Saturday, 12 November 2011 07:30

መንግስት መልካም መልካሙን ቢኮርጅልን …

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

የሌሎች ሀገራትን ተመክሮዎች በፍጥነት በመኮረጅና በዚያኑ ያህል ፍጥነትም ወደ ተግባር በመቀየር ላለፉት ሃያ አመታት ሀገራችንን የመራት የኢህአዴግ መንግስት የምርጥ ሪከርድ ባለቤት ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሌሎች ሀገራት ተመክሮዎችን መኮረጁ በራሱ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ችግሩን ግን ሁሌም የሚኮርጅው ክፉ ክፉዎቹን ብቻ እየመረጠ ነው፡፡
ይሄ ዝም ብሎ በምቀኝነት የተሰነዘረ ትችት ከመሰላችሁ ኢህአዴግ በመስኩ የካበተ ልምድ ካላቸው አገራት የወሰድናቸው ናቸው ያላቸውን አዋጆችና ደንቦች ተመልከቱ፡፡
ለዜጎች መብትና ነፃነትን የሚያጐናፅፉ ናቸው ወይስ ክልከላና አፈናን የሚያጠናክሩ? በቅርቡ በፓርላማ ስለ ፀረ ሽብር አዋጁ ያብራሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ህጉ የተወሰደው በዘርፉ የካባተ ልምድ አላቸው ከተባሉ የምዕራብ አገራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


ጠ/ሚኒስትሩ ከም/ቤት አባላት ይሁን ከጋዜጠኞች አንዳንድ ሞጋች ጥያቄዎች ሲቀርብላቸው የሚሰጡት በሃይለቃልና በዘለፋ የታጀቡ ምላሾችም ትዝብት ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲዬ ዓለምን ጉድ ያሰኘ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘገብዙ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ሲመልሱ በእርግጋታና በጥሞና ሳይሆን “የኢኮኖሚክስ ሀሁ የማይገባችሁ” በሚል የማናናቅ ስሜት እንደሆነ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚሻለው ግን ለእኛ የኑሮ ውድነት እያንዳንዱን ቀን ፈተና ላደረገብን ዜጐች የኢኮኖሚውን ዕድገትም ሆነ የኢኮኖሚ መርህ ሀሁን በሚገባንና በአሳማኝ አቀራረብ ማስረዳት ነበር፡፡
አብዛኞቻችን በዚህች በዜጐች የመብት ጥበቃ አያያዟ፣ በኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴዋ ቀን ከሌት በሚዘመርላት ሀገር እየኖርን፣ ነገር ግን አንድ ብር ከሀምሳ ሳንቲም የሚያወጣ ዳቦ በሌማታችን ውስጥ ከሳምንቱ ቀናት በሁለቱ እንኳ ማሳደር አቅቶን በችጋሩ የተነሳ በህይወት የመቆየትና የመሞት ልዩነቱ ጠፍቶብን፤ አለን ወይስ ሞትን ነው የምንባል እያልን ነጋ ጠባ ራሳችንን ለምንጠይቀው ምንዱባኖች እንዲህ ላለ ክፉ እጣ የተጋለጥነው ምን ሀጢያት ሰርተን እንደሆነ ቢነግሩን እንደፅድቅ ይቆጠርላቸው ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ በሌሎች ሀገራት አሠራር ከቀናን መቅናት ያለብን በልባሞችና ለህዝቦች የተሻለ መብትና ነፃነት በሚያጐናጽፉት ህጐችና አሠራሮች መሆን ነበረበት፡፡ የሌሎችን ሀገራት አሠራር ለመኮረጅ ይህን ያህል ትጋትና ተነሳሽነት ካለን ዋነኛ ትኩረታችን መሆን የነበረበት በአሪፎቹ የህግ አንቀጾች ላይ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የምርጫ ስርአት ህጉ አሪፍና አፈፃፀሙም በህግና ህግን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በአሜሪካ የፕሬዚዳንቱን፣ የሴኔቱንና የኮንግረሱን አብላጫ መቀመጫ የተቆጣጠረው የሪፐብሊካኑ ፓርቲ ቢሆን የተፎካካሪውን የዲሞክራቲክ ፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ ለማፈንና ለማከዋብ ቀርቶ አፍንጫው ላይ የሚቀናጡትን ዝንቦች እሽ ለማለት እንኳ ከደፈረ፣ ለሁሉም እኩል የሚሠራው ህግ ለዚህ ድፍረቱ እንዴት ያለ ቅጣት እንደሚያከናንበው ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ አይሞክረውም፡፡
በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ለራሱ የተለየ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ፣ ከህግ አግባብ ውጭ የፖለቲካ የመጫወቻ ሜዳውን ለማጥበብ መሞከር ቀድሞ ነገር አይታሰብም፡፡ ከተሞከረ ግን ለሞከረው መንግስትና ፓርቲ ድርጊቱ ራስን ለማጥፋት እንደተሞከረ እርምጃ ይቆጠርበታል፡፡ ለምን ቢባል የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ሊሸከሙት የማይቻል ከባድ መዘዝ ያስከትላልና፡፡
በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የህዝብንና የሀገርን ደህንነትና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል የተለየና አጣዳፊ ችግር ተፈጥሮ፣ ይህንን ለመቀልበስ የሚረዳ የተለየ ህግ አውጥቶ ለመተግበር የሚያስገድድ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ፤ ለራስ ፓርቲና መንግስት የተለየ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስገኘት በሚል እሳቤና እቅድ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለይ ደግሞ የህዝብን ነፃነትና የዲሞክራሲ መብት በሰበብ አስባብ መነካካትና መሸራረፍ ጨርሶ የማይፈቀድና የማይቻል ድርጊት ነው፡፡ ይልቁንስ ዋናው ትኩረታቸው በስልጣን ላይ በሚቆዩበት የተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከሌላው የተሻለና የላቀ ስራ በማከናወን ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን የሚያበቃ የህዝብ ድጋፍ ማሰባሰብና ማፍራት ነው፡፡
በእነዚህ ሀገራት የተለየ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የያዙትን ስልጣንና የመንግስት ሀብት ተቃዋሚዎችን ለማዋከብ፣ የራስ ደጋፊን ደግሞ ለይቶ ለመጥቀም መገልገያ ማድረግ በህግ አጥብቆ የተከለከለ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ በእነዚህ ሀገራት ፕሬሱ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የመደገፍ መብቱ በህግ የተጠበቀና የተረጋገጠ ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ መንግስትን በፖሊሲዎቹና በጠቅላላው የመንግስትነት እንቅስቃሴዎቹ የመቃወምና የመተቸት መብቱም በህግ የተጠበቀና የተረጋገጠ ነው፡፡
በእነዚህ ሀገራት ፖሊሲዎችን አሊያም የመንግስትን ድርጊቶች ተቃወማችሁ ወይም ተቻችሁ በሚል ፕሬሱንና አባሎቹን ማዋከብ ማንገላታት፤ ሙሾ ደርዳሪ፣ መርዶ ነጋሪ ወዘተ እያሉ በመንግስት እጅ ያለውን የመጨቆኛ መሳሪያ በመጠቀም የአፈናና የክልከላ እርምጃ እንዲወስድ ግልጽ ቅስቀሳ ማድረግ በህግ የሚያስጠይቅ ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ የመንግስትነት ስልጣን የሚገኘው በነፃና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ፣ በህዝብ ፈቃድና ይሁንታ እንጂ ተቃዋሚን የእግር መትከያ ቦታ በማሳጣትና በማዋከብ፤ የምርጫ ሳጥንንም በመቅደድና በመገልበጥ እንዳልሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የሌሎች ሀገራትን ህግ ከኮረጅን አይቀር መልካም መልካሙን ቢሆን ከሁሉ በላይ ጥቅሙ ለራሱ ለመንግስት ነው፡፡
ሌላው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ የመንግስትን የተለያዩ የተሳሳቱ ድርጊቶች እውነተኛ ለማስመሰል የሌሎችን ሀገራት ድርጊት እንደማስረጃ የማቅረብ አባዜያችን ጉዳይ ነው፡፡ የአሜሪካ ህገመንግስት መቼም ምንም ቢሆን የሚያገለግለው ለአሜሪካ እንጂ ለኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚሁ አግባብ የአሜሪካ የፀረ ሽብርተኝነትም ሆነ ሌላ ጉዳይ ህግ የሚሠራው ለራሷ እንጂ ለእኛ ከቶም ሊሆን አይችልም፡፡
የእኛ ዋነኛ ህጋችን የራሳችን ህገመንግስት እንጂ የአሜሪካ ህገመንግስት አይደለም፡፡ እናም የአሜሪካ የተሳሳተ ድርጊት ለእኛ የስህተት ማስተባበያ ወይም ለእኛ የተሳሳተ ድርጊት የይለፍ ፈቃድ ሊሆን አይችልም፤ አይገባምም፡፡
አሜሪካ ሽብርተኛ የምትላቸውን ሰዎችና ቡድኖች በልዩ ኮማንዶ ሃይልና በአብራሪ አልባ አውሮፕላን በሚሳይል ያለ አንዳች የህግና ፍትህ ሂደት ስለገደለችና ስላስገደለች እኛም ተቃዋሚዎቻችንን እንደፈለግን ማድረግ እንችላለን ብሎ ማሰብና መንቀሳቀስ በምንም አይነት መለኪያ ተቀባይነት የለውም፤ የምንመራውና የምንገዛው በህግና ለህግ እንጂ በጉልበተኛ ሀገር ህገወጥና ፍትህ የጐደለው ድርጊት ሊሆን አይገባም፡፡
መንግስት የጣረውን ያህል ጥሮ በምግብ እህል ራሱን ለመቻልና ህዝቡን ለመመገብ ቢሞክርም በተለያየ ጊዜ በሚከሰት ድርቅና ሌላም አደጋ የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐቹን ከምግብ እጥረትና የረሀብ ጠኔ ችግር ለማዳን እንዳልቻለ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተፈጥሮን የድርቅ አደጋ ለምን ልታስቀረው አልቻልክም ብለን መንግስትን መውቀስ ተገቢ ባይሆንም፤ ለተደጋጋሚ የምግብ እጥረት ችግር የሚጋለጡት የህብረተሰባችን ክፍሎች የተወሰኑና በተወሰነ አካባቢ ላይ የመሆኑን ጉዳይ በማንሳት፣ በዚያ አካባቢና በዚያ ህብረተሰብ ላይ ተገቢው የልማት ስራ እንዳልተሠራ በማውሳት መንግስትን መውቀስ እንችላለን፡፡ የዚህን ችግር መፍትሔ በማፈላለግ ላይ መነጋገር እንጂ “በአሜሪካም እኮ ረሃብተኛ ህዝብ አለ” በማለት አስቂኝ ማስረጃ ማቅረብ የእኛን ስንፍና ጨርሶ ሊሞላውና ሊሸፍንልን እንደማይችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ደጋግመው እንዳስገነዘቡን፤ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በድህነት የሚኖር በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ማንም በቀላሉ ሊያረጋግጠው የሚችል ቀላል መረጃ ስለሆነ ሀሰት ነው በሚል ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የሚሟገት አይኖር ይሆናል፡፡ ከተገኘም የኢኮኖሚክስ ሀሁ የማያውቅና ራሱን ከወቅታዊ መረጃ ያገለለ ወይም የህብረተሰብ ሳይንስን ሀሁ ያልተገነዘበ ነው ብለን መጠነኛ ውረፋ ልንወርፈው እንችላለን፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የዘለሉት ወይም ሳይነግሩን ያለፉት ዋና ጉዳይ በአሜሪካና በአውሮፓ ያለው ድህነትና እዚህ እኛ ሀገር ያለው ድህነት በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ትልቅ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፡፡
ምናልባት እነሱ የፈለጉትን ወይም የመረጡትን አይነት ምግብ በፈለጉበት ሰአት እያገኙ ካልሆነ በስተቀር የተራበ አንጀታቸውን የሚፈቱበት ምግብ አጥተው በሺና በመቶ ሺዎች በጠኔ አይረግፉም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የነፍስ አድን ድረሱልኝ ጥሪም አያስፈልጋቸውም፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ ድሆች ከመንግስታቸው አይንና እጅ ለአፍታም እንኳ ርቀው አያውቁም፡፡ እንኳን በረሃብ ጠኔ ተመተው ይቅርና ስራ አጥ ሆነው ለተንከራተቱበትም መንግስታቸው እንደባለጠግነቱ መጠን ድርጐ ይሰፈርላቸዋል፡፡
እጅግ በርካታ ከሆነው የልዩነታችን ዝርዝር ውስጥ ለአብነት ያህል ያነሳናቸውን እነዚህን ሁለት ጉዳዮች በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ጥበብ መራቀቅ ሳያስፈልገን ከምናየው እውነት በመነሳት ብቻ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡
እዚህ እኛ ሀገር ግን ድህነት ማለት ምን ማለት እንደሆነና ደሀ የሆኑ ሰዎችም በየእለቱ የሚያስተናግዱትና የሚጋፈጡት ዘርፈ ብዙ ፈተና ምን አይነት እንደሆነና፤ የፈተናው ህመም ልኩ የት ድረስ እንደሆነ በርካቶች በየቤታችን ጥንቅቅ ብጥር አድርገን እናውቀዋለን፡፡
ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ እንደሚባለው፣ የመንግስት የስራ አጥነት ድጐማና ሌሎች ተመሳሳይ ድጋፎች ለጊዜው ይቆዩንና፣ ከእኛው መቀነት ተፈቶ በታክስና ግብር በሰበሰበው ጥሪት ገዝቶ ያመጣውን እህል ልክ ከሰማይ በተአምር መና የወረደለት ይመስል “ለእናንተ ለድሆች ብዬ ከዋጋው ላይ በግማሽ ደጉሜ አቅርቤላችኋለሁና ይፍቱህ በሉኝ” እያለ በፕሮፖጋንዳ ንትረካ ከማሰልቸት ውጭ ለሽያጭ ያመጣውን እህልና ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በወጉና ባግባቡ ማቅረብና ማከፋፈል እንኳ አልቻለበትም፡፡
ይህን ስሞታ የምናቀርበው እንዲያው የውለታቢስነትና የምስጋና ችጋር ገብቶብን ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ሆነ ዛሬም እያየን የታዘብነውን እውነት ለመተንፈስ ብቻ ነው፡፡ ድሆችን ወይም በመንግስት ልዩ አገላለጽ የባለ ዝቅተኛ ገቢ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር ለማቃለል በሚል መንግስት ከወሰዳቸው የተለያዩ የዋጋ ቁጥጥርና ተጓዳኝ እርምጃዎች፣ ድሆች ያገኘነውን ጥቅም ከመናገር ይልቅ የተጐዳነውን መዘርዘር ይቀለናል፡፡ ለምን ቢባል ደግሞ ካገኘነው ጥቅም ይልቅ የደረሰብን ጉዳት በብዙ እጥፍ የበለጠ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህንን መመስከርም መንግስትን ከመጥላት እንደመነጨ ተደርጐ ሊወሰድ አይገባውም፡ ምክንያቱም ጉዳዩን በተመለከተ ከበርካታ ዝርዝር ነገሮች ውስጥ በጣም ቀላል የሆኑትን ብቻ በማንሳት ማስረዳት ስለሚቻል ነው፡፡
ለምሳሌ የስኳር፣ የስንዴ፣ የዳቦ፣ የዘይት፣ ወዘተ .. የሽመታ ዋጋ መንግስት የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ አዋጁን ከማውጣቱ በፊትና ያወጣውን አዋጁን እንዴትና መቼ እንደሠረዘው ለማስረዳት ሳይሆን እንዲሁ ለመንገር እንኳ ግድ ሳይሠጠው ከሠረዘው በሁዋላ ስንት እንደሆነ የመንግስት ሠዎችና የአብዮቱ ልጆች የሆናችሁት ሳይሆን የእኔ ቢጤ ድሆች ብቻ አስታውሳችሁ መልስ ስጡ፡፡ መንግስት ለዚህች ሀገር ድሆች ከእኔ ወዲያ ቅንና አሳቢ ከየት ተገኝቶ በሚል ለወራት ጐሮ ወሸባዬ የሸለለበትንና እኔው ራሴ በመረጥኳቸው ድርጅቶችና የአስተዳደር ተቋማት፣ በግማሽ ዋጋ እንድትከፋፈሉ በበቂ አቅርቦትና በአስተማማኝ አቅም አቅርቤላችኋለሁ ያላቸውን የመሠረታዊ የምግብና የፍጆታ ሸቀጦች፣ አሁንም የመንግስት ሀላፊዎችና የአብዮቱ ልጆች የሆናችሁ ሳይሆን ድሆች የሆናችሁት ብቻ ስንቶቻችሁ እንደተባለው ማግኘትና መጠቀም ቻላችሁ?
እነዚህን አይነት ነገሮችን ሁሉ ሳስብ ጠቅላይ ሚኒስትራችንና እኛ በሁለት የተለያዩ ግን ስማቸው ኢትዮጵያ በሆነ ቁጥር 1 እና 2 ሀገሮች የምንኖርና ጨርሰን የማንተዋወቅ የሆንን መስሎ ይሠማኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በፓርላማም ሆነ በሀገር ውስጥና በውጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየመሯት ያለችውን ሀገር ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚናገሩት ንግግርና የሚሠጡት መግለጫ፣ እኛ ለምንኖርባት ኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ሳይሆን እሳቸዉ፣ የመንግስታቸውና የፓርቲያቸው ባለስልጣናትና የአብዮቱ ልጆች ብቻ ለሚያውቋት ልዩዋ ኢትዮጵያ ቁጥር ሁለት ብቻ ይመስለኛል፡፡
አለምን ጉድ ስላስባለውና ለበርካታ አመታት በሁለት አሀዝ ስለተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገትና የህዝቦች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል በተደጋጋሚ የሚነግሩን፣ እኛ እየኖርንባት ስላለችው ቁጥር አንድ ኢትዮጵያ ከሆነ ግን፣ ያሉንን ሁሉ ተሠባስበን ፈልገን ስላጣነው የሚያሳየን ባለሙያ እንዲመድቡልን በትህትና እንጠይቃለን፡፡

Read 3179 times