Saturday, 06 April 2013 14:33

ስልቻ ተበላሸ፡፡ ምኑጋ? ሲነፋ፡፡ ሲነፋ አይደለም፣ መጀመሪያ ሲገፈፍ ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ሰው፣ ለወዳጆቹ የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፈ፡፡ ኑ አቃብሩኝ ዛሬ የጥንቱ የጠዋቱ ወዳጃችን አቶ “ማኅበራዊ-ብስለት” (Common Sense) የቀብሩ ሥነ ስርዓት ስለሚካሄድ ቀብር ላይ ተገኝታችሁ አብረን እንቀብረው ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደምታውቁት አቶ “ማህበራዊ-ብስለት” የሁላችንም የረዥም ጊዜ ወዳጅ ነው፡፡ ዕድሜውን ማንም አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ከልጅነቱ ጀምሮ በቢሮክራሲው ቀይ-ጋዲ (bureaucratic red tape) በየጊዜው እየተተበተበና እየታሠረ በመኖሩ ነው፡፡ ትቶልን የሄደው ቅርስ ግን አይረሴ ትምህርት ነው፡፡ ይኸውም፡- ከዝናብ መቼ መውጣትና መጠለል እንዳለብን በጠዋት የተነሳች ወፍ በጊዜ ቀድማ ትል መያዝና መብላት እንደምትችል ህይወት ሁሌ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነችና ሁሌም ሚዛናዊ ሆኖ እንደማናገኛት ምናልባት ጥፋቱ ከኔ ነው ብሎ ማሰብ እንደሚገባ፡፡ “ማኅበራዊ-ብስለት” በህይወት ሳለ፣ ህይወትን ቀለል አድርጎ የሚያይ ከመሆኑም በላይ፤ “ከምታገኘው በላይ አታውጣ! አታጥፋ” የሚል የፋይናንስ ስትራቴጂ እየተከተለ ነበር የሚኖረው፡፡

በተጨማሪም አዋቂዎች እንጂ ልጆች ኃላፊነት እንደሌለባቸው እንድንገነዘብ አስተምሮናል፡ “ማኅበራዊ - ብስለት” ጤንነቱ ድንገትና በፍጥነት መታወክ የጀመረው ለመልካም ታስበው የተፀነሱት ህግጋትና ደምቦች ከታወጁ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ይኸውም፤ አንድ የ6 ዓመት ህፃን የክፍል ጓደኛውን ፆታዊ ጥቃት አድርሶባታል ተብሎ ሲከሰስ፣ አስተማሪ ተማሪ አባረረ ተብሎ ሲከሰስ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በግብረ-ገብነት ገርተው መያዝ ሲገባቸው፤ አስተማሪዎችን ሲወቅሱ፤ ወላጆች የተማሪዎችን የፀጉርና የፊት-ቅባት አጠቃቀምን፤ እንዲሁም የአስፕሪን አዋዋጥን በተመለከተ የምክር አገልግሎት ያገኙ ዘንድ ት/ቤት ድረስ ሲጠሩ፤ ያም ሆኖ ሴት ልጃቸው ማርገዝዋንና ማስወረድ እንደሚያስፈልጋት ሳይነገራቸው ሲቀሩ፤ “ማኅበራዊ-ብስለት” ታሞ አልጋ ላይ ዋለ! እጅግ በሽታው የባሰበትና መኖር ያስጠላው ደግሞ፤ ቤተክርስቲያኖች የንግድ ቦታ ሲሆኑና ወንጀለኞች ወንጀል ከተፈፀማባቸው፤ ከተበዳይ ወገኖች ይልቅ፤ ምቾትና እንክብካቤ ሲደረግላቸው ሲያይ ነው፡፡ ህይወት እጅግ በጣም ከፍታ ውጪ-ነብስ፣ ግቢ-ነፍስ የሆነበት ደግሞ፤ ዘራፊ ወሮ-በላ፤ ሰው ቤት ገብቶ ባለቤቱ መከላከል ሲያቅተውና ዘራፊው ራሱ ዘርፎ ሲያበቃ፣ ራሱ ከሳሽ ሆኖ ሲገኝ ነው! በመጨረሻ ፍፁም ተስፋ የቆረጠውና ለጣር የበቃው ግን፤ በአሁኑ ዘመን፣ እንፋሎቱ እየተነነ ያለ ቡና ትኩስ መሆኑን መገመት ያቃታት ሴት ሲያይ ነው፡፡

ትንሽ እጭኗ ላይ ጠብ ስታደርግ ዋጋውን አገኘች!! “ማኅበራዊ ብስለት” ሲሞት፤ አምስት ልጆቹን እዚህ አገር ትቶ ነው የሄደው፡፡ ሦስቱ የእንጀራ ልጆቹ ናቸው፡፡ ስማቸውም - (የመጀመሪያው) መብቴን አውቃለሁ (ሁለተኛው) አሁኑኑ እፈልገዋለሁ (ሦስተኛው) ጥፋተኛው ሌላ ሰው ነው (አራተኛው) እኔ ተበዳይ ነኝ (አምስተኛው) ምንም ሳልሠራ ክፈለኝ፤ ይባላል፡፡ ብዙ ሰዎች ቀብሩ ላይ አልተገኙም፡፡ ምክንያቱም “ማኅበራዊ-ብስለት” መሞቱን አላወቁም፡፡ አሁንም “ማኅበራዊ-ብስለትን የምታስታውሱት ካላችሁ ይህንን ልቅሶ ላልሰሙ አሰሙ፡፡ ካልሆነ፤ ከብዙሃኑ ጋር ምንም ሳትሠሩ፣ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ፡፡ የጥንት ወዳጃችሁ በማናቸውም ህይወታችን ረገድ፣ በየእርከኑ ከሚያጋጥመን ውሽንፍር-አዘል ዝናብ የምናመልጥበትና የምንጠለልበት ልዩ ብስለት ያሻናል፡፡ ጊዜን ለይተን፣ በጠዋት ነቅተን፣ ግባችንን ለመምታት የጧት - ተነሽ (ማላጅ - Early – riser እንዲሉ) መሆን ይገባናል፡፡ ዘርቶ፣ አጭዶ፣ ወቅቶና ጐተራ ከቶ፣ ከዚያም አብስሎና ቆርሶ፣ የሚያበላንና የሚያኖረን ከራሳችን በቀር ማንም የለም፡፡ የባዕድ አንጐል እንጂ የባዕድ እጅ ማየት የለብንም፡፡ የመተሳሰብ፣ የመቻቻል፣ የመማማር ክህሎት መጀመሪያ አንቀጽ፤ እኔ ተሳስቼስ ቢሆን? የማለት ትሁት ብስለት ነው፡፡

“ተጣልቶ ለመታረቅ የማይችል ወይም የማይሻ፤ ካብ - አይገባ - ድንጋይ ነው፡፡ ሳይጣላ የሚታረቅም ያለዕዳው ዘማች ነው” ይላሉ አበው፡፡ አንድ ብስለት ይሄን ማወቅ ነው፡፡ የብስለት ሌላኛው እጁ ሰው ከሰው መቻቻሉ ነው፡፡ ሎሬት ፀጋዬ በ”ነይ መርካቶ” ግጥሙ እኒህን መስመሮች ለግሶናል-እንድንቻቻል፡- “በአራዳው ጊዮርጊስ ፈረስሽ፣ ተንጠራርተሽ እስከአንዋር “ኪራራ ይሶን” ጥሪሽን፣ አሸጋግረሽ “በአላህ አክበር” በአባ መቻል ላይ ድልድይሽ፣ ታጅበሽ እስካማኑኤል ዳር በአባ መቻል ላይ ድልድይሽ፣ ታጅበሽ እስካማኑኤል ዳር መርካቶ ነይ እንደገና፤ ፀሎታችን ይታደግሽ ምርቃታችን ያካብትሽ፣ የከርታቶች መጠለያ መርካቶ ያዲሳባ አድባር ከሰባት ቤት ጉራጌሽ ቤት፣ ከኦሮሞሽ አውድማ ዳር ከወሎሽ ጀበና መጀን፣ ከጊሚራው በርሽ አፋር ከአማራሽ የሰብል አውጋር፣ ከጎጃም በረንዳሽ ግንባር እንደገና ነይ መርካቶ፡፡ ሌላው ብስለት የወራሽና አውራሽ መንገዳችን ነው፡፡ አዲሱ አሮጌውን መተካቱ፣ ገፍቶ መጣሉ ወይም ከናካቴው ማጥፋቱ፤ ያለና የነበረ ዲያሌክቲካዊ ሀቅ ነው፡፡ “በሕግ አምላክ”፣ “በንጉሥ አምላክ!” ብሎም ቢሆን፤ መግፋት የተለመደ ነው፡፡

“ወድቆ በተነሳው ነው ተነስቶ በወደቀው ባንዲራ የሚባለው?” ትላለች አንድ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ዕብድ ገፀ-ባህሪ! ስለመተካካት ስናስብ አንድ አንድ መሠረታዊ ነቁጦችን ልብ እንበል፡፡ “ከአንተ ቀድሞ በነበረው ባለሥልጣን ወይም አባት ሰው፤ የተለየሁ ነኝ ብለህ ታምን ይሆናል፡፡ ሆኖም እያደግህ ስትሄድ እስከወዲያኛው ቆራጥ ካልሆንክ ተፃርረኸውና አምፀኽበት የነበረውን አባትህን ትሆናለህ” ይላል አንድ የፖለቲካ ፀሀፊ፡፡ አባትህን መተካት በአያሌው ያንተን ፅንዓት ይጠይቃል፡፡ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፤ ሲል ነው፡፡ “ውሎ አድሮ አንተ የራስህን አባት መሆንህን አትርሳ! ስለዚህም ዞረህ ዞረህ መከላከያህን መክነህ፣ ጭምብልህን አውልቀህ ያው የትላንቱ ጣረ-መንፈስ ማለትም፤ አባትህ፣ ልማድህና ታሪክህ-መልሶ መምጣቱ ላይቀር፤ ሌላ አንተነትህን ለመፍጠር ስትፍጨረጨር ዕድሜህን አትፍጅ” የሚለውን አፅንዖት ይሰጠዋል ያው ፀሀፊ፡፡ ሆኖም አንድን ዕውነት ዋና መልሕቅ አድርጐ ጠንካራ አደራ ያሰፍራል፡፡

በግጥም ስናስቀምጠው የቁም ነገሩ ቡጥ የሚከተለው ነው፡፡ “አየህ፤ ከትላንትህ ተጋጭተህ፣ ትላንትናህ ላይ አምፀህ ጉልላት አናት የወጣህ፤ ግርጌህ ያሉትን አትርሳ፤ ከቶም ዐይንህን አትንቀል አመፃ ያንተው ቅጂ ነው፣ በተከሉት የሚተከል! ይነሳሉ፤ ያው እንዳንተው አንድም ዕድል አትስጣቸው፤ ካይንህም አታርቃቸው ወንድሜ ዕንቅልፍ አይጣልህ፣ መንገዱ ያንተው መንገድ ነው!!” በሀገራችን ረጅም የፖለቲካ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ከመሠረቱ የተበላሹ ስህተቶች እንደጥቁር ጥላ ይከተሉናል፡፡ እንደ ዲሞክራሲ፤ እንደ ኤትኒክ-ፌዴራሊዝም፣ ስለ ጠረጴዛ ውይይት፤ ማለትም ስንታረቅና ስንጣላ፣ ስንደራደርና ስንግደረደር ብስለት ለማጣታችን፣ እንደምርጫ፣ እንደ ዕርቅና ሽምግልና ያሉ፤ አንጓ አንጓ ጉዳዮች ከነእንከናቸው ያሳድዱናል፡፡ መሻሻል፣ መቃናት፣ ፈር-መያዝ አለባቸው፡፡ “አሳማ ነው እንጂ ጨዋ ወደ ትፋቱ አይመለስ” ይላል ገጣሚው፡፡ ከውሉ፣ ከመሠረቱ ያለውን መርምሮ፣ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሳይሉ፤ ማቃናት ደግ ነው፡፡ ለዚህም፤ “ስልቻ ተበላሸ፡፡ ምኑጋ? ሲነፋ፡፡ ሲነፋ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ሲገፈፍ ነው”፤ የሚለውን ተረትና ምሳሌ ልብ ማለት መልካም ነው፡፡

Read 4266 times