Monday, 15 April 2013 07:38

“ዋስትና ለተሠጠበት እቃ ሲበላሽ የማሠሪያ እንከፍላለን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“ዋስትና ለሠርቪስ ብቻ ነው” ሃሮን ኮምፒውተርስ

 የሂሣብ መመዝገቢያ ማሽኖች (ካሽ ሬጅስተር) እያስመጣ ከሚያከፋፍለው “ሃሮን ኮምፒውተርስ” በቅርቡ የሂሣብ መመዝገቢያ ማሽኖችን የገዙ ተጠቃሚዎች ማሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ፕሮግራሞች ሣይሟሉለት እንደተሠጣቸውና ማሽኑ የአንድ ዓመት ዋስትና እያለው ለማሠሪያ ተጨማሪ ክፍያ እንደተጠየቁ ተናገሩ፡፡ በመርካቶ የንግድ መደብር ያላቸው አቶ መካ ጀዛ እንደሚሉት፤ ታህሣስ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ከሃሮን ኮምፒውተርስ በ5ሺህ 298 ብር ከአርባ አንድ ሣንቲም የገዙትን የሂሣብ መመዝገቢያ ማሽን ወደ ንግድ መደብራቸው ወስደው ሲሞክሩት እንደማይሠራ በማረጋገጣቸው ወደ “ሃሮን ኮምፒውተርስ” ቢመልሱትም “አልተበላሸም ይሠራል” ተብለው እንደተመለሠላቸው፤ ይሁን እንጂ በድጋሚ ወስደው ሲሞክሩት አሁንም መስራት ባለመቻሉ ለሁለተኛ ጊዜ ሲያመለክቱ ባለሙያዎች መጥተው 280 ብር አስከፍለው እንደሠሩላቸው ተናግረዋል፡፡

እቃውን ሲገዙ የአንድ አመት ዋስትና እያለው የማሠሪያ እንዲከፍሉ መደረጉ እና አዲስ እቃ ገዝተው ሣያገለግል መበላሸቱ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ጀዛ ገልፀዋል፡፡ ሌሎች ደንበኞችም ባቀረቡት ቅሬታ ዋስትና ላለው እቃ ከ300-400 ብር ድረስ እንደሚጠየቁና የፕሮግራም ተሟልቶ አለመቅረብ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡ የ “ሃሮን ኮምፒውተርስ” ስራ አስኪያጅ አቶ ኑር ሁሴን ሠማ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከተቋቋመ ከ20 አመት በላይ እንደሆነውና በነዚህ የስራ ዘመናት በተሠማራበት የስራ መስክ በጥራቱም ሆነ በአገልግሎት ቅልጥፍናው ደንበኞቹን እያረካ መሆኑን አመልክተው፤ ተፈጠረ የተባለው ችግርም አልፎ አልፎ የሚያጋጥም እንጂ እንደተባለው በጅምላ ያጋጠመ ችግር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ድርጅቱ ማሽኖቹን ሲያስገባ የጥራት ደረጃው በመንግስት አካላት ታይቶ እውቅና ተሠጥቷቸው ነው” የሚሉት አቶ ኑር ሃሠን፤ በእቃዎቹ ጥራት ላይ የሚቀርቡት ቅሬታዎች ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡ ምናልባት እንኳ በአምራች ኩባንያው የተሠራ ስህተት ካለ ማሽኖቹ ከኛ እጅ አይወጡም የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ በስህተት ከወጣ እንኳ ወዲያውኑ ያለ ምንም ተጨማሪ ክፍያ ለገዢው አዲስ ማሽን እንተካለታለን ብለዋል፡፡ ዋስትና ለሰጣችሁት እቃ የጥገና ክፍያ ትጠይቃላችሁ ለተባሉት ሲመልሱም፤ አዲስ ለገዙ ደንበኞች እስከ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብልሽት አጋጥሞ የሚቀየር እቃ እንኳ ካለ ያለ ክፍያ ነው የምንጠግነው ያሉት አቶ ኑር፤ ሃሠን ጊዜው በገፋ ቁጥር ግን በብልሽት ምክንያት ለሚቀየሩ እቃዎች እንደየእቃዎቹ ዋጋ ክፍያ እንጠይቃለን ለሠርቪስ ግን የዋስትና ጊዜው እስኪጠናቀቅ አናስከፍልም ብለዋል፡፡

Read 1896 times