Monday, 08 April 2013 09:36

‹‹ በ‹‹አይፋ›› እየተጓጓዝን ነበር የምንሠራው ›› አርቲስት ጸጋዬ እሸቱ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ዱሮ የሠራሃቸውን ዘፈኖች እንደገና ተቀርጸሐል፤ ከአሁኑና ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር እና ቴክኖሎጂ የትኛው ተሻለህ?

ከሃያ አራት ዓመታት በፊት የነበረው ጊዜ ስህተት ላለመሥራት የምንጠነቀቅበት በጣም ከፍተኛ የኾነ ትግልና ልፋት የሚጠይቅ፣ ጊዜ ነበር፡፡ እኔ በተለይ የመጀመሪያውን አልበሜን ላወጣ ሥራዬን ከሮሃ ባንድ ጋር ሠርቼ ካጠናቀቅኹ በኋላ ባንዱ ሁለት ዘፈኖችን እንዲያስተካክል አሣታሚው ሲጠይቃቸው ሥራ ስለሚበዛባቸው ይሁን መሥራት ባለመፈለጋቸው ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀሩ፡፡

ዘፈኖቹን ናሙናው ላይ እንደነበሩት አድርጌ አለመምራቴን አሣታሚው ስላመነበት ሌላ ስቱዲዮ ገብተን ሁለቱን ዘፈኖችና ሁሉንም አፍርሰን በአንድ ዓይነት አሠራር ለመቅረጽ ተስማምተን እንደገና ሠራናቸው፡፡ ሙዚቃውን የሠሩት ፈለቀ ኃይሉ፣ኃይለእግዚአብሔር ገዳሙና ነፍሱን ይማረውና ደረጀ ተፈራ ነበሩ፡፡ የቀረጸው ደግሞ እሱንም ነፍሱን ይማረውና አሣታሚው የ‹‹ሶል ኩኩ›› ባለቤት ሣህለ ነበር፡፡ ሙዚቀኞቹ ከሮሃ ባንድ የወጡ ስለነበሩ ‹‹አሞራ ባንድ›› የሚል አዲስ ስም አውጥተው አብረን ጥሩ ነገር ሠራን፡፡ ለእኔ ግን በጣም ፈታኝ እና አድካሚ ነበር ፡፡

ጨረስኩ ብዬ ሳስብ ከአንድ ባንድ ወደ ሌላ ባንድ ተሸጋግሬ መሥራቴ በጣም ልፋት ነበረው፡፡ ቴክኖሎጂውን በሚመለከት የመጀመሪያውን አልበሜን ዘፈን ለመቅረጽ ስንሰባሰብ ሰባራ ባቡር ይባል በነበረው ሰፈር ውስጥ አነስተኛ ሙዚቃ ቤት እና ከጀርባው ደግሞ ትንሽዬ ስቱዲዮ የመሰለ ቤት የነበረው ተክሌ ተስፋዝጊ ጋር ነበር የምንሠራው፡፡ ቤቷ በጣም ጠባብ ስለነበረች ሁላችንም በቅርበት ተጠጋግተን ዙሪያ ሠርተን ነበር የምንቀርጸው፡፡ ሁለተኛውንም አልበም ስሠራም ከ‹‹ሶል ኩኩ›› ሙዚቃ ቤት ጋራ በጋራ ይሠራ የነበረው የ‹‹ናዲ›› ሙዚቃ ቤት ባለቤት የእነኑረዲን መኖሪያ ቤት እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ይገኝ ነበር፡፡ ሳሎን ቤታቸው ሰፋ ያለ ስለነበር እዛ ነበር የቀረጽነው፡፡ ዘፈኑ የሚቀዳው ደግሞ በዴክ ስለነበር ሁሉም ነገር የሚቀረጸው አንድ ላይ ነበር፡፡

ቀረጻው ከተበላሸ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደገና ይቀዳል፡፡ ዛሬ ግን እኔ ባበላሽ የሚደገመው የእኔ ብቻ ነው ያውም ያበላሸኋት ቦታ ተለይታ፡፡ አንዱ ሙዚቀኛ ቢበላሽበትም እንደዚያው ለብቻው ገብቶ ይሠራዋል፡፡ የአሁኑ አደረጃጀቱም ኾነ የድምጽ መቅረጫ መሳሪያዎቹ ዘመናዊነት የሚያጠያይቅ አይደለም ከዚህ አንጻር ሳየው የቀድሞው የእኛ ልፋት ተወዳዳሪ አይገኝለትም፡፡ ለድምጻዊው ግን በጣም ጠቃሚ የኾነ አሠራር ነበር፡፡ ለዘፈኖቹ ከፍተኛ ግምት በመስጠት በተደጋጋሚ ጥናት የዳበረ ሥራ ስለሚኾን ወደ ሰው ጆሮ ሲደርስ የሚደመጥ ያደርገዋል፡፡ መድረክ ላይ ሲወጣም የተዋጣለት ሥራ ለመሥራት ያስችላል፡፡

ዛሬ ለሥራው ግምት አይሰጥም ማለቴ ሳይኾን ያለምንም ጥናት በአንድ ቀን ሁሉንም ነገር የሚጠናቀቅበት አሠራር አለ፡፡ ከዚህ አንጻር የዛን ጊዜውን ያህል የጠነከረ ሥራ ይሠራል ማለት ይከብዳል፡፡

ዘፈኖቹን የተቀረጽከው እንደ አዲስ በመኾኑ ልፋቱ እንዴት ነበር?

ዘፈኑን የሚያውቁትን ባለሞያዎች አሰባስቤ በክብረት መሪነት የተሠራ ነው፡፡ ዘፈኖቹን በጥሩ ሁኔታ ያደራጃቸው እና በሙዚቃው ሕግ መሠረት መስመር ያስያዘው ደግሞ ፈለቀ ነው፡፡ እኔ ድምጼን የሰጠሁት ፈለቀ አስተካክሎ ባመጣው ሙዚቃ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ሙዚቀኞቹ ገብተው ሠሩት፡፡ በዚህም ምክንያት ምንም የሥራ ጫና ሳይኖርብኝ በተረጋጋ ሁኔታ ነው የሠራነው፡፡ በዚህ በኩል ባለሞያዎቹ ትልቅ አስተዋፆ አላቸውና ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

ለምን እንደገና መሥራት ፈለክ?

ዘፈኖቼ በብዛት የነበሩትና አሁንም ያሉት በኦዲዮ ካሴት ላይ ነው፡፡ የዛን ዘመን ቴክኖሎጂ እየቀረና በአዳዲስ እየተተካ ሲመጣ ይህ ትውልድ ከእኔ ዘፈን ጋር እየተራራቀ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት አደረብኝ፡፡ ዕድሜዬም ለዱላ ማስያዝ ከመድረሱ በፊት መዘጋጀት እና ለትውልዱ አንድ ነገር ትቼ ማለፍ አለብኝ በሚል አስቤ ነው እንደ አዲስ ስቱዲዮ ገብቼ ነው የሠራሁት፡፡ ዘፈኖቹን ከየአልበሞቹ ላይ እንዴት መረጥካቸው? ለሰው ጆሮ ቅርብ ናቸው ያልኳቸውን ዘፈኖች ነው የመረጥኩት፡፡ በዛን ዘመን ዘፈን ስናወጣ የአልበም ስያሜ አልነበረውም፡፡ አንዱን ዘፈን መርጠን ነው መጠሪያ የምናደርገው፡፡ ‹‹እሄዳለሁ ሐረር›› የሚለው ዘፈን ካለበት የመጀመሪያው አልበም ላይ ስድስት ዘፈን መረጥኩ፡፡ ‹‹ለሠርጓ ተጠራሁ›› ካለበት ሁለተኛው አልበም ደግሞ አራት ዘፈን መረጥኩ፡፡ ከሦስተኛው አንድ ዘፈን መረጥኩና ሌሎቹን ከተለያዩ ድምፃውያን ጋራ ከሠራኋቸው ኮሌክሽኖች በአጠቃላይ 14 ዘፈን ነው መርጬ በድጋሚ የሠራሁት፡፡ በምርጫዬም የተከፋ ሰው የለም፡፡

ከቀድሞው ጋራ የድምፅ ልዩነት የለውም?

ብዙ የተለየ ነገር የለውም፡፡ ምናልባት በጉርምስና ወቅት የተሠራና ዕድሜ 40ን ካለፋ በኋላ የሚሠራ ሥራ ትንሽ ልዩነት ያመጣል የሚል ሐሳብ ከተነሳ አሁን ያኔ ከነበረኝ ነገር ትንሽ በሰል ያልኩበት ሥራ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለውን ዘፈን ለምን አላካተትክም ያለህ የለም? እንደሱ የሚልማ በጣም በርካታ ሰው አለ፡፡ በአብዛኛው የሚወደውን ዘፈን እያስታወሰ ለምን እንዳስቀረሁት ይጠይቀኛል፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉኑም ዘፈን ማካተት ስለማይቻል የቀሩትን ዘፈኖች አሰባስቤ የማውጣት ሐሳብ እንዳለኝ እነግራቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ይፋ በማላደርገው መንገድ የምሠራው አንድ አልበም፣ አንድ አልበም ደግሞ በተለመደው ስልት የምሠራው እንዲሁም ከአብርሃም ወልዴ ጋራ አንድ ነጠላ ዜማ እስከነ ቪዲዮ ክሊፑ የመሥራት ዕቅድ ስላለኝ እነዚህን ስጨርስ በኦዲዮ ካሴት ያሉትን ሁሉንም ሥራዎቼን አሰባስቤ ወደ ሲዲ መቀየር እፈልጋለሁ፡፡

ከመጀመሪያው አልበምህና ከአሁኑ በወጪ ደረጃ የቱ ፈታኝ ነው?

የመጀመሪያውን አልበሜን ስሠራ ሁሉንም ወጪ የሸፈነው ሙዚቃ ቤቱ ነበር፡፡ እኔን ከፍሎ አዘፈነኝ እንጂ ለማን ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈለ የማውቀው ነገር እንኳን አልነበረም፡፡በወቅቱ የማውቀው ነገር ቢኖር ለሮሃ ባንድ ተከፍሎት የነበረውን ዐስራ አንድ ሺሕ ብር ብቻ ነው፡፡ሆኖም የቱንም ያህል ቢከፍል አሁን እኔ ለዜማ፣ለግጥም እና ለቅንብሩን ካወጣሁት ወጪ ጋር የሚደራረስ አይሆንም፡፡ እኔም አሁን ማስተሩን ለናሆም ሪከርድስ የሸጥኩበት ዋጋ ያኔ ከተከፈለኝ ጋር በፍጹም የሚቀራረብ አይደለም፡፡

ለመጀመሪያው አልበም ሥራህ ሙዚቃ ቤት ያገናኘህ ኮመዲያን ልመንህ ነበር፡፡ ኮሚሽን ከፍለኸው ነበር?

ልመንህ ታደሰ እኔን ብቻ ሳይኾን ነፍሱን ይማረውና ኬኔዲ መንገሻንም ከሶል ኩኩ ሙዚቃ ቤት ጋራ ያገናኘው እርሱ ነበር፡፡ እኔ በዛን ጊዜ የተዋዋልኩት በሦስት ሺሕ ብር ነበር፡፡ ግማሹን መጀመሪያ ተቀብዬ ቀሪው መጨረሻ ላይ ነው የተከፈለኝ፡፡ በወቅቱ ደግሞ አብረን አንድ ኪነት እንሠራ ስለነበር እርሱም ስጠኝ አላለኝም እኔም ኮሚሽን አልከፈልኩትም፡፡ በዛን ጊዜ ደግሞ ኮሚሽን የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር፡፡

ሐሳቡም ቢተነፈስ ክፍያ የሚጠየቅበት ዘመን ላይ የደረስነው አሁን ነው፡፡

ልመንህን አግኝተኸው ታውቃለህ?

አሜሪካ እያለ በብዛት አገኘው ነበር እዚህ ከመጣ በኋላ ግን አግኝቼው አላውቅም፡፡ ለማግኘት በጣም ሞክሬ ነበር ስልም አልዋሽም፡፡ አልበምህን ባወጣህ ሰሞን ወደ ድሬደዋ እና ሐረር ለ27 ቀናት ኮንሰርት ሠርተህ ነበር ክፍያው ጥሩ ነበር? ለሥራው የወሰዱኝ ጅጅጋ ውስጥ የነበሩ የወታደር ባንድ ነበር፡፡ በቀን 700 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ መድረክ ላይ በወጣሁ ቁጥር ደግሞ ሽልማት ነበረኝ፡፡ የሄድኩት አልበሜ በወጣ በአንድ ወሩ ስለነበር በዚያች በአጭር ጊዜ ድሬደዋ፣ሐረር፣ጅጅጋ፣አለማያ፣ ሂርና እያዞሩኝ ስዘፍን ሕዝቡ ዘፈኖቼን ለምዶና ወዶት ስለተቀበለኝ ገንዘቡ ላይ ትኩረት አላደረኩበትም እንጂ የቆየሁበት ቀናት ተቆጥሮ ለወቅቱ በጣም ጥሩ ክፍያ ነበር የተከፈለኝ፡፡ በዛ ላይ ሁሉንም ወጪዬን ችለው እንዲሁም የምንጓጓዝበትን ትራንስፖርት ሸፍነው ስለሚያንቀሳቅሱኝ የሰጡኝን ገንዘብ ሳልነካው ነበር አዲስ አበባ የተመለስኩት፡፡

በምን ነበር የምትጓጓዙት?

ዘፋኝ ስለነበርኩ ጋቢና ይታዘዝልኛ እንጂ በ‹‹አይፋ›› (ትልቁ የወታደር መኪና) እየተጓጓዝን ነበር የምንሠራው፡፡

ምን ዓይነት መድረክ ላይ ነበር የምትሠራው? ምን ያህል ሰው ይታደም ነበር?

በተለያዩ አዳራሾች ውስጥ ነበር፡፡ እኛ ከመድረሳችን በፊት ከተማ ውስጥ እየገቡ የሚቀሰቅሱ ልጆች ስለነበሩ የከተማውን ሰው አነቃቅተው ይጠብቁናል፡፡ በአንድ መድረክ እስከ 400 ሰው ይታደም ነበር፡፡ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር፡፡

‹‹እሄዳለሁ ሐረር ባቡር ተሳፍሬ›› የሚለው ዘፈንህን የሚያዳምጡ ሰዎች ‹‹አንደኛ ሐረር ባቡር የለም፡፡ ሁለተኛ እርሱ የሚለውን ፍራፍሬ የለም›› ሲሉ ይወቅሱሃል፡፡ የቪዲዮ ክሊፑንስ እዛው ሄደህ ነበር የተቀረጽከው?

አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ስቱዲዮ ውስጥ ነው የተቀነባበረው፡፡ ግን ቦታው ሂርና አካባቢ ነበር፡፡ ሐረር ከባቡር ጋራ ለምን ተያያዘ ለሚባለው መውረጃው ድሬደዋ ይሁን እንጂ ሐረር ለመሄድ እኮ ባቡር መሳፈራችን ግድ ነበር፡፡ከድሬደዋ በኋላ በመኪና ሐረር እንገባለን፡፡ ፍራፍሬውም በወቅቱ የነበረው ነው፡፡ ያን ግዜ ስንሄድ የነበረው ጫካ ውበት ራሱ ትዝ ይለኛል፡፡ እንደዛኛው ግዜ በብዛት አይኑር እንጂ በፍራፍሬ እንኳን ሐረር እና ድሬደዋ አሁንም አይታሙም፡፡ ሁለቱም በጣም የምወዳቸውና የሚመቹኝ ከተሞች ናቸው፡፡

የሠርግ ሥራዎችህን ቀጠሮ በመያዝና በመደራደር በአገር ፍቅር ትያትር ቤት የዘመናዊ ዳንስ አሰልጣኟ ባለቤትህ ወ/ሮ ዘነበች ጌታሁን እንደምታግዝህ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንተ እና ከእርሷ ዋጋ ማን ይቀንሳል?

ባለቤቴ ሥራ ስላላት የምታግዘኝ በትርፍ ጌዜዋና ከኢትዮጵያ ውጭ ስሆን ነው እንጂ እኔ ሁልጊዜ እርሷ ብትሆንልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እኔ ብዙ የማወዳድራቸው ነገሮች አሉ አንዳንድ ግዜ እኔ ተጎድቼ ብሠራስ የምልባቸው ሥራዎች አሉኝ፡፡

ሴቶች ሰዎችን አግባብቶ የማሠራት አቅም ስላላቸው ለንግድ ሥራ ጎበዝ ናቸው፡፡ ስለዚህ እርሷ ስትሆን ጠንከር ስለምትል ጥሩ የመደራደር አቅም አላት፡፡

አልበም ከማውጣትህ ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ በዓመት ከ30 እስከ 40 ሠርግ ትሠራለህ?

በተለየ ሁኔታ የምታስታውሰው ሠርግ እና ሙሽራ አለ? ማስተካከያ ይደረግልኝ፡፡ የተጠቀሰው ቁጥር ቀደም ሲል የነበረ ነው፡፡ ካለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ወዲህ የሠርግ ሥራ ቀንሷል በዓመት 15 ሠርግ እንኳን አይገኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ያመጣቸው የተለያዩ ምክንያቶቹ አሉ፡፡ በእኔ በኩል ግን ይችን ታህል ካገኘን ተመስገን ይበቃል ነው የምለው፡፡ የሚገርመው ከዚህ ሁሉ ሙሽራ ላወራበት የምችለው በተለየ የማስታውሰው የተጋነነ ነገር የለኝም፡፡

የሠርግ ሥራ መለያህ ኾኗል፤ ኮንሰርት ትሠራለህ?

አዎ ከኢትዮጵያ ውጪ እየተጋበዝኩ ለተለያዩ ፕሮግራሞች እሠራለሁ፡፡ እዚህ አገር ግን ፕሮግራም ይኖረዋል ወይም ደግሞ ጸጋዬ የሠርግ ድምፃዊ ብቻ ነው ተብሎ እንደሆነ አላውቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አልታይም፡፡ ምናልባት ነገ ከነገወዲያ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም፡፡      የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ ተጠቃሚ ነህ?

አዎን ተጠቃሚ ነኝ፡፡ ፌስቡክ በጣም ጠቃሚ ነገር መሆኑን ያወኩት አሁን ነው፡፡ ዱሮ አልበም ስናወጣ የሕዝቡን አስተያየት ማግኘት የምንችልበት መንገድ በጣም የተጣበበ ነበር፡፡ ግፋ ቢል አንዳንድ ታታሪ ሰዎች በፖስታ ከሚልኩት አስተያየት በቀር እንዲህ በቀጥታ አስተያየት የምናገኝበት እኛም የምንፈልገውን መልእክት በፈለግነው ሰዓት በቀጥታ የምናስተላልፍበት መንገድ አልነበረም፡፡ አሁን ይህንን አዲሱን ሥራዬን ስሠራ ሥራዬን አስተዋውቄበታለሁ፡፡ ወዳጆቼም ከሚገባው በላይ አስተያየት በመስጠት አበረታተውኛል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስደስቶኛል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የድምፃውያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ነህ ከምስረታችሁ በኋላ ምን ሠራችሁ? ማኅበሩን የመሰረትነው በቅርብ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜያት ለድምፃውያን የሚናገሩላቸው ሌሎች ሰዎች ነበሩ፡፡

ነገር ግን የራሳቸው የኾነ በርካታ ችግሮች አሏቸው፡ ይህን ችግራችንን ሰብሰብ ብለን በጋራ ለምን አንፈታውም በሚል የሞያ ማኅበር መቋቋሙን አምነንበት ነው የመሠረትነው፡፡ የማኅበሩን ፈቃድ ካገኘን በኋላም በርካታ ድምፃውያንን በአባልነት ተቀብለን ደስ በሚል መንፈስ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤያችንን አካሂደን ጉባኤው አመራሩን መርጧል፡፡ ለቦርድ አመራርነት የተመረጥነው እኔን ጨምሮ አመልማል አባተ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ቴዎድሮስ ሞሲሳ፣ ጸደኒያ ገ/ማርቆስ፣ ታደለ ገመቹ እና ብርሃኑ ተዘራ ነን፡፡ አሁን ብሬ ላልተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ ስለምሄድ በሌላ ሰው ተኩኝ እያለ ነው፡፡ እናም አሁን ማኅበሩን በገንዘብ ለማጠናከር የሚያስችለንን ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በቀጣይ ባለን ዕቅድ ለባለሞያው ጠቃሚ የኾነ ጥሩ ሥራዎችን ለማከናወን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህን ደግሞ ወደፊት የምታዩት ይኾናል፡፡

Read 5490 times Last modified on Thursday, 11 April 2013 11:33