Monday, 08 April 2013 10:24

ጀስቲን ቲምበርሌክ ወደ ሙዚቃ ለመመለስ ተገደደ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጀስቲን ቲምበርሌክ ከ4 ዓመታት በፊት ከላይቭ ኔሽን ጋር በተፈራረመው የኮንሰርት ውል አስገዳጅነት ወደ ሙዚቃ ስራው ሊመለስ መወሰኑን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገበ፡፡ አርቲስቱ የሙዚቃ ስራውን ለተወሰነ ጊዜያት በማቆም በፊልም ትወና ለማተኮር የነበረውን ፍላጎት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ከአራት አመት በፊት ላይቭ ኔሽን ከተባለው የኮንሰርት አዘጋጅ ድርጅት ጋር የገባውን ውል በማደስ ጀስቲን ቲምበርሌክ ወደ ሙዚቃ ፊቱን ያዞረው የ20 ሚሊዮን ዶላር ስምምነቱ ስላማለለው እንደሆነ ቢዝነስ ኢንሳይደር በዘገባው አትቷል፡፡ ከእነ ማዶና እና ጄይዚ ጋር በመስራት ዓለም አቀፍ ሽፋን ያላቸውን ኮንሰርቶች የሚያዘጋጀው ላይቭ ኔሽን በውሉ መሰረት ለጀስቲን ቲምበርሌክ በመላው ዓለም ለሚያቀርበው ኮንሰርት 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ገልጿል፡፡

ከ4 ዓመት በፊት ጀስቲን ቲምበርሌክ ከላይቭ ኔሽን 5 ሚሊዮን ዶላር ቀብድ ተከፍሎት እንደነበር ያስታወሰው ቢዝነስ ኢንሳይደር ይህን ቀብድ መልሶ ውሉን የማፍረስ መብት ነበረው ብሏል፡፡ ጀስቲን ቲምበርሌክ ከ3 ወራት በፊት ‹‹ዘ 20 /20 ኤክስፒሪያንስ›› በሚል የሰራውን አልበም ለገበያ ካበቃ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ከሙዚቃ ስራው ለማረፍ ፈልጎ እንደነበር የገለጸው ቢዝነስ ኢንሳይደር ሊመለስ መወሰኑ ያልተጠበቀ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በትወና ስራው ትኩረት አድርጎ የነበረው የፖፕ ሙዚቀኛው 3ቱን ፊልሞች ‹‹ባድ ቲቸር››፤ ‹‹ፍሬንድስ ዊዝ›› እና ‹‹ኢንታይም›› ተውኖ ነበር፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት ከክሊንት ኢስትውድ ጋር ትራብል ዊዝ ከርቭ የተባለውን ፊልም የሰራው ጀስቲን ቲምበርሌክ በሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች ተፈላጊነት እያገኘ ነበር፡፡

Read 1760 times