Saturday, 06 April 2013 14:27

ቢራቢሮ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቢራቢሮ እንደ ደብተር ተከፍታ ደረቷን ለጧት ፀሀይ ሰጥታለች፡፡ ደስ ማለቱ! የጧት ፀሀይ ሙቀቱ! ሽው ብሎ በላይዋ ላይ አለፈ - አስደንጋጭ የድምቢጥ ጥላ ክንፏ ዝግት! ጸጥ! ከነድንቢጥ ሆነ ከሌሎቹ የሞት መላእክት ራሷን የምትከላከልበት አንድም መሳሪያ የላት፡፡ ወላ ጥርስ - ወላ ቀንድ - ወላ መርዝ - ምንም! ምክር ፍለጋ ዶክተር አሊ ዘንድ ሄደች፡፡ ዶክተር ኤሊ ጥንት ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ነበሩ፡፡ የመፃህፍትና የአበው ጥበብ በድንጋይ ልብሳቸው ሙሉ ተጽፏል እየተባለ ይነገርላቸዋል፡፡ “አበባን የፈጠርክ ፈጣሪ! አቤት አፈጣጠሩን ስታውቅበት! ኧረ ተመስገን!” እያለች ቢራቢሮ አበባዋ ላይ አረፈች፡፡ ወለላውን ልትጠጣ ብትሞክር ታድያ፣ በየት በኩል? ጥርሶቿ - እንዲያ በጥንቃቄ የመረጠቻቸውና እንዲያ ስትመካባቸው የቆየች ጥርሶቿ፣ አላስጠጣ አሏት፡፡

ይባስ ብለው ደሞ ያችን የጠራቻትን አበባ ቦጫጨቋት እነዚያ ባይተዋር ጥርሶች! ቅፅበታዊ ውስጣዊ ፀጥታ … ክንፏ ፀጥ እርጥ እስኪል ድረስ … “እንግዲያውስ ጥርስ ምን ሊያደርግልኝ ኖሯል? የኔ ምግብ እንደሆነ አይታኘክ፡፡ ለሳቅ ለፈገግታ እንደሆነ፣ የኔ ሳቅ ፈገግታዬ ክንፌና በረራዬ ውስጥ ያበራሉ፡፡ ሌላው ትርፍ ሸክም!” አለችና፣ እነዚያን የሾሉ ሹላሹል ጥርሶች ወድያ አሽቀንጥራ ጣለቻቸው (እዝጌርን ስትጐበኝ በስውር ሲሰልላት የነበረው ዲያብሎስ እንኳ ወደ ገሀነብ መቀመቅ ያን ያህል አልተወረወረም!) ከአበባዋ ወለላዋን ጠጣችና ጉዞዋን ስትቀጥል “ሆ! ኧረ‘ንኳንም ጥርስ አልፈጠረልኝ!” አለች፡፡

በሚቀጥለው ምእራፍ (ማለቴ በረራ) ቢራቢሮ ሲሾል የኖረ ሹል ጦሯን ወደ ሰማይ አሾለች አመቻቸችና፣ ክንፎቿን እስከ ጫፍ ዘርግታ ደረቷን ለፀሀይ ሰጥታ ስታበቃ “እነሆ በረከት! እነሆ ቢራቢሮ ለምሳ!” አለች፣ በክንፎቿ ክፍት ክድን የቢራቢሮ ሳቅ እየሳቀች፡፡ ሽው! ብሎ ወረደ - ለቢራቢሮ ሞትን የጫነ ድምቢጥ! ከሰማይ ያመጣችው ጦር ጥልቅ ሲልበት፣ ከህመሙ ይልቅ መገረሙ፣ መደንገጡ ብሶበት እዚያው ክንችር አለ፡፡ “አይ አቶ ድምቢጥ! ለካ የተጫንከው የኔን ሳይሆን የራስክን ሞት ኖሯል! ተመስገን!” እያለች ቢራቢሮ ሆዬ፣ ጦሩን ከድምቢጥየው ሬሳ ላይ ለመንቀል ብትሞክር ብትፍጨረጨር፣ እሷ ትቦጨቅ እንደሆነ እንጂ ጦሩ የማይነቃነቅ ሆነ፡፡ ደሞስ የደሙ ክርፋት! “እንግዲያውስ ጦር ምን ሊያደርግልኝ ኖሯል? ገድያቸው እንዲህ ከሚገሙኝ፣ እንዲህ እንደ ሰይጣን ፈስ ከሚከረፉኝ፣ ብቅ ሲሉ ክንፌን እጥፍ አድርጌ አልሰወርባቸውም? ይሻለኛልም ይቀለኛልም አለችና ጦሩን እዚያው ለድምቢጡ “ማስታወሻ ይሁንህ፣ ትቼልሀለሁ” እያለች ወደ ሰፈሯ ሄደች (ማለቴ በረረች)

 ሌላ የቢራቢሮ ምእራፍ (ማለቴ በረራ) እነሆ፡- ውድቅት ነው፡፡ ፍጡራን እንደየ ፍጥርጥራቸው በየፊናቸው ሲመገቡ አርፍደው፣ እንደአይነታቸው ውሀ ቸውን ጠጥተው፣ በየስፍራቸው እፎይ ብለው በማረፍም በማንቀላፋትም ላይ ናቸው፡፡ ይህን ጊዜ ቢራቢሮ አበባ ላይ ተመቻቸችና እዝጌር የሰጣትን፣ ከአንበሳ ጩኸት ሰባት ጊዜ ጐልቶ የሚጮኸውን አዲስየውን ጩኸቷን ለቀቀችው! ፍጡራን ከመበርገግ የባሰ በረገጉ፣ ብዙ ሯጮች ወለም አላቸው፣ በርካታ በራሪዎች ክንፋቸውን ቅርንጫፍ አቆሰላቸው፡፡ ፍጡር ሁሉ በየበረገገበት እንደየፍጥርጥሩ አደፈጠ፡፡ ብዙ ብዙ ቆይቶ በየፊናው አደጋውን ለማየት እዚህም እዚያም ተገላመጠ፡፡ ማንም የለም፡፡ ቀስ በቀስ ወደየስፍራቸው ተመለሱ፡፡ “እኔ ብቻ ሳልበረግግ” አለች ቢራቢሮ “እሱን ተይው! ያልበረገገ የለም” አሉዋት “ከኔ በስተቀር” “ኧረ ባክሽ? አሁንስ አንጎልሽም እንደ በረራሽ አበደ'ንዴ? አንበሳ ራሱ በርግጓል እንኳን አንቺ” “ሸረሪት ትጠየቅ” አለችና ቢራቢሮ የውልብልብ እየበረረች ሄደች … … እንግዲህ ሸረሪት ስትበረግግ መብረር ወይ መሮጥ ሳይሆን፣ ጥልቅ! ድብቅ! ሽፍን! ነው በዚያ በድርዋ - የምግብ ማግኛ መሳሪያዋ - ልብሷ - ቤትዋ - እንቁላል መጣያዋ - በጥበቧ ከገዛ ውስጧ የፈጠረችው ድርዋ፡፡ የምን ከንቱ ልፋት? ጥበቡን ሰጥቷታል፡፡

እና ከተሸሸገችበት ቀስ ብላ ብቅ ብትል፣ ቢራቢሮ ሆዬ አበባዋ ዙሪያ እየበረረች፣ ራሷን በራሷ እያባረረች በሳቅ ትንከተከታለች - የክንፍ ሳቅ “በረራሽ የእብድ መሆኑን አይቻለሁ” አለቻት ሸረሪት፡፡ ግን ፍጥረትን በሙሉ የሚያስበረግግ ጩኸት ሲያስቅሽ ሰባቴ ነው ያበድሽው፣ አንዴም አይደለ” “ያላስበረገገኝ ምክንያቱ የጮህኩት እኔ ራሴ ስለሆንኩ ነው’ኮ!” አለቻት - ቀለማት ክንፎቿን እያክነፈነፈች፡፡ “እየባሰብሽ ሄደ፡፡ አሁንማ ሰባ ጊዜ ሰባት አበድሽ!” ቢራቢሮ በረራዋን ትታ አበባዋ ላይ ቆመች - ተቀመጠች - ተሰየመችና፡- “አንቺ ተአምራዊ ድር ሊኖርሽ ከቻለ፣ እኔ ሃያል - መርእድ - መደንግጽ ጩኸት ሊኖረኝ ለምን አይችልም? ወይስ የተፈጥሮን ምስጢር ሁሉ ታውቂዋለሽ?” ሸረሪት ብዙ ስለማትንቀሳቀስ በጥሞና ለማሰብ ጊዜ አላት፡፡ ያውም ከድርዋ እኩል ተአምር የሆኑ ሀሳቦች፡፡

እርጋታ አለ ሸረሪት ቤት (ማለቴ ድር) ተረታችን ውስጥ፣ የመነኑት ባህታውያን እርጋታን ለመማር ወደ ሸረሪት ያተኩራሉ፣ ለሰባት ሙሉ ሰአት! (ያሬድ ማህሌታይን ሰባት አመት እናስታውሳለን) ስለዚህ ሸረሪት በእርጋታ “አሳምኚኝ” አለቻት ቢራቢሮን፤ “አዳሜ ፍጡሬ ከብርገጋዋ ተመልሳ በየስርፋዋ ታርፋለች፣ እማደል? ያን ጊዜ ትኩር ብለሽ እዪኝ፡፡ እጮሀለሁ፣ ይበረግጋሉ፡፡ አንቺ ግን ስጮህ እያየሽኝ ስለሚሆን አትደነግጪም” እንደተባባሉት ፍጡር ሁሉ እንደየድፍረትዋ፣ በየተራዋ በየስርፋዋ ተመልሳ አረፈች፡፡ ቢራቢሮ ለምናልባቱ ሸረሪትን ለማስጠንቀቅ ጥቂት በራረረች … አበባዋ ላይ አረፈች … እና ድምፁን … ጩኸቱን … ከፈጣሪ ቤት ያመጣችውን (እና፣ እብድም ይጠነቀቃልና፣ በጥንቃቄ የክንፏን ቀለም አስመስላ ክንፉ ላይ ለጥፋ ደብቃው የነበረውን ጩኸት) አነሳችና፡- አንድ ጊዜ ስትጮኸው ጊዜ፣ ፍጡሬ አዳሜ እንደ ቅድሙ አልበረገገላችሁም!? ቢራቢሮ እየበረረች ባበባዋ ዙሪያ በክንፏ ስትስቅ … ስትስቅ … ስትስቅ … “እሽ! እስቲ ዝም በይ አንዴ” አለቻት ሸረሪት “ሳይመለሱ ስሚኝ፣ ሲመለሱ ምንም እንደማናውቅ እናስመስል፡፡

በኋላ በየስርፋቸው ጩኸትሽን ስጪኝና አንዴ ልጩኸው” “እኔ ገና አልጠገብኩትማ!” “ተይ ተይ ተይ! አንዴ ብቻ? እሺ እንለዋወጥ፡፡ ያንቺን ጩኸት ላንዴ ብቻ ስጪኝ፣ የኔን ድር ጥበብ አስተምርሻለሁ፡፡ አቤት አንዴ ብትወዘውዢ! በኔ ድር! ሸሪሪት በሆንኩ! ትያለሽ፡፡” “እሺ” አለቻትና ተለዋወጡ፡፡ ቢራቢሮ በሀር ክር ጥቂት ከተወዛወዘች በኋላ ሰለቻትና “እንቺ ድርሽን፡፡ እኔ መሄዴ ነው” አለቻት “አንዴ’ንኳ ሳልጮህባቸው? ያውም እሺ ብለሽኝ?” “ኧረ አስር ጊዜ ጩሂ ተፈለግሽ! ጩኸቱን መርቄልሻለሁ” “ገና አልጠገብኩትም አላልሽም?” “አሁን ጠገብኩታ” አለችና ቢራቢሮ፣ የውልብልብ እየበረረች ሄደች “ደሞ ጩኸት ምን ያደርግልኛል?” እያለች ለራሷ “ትርፉ ሸክም!” ሸረሪትም “ቢራቢሮን ያሳበድክ ተመስገን!” እያለች ጩኸቱን ለእንስሳቱ እያከራየች እጅጉን ከበረች፡፡ ምን መክበር ብቻ? ሚሊዬነር ሆነች፡፡ ለፈጣሪ ምን ይሳነዋል? እያለች

Read 5122 times