Saturday, 13 April 2013 15:12

“ሁላችንም በኪሳችን ትናንሽ ዘውድ ይዘን ነው የምንዞረው!”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ማን ያውቃል!?

ኢህአዴግና ህዝብ፣ ኑሮና “መታደስ”

ቀጠሮ እንዳላቸው፣ የምርጫ ቀን ሲደርስ-

የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በአዘቦቱ ቀን የት እየገቡ ነው?

 እናንተ---- በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ፋውንዴሽን ምስረታ ላይ የተገኙት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ያሉትን ሰማችሁልኝ? የእኛን አገር ለማመስገን ብለው የራሳቸውን ሞለጩት እኮ፡፡ ለነገሩ አሳዘኑኝ እንጂ አላዘንኩባቸውም፡፡ እንዴ --- የእውነት ተቸግረው ቢሆንስ! (ወልደው ሳይጨርሱ አሉ--) እናላችሁ --- የእኛ አገር ከሳቸው አገር ዩጋንዳ የተሻለች መሆኗን ሲናገሩ እንዲህ አሉ - “እዚህ አገር ጥሩ ነው ፤ አየር መንገዳችሁ ጥሩ ይሠራል ፤እኛ አገር እኮ ፓይለቶቹ ራሳቸው ከአውሮፕላኑ ላይ ኢንጂኑን ይሰርቁታል” (ሃሳቡ እንጂ ንግግራቸው ቃል በቃል አልተቀዳም!) እኔ የምለው ግን ---- ሰውየው “ገበና” የሚባል ነገር አያውቁም እንዴ? ወይስ ኡጋንዳ “ገበና” የለም? (ባይኖር ነዋ!) ሌላው ሁሉ ቢቀር ግን “የአገር ገፅ ግንባታ” የሚባል ነገር አያውቁም እንዴ? ምናልባት ገንብተው ጨርሰው ይሆናላ! አያችሁ ---- እኛ እኮ ሁሌ እያፈረስን ስለምንገነባ ነው! በነገራችን ላይ ሙሴቪኒ ለ“መለስ ፋውንዴሽን” 500ሺ ዶላር ነው የለገሱት፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ 1ሚ ዶላር ሰጥታለች፡፡

ሱዳን 2ሚ ዶላር --- ለግሳለች፡፡ በዚህም በዚያም ብሎ ብቻ 50ሚ ዶላር የተሰበሰበ መሰለኝ፡፡ እኔ የምለው---ለምን እንዲህ አናደርግም! አንድ ቀን ሁሉንም የአፍሪካ መሪዎች ሰብስበን (ዲሞክራት ነው አምባገነን ሳንል) ለህዳሴው ግድብ እንዲያዋጡ ብንጠይቃቸውስ? እውነቴን እኮ ነው ---- በተለይ ነዳጅ ያላቸው አገራት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይሰጡናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኛን ያቅተናል ብዬ እኮ አይደለም ---(50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ---ለ50 አገራት ጌጡ ብዬ እኮ ነው!) በዚያ ላይ -- ግድቡ ሲጠናቀቅ “ሃይል” መዋሳቸው ይቀራል? (ነውር ከሆነ ግን ይቅር !) እኔ የምላችሁ --- ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ወደ ክልሉ ይመለሱ መባሉን ሰማችሁ? (የሰው አገር ስደት አንሶን በገዛ አገራችን---?) የክልሉ ፕሬዚዳንት ስለተፈናቀሉት ዜጎች ተጠይቀው ሲመልሱ ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ --- “ነገሩ የተፈፀመው ኪራይ ሰብሳቢ በሆኑ የበታች አመራሮች ግብታዊ እርምጃ ነው” ብለዋል፡፡

እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ይሄ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚል ቃል ፍቺው ተለወጠ እንዴ? ምናልባት ኢህአዴግ የቃሉን ትርጉምና አጠቃቀም ለውጦት ከሆነም “ኢንፎርም” እንደረግ ! እንዴ --- ዜጎችን ከገዛ አገራቸው በሃይል ያፈናቀሉ የወረዳ “አምባገነኖች” እንዴት በአቅም ማነስ የተገመገሙ ይመስል “ኪራይ ሰብሳቢ” በሚል ይታለፋሉ? (ማን ነበር “ሁላችንም በኪሳችን ትናንሽ ዘውድ ይዘን ነው የምንዞረው” ያለው?) አይገርምም --- ሁሉም መንገስ ይፈልጋል ለማለት እኮ ነው! እውነቴን ነው --- ኪራይ ሰብሳቢ የተባሉት የበታች አመራሮች እኮ ህዝብ ብቻ አይደለም ያፈናቀሉት፤ ህገመንግስትም ነው የናዱት፡፡

ህገመንግስት በኀይል መናድ --- ከዚህ በላይስ አለ እንዴ? (ሥልጣን ብቻ ሳይሆን የዜጎች መብትም ሲጣስ እኮ ህገመንግስት መናድ ነው!) “ኪራይ ሰብሳቢዎቹ” የዜጎችን ሰርቶ የመኖር መብት ብቻ አይደለም የደፈጠጡት! ህዝብን ከህዝብ ፤ ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት-- ለማፋጨት---ለማቃቃር---- ለማናቆር ሞክረዋል (ህዝቡ ኩም አደረጋቸው እንጂ!) ይሄ ማለት ደግሞ --- አገርን መበጥበጥ--- ማናወጥ ---መቀወጥ --- ይመስለኛል (ጀርባቸው ይመርመር!) እናላችሁ ----- እነዚህ የበታችም ይሁኑ የበላይ አመራሮች “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚለው ታፔላ ጨርሶ አይመጥናቸውም (ኒውክሌር ላስወነጨፈ ድንጋይ እንደመወርወር እኮ ነው!) የሽብር ሥራ ሰርቶማ በ“ኪራይ ሰብሳቢነት” ስም ማምለጥ የለም (ፌር አይደለማ!) ለማንኛውም ግን የክልሉ መንግስት ጥፋት መፈፀሙን አምኖ --- የተፈናቀሉት እንዲመለሱ መጠየቁ ያስመሰግነዋል (እንደሌሎቹ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ባለማለቱ!) አሁን የሚቀረው እንግዲህ ህዝብን ያፈናቀሉ አመራሮችን ለህግ ማቅረብ ብቻ ነው (አደራ እንዳይዘነጋ!) ዛሬ ምን እንዳማረኝ ታውቃላችሁ? (ሥልጣን እንዳትሉ ብቻ!) እኔን ያማረኝ ምን መሠላችሁ ---- ከኢህአዴግ ጋር ፊት ለፊት መፋጠጥ! (“ከኢህአዴግ ጋር ወደፊት!” አልወጣኝም!) እንደዚህ ካልኩማ ---ቅስቀሳ አደረግሁ ማለት ነው - የምርጫ! (ምን ቤት ነኝ ብዬ?) እናላችሁ… ከኢህአዴግ ጋር ትንሽ ብንፋጠጥ ደስ ይለኛል፡፡ በ“ሃርድ” እኮ አይደለም፤ በ“ፒስ ነው”፡፡

እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… እኔ ተአምር ቢመጣ ከኢህአዴግ ጋር አልጣላም፡፡ ሰው እንዴት ከ20 ዓመት በላይ የገዛውን መንግስት ይጣላል? (አንዳንዴ በኃይል አንዳንዴ በልምምጥ ቢሆንም ) ወዳጆቼ… የእኔ ዓላማ ጠብ ሳይሆን መፋጠጥ ነው - ፊት ለፊት መነጋገር፣ መመያየጥ---- ያለ ፍርሃት፤ ያለ ይሉኝታ--- እውነቷን ---- ማፋጠጥ! አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ይሄን ምኞቴን ሰምተው ምን አሉ መሰላችሁ ? “መጀመርያ የሥነምግባር ደንብ ፈርም!” እኔ እኮ --- እንደ አንዳንድ ተቃዋሚዎች “እንደራደር” ወይም “የጋራ መንግስት እናቋቁም” አልወጣኝም፡፡ እንድንፋጠጥ ብቻ ነው የፈለግሁት፡፡ የሆድ የሆዳችንን እንድናወራ! አስተዳድርሃለሁ ያለኝን መንግሥት ፊት ለፊት መጠየቅ ደሞ መብቴ ነው (ልማታዊ መንግስት ይከለክላል እንዳትሉኝ!) በነገራችሁ ላይ ኢቴቪም እኮ በቅርቡ “ፊት ለፊት” የሚል “የማፋጠጫ” ፕሮግራም ጀምሯል (የአበሻ Hard talk በሉት!) የእኔ ከኢቴቪ የሚለየው በምን መሰላችሁ? እነሱ የመንግስት መ/ቤት ሃላፊዎችን ብቻ ነው የሚያፋጥጡት፡፡ እኔ ግን ትላልቆቹን ነው (“የአመራሩ ቁንጮ” የሚባሉትን!) የእድል ነገር ሆኖ ግን የተመኘኋቸውን የአመራር ቁንጮዎች ለማናገር አልቻልኩም ለምን አትሉም ? የአመራሩ ቁንጮዎች ሁሉ ሰሞኑን ቢሮ አልነበሩም - የህዝብ እሮሮ እንዲያዳምጡ በየክፍለከተማው ተልከው ነበር፡፡

ህዝቡንና እቺን አገር ወደፈለጉት አቅጣጫ የሚቀዝፉት “ካፒቴኖች” እንኳንስ እኔን ሊያናግሩ እርስ በርስም የሚነጋገሩ አይመስለኝም፡፡ እንዴ ሰሞኑን ጊዜ የለማ! (የህዝቡ እሮሮ ተሰምቶ የሚያልቅ መሰላችሁ?) የኑሮ ውድነት--- የመብራትና የውሃ ችግር----የቴሌኮም ኔትዎርክ መቆራረጥ----የመኖርያ ቤት እጦት---- የስኳርና የዘይት መጥፋት----የእህል ዋጋ መናር---- ሥራ አጥነት---የትምህርት ጥራት ችግር----ወዘተ ሲሰሙ እየዋሉ ሲሰሙ ማደር ነው (ተጠራቅሞ እኮ ነው!) አያችሁ --- የኢህአዴግ አመራሮች ከህዝብ ጋር የሚገናኙት በአምስት አመት አንዴ ነው - ምርጫ ሲጠባ! ያን ጊዜ ነው ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን የምንዘከዝከው፡፡ እነሱም ይሰሙናል፤ እኛም እንናገራለን፡፡ በምርጫ ሰሞን የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንኳንስ የመልካም አስተዳደር ችግር ቀርቶ --- የትዳር ችግራችንንም ብንነግራቸው በደንብ ይሰሙናል፡፡ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የአብዬ መንግሥቱ ለማ “ማን ያውቃል” የምትል ግጥም - ማን ያውቃል? የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ---- እቺን ግጥም ከኢህአዴግ የመስቀል ወፍነት ጋር ያስታወስኩት አንድ ወዳጄ ደግሞ፣ የጥበብ ቆሌ ቀረበችውና (ኢንስፕሬሽን ለማለት ነው) በአብዬ መንግስቱ ስታይል እንዲህ ሲል ተቀኘልኝ- ማን ያውቃል!? ኢህአዴግና ህዝብ፣ ኑሮና “መታደስ” ቀጠሮ እንዳላቸው፣ የምርጫ ቀን ሲደርስ--- (ለኢህአዴግና ለዘንድሮ ምርጫ ይሁንልኝ) እኔ ግን አንዳንዴ የኢህአዴግ ነገር ግርም ይለኛል፡፡ እስካሁን አራት ያህል ምርጫ አካሂዷል አይደል --- ግን ሁሌ ጀማሪ ነው የሚመስለው፡፡

በቃ ትዝ የምንለው ምርጫ ሲመጣ ብቻ ነው፡፡ ያኔ ሩጫ ነው -ዘመቻ! (“ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ”) በጣም የሚገርመው ደግሞ ምን መሠላችሁ --- ዘመቻ ከመውደዱ የተነሳ የህዝብ እሮሮ እንኳን የሚሰማው በዘመቻ ነው፡፡ እናላችሁ… ሰሞኑን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት (የመርከቧ ካፒቴኖች የሚባሉት) የህዝብ እሮሮና አቤቱታ በማዳመጥና በማወያየት ተጠምደው ሰነበቱላችሁ፡፡ በኢቴቪ አይታችሁ ከሆነ እኮ --- የቀረ ባለሥልጣን የለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን ብቻ ነው ያላየናቸው፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና ---- እነዚህ ቱባ ቱባ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአዘቦት ቀን (ምርጫ በሌለበት ጊዜ ማለቴ ነው) የት ነው የሚገቡት? (ሰው ይናፍቃል አይሉም እንዴ?) እኔማ መብራት ሌሊት ሌሊት ለጅቡቲ እንሸጣለን እንደሚሉት፣ ራሳቸውንም እየሸጡ እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡ ገብቷችኋል አይደል ---- ምርጫ የሌለ ጊዜ --- ጎረቤት አገር የሚያስተዳድሩ ስለመሰለኝ እኮ ነው! (ለምሳሌ ሶማሊያ ወይም ደቡብ ሱዳን) ለማንኛውም ግን ለጊዜው እኛም ናፍቆታችንን ተወጥተንባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የምናገኛቸው በ2007 ምርጫ ነው፡፡ እስከዚያ መቻል ነው - ናፍቆቱን! (ወደን ነው!)

Read 4126 times