Monday, 08 April 2013 12:17

ጊዮርጊስ እና ደደቢት በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ናቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመግባት ነገ ወሳኝ የመልስ ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ የሆነው ደደቢት ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም በመጀመርያ ዙር የመልስ ጨዋታ የሱዳኑን አልሼንዲ ያስተናግዳል፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት ደደቢት የመጀመርያ ጨዋታውን ከአልሼንዲ ጋር በሱዳን አድርጎ 1ለ0 ተሸንፎ የነበረ ሲሆን ነገ በሜዳው ይህን ውጤት ለመገልበጥ 2ለ0 በላይ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡በኮንፌደሬሽን ካፑ የመልስ ጨዋታ ከደደቢት እና ከአልሼንዲ የሚያሸንፈው በሁለተኛ ዙር ሊገናኝ የሚችለው ከግብፁ ኢስማኤልያ እና ከማላጋሲው ቲኮ ቦኒ አሸናፊ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በመጀመርያ ጨዋታቸው ሲገናኙ 2ለ0 ያሸነፈው ኢስማኤልያ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጀመርያ ዙር የመልስ ጨዋታ ከዲጆሊባ ጋር ለመፋለም ወደ ማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ትናንት ተጉዟል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ሳምንት በፊት በሜዳው የማሊውን ዲጆሊባ 2ለ0 አሸንፎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከዲጆሊባ የሚያሸንፈው በሁለተኛው ዙር ሊገናኝ የሚችለው ከግብፁ ዛማሌክ እና ከዲ.ሪ. ኮንጎው አኤስ ቪታ አሸናፊ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በመጀመርያ ጨዋታ ተገናኝተው 1ለ0 ያሸነፈው ዛማሌክ ነበር፡፡ የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በአዲስ የውድድር አካሄድ ከ15 አመታት በፊት ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያን በመወከል ዘንድሮ 10ኛውን ተሳትፎ የሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለተኛው ዙር ለማለፍ ተቸግሮ መቆየቱን ስለክለቡ የአህጉራዊ ውድድር ታሪክ በኢትዮፉትቦል ድረገፅ የቀረቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በአዲስ የውድድር አካሄድ ሲጀመር ተሳታፊ ሊሆን የበቃው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ የተሰናበተው በግብፁ ክለብ ዛማሌክ ተሸንፎ ነበር፡፡

ግብፅ ላይ 2ለ0 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይቶ 3ለ1 በሆነ ድምር ውጤት ተበልጦ ነበር ፡፡ ቀጣይ ተሳትፎውን ያገኘው ከ2 የውድድር ዘመናት በኋላ ነበር፡፡ በቅድመ ማጣሪያው የኡጋንዳውን ቪላ ካምፓላን 5ለ2 በሆነ ድምር ውጤት ረትቶ አለፈ፡፡ ከዚያ በኋላ በመጀመሪያው ዙር ከቡሩንዲው ክለብ ቪታሎ ተገናኘ፡፡ ከሜዳው ውጭ 2ለ2 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ1 ተሸንፎ በድምር ውጤት በቪታሎ ተበልጦ ወደቀ፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ በቅድመማጣርያው ነው ውድደሩን የተሰናበተው፡፡ ከኬንያ ተስካር ጋር ተገናኝቶ አዲስ አበባ ላይ 1ለ1 ኬንያ ላይ ደግሞ ያለግብ አቻ ተለያይቶ ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ህግ መሰረት ተስካር ሊያልፍ በቅቷል፡፡በ2003 እኤአ ላይ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመሳተፍ እድል ባገኘበት ወቅትም ቅድመ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለም፡፡

በኡጋንዳ ክለብ አዲስ አበባ ላይ 3ለ1 ተሸንፎ ከሜዳው ውጭ 1ለ0 ቢያሸንፍም አላለፈም፡፡ በ2004 እኤአ ላይ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ሲሰናበት በሱዳኑ አልሂላል ኦምዱርማን ተሸንፎ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳውና ደጋፊው ፊት 2ለ1 ተሸንፎ ስለነበር ካርቱም ላይ አንድ አቻ መለያየቱ ሊያሳልፈው አልቻለም፡፡በ2006 እኤአ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው በመጀመሪያው ዙር የተገናኘው ከግብፁ ኢኤንፒፒአይ ጋር ነበር ፡፡ ከሜዳው ውጭ 0ለ0 በመለያየት በሜዳው ደግሞ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ገባ፡፡ ያጋጠመው የጋናውን ኸርትስ ኦፍ ኦክ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ 4ለ0 በሆነ ውጤት ሀርትስ ኦፍ ኦክን አሸነፈ፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን ያልተጠበቁ ክስተቶች ተፈጠሩ፡፡ በጊዮርጊስ ላይ በጋና ዋና ከተማ አክራ እንግልት ደረሰበት፡፡

የጨዋታው ዳኛ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን አሳለፉ፡፡ ባለሜዳዎቹ 2ለ0 እየመሩ ተጨማሪ የፍፁም ቅጣት ምትም አገኙ፡፡ በዚህ ወቅት በደሉን መቋቋም ያልቻሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የኦህንጃን ስታድየምን ሜዳን ጨዋታው ሳይጠናቀቅ አቋርጠው ወጡ፡፡ የውድድሩ አስተዳዳሪ ካፍ ውሳኔም ወደ ጋናው ክለብ አጋደለ፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ወድቆ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እንዲያልፍ ተደረገ፡፡በተከታዩ የውድድር ዘመን በ7ኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመርያ ዙር የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤቶል ዲ ኮንጎን በማስተናገድ 1ለ0 አሸነፈ፡፡ በመልሱ ጨዋታ ግን 2ለ0 ተሸነፉ ፡፡

ከዚህ በኋላ በቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዘመናት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ፊፋ ሀገሪቱን ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ውድድር በማገዱ ቅ/ጊዮርጊስም መሳተፍ በነበረበት ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ በ2009 እኤአ ላይ ሣይሳተፍ ቀረ፡፡ በ2010 እኤአ ላይ ወደ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመለሰ፡፡ በቅድመ ማጣርያ የተደለደለው ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሁለቱ ክለቦች አንድ እኩል አቻ ተለያዩ፡፡ የመልሱ ጨዋታ በኤልሜሪክ ስታዲየም ሲደረግ ቅ/ጊዮርጊስን 3ለ1 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ ነገስ ምን ይገጥመው ይሆን?

Read 4452 times