Monday, 08 April 2013 12:13

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› የመጀመርያ ዙር ተጠናቀቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› የመጀመርያ ዙር ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን ነገ በጊዮን ሆቴል በሚደረግ ስብሰባ አጠቃላይ ሂደቱ ሊገመገም ነው፡፡ የሊጉ ውድድር ዘንድሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ግጥሚያ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአህጉራዊ ውድድሮች በነበራቸው ተሳትፎ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ፉክክሩ ከመደብዘዙም በላይ፤ በተመልካች ድርቅ እና በየስታድዬሙ በሚያጋጥሙ የዲስፕሊን ግድፈቶችም አስቀያሚ ገፅታ የተላበሰ ነበር፡፡ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› የመጀመርያ ዙር ሲጠናቀቅ እሰከ 13ኛ ሳምንት በተደረጉ 85 ጨዋታዎች 186 ጎሎች ከመረብ ሲያርፉ በሊጉ አንድ ጨዋታ በአማካይ 2.19 ጎሎች ሲመዘገቡ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለስፖርት አድማስ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የሊጉ የመጀመርያ ዙር አፈፃፀም ነገ በግዮን ሆቴል ሲገመገም በስብሰባው ላይ የክለቦች የቦርድ ሰብሳቢዎች ወይም ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ስራ አስኪያጆቻቸው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል የሃገር ውስጥ ተጨዋቾች ዝውውርን በተመለከተ አዲስ የዝውውር ወቅት እንደሚጀመር የፌደሬሽኑ ኢመርጀንሲ ኮሚቴ አሳውቋል፡፡ ኢመርጀንሲ ኮሚቴው መደበኛው የሃገር ውስጥ ተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 15 መካሄዱን ገልፆ አዲሱ የዝውውር መስኮት ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ በኋላ ለ15 ቀናት እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› ሁለተኛ ዙር ሚያዚያ 3 እንደሚጀመር ሲታወቅ አዲሱ የሃገር ውስጥ ተጨዋቾች የዝውውር መስኮት እሰከ ሚያዝያ 18 የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በተያያዘ ዜና በፊፋ እውቅና የሚያገኝ የተጨዋቾች ወኪልነትን ለመስራት ለሚፈልጉ አመልካቾች ባለፈው ማክሰኞ ፈተና የተሰጠ ሲሆን ከፊፋ የመጣውን የፅሁፍ ፈተና 5 ሴት እና 15 ወንድ አመልካቾች እንደተፈተኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሰሞን በአዳማ ከተማ በሚገኘው የአበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ እና መከላከያ ባደረጉት የሊግ ጨዋታ በተፈጠሩት የዲስፕሊን ግድፈቶች ላይ የሊግ ኮሚቴ ከውድድሩ አመራሮች በቀረበው ሪፖርት መሰረት ልዩ ልዩ መረጃዎችን በመመርመር ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ መሰጠቱን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በአዳማ ከተማና በመከላከያ ክለቦች መካከል በተደረገው የሊግ ጨዋታ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች እና የዲስፕሊን ግድፈቶች ግጥሚያው ለ20 ደቂቃ ተካሂዶ እንደተቋረጠ ይታወሳል፡፡ከኮሚሽነሩ እና ከ4ኛ ዳኛው በቀረበው ሪፖርት መሰረት ዋና ዳኛ ደረጃ ገብሬ ለመከላከያ ቡድን በሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት አግባብነት ዙርያ ውሳኔያቸውን በመቀያየር በራሳቸው ላይ ሁከት በመፍጠር ወጥ አቋም ይዘው የዳኝነት ተግባራቸውን ባለመወጣታቸው የሚመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውሳኔ እንዲሰጥበት መወሰኑን የሊግ ኮሚቴው መግለጫ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮሚቴ ስለጨዋታው መቋረጥ ከዕለቱ የውድድር አመራር አካላት በቀረበው ሪፖርት መሰረት በየአዳማ ከተማ ክለብ ተጨዋቾችና አመራሮች ጨዋታውን አንቀጥልም በማለት ለመጫወት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን መገለፁን ጠቅሶ፤ ጨዋታው በእነሱ ምክንያት የተቋረጠ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ እና የክለቦች የውድድር ደንብ መሰረት 0 ነጥብና 0 ግብ ተመዝግቦለት ክለቡ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ ለፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ብር 15 ሺህ ብር እስከ ሚያዚያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. 6፡00 ሰዓት ድረስ በቅጣት ገቢ እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡ የአዳማ ከተማ ተጨዋች ዳኛውን ጠልፎ በመጣሉ፤ የአዳማ ቡድን አመራር ቡድናችን ጨዋታውን አይቀጥልም በማለት ጨዋታው እንዳይቀጥል እና ለጨዋታው መቋረጥ ምክንያት በመሆናቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተወስኗል፡፡ የአዳማ ከነማ ቡድን በጉዳዩ ላይ ያቀረበው የክስ አቤቱታ በተመለከተ የሊግ ኮሚቴው ባስተላለፈው ውሳኔ አንድ የቴክኒክ ክስ የሚመሰረትበትን መስፈርት ስላላሟላ ከደንብ ውጭ ተመዝግቦ የቀረበ የክስ አቤቱታ በመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲሆን መወሰኑንም አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮሚቴ የመከላከያ ቡድንን በተመለከተ ባሳለፈው ውሳኔ ክለቡ ጨዋታውን ለመቀጠል ፍቃደኛ ሆኖ እያለ የአዳማ ከነማ ቡድን ጨዋታውን ለመቀጠል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ዳኛው ያሰናበተው እንደሆነ ገልፆ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት በፎርፌ አሸናፊ ሆኖ 3 ነጥብና 0 ግብ እንዲመዘገብለት ወስኗል፡፡

Read 3299 times Last modified on Monday, 08 April 2013 12:17