Print this page
Saturday, 20 April 2013 12:03

በ‘ኋላ ማርሽ መንደርደር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

መቼም ስለራሳችን እኛ የምንለውንና ሌሎች ስለ እኛ የሚሉት ምንና ምን እንደሆነ ታውቁታላችሁ። ነገርዬው የሴት እንትንዬውን ለጓደኛው ያሳየው ምስኪን የገጠመው ነገር ነው፡፡ “ታያታለህ፣ ቆንጆ አይደለችም!” ይለዋል፡፡ ያኛው ቁንጅናዋ ብዙም ስላልታየው ያመነታበታል፡፡ ይሄኔ ሰውዬው “ለእኔ ቆንጆ ነች” ይላል፡፡ እና ለእኔ ቆንጆ ነች ለእንትናዬ ምናምን ይሠራል፡፡ ግን በሌለ ከብት “የቢላ እጥረት ነው እንጂ ጮማው እንደ ልብ ነው…” አይነት “ለእኔ ቆንጆ ነች…” ብዙም እርፍና የለውም፡፡ እናላችሁ…የምንሰማውን ሁሉ እንመን ከተባለ ቱሪስቶች ስለ እኛ “እያደነቁ…” በሚናገሩት የተነሳ የጂ ስምንት አገሮች ሁሉ ቢቀኑብን ምን ይገርማል! አንዲት እኛን ‘ማድነቅ ይገባት የነበረች…’ ቱሪስት ያለችውን ‘እውነተኛ ታሪክ’ …ሴትዮዋ ካናዳዊት ነች፡፡ ታዲያላችሁ… እዚህ ትመጣና ለሁለት ወር ምናምን ትከርምና አገሯ ትመለሳለች፡፡ እዚህቹ አገራችን ውስጥ ምን ተምራ እንደ መጣች እዛ ያሉ ቀጫጭን ሀበሾች ይጠይቋታል፡፡

በ‘ፈረንጅ አማርኛ’ እጇን እያጨበጨበች ምን አለች አሉ መሰላችሁ…“መብራት መጣ! ውሀ ጠፋ!” እኛ እንግዳ ተቀባይነታችን ምናምን ትነግርልናለች ስንል ጭራሽ የመብራትና የውሀ ጉዳችንን ትዘከዝክብናለች! የመብራትና የውሀ ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…የፈረደበት ፌስ ቡክ ላይ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ምን ይላል መሰላችሁ… የፈረንጅ አባት ለልጁ ባቡር እያሳየ “ባቡር መጣ፣ ባቡር ሄደ…” ይላል። የሀበሻ አባት ደግሞ ለልጁ ቧንቧ እየሳየ “ውሀ መጣች፣ ውሀ ሄደች…” ይላል፡፡ አሪፍ አይደለች! እንዲሁ ‘እያፌዝን’ ተንፈስ እንበል እንጂ፡፡ እግረ መንገዳችንን…ኮሜዲያኖች እንግዲህ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ የግብፁ ኮሜዲያን ይኸው “ቀለድክ…” ብለው መከራውን እያሳዩት አይደል! እናማ…እያዩ መራመድን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ልጄ…ሰምና ወርቁን ትቶ…በቃ…ነገሩን ሁሉ ሮማንቲክ ኮሜዲ ማድረግ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ሮማንቲከ ኮሜዲ በቀላሉ ግምገማ ያልፋላ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆነ ቦታ ያነበብኳት ነገር ትዝ አለችኝማ፡፡ ቸርችልና ስታሊን በሆነ ኮንፍረንስ ላይ ይገናኛሉ፡፡

እና በትርፍ ጊዜያቸው ምን እንደሚሠሩ ይነጋገራሉ፡፡ ቸርችል “እኔ ሰዎች ስለ እኔ የሚናገሯቸውን ቀልዶች እሰበስባለሁ” ይላሉ፡፡ ስታሊን በበኩላቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“እኔ ደግሞ ስለ እኔ ቀልድ የሚናገሩ ሰዎችን እሰበስባለሁ፡፡ ስሙኝማ…የእነሱ አገር ‘ቦተሊከኛ’ ነው አሉ። እናላችሁ ለጸሀፊው እንዲህ ይላታል፡፡ “ሦስት የተቀረጹ እርሳሶችና በርከት ያለ ወረቀት አምጪልኝ።“ “ለምን?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ እሱም ምን አለ መሰላችሁ…“ብመረጥ ልሠራቸው ቃል የገባኋቸውንና ከተመረጥኩ በኋላ የምረሣቸውን ነገሮች ሁሉ እንድጽፍበት፡፡” ቢያንስ፣ ቢያንስ እሱ ወንዝ ባይኖርም “ድልድይ እሠራለሁ…” መሀል ከተማ ቢሆንም የእርሻ ኤክስቴንሽን አስፋፋለሁ…” ብሎ ይሆናል፡፡ እኛ አለን እንጂ…ሁልጊዜ ‘የአልበም ፎቶ’ የምንመርጥ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ! አሀ…አንዳንዴም እኮ ከ“የቡድንና ቡድን አባቶች…” ምናምን ነገር ወጣ ብሎ ‘በሁለት እግር የቆመ ሰው’ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ የምንሰማቸው የነበሩ አንዳንድ ነገሮች የምር አስቸጋሪ ናቸው፡፡ አሀ…ሁሉንም ነገር ‘በኋላ ማርሽ ማንደርደር’ አለብን እንዴ! ብዙ ነገሮች ላይ ካያችሁ…አለ አይደል…የሆናችሁትን የአሁኑን እናንተን ከምገልጽ ይልቅ አሽቀንጥራችሁ የጣላችሁትን የትናንት እናንተን ‘አቧሯ የጠጣ ሰነድ ’መምዘዝ የሚወዱ መአት ናቸው፡፡ (በተለይ ‘ቦተሊከኞች’!) እኔ የምለው ኮሜዲያኖች ቆጠብ ነው፡፡

የግብጹ ኮሜዲያን ቀለድህ ተብሎ መከራውን እያየ አይደለም። እነዚህ ፈረንጆቹ “Time Heals” የሚሏት ነገር አላቸው፡ የእውነትም እነሱን ስናይ ጊዜ የሁሉም ነገር መድሀኒት ነው፡፡ መቼ ነው ጃፓን አሜሪካንን “ሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ የጣልሻቸውን ቦምቦች የረሳን መሰለሽ!” ምናምን ስትላት የምንሰማው? መቼ ነው የአውሮፓ አገሮች ጀርመኖችን “በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ያደረሳችሁብንን እልቂትና ውድመት የረሳነው መሰላችሁ?” ሲሉ የምንሰማው! እንደውም ብዙዎቹ ያላቸው ወዳጅነት “ከተዋደዱስ እንዲህ ነው…” የሚያሰኝ አይነት ነው፡፡ ይሄን ነው እያጣን ነው ያለነው፡፡ ያለፈውን ‘አሽቀንጥረን መጣል’ ነው ያቃተን፡፡ በተለይ… ይሄ ነገር ‘ቦተሊካችን’ ውስጥ የበዛ ቢሆንም በማህበራዊ ህይወትም እንዲሁ ነው፡፡ ጥራ ግራ ኑሮዋን ያሻሻለች ከሆነች “አናውቅትምና ነው…እንትን መሥሪያ ቤት የጽዳት ሠራተኛ አልነበረችም እንዴ!” ትባላለች፡፡ በፊት ሰፈር የሚያስቸግር የ‘ሰይጣን ቁራጭ’ የሚሉት አይነት ይሆንና ሁሉንም እርግፍ አድርጎ ሰው አክባሪና ስርአት የተላበሰ ይሆናል፡፡

ይሄኔ “ድሮ የሰፈሩን ሰው መግቢያ መውጫ ሲያሳጣ የኖረ አይደለም እንዴ!” ይባላል፡፡ ብቻ ይሄ አቧሯ ጠጥቶ ‘የአገልግሎት ዘመኑ ያበቃ’ ሰነድ እያወጡ ማጣቀሻ ማድረግ ቀሺም ነገር ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ…አሁን አሁን ሚጢጢ ያገባኛል ባዩ እየበዛ ሄደ፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ‘ካርድ ለመውሰድ’ ትንሽ የሚያቅማማ ከተገኘ “ማን መሰለህ ኮንዶሚኒየም ፎቅ ላይ ያወጣህ!” የሚሉ ትኩስ ‘ያገባኛል ባዮች’ ነበሩ ሲባል ሰምተናል። (ተመቸ ተብሎ እንዲሁ የሰው በር ማንኳኳት አለ እንዴ!) ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሚዲያ ነገር…ያው ‘የሚዲያ ነገር’ ሆኖ ቀርቷል፡፡ እናላችሁ…ሚዲያ ላይ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ልብ ወለድ አይነት ነገር ሲበዛ አሪፍ አይደለም፡፡ በዛ ሰሞን ስብሰባ ላይ ሚዲያው ምን እየሠራ ነው ምናምን ነገር ሲባል አልነበር! (እንደተለመደው ነገርዬው ያው ‘ብለው ነበር’ ሆኖ ቀረ እንጂ!) በማፊያዎቹ ሳይሆን በኮሚኒስቶቹ ሶቪየት ህብረት ነው፡፡ እናላችሁ… በዛቹ ሶቪየት ህብረት የመዋዕለ ህጻናት አሉ፡፡ አስተማሪው ስለ ታላቋ ሩስያና “ዓለም ያደነቀው እንቅስቃሴዋን…” (ቂ…ቂ…ቂ…) እየገለጸላቸው ነበር፡፡ “በሶቪየት ህብረት ህጻናት ሁሉ ደስተኛ ናቸው፡፡ በሶቪየት ህብረት ሁሉም ህጻናት ቆንጆ፣ ቆንጆ አሻንጉሊቶች አሏቸው፣ በሶቪየት ህብረት ህጻናት ውብ በሆኑ አፓርትመንቶች ይኖራሉ…” እያለ ያስረዳ ነበር፡፡ ይሄኔ አንዱ ህጻን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡ አስተማሪውም “ቫንያ፣ ምን ሆንክ?” ሲለው ህጻኑ ምን ቢል ጥሩ ነው…“ሶቪየት ህብረት መሄድ እፈልጋለሁ!” የእኛን ልጆች “የምትሏት አገራችን መሄድ እንፈልጋለን…” የሚል ጊዜ እንዳይመጣባቸው አንድዬ ይርዳንማ! እናላችሁ… እዚህ አገር ብዙ ነገሮች የሚነሱት…አለ አይደል… ነገና ከነገ ወዲያን እያሰቡ ሳይሆን ትናንትና ከትናንት ወዲያን እየቆፈሩ ‘አቧራ በማራገፍ’ ነው፡፡

ከአምስቱ ማርሾች አራቱ የኋላ የሆኑባት አገር የእኛዋ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ “እሱ አናውቀውም እንዴ? ትናንት የደርግ ካድሬ አልነበረም እንዴ?” አይነት የኋላ ማርሽ ቀሺም ነው። እንዲህ የሚለው እሱ ራሱ እኮ…አለ አይደል…አሪፍ ‘ደርጊስት’ የነበረ ሆኖ… ጊዜ ከድህነት ወለልና ከሚጢጢ ስልጣን ወለል ከፍ ያደረገው ነው! አባቶቻችን “በድሮ በሬ ያረሰ የለም” የሚሏት አሪፍ አባባል ነበረቻቸው፡፡ አሁን ችግራችን እሱው ነው፣ በድሮ በሬ የምናርስ በዝተናል፡፡ ከማታው የድራፍት ማህበር አልፎ ማየት ሲያቅተን፡ አዲስ ሀሳብ ማመንጨት ሲያቅተን፣ በኋላ ማርሽ እየተንደረደርን ነን፡፡ አንድ ንጉሥ ለማወደስ ሌላ ንጉሥን ማጣጣል እንደሚወዱ ‘አንዳንድ ምሁራን’ (በ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ቢተካም… ድርጊትና አስተሳሰብን በተመለከተ ልዩነቱ ስለጠበበ…ሊያግባባን ይችላል) ሁላችንም በህይወት ካለው ‘ዛሬ’ ይልቅ ያለፈውን ‘ነገ’ን እያነሳን በ‘ኋላ ማርሽ መንደርደርን’ የነገራችን ሁሉ መቋጠሪያ ስናደርገው አሪፍ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3888 times