Saturday, 13 April 2013 14:34

ንጉሥና ዝንጀሮ፣ ራሱ ይከምራል፣ ራሱ ይበትናል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ጐራዴን፣ እጀታዋን የያዘ ያሸንፋል

                    ***

(የትግሪኛ ተረት) በዓላት ሁሉ ቢሰባሰቡ መስቀልን አያህሉም!

ቂል ከሰረቋት በኋላ ትነግዳለች!

ያለ የማያልፍ ይመስለዋል፣ ያለፈ ያልነበረ ይመስለዋል!

(የጉራጊኛ ተረት)

                     ***

ሞኝ ባል ሚስቱን ይስማል!

ዕዳ የሌለበትን ድህነትና በሽታ የሌለበትን ክሳት የመሰለ የለም (የወላይታ ተረት)

ያለ ጊዜዋ የበቀለች ማሽላ፣ ወይ ለወፍ ወይ ለወንጭፍ! (የአማርኛ ተረት)

አንድ የጃፓኖች ተረት እንደሚከተለው ይተረታል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ዛፍ ላይ በመውጣት በጣም ድንቅና አንደኛ የተባለ ሰው ነበረ፡፡ ምስኪን ደሃ ነው፡፡ ግን ባለሙያ ዛፍ - ወጪ ነው፡፡ አንድ እጅግ ረዥም የሆነ ዛፍ ላይ እንዲወጣ፣ ላንድ ሌላ ሰው ሊያስተምር መመሪያ እየሰጠው ነበር፤ አሉ፡፡ የሚማረውን ዛፍ-ወጪ ከላይ ከላይ ያሉትን ቅርንጫፎች እንዲቆርጣቸው፤ ትዕዛዝ ሲሰጠው፤ “በል፤ በጣም ከፍ ያሉትን ቅርንጫፎች በደንብ ቁረጣቸው” አለው፡፡ ዛፍ-ወጪው ተማሪም እንደታዘዘው የጫፍ የጫፎቹን ቅርንጫፎች ቆረጠ፡፡ እየቆረጠ ሳለ ግን ታች ወርዶ ሊከሰከስ የሚያስችልበት በጣም አንሸራታች ጫፍ ላይ ደረሰ! አስተማሪ ሆዬ አደጋ ላይ ሊወድቅ መድረሱን እያየ ዝም አለ፡፡ የዛፍ አወጣጥ ተማሪው እንደምንም አንሸራታቹን ቦታ አልፎ መውረድ ጀመረ፡፡

መሬት ሊደርስ በጣም ጥቂት ሲቀረው፤ “ተጠንቀቅ! የምትረግጠው እርከን እንዳያንሸራትትህ በጣም በጥንቃቄ፤ ውረድ!” አለው አስተማሪው፡፡ ይሄኔ አንድ መንገደኛ ሰማና፤ “ይገርማል! ዋናው አደጋ ጋ ሲደርስ ዝም ብለህ ስታበቃ አሁን ትመክረዋለህ እንዴ? ከዚህ ከፍታማ እራሱ በመረጠው መንገድ ዱብ ሊል ይችላል” አለና ጠየቀው፡፡ “ዋናው ነጥብ እሱ ነው፡፡ ሰውዬው በጣም አደገኛ ከፍታ ላይ ሳለማ ከአሁን አሁን ወደቅሁኝ በሚል ሥጋት፣ እራሱ ይጠነቀቃል፡፡ እራሱ ለራሱ ይፈራል፡፡ አሁን መሬት ሊደርስ ሲል ግን ሀሳቡን ጥሎ፣ ሰውነቱን ያላላና ሁሉን ይንቃል! ይሄኔ ነው አደጋ ያለው! ሁሌ ስህተቶች የሚሠሩት ሰዎች ቀለል ያለ ቦታ ሲደርሱ ነው” ይህንን ሀሳብ ያቀረበው አስተማሪ ሰው በጣም ደሀ ከሆነ መደብ የተፈጠረ ሰው ነው፡፡ የተናገረው ነገር ግን ከጠቢባን ደረጃ የሚመደብ ነው፡፡ በእግር ኳስ ጨዋታም ላይ ይሄ አባባል ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ በጣም ከሚያጨናንቅ አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ኳሷን ካራቁ በኋላ፤ የምትቀጥለው ኳስ ቀላል ትመስላለች፡፡ ያለ ጥርጥር ግን ብዙ ጊዜ ኳሷን ይስቷቷል!

                                                        ***

ዛፍ አወጣጥ የሚያስተምረን ሰው አወራረድ ያስተምረን ዘንድ እንመኝ፡፡ የወጣ ሁሉ አይቆይም፡፡ የቆየ ሁሉ ደግሞ መውረድ አይቀርለትም፡፡ በአናቱ ቅቤ ጣል ያለበት ሽሮ ከበላን በድህነታችን ላይ ካፒታሊዝም ሥርዓት እንደመጨመር ነው፡፡ የታደልን እኛ ብቻ ነን ብንል ምፀቱ አይገለንም!! በአናቱ ከሚጨመር ሥርዓት ያድነን!! አንድ ኢትዮጵያዊ ፀሀፊ የሮዛ ሉክሰምቡርግን አስተሳሰብ በመጥቀስ የነቆጠውን፤ ስለ ምርጫ ስናስብ አቅም ይሆነን ዘንድ አሁን እናስበው፡- “ነፃነት፣ ቁጥራቸው የፈለገውን ያህል በርካታ ቢሆን፣ ለመንግሥት ደጋፊዎችና ለፓርቲ አባሎች ብቻ የሚሰጥ መብት አይደለም፡፡ ነፃነት ሁልጊዜም የተለየና ተቃዋሚ ሀሳብ ያለው ወገን መብት ነው፡፡ ይህን የምለው ለፍትህና ለርትዕ፣ ልዩና አምልኮ - ባዕዳዊ ፍቅር አድሮብኝ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ነፃነት ህብረተሰብን የሚያድሰው፣ በዚህ ሀቅ ላይ ሲመሰረት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ነፃነት የተወሰኑ ምርጥ ወገኖች ልዩ-መብት (ፕሪቪሌጅ) ከሆነ የይስሙላ ነፃነት ነው የሚሆነው፡፡ ከላይ የጠቀስነው አበሻ ፀሀፊ፤ የምርጫውን አሀዝ ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ልብ እንገነዘብ ዘንድ የሚከተለውን እንመርምር ይለናል፡- “ወድቀው ከታሪክ ፊት በሀፍረት ሊሰናበቱ ሳምንት ሲቀራቸው ሁሉ 98 ከመቶ በሆነ ድምፅ ይመረጡ የነበሩት የምስራቅ አውሮፓ “ዲሞክራቶች” ነበሩ፡፡ “ዲሞክራሲያዊ ምርጫ”ን የይስሙላ ያደርገው የነበረውም ይኸው ነው፡፡ 90 በመቶም በላይ ድምፅ እያገኘ በሕዝብ ዘንድ ይጠላ የነበረውን የ (ምስራቅ) ጀርመን ኮሙኒስት ፓርቲ አስመልክቶ “ሕዝቡ ሌላ ፓርቲ መምረጥ ካልቻለ፣ ፓርቲው ሌላ ሕዝብ ይምረጣ እንግዲህ” ብሎ ቀልዶ ነበር ቤርቶልድ ብሬሸት፡፡” ለለውጥ ያህል ደግሞ የዛሬን ትንተና በተረቶቻችን ግንዛቤ እናጅበው፡፡ ስለ ፊውዳላዊ ሥርዓት ቅሪታችን ይህን ልብ እንበል፡- እንኳን ራሳቸውን ተመተው፣ ምንጊዜም ካሣ ተቀባይ ናቸው!! ስለምርጫችን ይህን ልብ እንበል፡- ልቅደም እንጂ፣ የሩጫ መልክ አለው ወይ! እማሆይ የተቆረጠ ማሽላ ይጠብቃሉ እናቷ መራቂ ልጇ አሜን ባይ! ቂል ከሰረቋት በኋላ ትንግዳለች ያለጊዜዋ የበቀለች ማሽላ፣ ወይ ለወፍ ወይ ለወንጭፍ ብትሸልም ለሚስትህ፣ ብትፎክር በሠርግህ ዋዜማ! ብትቆርጥ እሾሃም ዛፍ፣ ብትፎክር በሰርግ ዋዜማ! ስለተቃውሞዋችን ይህን አንርሳ አህያ ቢጠፋው ደውላ ገልጦ አየ! ሰለ ጊዜ ምርጫችን ይህንን እናስምር ያለጊዜዋ የበቀለች ማሽላ፣ ወይ ለወፍ - ወይ ለወናፍ ንገሥ ቢሉት ዛሬ ሰንበት ነው አለ፣ ስለ ፕሬሳችን ይሄን በጥልቅ እንመርምር አፌ ዝም ብሎ እጄን ይጐራረሱበታል ስለሙስናችን ይህን እንፀልይ ካመጡ እንበላለን፣ ከሞቱ እንሰማለን፤ አለች የሌባ ማስት ስለ መልካም አስተዳደራችን ይህን እንበል ምን እንዳታደርግ ያሏትን በቅሎ፣ ሙጃ ላይ ያስሯታል ስለ ኢኮኖሚ መብታችን ይህን እንነቁጥ የደሀ ጀርባ በይሰጡኛል ያልቃል? ስለ ፖለቲካ ሥልጣን ይህን ምንጊዜም አንርሣ ጥፍሯን ሳትቆረጥ ቀለበት አደረጉላት ከላይ የርዕሰ አንቀጽ ፍሬ - ርዕስ ያደረግናቸው ተሰብስበው የነገ ምርጫችንን ይባርኩልን ዘንድ እንፀልያለን!!

Read 5133 times