአገሩን ‹ዴሞክራሲያዊ› የምርጫ ሂደት በሒስ ሲሰልቀው አሰብኹና ለቦብ ሥቅቅ አልኹለት፡፡

ቦብ ውድዋርድ ማንን ፈርቶ፤ የስቴት ዲፓርትመንት ከፍተኛ ባለሥልጣናት “The price of politics” የሚለውን ባለ30 ዶላሩን የቦብ መጽሐፍ ፈርሞ በቦታው ለተገኘነው ጋዜጠኞች በስጦታ እንዳበረከተልን ተናግረው ሲያስጨበጭቡ በስጨት ብሎ አቋረጣቸው፡፡ እንዲህም አለ፣ ‹‹መጽሐፌን ለማንም በነጻ አልሰጠኹም፤ ስቴት ዲፓርትመንቱ ነው ገዝቶ የሰጣችኹ››፡፡ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ቁጣ መጽሐፉ በተገለጸው መጠን በነጻ ከታደለ ‹ዋጋ ቢስ› ይባላል ከሚል መንፈስ ሊመነጭ እንደሚችል ገመትኹ፡፡ ውይይቱ ሲያበቃ ለጋዜጠኛው ክብር ሲባል በየቡድናችን እየተጠራን ባለበት ሄደን የማስታወሻ ፎቶ እንድንነሣ ተጋበዝን፡፡ ሞጋች ጋዜጠኞች ከሚሰደዱበት፣ ከሚታሰሩበት አልያም በፍራቻ ሥራ ከሚያቆሙበት ወይም ከፍ ዝቅ ተደርገው እየተመናጨቁ መረጃ ከሚከለከሉበት፣ ከፖለቲካዊና ገዢዎችን ከሚነካ ዘገባ ይልቅ ወደ ማኅበራዊና መዝናኛ ጉዳዮች እንዲያተኩሩ በእጅ አዙር ከሚገደዱበት አገር ለሄደች ጋዜጠኛ፣ የስቴት ዲፓርትመንቱ ባለሥልጣናት ለአንጋፋው የዋሽንግትን ፖስት ጋዜጠኛ ቦብ ውድዋርድ የቸሩት አክብሮት አስደማሚ ነበር፤ ከዚያም በላይ ግን በመንፈሳዊ ቅናት እርር ድብን ብዬ እንደነበር እንደምን እሸሽገዋለኹ፡፡

አሜሪካኖቹ ጀግኖቻቸውን ማወደስና ማስታወስ ያውቁበታል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ለምሳ የታደምንበት በሕንጻው ስምንተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘውን የተንጣለለው አዳራሽ÷ በዕውቁ አሜሪካዊ ጸሐፊ፣ ሳይንቲስትና ዲፕሎማት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ስም የተሠራው የዲፕሎማት መመገቢያ አዳራሽ ነው፡፡ በአዳራሹ ደረጃውን የጠበቀ የምሳ ግብዣ ተደረገልን፡፡ በእጅጉ የተዋበውን ታሪካዊ የመመገቢያ አዳራሽ በአካል ይቅርና በፊልም መመልከቴን ተጠራጠርኹ፡፡ ወደ መመገቢያው አዳራሽ ከመገባቱ በፊት ቤንጃሚን ፍራንክሊን የሚዘከርበት የተለየ ክፍል ይገኛል፡፡ በክፍሉ ብቻ ሳይኾን በመጸዳጃ ቤቱ ውስጥም የትውስታ ፎቶ የሚነሡትን የጋዜጠኞች ኹኔታ ስመለከት በቦታው ውበት የተደመምኹት እኔ ብቻ አለመኾኔን አረጋገጥኹበት፡፡ በዴሞክራሲያዊነቱ ከሚደነቀው የአሜሪካ ምርጫና ከሚዲያ ነጻነታቸው (የእነርሱ ጋዜጠኞች እንዲህ አይሏቸውም) ቀጥሎ ከአሜሪካኖቹ የወደድኁላቸው ነገር የቀደመውን አስታዋሽነታቸውንና አክባሪነታቸውን ነው፡፡ የካፒታል ኮሚዩኒኬሽን ግሩፕ አስጐብኚው ወጣቱ ሮበርት ዩል በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችንና መታሰቢያ ሐውልቶችን ሰፋ ካለው ማብራሪያ ጋራ ሲያስጐበኘን፣ ‹‹አሜሪካ ለታሪክ ሠሪዎችና ባመኑበት መንገድ አገራቸውን ላገለገሉ ዜጐቿ ቦታ አላት፡፡

ይህ ደግሞ ሌሎች ታሪክ ሠሪዎችን ያበረታታል፤›› ብሎን ነበር፡ ልክ እንደ ፍራንክሊን የዲፕሎማት መመገቢያ ክፍል ከጎዳና ሥያሜዎች ጀምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ቤተ መዘክሮች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ታሪካዊ ቦታዎች. . .ብቻ የቱ ተዘርዝሮ የቱ ይቀራል ለሁሉም ባለውለታዎቻቸው በየከተሞቹ እንደየታሪካቸው መታሰቢያ አኑረውላቸዋል፡ በዋሽንግተን ዲሲ በስም ብቻ ከገነነችው ትንሿ ‹‹ኋይት ሃውስ›› ጀምሮ እስከ ኮንግረሱ መቀመጫ ‹‹ካፒቶል ሂል››፤ ለተለያዩ የቀደሙ ፕሬዝዳንቶች መታሰቢያ ከተገነቡት ግዙፍ ሐውልቶች ጀምሮ በቪየትናም ጦርነት ወቅት በውጊያ ሕይወታቸውን ያጡ 56 ሺሕ አሜሪካውያን ስማቸው የተቀረጸበት የመታሰቢያ ደንጊያ፤ የአሜሪካ ሚዲያ ታሪክ፣ የጋዜጠኞቻቸው ገድል፣ ለሞያቸው ሲሉ በሥራቸው ላይ ሕይወታቸውን ለገበሩ ጋዜጠኞች መታሰቢያ የተበጀው ‹‹ኒውስ ሙዚየም››፤ በአሪዞና ፊኒስክ የናሽናል ናባል አቪየሽን ሙዝየም፤ የቺካጐ አፍሪካ አሜሪካውያን መታሰቢያ ሙዝየም፤ በአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ተዘርዝረው የማያበቁ መታሰቢያዎችን ስመለከት የወጣቱ አስጐብኚ ሮበርት ማብራሪያ ልክ ነበር - እውነትም አሜሪካ ለቀደሙት መሪዎቿ ክብር ትሰጣለች አልኹ፡፡

በአመዛኙ ሥልጣን ላይ ባሉበት ወቅት ብቻ ለሚወደሱት የአገሬ ባለታሪኮች አዘንኹ፡፡ አሜሪካ ታሪክ ሠሪዎቿንና ባለውለታዎቿን ለትውልድ ከመዘክርና ለዓለሙ ከማስተዋወቅ ባሻገር የታሪክ ገጽ የጠቃቀሳቸውን ንዋያትና ጓዳ ጎድጓዳዎቿን ለጐብኚዎች እንዲመች አድርጐ በማስዋብ የቱሪዝም ገንዘብ ትሰበስባለች፡፡ ሌላው ቀርቶ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቺካጐን በረገጡበት በአንድ ወቅት ያረፉበት የሆቴል አልጋ በክብር ተቀምጦ በርከት ያሉ ዶላሮች እየተከፈለበት እንደሚጐበኝ አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ በስቴት ዲፓርትመንት የቤንጃሚን ፍራንክሊን ዲፕሎማት መመገቢያ ክፍል ከታደምነው የምሳ ግብዣ በኋላ የአሜሪካ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ከአገራቸው ውጭ ያሉ ጉዳዮችን ለመዘገብ የሚከተሉትን ዘይቤ በሚመለከት ከባለሞያዎች ጋራ፤ ስለ አሜሪካ የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ ደግሞ ከስቴት ዲፓርትመንት ባለሥልጣናት ጋራ ውይይት አደረግን፡፡ ለውይይት በተያዙት ጭብጦች ላይ በተለይ ከዐረብ አገሮች የመጡ ጋዜጠኞች ጠንካራ ትችትና ጥያቄዎች ይሰነዝሩ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ባለሞያዎቹና ባለሥልጣናቱ ግን ለሁሉም ትችት አዘል ጠንካራ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የሚመልሱት በለዘብታ ቃልና በትዕግሥት ነበር፡፡ ‹‹በገዛ ገንዘባቸው ምድረ ጋዜጠኛ ከመላው ዓለም ሰብስቦ የመረረ ትችት መቀበል ምን የሚሉት ቅብጠት ነው፤›› ብዬ መታዘቤ አልቀረም፡፡ ስንኳን ከፍለው ተከፍሏቸው ለመተቸት የማይፈቅዱትን አስታውስኹ፡፡

ምኞት አይከለከልም - በወ/ሮ ሂላሪ ክሊንተን ቢሮ ስለ አሜሪካ የተደረገው ውይይት ለግማሽ ቀንም ቢኾን በእኛ ሹማምንት ቢሮዎች ውስጥ እንዲደረግ ተመኘኹ፡፡ ለጉብኝቱ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ቀጣዩ መሰናዶ ከተመረጡ ባለሥልጣናት ጋራ በየቡድናችን ለመነጋገር የተያዘ የውይይት መርሐ ግብር ነው፡፡ ከዐሥራ ሰባት የአፍሪካ አገሮች የተውጣጣውን የጋዜጠኞች ቡድን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ጆኒ ካርሰን እንደሚያነጋግሩን በመርሐ ግብሩ ላይ ተመልክቷል፡፡ ለውይይቱ አነስ ባለች አዳራሽ ተካተትን፡፡ ከአፍሪካውያን ጋዜጠኞች አብዛኛዎቻችን በዐምባገነን መሪዎቻችን የምንገዛ ነንና ጆኒ ካርሰን መፍትሔ ይሰጡ ይመስል ሁሉም የአገሩን ጉዳይ እያነሣ ሮሮውን አሰማ፤ ሚኒስትሩንም ስለ መንግሥታቸው አቋም ወተወተ ማለት ይቀላል፤ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሩ በእያንዳንዱ አፍሪካዊ አገር ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ክትትልና ዕውቀት በሚያስረግጥ አኳኋን ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ሰጡ፤ ነገር ግን ምን ዋጋ አለው - ውይይቱን ያካሄድነው በድምፅ ለመሰነድ በማይፈቀድበት ኹኔታ ውስጥ (ኦቭ ዘሬከርድ) ነበር፡፡ በደምሳሳው የውይይቱ ጠቅላላ ጭብጥ የመናገርና የመጻፍ ነጻነት በሚገባ ባልተረጋገጠባቸው አገሮች ስላለው የጋዜጠኝነት ሞያ ነበር፡፡ ረዳት ሚኒስትሩ በዚህ ዐይነት የስልታዊና ግልጽ ዕመቃ ኹኔታ ውስጥ ጋዜጠኝነት በየትኛውም ወገን በኩል ነጻ ነው ብለው እንደማያምኑ፣ ነገር ግን የሞያውን ግዴታዎች አሟልተው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን አገራቸው እንደምታበረታታ አጽንዖት የሚሰጥ ነበር፡፡

**************** አምስት ቀናት በፈጀው ውይይት ከቦብ ውድዋርድ በተጨማሪ ከዋሽንግተን ፖስት የፖሊቲካ አዘጋጅ፣ ከአሶሼትድ ፕሬስ ዓለም አቀፍ የፖሊቲካ ጉዳዮች ጸሐፊ፣ ከፎክስ ኒውስ የፖሊቲካ ተንታኝ፣ ከኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ፣ ከኤን.ፒ.አር አዘጋጅ፣ ከኤቢሲ ኒውስ ሪፖርተርና ከሌሎች አንጋፋና ወጣት የኅትመት፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ዲጂታል ብዙኀን መገናኛ ጋዜጠኞች ጋራ ተወያይተናል፤ ተሞክሮዎቻችንንም ተለዋውጠናል፡፡ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሂደት ምን መልክ እንዳለው ለመታዘብም ለረጅም ዓመታት በሪፓብሊካን ፓርቲ ደጋፊነታቸው የሚታወቁ ሕዝቦች ወዳሏት ፊኒክስ - አሪዞና ተጓዝን፡፡ የዴሞክራቲክ ይኹን የሪፓብሊካን ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ለዋናው ምርጫ ከማቅረባቸው በፊት በፓርቲያቸው ጉባኤ ይለያሉ፡፡ ዕጩዎቹ ከታወቁ በኋላ የምረጡኝ ዘመቻ ያደርጋሉ፡፡ ፊኒክስ ስንደርስ ዕጩዎቹ የምርጫ ክርክራቸውንና የምረጡኝ ቅስቀሳዎቻቸውን በማጠናቀቃቸው ሕዝቡ ድምፁን ለማን እንደሚሰጥ ወስኖ ነበር ፡፡ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ዕጩዎቹ የሚያደርጓቸው ቀልብ ገዢ ንግግሮች ብቃት ባላቸው ታዋቂ ጸሐፊዎች የተቀናበሩ በመኾናቸው መራጩ ሕዝብ በመጨረሻ ድምፁን የሚጥልለትን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ በቁርጥ የማስወሰን ከፍተኛ አቅም የሚፈጥርለት በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፈው የምርጫ ክርክሩ ነው፡፡

ስለዚህ በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፈውና ታዋቂና አንጋፋ ጋዜጠኞች የሚያስተባብሩት ክርክር የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ ለዚህም ነበር በዴንቨር ከተማ በአንጋፋው ጋዜጠኛ ጂም አወያይነት በተካሄደው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ባራክ ኦባማ በሚት ሮምኒ በመበለጣቸው ሁለቱን ተወዳዳሪዎች አንገት ለአንገት የሚያተካክል የሕዝብ አስተያየት መጉረፍ የጀመረው፡፡ ኦባማ በክርክሩ ሸብረክ እንዳሉ ቢቀጥሉ ኖሮ ሁለተኛው ዕድል በዐይናቸው ፊት ያመልጣቸው ነበር፡፡ ዕጩዎቹ የግል ጉዳያቸው ሳይቀር ለዐደባባይ እየወጣ የምርጫ መቀስቀሻ አጀንዳ ኾኖ የሚቀርብበት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ÷ የምረጡኝ ዘመቻዎቹና የምርጫ ክርክሮቹ ሐሳቦችም በፖለቲካ ተንታኞችና ጋዜጠኞች እየተተነተነ ውይይት ይደረግበታል፡፡ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለሀብቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና ግለሰቦች ለመረጡት ዕጩ ግልጽ ድጋፋቸውን ይሰጣሉ፡፡ ከሕግ ይኹን ከዴሞክራሲያዊ መመዘኛ አኳያ የማይገቡ ድርጊቶችን የሚፈጽም፤ እንደተመቸው ሕግ፣ መመሪያና ደንብ የሚያወጣ፤ አባላትና ደጋፊዎችን ከሥራ የሚያፈናቅል፣ የሚያዋክብ፣ የሚያስር፣ ደብዛቸውን የሚያጠፋ፤ የአገሪቱን ሀብት በተለያዩ አደረጃጀቶች ጠርንፎ መያዣ የሚያደርግ፤ የፓርቲዎችን ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ የሚያላላ፤ መሪዎችን የሚያስርና ተቃዋሚዎች ‹‹በምርጫ ቢሳተፉ ባይሳተፉ ለውጥ አያመጡም›› የሚል ገዢ ፓርቲ በአሜሪካ የለም፡፡ ለዚህም ነው በፊኒክስ ጸጥታና ሥርዐት በሰፈነባቸው ምርጫ ጣቢያዎች መርጠው የሚወጡት መራጮች ያለምንም ስጋት÷ ‹‹እኔ የመረጥኹት ኦባማን ነው››፤ ‹‹እኔ ኦባማን ስለማልወደው የመረጥኹት ሮምኒ ነው፤›› ሲሉ ያዳመጥኳቸው - ያውም ከየት እንደመጡ ለማያውቋቸው የአፍሪካ አገር ጋዜጠኞች፡፡

ቀድመው በሚመሹ ግዛቶች ምርጫው ተጠናቆ የምርጫው ውጤት መገለጽ ሲጀምር የየፓርቲው ደጋፊዎች በከተማዋ መሀል እንብርት በተዘጋጁት የውጤት መከታተያ መድረኰችና ድግሶች ላይ በመገኘት ውጤቱን በጉጉት ሲጠባበቁ ያየኋቸው ያለአንዳች ግርግርና ስጋት ነበር፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የአሪዞና ጽ/ቤት በሬነሳንስ ሆቴል፣ ሪፓብሊካኑ ፓርቲ ደግሞ ከዚሁ ሆቴል አጠገብ ባለው ሃያት ሆቴል ባዘጋጁት የምርጫ ውጤት መከታተያ ድግሶች ላይ ፕሮግራሙ በቀጥታ ስርጭት ስለመተላለፉ ምንም ስጋት ያልገባቸው ደጋፊዎቻቸው የዕጩዎቹን ምስል የያዘ ቲሸርት ለብሰው፣ መፈክራቸውን ከፍ አድርገው ድጋፋቸውን ያለ ፍርሃት ሲሰጡ አስተውዬአለኹ፡፡ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መመረጣቸው ከታወጀ በኋላም ፕሬዝዳንቱ ተፎካካሪያቸው የነበሩት ሚት ሮምኒ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ላደረጉት ጠንካራ ፉክክር ሲያመሰግኗቸው፣ ሚት ሮምኒ በበኩላቸው ለፕሬዝዳንት ኦባማ  የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት አስተላልፈዋል፤ ሁለቱም ተፎካካሪዎች ለአገራቸው በአንድነት እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ተሰነባብተዋል፡፡

የአሪዞናዎቹ የሪፓብሊካንና ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች ደጋፊዎችም እንዲሁ ተመሰጋግነው ተለያይተዋል፤ ‹‹መልካም ሥራ›› ተባብለው ተሸኛኝተዋል፤ ያዘኑት ለተደሰቱት መልካሙን ተመኝተው ‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ›› ብለው የምርጫውን ወሬ ዘግተው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ በሐረርና ድሬደዋ ከተሞች ተገኝቼ ነበር፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በተነሣ አለመግባባት ምርጫው ይደገም በተባለባቸው ሆሳዕናና አካባቢዋ እንዲሁም ወሊሶ ለተከሠቱት ኹኔታዎች የዐይን እማኝ ነበርኹ፡፡ በ2002 ዓ.ም ምርጫ ደግሞ በትግራይ ክልል ተንቤን ተገኝቼ ምርጫውን የመዘገብ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ ይካሄዳል፡፡

በአንድ ወገን÷ ጥቂት የማይባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹ምኅዳሩ ተዘግቷል›› በሚል ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች እየተከታተልኹ ነው፡ በሌላ ወገን÷ ‹‹ባለፉት 21 ዓመታት በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዐት እውን ኾኗል፤ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መኾኑ ተረጋግጧል›› የሚሉና መሰል መልእክቶችን በመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች በተደጋጋሚ እየሰማኹና እየተመለከትኹም ነው፡፡ እኔ በመሀል ÷ ከአምስት ወራት በፊት ተዘዋውሬ የታዘብኹት የአሜሪካ ምርጫ ትዝታው ከጠቅላላ ትዕይንቱ ጋራ እየመጣብኝ የኢትዮጵያው ምርጫ ‹‹ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ›› ከተባለ የአሜሪካኑ ምን ሊባል ነው? እያልኩ ራሴን ስጠይቅ እውላለኹ፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4089 times