Monday, 15 April 2013 10:09

በእባብ የተነደፈው ግለሰብ እባቡን ነክሶ ገደለ

Written by 
Rate this item
(79 votes)

በእባብ የተነደፈ የኔፓል ተወላጅ እባቡን መልሶ በመንከስ ብድሩን እንደመለስ ሰሞኑን ተዘግቧል፡፡ ሮይተርስ የኔፓል ዕለታዊ ጋዜጣ አናፑርና ፖስትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሞሃመድ ሳልሞ ሚያ የተባለውን ግለሰብ ኮብራ እባብ የነደፈው በሩዝ ማሳ ውስጥ ነበር፡፡ ሞሃመድ ግን ዝም አላለም፡፡ የገባበት ገብቶ በመያዝ ነክሶ ገድሎታል - እባቡን፡፡ “በዱላ ልገድለው እችል ነበር፤ ነገር ግን በጥርሴ ነክሼ ገደልኩት፤ ምክንያቱም ተናድጄ ነበር” ብሏል ከአገሪቱ መዲና ከካትማንዱ ደቡብ ምስራቅ 200ኪ.ሜ ላይ በምትገኘው መንደር የሚኖረው የ55 ዓመቱ ሞሃመድ፡፡ በኔፓል “ጐማን” እየተባለ የሚጠራው ይሄ የእባብ ዝርያ “ኮመን ኮብራ” በሚል ስያሜም ይታወቃል ብሏል አናፑርና ፖስት፡፡ በእባቡ የተነደፈው ሞሃመድ ሳልሞ ሚያ፤ በመንደሩ የጤና ጣቢያ ህክምና እየተደረገለት ሲሆን ለህይወቱ እንደማያሰጋው ተገልጿል፡፡

እባቡ በኔፓል በመጥፋት ላይ ካሉ የማያጠቡ እንስሳት ዝርያ ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ባለመሆኑ እባቡን ነክሶ የገደለው ግለሰብ ከክስ እንደዳነ የአካባቢው ፖሊስ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ እባቡን ነክሶ በመግደሉ ፍ/ቤት ይቆማት ነበር ተብሏል፡፡ ይታያችሁ … ሞሃመድ እባቡን ነክሶ የገደለው ለአደን አይደለም - ስለነደፈው እንጂ፡፡ ቢሆንም በመጥፋት ላይ ያሉ እንስሳትን መግደል በኔፖል ያስጠይቃል ብሏል - ሮይተርስ፡፡

Read 18700 times