Monday, 15 April 2013 08:29

“የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ዝናቡ ትንሽ አቀዘቀዘንማ! እንዲሁ ‘በነካ እጁ’ በሌሎች እየነፈርን ባለንባቸው ነገሮች ቀዝቀዝ የሚያደርገውን ተአምር ይላክልንማ! ስሙኝማ…መቼም ብሶት አውሩ ብሎን የለ…እስቲ ‘እንነጫነጭ’፡፡ (እግረ መንገዴን…እንግዲህ በየጋዜጣው፣ በፖኤቲክ ጃዙ፣ ባስ ሲልም በየስብሰባው…“የፖሊስ ያለህ አትሉም ወይ፣ የዳኛ ያለህ አትሉም ወይ…” ስንል አለ አይደል…ጎልድ ሌብል፣ አበሶሉት ቮድካ እየቀነደቡ “ምን ይነጫነጩብናል!” የሚሉ ‘ሊያገለግሉን የተቀመጡ ባለወንበሮች’ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳለኝ ይመዝገብልኝማ!) እናላችሁ…የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው ተይ አንዱን እንያዘው፣ የሚሏት ዘፈን ቢጤ ነበረች፡፡ ዘንድሮ የማህበራዊ ግንኙነቶቻችን አድማስ እየጠበበ፣ እየጠበበ መጥቶ… ዛሬ ይኸው ብዙ ነገር “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ሆኗል፡፡ በየቦታው ችሎታ፣ ብቃት፣ የሥራ ፍላጎት…‘ቅብጥርስዮ’ (ነገሮቹ ወደ ‘ቅብጥርስዮ’ ወርደዋላ!) እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምር አሳዛኝ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…አለ አይደል… የሚዘጉ በሮች ሲበረክቱባችሁ፣… ትከሻውን የሚያሳያችሁ ሲበዛባችሁ፣…ፈራሚውና አስፈራሚው ሲምታታባችሁ፣ የመዝገብ ቤት ሠራተኛዋ ከመምሪያ ኃላፊው የበለጠ ስልጣን ያላት ሲመስላችሁ፣…

የሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ “የእንትን አገር ሰው ትመስላለህ፣ እዛ ነው እንዴ የተወለድከው?” አይነት ነገሮች ሲበዙባችሁ በፊት ነገሬ በላችሁ የማትጠይቋቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ ትጀምራላችሁ፡፡ አገልግሎት ለማግኘት የሄዳችሁባቸው ቦታዎች ‘ወረቀቶቻችሁን ሁሉ አሟልታችሁ’…አለ አይደል… ከመጤፍ የሚቆጥራችሁ ስታጡ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ከላይ እስከታች ድረስ አገልግሎት ለማግኘት የመጣችሁ ሳይሆን የግል ቤታቸው ‘ድንኳን ሰብራችሁ’ ገብታችሁ “እፍኝ ቆሎና ጣሳ ውሀ እርጠቡኝ…” ለማለት የመጣችሁ ሲያስመስሏችሁ… ‘በሌሎች የጠላችኋቸው’ ጥርጣሬዎች ይመጡባቸኋል፡፡ እናማ… “እዚህ መሥሪያ ቤት ሰው የሚቀጠሩት ዝም ብለው ችሎታ ምናምን ሳይባል ነው!” ትሉና ለሆነ ወዳጅ (“የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ላልሆነ ወዳጅ…) ታዋያላችሁ፡፡

ያኔ ነው ‘ናሽናል ሴክሬት’ አይነት ነገር የምትሰሙት፡፡ “እዛ ቤት ያሉት ሁሉ እኮ ዘመዳሞች ናቸው…” ይላችኋል፡፡ ከዛ እከሌ፣ እከሌ እያለ ሲቆጥርላችሁ…በቃ ምን አለፋችሁ…‘ዋርካው እንዳለ’ ይታያችኋል፡፡ ታዲያላችሁ…ከመሥሪያ ቤት የቅጥር መመዘኛዎች አንዱ “ከሥራ አስኪያጁና ዘመዶቻቸው የትውልድ ቦታ የመጣ/የመጣች…” የሚል ነገር ያለበት ነው የሚመስላችሁ፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰሞኑን ብዙ ጉዳዮች “ነገርዬው እንዴት ነው!” እያሰኙን ነው፡፡ ብቻ… ህዝባዊ አገልግሎቶች ሁሉ በትክክል ሊሠሩ አለመቻላቸው ግራ አልገባችሁም! ውሀ ብዙ ቦታ ይጠፋል (አንዳንድ ቦታ ለሳምንታት)፣ የኔትወርክ ጉዳይ ብለነው፣ ብለነው ‘ሆድ ይፍጀው’ የማለት ደረጃ ልንደርስ ምንም አልቀረን…መብራት ደግሞ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አራት፣ አምስት ጊዜ ደጋግሞ ይጠፋል፣ ይመጣል፡፡ እናማ…መቼም የፈረንጅ አባዜ ለጠበልም ሊያስቸግር ደርሶ የለ ‘በፈረንጅ አፍ’… “ኋት’ስ ጎይንግ ኦን!” ብለን እንጠይቃለን፡፡ እኔ የምለው…‘የባለሙያ ችግር’ አለ እንዴ! እንዴት ነው በጥቂት ጊዜ ሁሉም ነገር “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም…” የሚሉት አይነት ነገር የሆነው! ስሙኝማ…በጣም ግራ የሚገባኝ ነገር ምን መሰላችሁ…ለምንድነው በጣም በአጭር ወራት ብዙ ነገሮች ከአንደኛ ማርሽ ወደ በኋላ ማርሽ የተሸጋገሩት? “እሺ… የመንገድ፣ የባቡር ምናምን ይሁን፡ ለየቢሮውም ሠራተኞች ከወዳጅ አገር ማምጣት አለብን!” ያሰኛችኋል፡፡ እናላችሁ…ብቻ ምን አለፋችሁ…ብዙ ቦታዎች የቤተሰብ ጉባኤ አይነት ሆነዋል፡፡ የግል ድርጅቶችም ብዙዎቹ ‘አጥንት እየተቆጠረ’ የሚሰበሰቡባቸው አይነት ሆነዋል፡ ወዴት እየሄድን ነው ብለው የሚጠይቁ ሰዎች እውነት አላቸው፡ ሲመች “የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው…” “ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ነው…” ምናምን እየተባለ…አለ አይደል…በሌላ በኩል ደግሞ በሁሉም ነገር “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ማፈላለግ ዓቢይ ጉዳይ ሲሆን የምር ያሳስባል።

ታዲያማ…አሁን ችግሩ “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” እንደ በፊቱ ዘፈን ብቻ መሆኑ ቀርቶ ‘ያልተጻፈ የውስጥ መመሪያ’ ነገር እየመሰለ ነው፡፡ ስሙኝማ…ድሮ ድሮ “እንትን መሥሪያ ቤት የምታውቀው ሰው አለ ምናምን ነበር የሚባለው። (እዚህ አገር ብዙ ነገር የሚሠራው በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ‘የሚታወቅ ሰው’ ሲኖር ነዋ! እናላችሁ… የሚታወቅ ሰው ካለ ነገርን ለማስፈጸም… “እከሌ ልኮኝ ነው…” የሚለው ‘መፍቻ ቁልፍ’ በቂ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ብሶበትና ቅሽምናው ማቆሚያ አጥቶ “አፈር ፈጭተን ጢብ ጢብ ተጫውተን አብረን ያደግን ነን…” “እናቶቻችን ቡና ይጣጡ፣ ሹሮ ይበዳደሩ ነበር…” “የታላቅ እህቴ ክላስሜት ነበረች…” “ዶሮ ማነቂያ ቀይ ሎተሪ አሥር ብር ነው እያልን ስንሸውድ የኖርን ነን…” ምናምን ብሎ ነገር ድሮ ቀረ፡፡ የዘንድሮ ማንኛውም በር መከፈቻ ቁልፍ… “የእንትን መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ የአገራችን ልጅ ነው…” አይነት “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ሆኗል። አሁን፣ አሁን መቼም አንድ እየተፋቀ ያለ ቀይ መስመር፣ የተማረ/ያልተማረ የሚለው ነው፡፡ አሀ…አንጎሉን ሲበጠብጥ የኖረውም ጨጓራውን ሲበጠብጥ የኖረውም በ‘አንድ ሞገድ’ ሲያስቡ፣ በአንድ ‘ቅላጼ’ ሲናገሩ ምን ማለት ይቻላል! እንደውም…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አሁን፣ አሁን “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ተምረዋል በሚባሉት አካባቢ ብሶበታል ይባላል፡፡ ሌላው በጣም ቀሺም ነገር ምን መሰላችሁ…“የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ውስጥ የሆነ ‘ጸጉረ ልውጥ’ ሰንሰለቱ መሀል ከገባ የትኛው አውሎ ነፋስ እንደወሰደው ሳይታወቅ ወይ ለይቶለት ይወጣታል፣ ወይም አስተማማኝ በሆነ ርቀት ላይ እንዲቀመጥ ይሆናል፡፡

(ሲመቱ እንጂ ሲወረወሩ የማይታዩ ነገሮች አሉ አይደል! የጸጉረ ልውጥም እጣ ፈንታ ይኸው ነው፡፡ ከእነ ተረቱ እኮ…“ባዕድ ከሳመው ዘመድ የነከሰው…” አይደል የሚባለው!) የባዕድ ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…በብሬዥኔቭ ዘመን ሩስያ ውስጥ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… በክሬምሊን ቤተ መንግሥት አይጦች ያስቸግራሉ፡፡ ብሬዥኔቭም የሆነ ነገር ተደርጎ እንዲጠፉ ያዛሉ፡፡ ታዲያላችሁ…በአይጥ መግደል የተካነ ባለሙያ ተፈልጎ ይመጣል። አንዲት ሜካኒካል የሆነች አይጥ ያወጣና ቡሎኗን ሞልቶ ይለቃታል፡፡ ‘አይጧም’ የአይጥ ድምፅ እያሰማች፣ እየተንደረደረች ወደ ውጪ ትወጣና ዘው ብላ ወንዝ ውስጥ ትገባለች፡፡ ታዲያ ክሬምሊንን ሲያምሱት የከረሙት አይጦች በሙሉ እየጮሁ ይከተሏትና አብረው ወንዝ ውስጥ ገብተው ያልቃሉ፡፡ ይሄኔ ብሬዥኔቭ ሆዬ ደስ ይላቸውና ባለሙያውን ምን ይሉታል መሰላችሁ…“ጓድ፣ በነካ እጅህ አንድ ሜካኒካል አሜሪካዊ ልትሠራልኝ አትችልም!” ባዕድነት ጥግ ሲደርስ እንዲህ ያደርጋል! እናላችሁ…በቀድሞ ጊዜ በፊት ሚስት/ባል የሚመረጠው በአብዛኛው የዘር ግንድ እየተቆጠረ ነበር፤ በኋላ ላይ በተለይ በከተማ ሰው አካባቢ እነኛ ነገሮች እንደ መስፈርት መሆናቸው እየቀረ ነበር፤ አሁን ደግሞ በዚህ ስልጣኔያችን ጣራ ጥሶ ሄዶ… ነገሮቻችን ሁሉ የ‘ጣር’ በሆኑበት ጊዜ ብዙ ቦታ ስትሰሙ…አለ አይደል…“ምንም ቢሆን የአገርን ልጅ ማግባት ይሻላል” የሚሉት ነገር መጥቷል፡፡

(እኔ የምለው…ሰዉ ሁሉ ‘የምናምን ነጻ አውጪ’ የሚባል ለማቋቋም እያሰበ ነው እንዴ አጥንት እየተቆጣጠረ መሰባሰብ ያበዛው! ልክ ነዋ…“ማን ማንን ያምናል…” በሚባልበት ዘመን የአገር ልጆች እየተፈላለጉ ያሉ ይመስላላ!) ስሙኝማ…የመጋባትን ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…የጋብሮቮ ወንዶች ለሚስትነት የሚመርጡት ቀጫጭን ሴቶችን ነው ይባላል፡፡ ለምን መሰላችሁ… ቀጭን ሴት መጀመሪያ ነገር ብዙ ቦታ አትይዝም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጭን ሴት ለልብሷ ትንሽ ጨርቅ ነው የምትመርጠው፡፡ አሪፍ አይደል! “በእናታችን በኩል የሩቅ ዝምድና አለን…” “አባቷና አባቴ የተወለዱትም፣ የተዳሩትም አንድ ቦታ ነው…” ምናምን ነገር ከማለት የጋብሮቮያዊው አይነት ወጪ ቆጣቢ ምርጫ እንክት አድርጎ ይሻላል፡፡ “ዘመድ በዘመዱ አይጨክንም ሆዱ…” የሚሏት አባባል አለች፡፡ እናላችሁ… የዘንድሮ ፍልስፍና “ዘመድ ከሆነ አይጨክንም…” ነገር ነው፡፡ እናላችሁ… ዘመድ መቅጠር ልክ እንደ የ‘ሕይወት ኢንሹራንስ’ አይነት ሆኗል፡፡ ልክ ነዋ…ዘምድ አሳልፎ አይሰጥም ይባላላ! ዘመድ ምንም ይሁን ምን አይቶ እንዳላየ… “ዓይኔን ግንባር ያድርገው…” ለማለት ይመቻላ! ነገርዬው…አለ አይደል…“ዘመድና መድሀኒት የተቸገሩ ዕለት…” እንደሚሉት ነው፡፡ ታዲያላችሁ…በየቦታው የዘመድና የባዕድ አይነት አስተሳሰብ በሚያሰጋ ሁኔታ እየተባባሰ ነው፡ (ለነገሩ…አለ አይደል… እዚህ አገር በሚያሰጋ ሁኔታ እየተበላሸ ያለ ነገር መአት ነው፡፡ ችግራችን ምን መሰላችሁ… ‘እንደ እኛ የሚሰጋ…’ መጥፋቱ! ልክ ነዋ…የተያዘው ነገር አለ አይደል…ፈረንጅ ‘ዳሜጅ ኮንትሮል’ የሚለው አይነት ሆኗል፡፡ “እዚህ ቦታ እንዲህ አይነት ነገር ተበላሽቷል…” ምናምን ሲባል መጀመሪያ ችግሩ መኖሩ ይታመናል፡፡

ከዛ በኋላ ምን ይሆናል መሰላችሁ… ‘ዳሜጅ ኮንትሮል’ ይቀጥላል፡፡ “ሰዉ ዝም ብሎ ያወራል እንጂ እንዲህ የሚያሳስብ አይደለም…”፣ “ሚዲያው ነው የሚያባብስው እንጂ…”፣ “…በአጭር ጊዜ የሚፈታ ነገርን ያለልክ መለጠጥ…” ምናምን አይነት “ካፈርኩ አይመልሰኝ…” አይነት ‘ዳሜጀ ኮንትሮል’ ይካሄድላችኋል፡፡ እናላችሁ…“የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” እንደገና ወደ ድንጋይ ዘመን እየወሰደን ነው፡፡ በፊት ድምጻችንን ዝቅ አድርገን ስንሾካሾክ የነበርንባቸው ነገሮች የዕለት ተዕለት ገጠመኝ እየሆኑ ሲመጡ የምር ሊያሳስብ ይገባል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ‘ሊትል ኢታሊ’…‘ሊትል ኢትዮዽያ’ ምናምን እንደሚሉት አይነት መሥሪያ ቤቶቻችንና፣ በሁሉም ደረጃ ያሉ ኩባንያዎቻችን ‘ሊትል ምናምን…’ እየተባሉ ኦፊሴላዊ ያልሆነ “የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው…” ተቀጥያ ስም ሊወጣላቸው ምንም አልቀራቸውም፡፡ ማንም ሳይገፋን ተንደርድረን እንደገባን ዋሻው ሳይውጠን አንደርድሮ የሚያወጣን ተአምሩን ይላክልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2948 times