Saturday, 06 April 2013 14:19

‹‹...ወንዱም...ሴቷም...እስከ አርባ አመት...››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

የሴትና የወንድ ልጅ ልጅ መውለድ የሚያስችለው እድሜ በምን ምክንያት ተለያየ? የሚል ርእሰ ጉዳይ አንስተን ከዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ማብራሪያ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ዶ/ር ሙሁዲን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና በሌሎችም የህክምና ትምህርት ቤቶች የህክምና ተማሪዎች አስተማሪ ናቸው፡፡ በዚህ እትም ከዶ/ር ሙሁዲን ቀሪ ማብራሪያ በተጨማሪ የተለያዩ ተሳታፊዎችን የህይወት ገጠመኝና ትዝብት እናስነብባችሁዋለን፡፡

------------------//////////----------------

... እግዚአብሄር አዳልቶአል ወይ አላችሁ? እኔ የሚገርመኝ በእግዚአብሄር ስራ መግባት ምን ያህል እንደማያስፈራ ነው... የሚሉን ተከታዩን መልእክት ያደረሱን ተሳታፊ ናቸው፡፡ ተሳታፊው አቶ ወንድወሰን መርሻ ይባላሉ፡፡ የአቶ ወንድወሰን አስተያየት ብዙም ወደሳይንሱ የሚያተኩር ሳይሆን በአብዛኛው ወደማህበራዊው መንገድ የሚያዘነብል ነው፡፡ ‹‹....እግዚአብሄር አዳልቶአል አላችሁ? እኔ የሚገርመኝ በእግዚአብሄር ስራ መግባት ምን ያህል እንደማያስፈራ ነው፡፡እና.. ልክ አርባ ሶስት አመት ሲሆናት የወለደቻት ሴት ልጅ ..እህ.... እያደገች ስትሄድ የአእምሮ ዘገምተኛ መሆንዋ ታውቆአል፡፡ ይኼው እስከአሁን ድረስ በልዩ ድጋፍ እያደገች ትገኛለች፡፡ ...እኔ እግዚሀርን እፈራለሁ፡፡ በእርግጥ ሳይንሱ በበኩሉ ስለተፈጥሮ የሚያስረዳው ብዙ ነገር አለ፡፡

እኔ ግን ሳይንሱ በሚለው ላይ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሲጨመር ሁሉ ነገር ሊሳካ እንደሚችል አምናለሁ ፡፡ ለመሆኑስ በሴት እና በወንድ መካከል ያለው የተፈጥሮ ልዩነት ልጅ በመውለድ እድሜ ላይ ብቻ ነው እንዴ? ሴት ልጅ ልጅን ስትወልድ ዘጠኝ ወር በሆዱዋ ተሸክማ ፣ጡትዋን አጥብታ እና በጀርባዋ አዝላ ነው የምታሳድገው፡፡ወንድ ልጅ ግን በወሲባዊ ግንኙነት እለት ወደሴትዋ እንቁላል የላከውን ዘር ሲፈራለት በደስታ መቀበልና ሚስቱ ስታረግዝ መመልከት ...ምናልባትም ሰውየው ቀና ከሆነ ሚስትየዋን መንከባከብ ...ልጁም ከተወለደ በሁዋላ ምናልባት ፈቃደኛ ከሆነ ልጁን አልፎ አልፎ መንከባከብ ነው ድርሻው፡፡ ከዚህ ውጭ ብዙም የሚጉላላበት መንገድ የለም፡፡ እናም ሴቷም እንደወንዱ የመውለጃዋ ጊዜ ይራዘም ቢባል ኖሮ እንዴት እንደምትጎዳ መገመት አያቅትም፡፡

ወንዱ ግን ብዙም የሚንገላታበት መንገድ ስለሌለ እስኪያረጅ ድረስ ሴቶቹን እያስረገዘ ሊያስወልድ ይችላል፡፡ አቅም ባይኖረውም አቅም ካላት ሴት... ልጅ አግኝቶአልና ታሳድግለታለች፡፡ ስለዚህ እኔ አጋጣሚ ውን ብዙም አልኮንነውም፡፡ ሴቷ በሀምሳ አመትዋ መውለድ ማቆምዋ ከተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ከኑሮ ድርሻዋና ከአቅምም አኩዋያ ልንቀበለው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኩዋን ወንድና ሴት እኩል ናቸው ቢባልም በተፈጥሮአዊው ሁኔታ እና በሰዎች ባህርይ የተነሳ ግን የተለያየ አቀባበል ስለሚኖረው በእኔ በኩል ምንም እንኩዋን ሰው ሊለውጠው የማይችላው የተፈጥሮ ሕግ ቢሆንም ሴት ልጅ በሀምሳ አመት እድሜዋ መውለድ ማቆምዋን እስማማለሁ፡፡›› ( የወንድወሰን መርሻ/ከመርካቶ) የአቶ የወንድወሰን አስተያየት ሴቶች ልጅ ወልዶ በማሳደግ በኩል በተፈጥሮም ሆነ በማህራዊው መንገድ ብዙ ጫና ያለባቸው ስለሆነ የመውለድ ጊዜው አጠር በማለቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይደሉም የሚል ስሜት ያለው ነው፡፡

በተጨማሪም ሴቷ እድሜዋ ከገፋ በሁዋላ የምትወልደው ልጅም የጤና መጉዋደል ሊደርስበት እንደሚችል ማሳያ የሚሆን ምሳሌም አጋ ርተውናል፡፡ ተከታዩ አስተያየት ደግሞ የወ/ሮ የትምወርቅ ተወልደ ነው፡፡ ወ/ሮ የትምወርቅ ከጉርድሾላ አካባቢ ናቸው፡፡ ‹‹...እኔ በአሁኑ ሰአት እድሜዬ ወደ 56/አመት ደርሶአል፡፡ እድገ.. አዲስ አበባ ነው፡፡ በጣም ባይሆንም በምችለው አቅም ተምሬአለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ትምህርትን እንደትልቅ ግብ ያዩት ስለነበር እኔም ከትምህርት ውጭ ለሌላ ለምንም ነገር ቅድሚያ ሰጥቼ አላውቅም፡፡ ስለዚህም አብሮ አደግ ጉዋደኞቼ በተለያየ ጊዜ ትምህርታቸውን እያቋረጡ ለባል ሲዳሩ በጣም አዝን ነበር፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቢማሩ እንጂ ባል ቢያገቡ ምን ይጠቀማሉ የሚል ስሜት ስለነበረኝ ነው፡፡ በእርግጥ ዲግሪያቸውን ሳይይዙ በመሀከል መዳራቸው እንደ አንድ ጉድለት ሊቆጠር ቢችልም የልጆቹ የትምህርት የመቀበል አቅምም የሚወስነው እንደሆነ አልክድም፡፡

እየዋለ ሲያድር ከአንድ መንደር ሴት ልጆች አብረን ትምህርት ጀምረን ወደ ሶስተኛው የትምህርት ደረጃ የበቃነው ከሶስት በላይ አንሆንም ነበር፡፡ ከእነሱም መካከል ከዲግሪውም በሁዋላ እኔ ብቻ ባል ሳላገባ ቀረሁ፡፡ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ እንዲያውም ትዳር ምን ያደርጋል? ማለት ጀመርኩ፡፡ ከስራ ስራ መለዋወጥ...ተምህርትን በተለያየ ደረጃ..በስልጠና...በኮርስ... እየለዋወጥኩ መማር የመሳሰሉት ላይ ጊዜዬን ፈጀሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ ዲግሪ እና በማናጅመንት ማስተርስ ዲግሪዬንም ሰራሁ፡፡ ከዚህ በሁዋላ እንግዲህ ወደ 42/አመት ሲሆነኝ ነበር ፊ..ን ወደትዳር ያዞርኩት፡፡ እኔ ቤት ሰርቻለሁ፡፡ እኔ መኪና ገዝቻለሁ፡፡ እኔ ትምህርት ተምሬአለሁ፡፡ እኔ ጥሩ ስራ አለኝ ፡፡ እድሜዬ ሀምሳ አመት ስላልሞላኝ አሁን ልጅ መውለድ እችላለሁ፡፡ይህ ነበር የእኔ ውሳኔ፡፡ ነገር ግን አልተቻለም፡፡

ለካንስ ሀምሳ አመት ማለት ለሁሉም ሴት የእርግዝና መቋረጫው እንጂ እስከሀምሳ አመት ድረስ ሁሉዋም ሴት የግድ ትወልዳለች ማለት አይደለም፡፡ ባለቤ..ም እድሜው ወደ ስድሳ አምስት አመት ገደማ ስለሆነ ከዚህ በሁዋላ ልጅ አልፈልግም ይላል፡፡ እኔ ግን እሱ ፈቃደኛ ቢሆን ልጅ አስወልዶ ቢያመጣልኝ እና ባሳድግ እኔ ፈቃደኛ ነኝ፡፡››ከላይ ያነበባችሁት አስተያየት ኑሮን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት ሲባል ብዙ ሰዎች የሚወድቁበት ችግር ነው፡፡ በተለይም ሴቶች የመውለጃ እድሜያቸው ውስን መሆኑን ከግምት ውስጥ ባለማስገባት በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ልጅ የመውለድን እድል እንደሚያጡ እሙን ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገሮች ጎን ለጎን እየመሩ ተፈጥሮአዊ እድልንም ሳያጡ መኖር እንደሚቻል ይህ አምድ የጋበዛቸው ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ሙያዊ ምክር ይሰጣሉ፡፡ እንደ ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህር ማብራሪያ በወንዱም ይሁን በሴቷ በኩል ልጅን ለማግኘት የሚያስችሉት ተፈጥሮአዊ ቅመሞች በጊዜ ሂደት የሚዳከሙበት ሁኔታ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ የወንዶች የመውለጃ ሂደት ረጅም ጊዜ የሚቆይ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የመራቢያ እድሜያቸውም ከአስራዎቹ የሚጀምር ነው፡፡

በሴቶቹ በኩል ደግሞ ቀድሞ በ12/አመት እድሜ የወር አበባ ያዩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ወደ አስርእና ዘጠኝ አመት እየወረደ ነው፡፡ ስለዚህም የወንዶቹ የመራቢያ ሂደት ከአስራዎቹ ጀምሮ እስከ ሰባ አመት ድረስ ምንም ሳይዛባ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ወደ ዘጠናዎቹ ሲገባ ተስቲስ የሚባለው ሆርሞንን ወይንም የወንድ ሕዋስን የሚያመርተው አካል በስራው እየተጉዋተተ ብቃቱን እያጣ የሚመጣበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ወደሴቶች ስንመለስ ግን ከ20 - 30/ ድረስ ባለው እድሜ ከፍ ባለ ሁኔታ ልጅ የመውለድ ሂደት የሚኖር ሲሆን ከዚያ በሁዋላ ግን እንደ የእድሜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለመውለድ የሚያበቃው እንቁላል ብቃት እና ጥራቱን እየቀነሰ መመረቱም እያቆመ ስለሚሄድ ሀምሳ አመት ሲሞላ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል ብለዋል፡፡ ልጅ መውለድ አለመቻል የሚባለው ችግር በዚህ ዘመን እየበዛ በመምጣቱ ሰው ሁሉ ልዩ ትኩረት ሊያደርግበት እንደሚገባ ዶ/ር ሙሁዲን አሳስበው እድሜን በሚመለከት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ተመራጭ የሆነውን እድሜያቸውን ማሳለፍ የለባቸውም፡፡

ከወንዶች ይልቅ የሴቶች እድሜ ሳይንሳዊው በሆነው መንገድ አንዳንድ እርዳታዎችን ከማድረግ አኩዋያ ጭምር አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲያጋጥም ምክንያት መሆኑ በሕክምናው ዘርፍ የሚታይ ነው ፡፡ አንዲት ሴት በእድሜዋ በሀያዎቹ ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ የሚኖሩአት እንቁላሎች ጥራትና ብቃት እና እድሜዋ ሰላሳውን ከዘለለ በሁዋላ የሚገኘው ውጤት ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ምናልባት እስከ ሀምሳው መውለድ ትችላለች ቢባልም እንኩዋን አሁንም ተፈጥሮአዊ አቋሙ ወይንም ጥራቱ የሚለያይ መሆኑ አይካድም፡፡ ወንዶችንም ስንመለከት እድሜያቸው ከአርባ በላይ በሚሆንበት ጊዜ የእስፐርም ጥራትና ተግባር እየቀነሰ መምጣቱ ግድ ነው፡፡ እናም ምናልባትም የሴትዋም እንቁላል ሆነ የወንዱ የዘር ፍሬ ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት እንዲውል ቢፈለግ በእድሜያቸው መጠን የሚወሰን ይሆናል፡፡ ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ማብራሪያቸውን ሲያጠቃልሉ ሴቶች ሌሎች ፕሮግራሞችን አስቀድሜ ልጅ መውለድን ግን አቆያለሁ ማለት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከሰላሳ አመት እድሜያቸው በላይ መሆን የለበትም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በስፋት የሚመከረው ሴቶች ልጅ ከማርገዛቸው በፊትም ሆነ ካረገዙ በሁዋላ ሐኪም እንዲያማክሩ ሲሆን ይህንን ልጅን ከመውለድ ማዘግየት የሚለውንም አርእስት ይዘው ወደባለሙያ መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ ባለሙያውም ቁልጭ ባለ መንገድ ልጅን ማዘግየት ያለብሽ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ነው በሚል መነጋገር ይገባዋል፡፡ ከዚያ በላይ ብታዘገየው ግን ... * እድሜ ከገፋ በሁዋላ ልጅን ማርገዝ ከተለያዩ ሕመሞች ጋር ግጭትን ሊፈጥር እንደሚችል ፣ * እድሜ ከገፋ በሁዋላ የምትወልደው ልጅ በጤናውም ችግር ሊገጥመው እንደሚችል፣ * እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እድሜው ሀምሳ ባይደርስም ልጅ ማርገዝ መቻል አለመቻልን በግምት ማወቅ እንደማይቻል.. ማጣትም እንደሚኖር.. ...ወዘተ መንገር ይገባል፡፡ ወንዶቹም ቢሆኑ እስከ ሰባ እና ዘጠና አመት ወይንም ከዚያም በላይ መውለድ እችላለሁ የሚለውን ወደጎን ትተው ተመራጭ የሚሆነው ከ35-50/ አመት ባለው እድሜያቸው ልጅ ቢያስወልዱ ትክክለኛውና ቀልጣፋው ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ባማከለ መንገድ ልጅ እንዲወልዱ ምክር ይሰጥ ቢባል እስከ አርባ አመት እድሜ ቢሆን ይመረጣል እንደ ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ማብራሪያ፡፡ ከምንም በላይ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሊረዱት የሚገባው ነገር ተፈጥሮ የለገሰችውን ልጅን እድሜ ሳይገፋ ወልዶ በተገቢው ሁኔታ ተሩዋሩጦ ማሳደግ እና ጥሩ ምሳሌ መሆን እንደሚገባ ከግምት ማስገባት ይጠቅማል፡፡

Read 12359 times