Monday, 15 April 2013 09:37

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(9 votes)

     መልክአ ኢትዮጵያ - ፲፫

እስከ ዛሬ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ስዘዋወር እንደ ጎብኚ ነበር፡፡ ዛሬ በምገኝበት የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርስቲ ቴምፒ ካምፓስ ግን ሠራተኛ ኾኛለኁ፡፡ ከዩኒቨርስቲው ዘርፈ ብዙ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎቶች መካከል አንዱ በኾነው ‹‹ዘ ስቴት ፕሬስ›› ጋዜጣ ማዘጋጃ ክፍል ውስጥ ተቀምጫለኹ፡፡ እንደ አዳራሽ በተንጣለለው የዜና ክፍል ውስጥ 20 ያህል በትምህርት ላይ የሚገኙ ተለማማጅ ጋዜጠኞች ነፍሳቸውን አጥተው በጥድፊያ ላይ ታች ይላሉ፡፡

የእኔ ቦታ አራት ማዕዝን ቅርጽ ያለውና ለእያንዳንዱ ጋዜጠኛ እንዲያመች እየተከለለ በተከፋፈለው ረጅም ዘመናዊ ጠረጴዛ መሐል ላይ ካለው ወንበር ነው፡፡ በእኛ ሀገር ጋዜጦች የዜና ዝግጅት ክፍሎች ለመድኃኒት ቢፈልግ እንኳ የማይገኘው የአፕል ማክ ባለ 21 ኢንች ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተር በእያንዳንዱ ጋዜጠኛ መቀመጫ ፊት ተደርድሯል፡፡ ተማሪ ጋዜጠኛ ይቅርና ለበርካታ ዓመታት በጋዜጠኝነት የለፉ የእኛዎቹ አንጋፋዎች ለመንካት አይደለም ለዐይናቸው የሚናፍቃቸውን ማክ ኮምፒዩተር ተማሪዎቹ እንደ ተራ ዕቃ በጣታቸው ይደበድቡታል፡፡

እነርሱን ተመልክቼ እኔም ከፊቴ የተቀመጠውን በዝግታ ነካኹት፡፡ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የተገኘኹት ከምርጫ ዘገባ ጋራ በተያያዘ እንደመኾኑ ለዚሁ የሚረዱኝን ድረ ገጾች ወደ ማሠሡ ገባኹ፡፡ ጠቃሚ ናቸው ብዬ ያሰብኋቸውን መረጃዎች በማጠራቀም የዕለታዊውን ጋዜጣ ሥራ ተቀላቀልኹ ማለት ነው፡፡ ከዝግ ድረ ገጾች የተረፉትን ለማየት ፈጣንና ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት አለ በተባለበት ሁሉ ከጓደኞቼ ጋራ የምንኳትነውን በዓይነ ኅሊናዬ እያስታወስኹ ፍጥነቱ በማያውከው የኢንተርኔት ትይይዝ አንዱን ከሌላው አፈራርቃለኹ፡፡ በደመ ነፍስ መጀመሪያ ታይፕ ያደረግኁትን የድረ ገጽ አድራሻ ስመለከት ለራሴ ፈገግ አልኹ፡፡ በስክሪኑ ላይ ያለምንም ከልካይ÷ በቅጽበት ክፍልፋይ የተከሠተው ‹‹ኢትዮ-ሚዲያ›› ነበር፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተቆላለፉብኝን ድረ-ገጾች ያለጓሮ በር ወይም ሌላ በር (ፕሮክሲ ድረ ገጾች) አጋዥነት ሰፈፍኩባቸው፡፡

በቦታው የተገኘኹት የአሜሪካንን ምርጫ ለመዘገብ ቢኾንም በሀገሬ ወቅታዊ ጉዳዮች እየተናጥኹና እየተላጋኹ ሳለ በቀጣዩ ቀን ገበያ ላይ ለሚውለው ጋዜጣ በሚሠሩ ዘገባዎች ላይ ለመወያየት ስብሰባ ተጠራን፡፡ ቀልቤን ሰብስቤ ወደ ስብሰባው አዳራሽ ገባኹ፡፡ ስብሰባውን የምትመራው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ናት፡፡ በዚህ ጋዜጣ ላይ አብራኝ ከተመደበችው የናሚቢያ ጋዜጠኛ ጋራ ከሰዓታት በፊት ስንደርስ መጀመሪያ የተዋወቅነው ዋና አዘጋጇን ነበር፡፡ ጋዜጣው የተማሪዎች ጋዜጣ ቢኾንም ሥራ ከመጀመራችን በፊት ዋና አዘጋጇን ማግኘት እንደሚገባን ሲነገረን በካርና በሞያው የሰነበተ ጋዜጠኛ ጠብቄ ነበር፡፡ ወደ ዋና አዘጋጇ ቢሮ ስንዘልቅ ግን ፊት ለፊት የተያየነው ከቀጭን፣ አጭር የ21 ዓመት ወጣት ጋራ ነበር፡፡ እርሷም ራሷን እስክታስተዋውቅ ድረስ እኔ የምጠብቀው ሌላ ልሂቅ አዘጋጅ ነበር፡፡ ወጣቷ ራሷን ስታስተዋውቅ፣ ስለ ጋዜጣው ገለጻ ስታደርግና እንኳን ደኅና መጣችኹ ስትለን መገረሜን መደበቅ እስኪያቅተኝ ድረስ በተማሪ እና የጋዜጣ አዘጋጇ የራስ መተማመን፣ ፍጥነትና ቅልጥፍና ፈዝዤ ቀረሁ፡፡ ግርምቴ ግን ጣራ የነካው በስብሰባው ላይ እኔንና ሌሎች ተማሪ ጋዜጠኞችን ለግዳጅ እንደሚሰማራ ወታደር የሥራ ትእዛዝ ስታዥጎደጉድ ነበር፡፡ ጋዜጣው ወደ ማተሚያ ቤት ስለሚላክበት ጊዜ ስታወራ በሰዓትና ደቂቃ ወስና ነበር፡፡ የዋና አዘጋጇ ርግጠኝነት ቢደንቀኝ ስለ አሠራሩ ጠየቅኹ፡፡

የተጠናቀቁ ገጾችን ከዴስካቸው ላይ ሳይነሡ የጋዜጣውን ኅትመት ወደሚያከናውነው የግል ማተሚያ ቤት ወዲያውኑ በኢ-ሜይል እንደሚልኩ ነገረችኝ፡፡ በሀገሬ የጋዜጣ አዘጋጅ መኾኔን የምታውቀው ዋና አዘጋጅ የእኛ ሀገር አሠራር ምን እንደሚመስል ልምዴን እንዳካፍል ጋበዘኝች፡፡ ይኼኔ ጉድ ፈላ! እንዴት በወረቀት አትመን እንደምንልክ፣ አንድ ለእናቱ በኾነች የመንግሥት ማተሚያ ቤት የኅትመት ወረፋ ለመያዝ በእሽቅድድም የምናደርገውን መራወጥ፣ የመንግሥት ጋዜጦች እኛ በምንታተምበት ሰዓት መጥተው በአናቱ በመግባት ኅትመታችን ተቋርጦ ዘግይተን ወይም ደግሞ በሌላ ቀን እንዳንወጣ የምንሰጋውን ስጋት በሠቀቀን ጥርሴን እያፋጨኹ አስረዳኹ፡፡ የተማሪ ጋዜጣ ዋና አዘጋጇ ከእኔ ከጠበቀችው ልምድ ይልቅ የምትሰማውን ማመን አልቻለችም፡፡ “አንቺ የምትነግሪንን አሠራር እኛ የምናውቀው የጋዜጠኝነትን ታሪክ በሚተርኩ መጻሕፍት ላይ ነው፤” አለችኝ፡፡ ይህን ስትል በወረቀት አትሞ መላኩን ማለቷ ነበር፡፡ ሌላውማ ለእነርሱ እንግዳ ነው፡፡ በመጨረሻ ዋና አዘጋጇ ለዘገባ ስታሰናብተን ከከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ጋራ ነበር፡፡ “የኦባማን ይኹን የሚት ሮምኒን ኩኪስ መብላትም ኾነ ውኃ መጠጣት አጠብቆ የተከለከለ ነው” ስትል ቁርጥ ያለ ትእዛዝ አስተላለፈች፡፡ ስለዚህ ዐይነቱ ማስጠንቀቂያ የሀገሬ አወዛጋቢው የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርና ተያያዘው የሚመጡ ቅሬታዎች ታወሱኝ፡፡ ተማሪዎቹ ለሞያው የሥነ ምግባር መርሖዎች የሚሰጡት ቦታ ከፍተኛ ነው፡፡ ‹ድሮስ ከዚህ ወዴት እንወላፈታለን› በሚል ታዛዥነት በሙሉ ልብና በመስማማት የዋና አዘጋጃቸውን ማስጠንቀቂያ በተግባር መፈጸማቸውን አረጋግጫለኹ፡፡

ምርጫውን ለመዘገብ በዕለቱ የተመደብነው 12 ነበርን፡፡ ትኩረቴን የሳበው ለአንድ ዘገባ የተመደበው ሰው ብዛት አልነበረም፤ ለፊልም ቀረጻ የምንወጣ ይመስል የተንጋጋው የመሣርያ ብዛት እንጂ፡፡ በሀገሬ ከፍ ባለ በጀት ይሠራሉ የሚባሉ ፊልሞች ይቀረጹባቸዋል የሚባሉት ካሜራ እስከ ጓዞቹ፣ ዘመናዊ የምስል ወድምፅ መቅረጫ መሣርያዎች አንዳቸውም አልቀሩም፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ግል መኪናቸው ሲያመሩ እኔም ከአንዷ ጋራ እንድዳበል ተደረገ፡፡ ኹኔታው የ97 ምርጫን ተከትሎ በተነሣ አለመግባባት ምርጫው ይደገም ከተባለባቸው ቦታዎች አንዱ በኾነው በሆሳዕና ገጠር ቀበሌዎች ለዘገባ የተዘዋወርኹበትን ጊዜ አስታወሰኝ - በወቅቱ የያዝኋት ሚጢጢዬ ካሜራና ከቀበሌ ቀበሌ በረዳት የዞርኹበት ሞተር ሳይክል - በትወስታዬ ለራሴ ፈገግ አልኹ፡፡ ሁለት ቀናትን ያሳለፍኁበት ‹‹ዘ ስቴት ፕሬስ›› የተማሪዎች ጋዜጣ ኅትመት ባለሙሉ ቀለም ነው፡፡ በየዕለቱ በ15 ሺሕ ኮፒ ይሠራጫል፡፡ ዕድሜውም ትንሽ አይደለም፡፡ ለአምስት ጊዜ ያህል ስሙ የተቀያየረው የተማሪዎች ጋዜጣ መታተም ከጀመረ 120 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ለምን አያስቆጥር!? በሀገሬው ጋዜጣ ብርቅ አይደለ፡፡ ለነገሩ አሜሪካኖቹ ደግ ናቸው፡፡ የዩኒቨርስቲው ጋዜጣ ትልቅነትና ዘመናዊነት በመንፈሳዊ ቅናት እንዳላብሰከሰከኝ፣ ፔንሳኮላ ፎሎሪዳ ወደምትባል ትንሽ ከተማ ወስደው የግለሰብ ቤት በሚመስሉ ቢሮዎች ውስጥ በአንድ ሰው የሚሠሩ ጋዜጦችን አስጎበኙኝና “ይቺ ይቺህማ እኛም ሀገር አለች” ብዬ ለመጽናናት አስቻሉኝ፡፡ ይቺም መጽናናት ግን የምታውል የምታሳድር አልነበረችም፡፡ እነ ኤ.ቢ.ሲ እና ሲ.ቢ.ኤስን የመሳሰሉ ታላላቅ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችን፣ እነቺካጎ ትሪብዩንን ዐይነት ስመ ጥር ጋዜጦችንና ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ያተረፉትን እንደ ቪኦኤ ዐይነት ሬዲዮ ጣቢያዎችን በመጎብኘት ትንታዋ ጠፋች፡፡ አትላንታ በሚገኘው የሲ.ኤን.ኤን የቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤት ለሁለት ሰዓት ያህል ቆይታ ሳደርግማ የሀገሬ ሚዲያ ጉዳይ ጨርሶ ቆረጠልኝ፡፡

                                ******************************

የሲ.ኤን.ኤን የቴሌቭዥን ሕንፃን ከተለጠፈበት ግዙፍ ማስታወቂያ የተነሣ በቀላሉ ከርቀት መለየት ይቻላል፡፡ ወደ ሕንፃው እየቀረብኹ በመጣኹ ቁጥር ግዙፉ ማስታወቂያውም እየቀረበ ይመጣ ጀመር፡፡ በቀይ የተጻፈውን “CNN” የሚለውን ዓርማ አየኹት፡፡ የእግረኛውን መንገድ አቋርጠን ወደ ሕንጻው ስንጠጋ መግቢያው ላይ በርከት ያሉ ነጫጭ ታክሲዎች ተኮልኩለዋል፡፡ አሽከርካሪዎቻቸው ዐይናቸውን በሩ ላይ ተክለው ከሕንጻው የሚወጡ ተሳፋሪዎችን ይጠባበቃሉ፡፡ ሁሉንም በተርታ አማተርኳቸው፡፡ የቆዳቸው ቀለም ከእኔ ጋራ ተመሳሳይ ነው፡፡ ከፊት ፈገግታ ጋራ አንገታቸውን ቀልበስ አደረጉልኝ፡፡ አጸፋውን ሰጠኋቸው፡፡ መቼም በሰው አገር ሁሉን በሆድ ችሎ ነው፡፡ በለሆሳስ “እስኪ አዲስ አበባ ሂዱና ኢ.ቴቪ በር ላይ ቆማችኹ ደንበኛ ጠብቁ!” ብዬ ማጉረምረሜ አልቀረም፡፡ እንኳንም አልሰሙኝ፡፡ ያለማንም ታጣቂ ጠባቂነት ጠጋ ሲሉት ወደሚከፈተው የጣቢያው መግቢያ በር አመራኹ፡፡ ወደ ውስጥ ከዘለቅኹ በኋላ እጅግ ሰፊ በኾነው ሕንፃ መሐል ለመሐል ቆሜ ግራ ተጋባኹ፡፡ በስተግራ በኩል የተሰቀለው ትልቅ የድርጅቱ ዓርማ ነው፡፡ በስተቀኝ በኩል ግን ራሱን የቻለ መግቢያ ያለው ሆቴል ነው፤ የተሳሳትኹ መስሎኝ ተደናገጥኹ፡፡

ዝም ብዬ አስጐብኚዎቼን ተከተልኋቸው፡፡ አንድ ደረጃ ከወጣን በኋላ ያየኹት ነገር ደግሞ ግርታዬን ይበልጥ አባባሰው፡፡ ስፋቱ የስታዲዬም ግማሽ የሚያኸለው የሕንፃው የመጀመሪያ ፎቅ የገበያና የመዝናኛ ነው፡፡ በመገበያያና መዝናኛ ቦታው ውስጥ እንደ ማክዶናልድና ስታር ባክስ መሰል የታወቁ የምግብና መጠጥ እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶች መሸጫ ሱቆች ዙሪያውን በመልክ በመልክ ተደርድረዋል፡፡ በሁሉም ሱቆች ማለት ይቻላል የቴሌቭዥን ጣቢያው ዓርማ የተለጠፈባቸው ቁሳቁሶች ለገበያ ቀርበው ይታያሉ፡፡ መካከሉ ላይ ለሰው መዝናኛ በሚመች መልኩ መቀመጫዎች ተሰትረው በሰዎች ተይዘዋል፡፡ ሕንፃው በቆሙም፣ በተቀመጡ እንዲሁም ወዲያና ወዲህ በሚሉ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ ያለሁበት ቦታ የሲ.ኤን.ኤን ዋና መሥሪያ ቤት ሳይሆን ቀድሞ የቴሌቭዥን ጣቢያው ይጠቀምበት የነበረው ሕንጻ ወደ ሙዚየምነት ተቀይሮ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ መቼም አሜሪካኖቹ የትም ይሁን የት ከውጭ ወደ ውስጥ የገባ እንግዳ ሲመለከቱ ከተፎዎች ናቸው፡፡ ከመ ቅጽበት “ምን ልርዳዎት?” በማለት በሥልጠና ከተቸሩት የይመሰል ፈገግታ ጋራ ከፊት መጥተው ድቅን ይላሉ፡፡ አንዱ አስጎብኚ ርዳታ መሻታችንን አይቶ ተጠጋን፡፡ ጣቢያውን መጐብኘት እንደምንፈልግ ስንነግረው ፊት ለፊት ወደሚታየን የፍተሻና የመረጃ ዴስክ እየመራ ወሰደን፡፡ ጣቢያውን ለመጐብኘት እያንዳንዳችን 15 ዶላር እንድንከፍል ተጠየቅን፡፡ አሜሪካ በዚህ አያያዟ በትንፋሽ ልክ ገንዘብ የሚያስከፍሉ ድርጅቶች ሳታቋቁም የምትቀር አይመስለኝም፡፡

በኢ.ቴቪ እንደሚደረገው በቦርሳዬ የያዝኁትን የኤሌክትሮኒክስ ዘር ሰብስቤ ለጠባቂ ለመስጠትና ቁጥር የተጻፈበትን ምትክ ካርድ ለመቀበል ተዘጋጀኹ፡፡ ከመግቢያ ክፍያው ውጭ ግን እንዲያ ያለውን ጥያቄ ያነሣ አልነበረም፡፡ ብቻ ጠንከር ካለ ፍተሻ በኋላ ዕቃችንን እንደያዝን እሳት በላሰ አስጐብኚ እየተመራን፤ በረጅሙ የኤሌክትሪክ ደረጃ (ስኬለተር) ሽር እያልን ጉብኝቱን ጀመርን፡፡ ከደቂቃዎች ጉዞ በኋላ በሕንጻው አናት ላይ ተገኘን፡፡ የገዘፈ የፎቶ ካሜራ የያዘ አሜሪካዊ በዚያች “ሥልጡን” ፈገግታ ታጅቦ በቴሌቭዥን ጣቢያው የስቱዲዮ ቅርጽ ወደተዘጋጀው ወንበርና ጠረጴዛ ወስዶ ልክ ስቱዲዮ ውስጥ ዜና እያነበብን በሚመስል መልኩ ፎቶ አነሣን፡፡ ለመጣው ሁሉ ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽማል፡፡ ወደ ጣቢያው በብዙ ቁጥር የሚጎርፈው ጐብኚ ማስታወሻ እንዲኖረው የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ መሪያችንን ተከተልን ጉብኝታችንን ቀጠልን፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያውን አመሠራረት በመተረክ የጀመረው አስጐብኚ አንባቢዎቹ ዜናውን በምን መልኩ ቀርጸው ለተመልካች እንደሚያቀርቡ መሣርያዎቹን እያሳየ ያስረዳን ጀመር፡፡ የቀድሞ የጣቢያው ዜና ማቅረቢያ ስቱዲዮ ከነሙሉ መሣርያው ለጉብኝት ክፍት ኾኗል፡፡ “ዜና አንባቢው በቴሌቭዥን መስኮት እንደምታዩት በቃሉ የሚያወራ አይምሰላችኹ፤ ሽወዳ ነው፡፡ ማንኛውም ዜና አንባቢ ዜናውን የሚያገኘው ከፊት ለፊቱ ካለው ስክሪን ላይ ነው፡፡ ይህ ስክሪን በድንገት ችግር ቢያጋጥመው እንኳን አንባቢው በወረቀት ከተዘጋጀው ላይ እንዲያነብ በፍጥነት ይተካለታል” አለን፡፡ ጣቢያው በሚከፍለው ደሞዝ፣ ጣቢያው አናት ላይ ቆሞ፣ “እየሸወዷችሁ ነው እንጂ እንዲህ እኮ ነው የሚሠሩት” ማለት፡፡ የአየር ትንበያን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንዴት እንደሚቀርቡ ከአስረጂ ጋራ እየቀረበ ተገለጸልን፡፡ የቤቱ ዙሪያ ክዳን በመስተዋት ወደተሸፈነው ዜና ክፍል አመራን፡፡ መስተዋቱ ላይ ተለጥፈን በቁጥር ለመገመት በሚያስቸግር ሰውና ኮምፒዩተር የተሞላውን የዜና ክፍል (News room) ተመለከትን፡፡ በማራኪ አኳኋን በተደራጀው የኮምፒዩተርና ዘጋቢዎች ብዛትና አቀማመጥ ድምፄን አጥፍቼ ጸጥ አልኹ፡፡

ሳይጠየቅ የሚያወራው አስጐብኚ ደግሞ “በዚህ ዜና ክፍል የሚሠራው ዜና የሚተላለፈው ለአገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ለዓለም አቀፉ ጣቢያ የሚሠሩት ዜና ክፍሎች ሌሎች ናቸው” በማለት ትንፋሽ አሳጣኝ፡፡ በአሜሪካን አገር የተለያዩ ግዛቶች በተዘዋወርኹበት ወቅት እንደ ኤ.ቢ.ሲ፣ ሲ.ቢ.ኤስ፣ ፎክስ እና አነስተኛ የመንደር የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን የመጐብኘት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ ሌሎቹ እንደ ሲ.ኤን.ኤን ግዙፍ ባይኾኑም የየራሳቸው ጠንካራ አደረጃጀት አላቸው፡፡ በሲ.ኤን.ኤን የአገር ውስጥ ዜና ዘጋቢዎች ዜና ክፍል አናት ላይ ቆሜ የእኛን አገሯን “አንድ ለእናቱ” ማፎካከር ቢያቅተኝ ያየኋቸውን ተራ በተራ እያስታወስኩ አቻ እፈልግለት ገባኹ፡፡ ብቻ እንደምንም አንድ አይጠፋለትም፤ ግን ኢቲቪ አስከፍሎ ያስጐብኝስ ቢባል ምኑን ያስጎበኝ ይኾን - አሰላሰልኹ፡፡ እዚያው ቆሜ አንድ ሐሳብ ተከሠተልኝ፤ ‹‹የሺሓት ዓመታት ታሪክ ባላት አገር የመጀመሪያና ብቸኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ›› በሚል መሪ ቃል አደራጅቶ ለጉብኝት ክፍት ቢኾን በቱሪስት መስብሕነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ቅርስ ይኾን ነበርi ከቱሪስቶቹ የሚገኘው ምንዛሬም ስንት ቀዳዳ ይሸፍን ነበርi ይቺን ሐሳቤን የሚቀባበልልኝ ባገኝ እንዴት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ጐብኚዎች አስጐብኚውን በጥያቄ ሲያጣድፉ እኔ ግን በበርካታ ሰዎች ዐይን ሥር ቁልቁል እየታዩ ስለመኾናቸው ልብ ያላሉት ወይም ምንም ሳይመስላቸው ትኩረታቸውን ፊት ለፊት ባሉት ኮምፒዩተሮቻቸው ላይ አድርገው በሥራ የተወጠሩትን ጋዜጠኞች ተመስጩ ነበር፡፡ የአስጐብኚውን እግር የምከተለውም ያለቀልቤ ነበር፡፡ የተሰማኝ ቅናት ይውጣልሽ ብሎ ነው መሰለኝ በጣቢያው ደረጃ እጅግ ዘመናዊ ወደተባለው የቴሌቭዥን ስቱዲዮ ወሰደን፡፡ ስቱዲዮውን በመስተዋት ውስጥ አሻግረን እንድናይ ጋበዘን፡፡

ዜና አንባቢዋ በአንድ እይታ ለማማተር በሚያዳግተው ሰፊ ስቱዲዮ መካከል ላይ ተቀምጣ ዜና ለማንበብ በዝግጅት ላይ ነች፡፡ ዙሪያዋን በተለያዩ ካሜራዎች ተከባለች፡፡ ክፍሉ በቀረፃ ዕቃዎች ታጥቋል፡፡ በረጅም ክሬን ላይ የታሰረ ካሜራ በባለሞያ አጋዥነት ሲንቀሳቀስ ተመለከትኹና ዋጋውን ጠየቅኹ፡፡ አስጎብኚያችን ካሜራው ከነክሬኑ ዋጋው 300ሺሕ ዶላር አካባቢ እንደኾነ ጠቆም አድርጐ ጥቅሙን ይዘረዝርልኝ ያዘ፡፡ እነርሱን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡ “ገንዘብ ነክ ነገር እንኳን ለመናገር ይከብደኛል፤ ቁጥሩን አላውቀውም እገሌን ብትጠይቂው ይሻላል፤ ይህን ከእኔ ይልቅ እገሌ ቢናገረው ይበጃል” በሚል ምክንያት ምኑንም ምኑንም ከምስጢር ቋት አይደባልቁትም፡፡ የካሜራውን ዋጋ ወደ ብር መንዝሬ ተመንኹት፤ ግና ምን ሊያደርግልኝ፡፡ ለእኛ ያለው መች አነሰና እርሱኑ ተራ እየጠበቁ ይሥሩበት ስል በስጨት አልኹ፡፡ ሐሳቤ ግን በካሜራውና ክሬኑ ላይ ተተክሎ ቀረ፡፡ ጉብኝቱን ስንጨርስ መውጫው ድረስ ሸኙን፡፡ ይቺ አሜሪካ ሳስባት ሳስባት ድንቅ ትለኛለች፡፡ በተለያየ ምክንያት ባየኋቸው ቦታዎች ሁልጊዜ የመውጫ በራቸው የሚወስደው በባለስጦታ ዕቃዎች መሸጫ መደብር በኩል አድርጎ ነው፡፡ የስጦታ መሸጫው ቤት ለተጐበኘው ቦታ መውጫ በር ኾኖ ያገለግላል፡፡ በእንዲህ ያሉ የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ ቦታ ከእኔ በቀር ‹የቋጠረ› ሰው አላየኹም፡፡ የሦስት ዶላር ዕቃም ቢኾን ገዝቶ ይወጣል፡፡ እናላችሁ የሲ.ኤን.ኤን አስጐብኚዎች መውጫ ብለው ያሳዩን በር መግቢያ ኾኖ አገኘነው፡፡

መግቢያው ላይ የተነሣነው ፎቶ በውብ መያዣ ውስጥ ተከትቶ ቀረበልኝ፡፡ ማስታወሻነቱ አስደስቶኝ እነሱንም አመስግኜ ልወጣ ስል 20 ዶላር መክፈል እንዳለብኝ ተነገረኝ፡፡ አይ ኢ.ቴቪ! ስንት እና ስንት ገበያ አመለጠው፡፡ በስጦታ መሸጫ ሱቁ ውስጥ የሲ.ኤን.ኤን ዓርማው (ሎጐው) ያልታተመበት አይገኝም፡፡ ከቁልፍ መያዣና የጠርሙስ መክፈቻ ጀምሮ በሁሉም ነገር ላይ ዓርማውን አሳትሞ ለገበያ አቅርቦታል፤ ገበያተኛም አላጣም፡፡ ሱቁ በገዢዎች ተጨናንቋል፡፡ ያላየነውን ሌላ ለማየት ሕንፃውን ለቀን ወጣን፡፡ ባለታክሲዎቹ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዐይናቸውን ጉብኝቱን አጠናቆ በወጣው ሰው ላይ ጥለዋል፡፡ ወደ ሲ.ኤን.ኤን ሕንጻ ስገባ “የእኛም ሀገር ባለታክሲዎች በኢ.ቴቪ ደጅ ቆመው በሠሩ ኖሮ” ስል የተመኘኹላቸውን ሰረዝኹት፡፡ ባለታክሲዎቹ ኢ.ቴቪ ደጅ ቢኮለኮሉ ኖሮ በካኪ ፖስታ ምሳ ሳሕናቸውን ይዘው ከሚወጡ የጣቢያው ሠራተኞች ውጭ የትኛውን ተሳፋሪ፣ የትኛውንስ ጎብኚ ያገኙ ነበር? (ይቀጥላል)

Read 3226 times Last modified on Monday, 15 April 2013 10:07