Saturday, 20 April 2013 11:50

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

                                       መልክአ ኢትዮጵያ - ፲፬

የቺካጎ ቆይታዬ የመጨረሻዋ ምሽት ላይ ነኝ። በዚህች ምሽት ከፍ ያለ ስምና ዝና ባለው ‹‹ካዲላክ ፓላስ›› (Cadillac Palace) ቴአትር ቤት ከታደሙት በሺሕ ከሚቆጠሩ ተመልካቾች አንዷ ኾኛለኁ። ተውኔቱ ሚልዮኖች በቴአትርና ሲኒማ ቤት ደጃፍ ተሰልፈው ላለፉት ኻያ ስምንት ዓመታት የተመለከቱትና የቪክቶር ሁጎ ድርሰት የኾነው ሌስ ሚዝራብልስ (Les Miserables) ሙዚቃዊ ብሮውዌይ ቴአትር ነው፡፡ የቤቱ አስተናባሪዎች በአክብሮት የሰጡኝን፣ ስለ ተውኔቱና ተዋንያኑ የተሟላ መረጃ የያዘውን የቴአትር ቤቱን ባለቀለም መጽሔት እያገላበጥኩ በተሰጠኝ የወንበር ቁጥር መሠረት ቦታዬን ይዣለኹ፡፡ በቴአትር ቤቱ ውበት የተማረክኹት ገና ከመግቢያው ጀምሮ ነበር፡፡ ከሰማንያ ሰባት ዓመታት በፊት በ12 ሚልዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የቺካጎው ‹‹ካዲላክ ቴአትር››÷ አዝናንተው በሚያስቀምጡ፣ ምቾት ባላቸው መቀመጫዎቹ 2400 ተመልካቾችን ክትት ያደርጋል፡፡ ቴአትር ቤቱ በየጊዜው በሚደረግለት እድሳትና የውስጥ ማሻሻያ ዲዛይን ለውጥ ወደር የሌለው የሥነ ሕንጻ ውበት ተላብሷል፡፡ በአዳራሹ ውበት በመመሠጤ የተውኔቱ በሰዓቱ አለመጀመር ብዙም ግድ አልሰጠኝም፡፡ የውስጠኛውን ክፍል ጣሪያ ለማየት ቀና ያደረግኁትን አንገቴን፣ ምን አንገቴን ብቻ ክሣደ ልቡናዬን፣ እዚያው ተክዬው ቀርቻለኹ፡፡

ዲዛይኑ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ወቅት የአእምሮ ፈጠራ ውጤት ብቻ መሠራቱ አጠራጣሪ ነው፤ ተጠበውበታል፤ ተጨንቀውበታል፡፡ ስፋቱ፣ የወንበሮቹ አደራደር፣ በመድረኩ ላይ የወረደው መጋረጃ ግርማ ሞገስ ተኩረው፣ ቆፍረው እንዲያዩት ያገብራል፡፡ የተገጣጠሙት ቁሳቁሶችና የተቀባው ቀለም ሕብሩ፣ ሥነ ርእዩ ውብ ነው ከማለት በቀር መግለጫ አጥቼለታለኹ፡፡ ሁሌም በሰው አገር ያየኹትን የሰው ነገር ከማውቀው ጋራ ለማነጻጸር በምናቤ ወደ አገሬ እመለሳለኹ፤ በሐሳቤም እዋቀሳለኹ፡፡ የካዲላክ ፓላስ ቴአትር ሥነ ኪን ባለአንበሳ ሐውልቱን ቴአትር ቤታችንን - ብሔራዊ ቴአትርን - አስታወሰኝ፡፡ በንጽጽሬ ግን ከመዝናናት ይልቅ ከፍተኛ ተግሣጽ እንደደረሰበት አዳጊ ዙሪያ ገባውን እያየኹ ሰውነቴን አሸማቅቄ፣ ድምፄን አጥፍቼ፣ ጥፍሬን እየቆረጠምኹ ‹‹ሌስ ሚዝራብልስ›› የተሰኘውን የብሮድዌይ ተውኔት መጀመር መጠባባቅ ያዝኹ፡፡ የተውኔቱ ታሪክ በፊልምም ተሠርቷል። በአሜሪካ ቦክስ ኦፊስ የሰንጠረዡን የላይ እርከን የተቆናጠጡ ፊልሞችን በትኩስነታቸው የሚያስኮመኩመው ‹‹ኤድናሞል ማቲ ሲኒማ›› ከወራት በፊት ሺሓት በአድናቆት የጎረፉለትን ‹‹ሌስ ሚዝራብልስ›› የተሰኘውን ፊልም አስመጥቶት ነበር፡፡

ፊልሙ በተመሳሳይ ርእስ ለአንባብያን በበቃው በታዋቂው ፈረንሳዊ ደራሲና ጸሐፊ ተውኔት ቪክቶር ሁጎ መጽሐፍ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ መጽሐፉ ‹‹ምንዱባ›› እና ‹‹መከረኞቹ›› በሚሉ ርእሶች ተተርጉሞ ለአገራችን አንባቢዎች ቀርቧል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የ‹‹ከመጻሕፍት ዓለም›› ፕሮግራም በተተረከበት ወቅት የመጽሐፉ ተወዳጅነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አስታውሳለኹ። ለዓመታዊው የኦስካር ሽልማት በበርካታ ዘርፎች ታጭቶ የነበረውና በሙዚቃዊ ድራማ ዘውግ የተሠራው ፊልሙ በኤድናል ማቲ ሲኒማ ቤት ለመቆየት የታደለው ግን ለአንድ ቀን ብቻ ነበር፡፡ በተመልካች ዘንድ አልተወደደም በሚል የመታያ ጊዜው በአጭሩ ተቀጭቷል፡፡ በኢትዮጵያ እምብዛም ተቀባይነት ያላገኘው ይህ ፊልም፣ በአሜሪካና በተቀረው ዓለም ሚልዮኖች በሲኒማ ቤት ተሰልፈውለታል፡፡ ተውኔቱን ደግሞ በ28 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 60 ሚልዮን ተመልካች ታድሞበታል፡፡ ለሁለት ሰዓት ከ50 ደቂቃ የታየው ተውኔት ከተጀመረበት እስከተጠናቀቀበት ደቂቃ ድረስ ለቅጽበት እንኳ ሌላ ነገር የማሰቢያ ጊዜ አልሰጠኝም።

የመድረክ ዝግጅቱ፣ ድምፁ፣ ሙዚቃው፣ አልባሳቱ፣ የተዋናያኑ የትወና ብቃት ከኹሉም በላይ ደግሞ የተጠቀሙበት ቴክኖሎጂ እጅግ ይማርካል፡፡ ታሪኩ የሚጠይቃቸው ነገሮች በሙሉ በመድረኩ ላይ በወጉ ተሟልተዋል፡፡ ቤቶቹ፣ መንገዱ፣ ዛፎቹ፣ ድልድዩ፣ ውኃው፣ ጦርነቱ ሳይቀር ልክ እንደ ፊልሙ በተውኔቱ ላይም ተሰናኝተው ታይተዋል፡፡ ቴአትሩ ተጠናቆ ተዋንያኑ ለተመልካቹ እጅ እስኪነሱ ድረስ ጠቅላላ መሰናዶው ለእውንነት የቀረበ፣ በእውኑ ዓለም የሚያቆይ ነበር፡፡ በአዳራሹ የሞላው ተመልካች ከመቀመጫው ተነሥቶ በከፍተኛ ጭብጨባ ለተዋንያኑ አድናቆቱን ገለጸ፡፡ የእኔ አድናቆት ግን ለአገሬ የጥበብ ሰዎች በዘርፉ የተሟላ መሰል ቴክኖሎጂንና ብቃትን አሟልቶ እንዲሰጣቸው ከመመኘት ጋራ ነበር፡፡ አዳራሹን ለቀን ወደ ሆቴላችን በሚያደርሰን አውቶብስ ውስጥ ስንገባ እንደተለመደው ስለውሎአችን ለሚጠይቀን ቡድን መሪው ጆን ሁላችንም በአንድ ላይ፣ ‹‹እጅግ በጣም ያምራል፤ እንዲህ ያለውን ጥበብ፣ ቴክኖሎጂ እንድናይ ስለጋበዛችኹን እናመሰግናለን›› በማለት ምላሽም ልባዊ ምስጋናም አቀረብን፡፡ ወደ ማደሪያችን እስክንደርስ ከቴአትሩና ተውኔቱ ሌላ ወሬ አልነበረንም፡፡ በርግጥም ቴአትሩ፣ ተዋንያኑና ተውኔቱ አፍሪካውያንን እጅግ በጣም አስደንቆንና አስደስቶን ነበር፡፡                                             ******************

አሜሪካ በመዝናኛ ኢንደስትሪው ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደምታደርግ ካዲላክ ፓላስ ቴአትርና ተውኔቱ ኹነኛ ማሳያ ነው፡፡ ቆየት ብዬ እንደታዘብኹት በየከተሞቿ እንደ ካዲላክና ከዚያም በላይ እጅግ የተጋነነ ውበት ያላቸው ቴአትር ቤቶች አላት፡፡ የኒውክሌርን ያህል ትቆጥራዋለች በሚባለው የፊልሟ ጥበብም ከራሷ አልፎ የዓለምን ቀልብ ስባበታለች። ራሷን ለገበያ የምታቀርበው፣ በሌሎች ዘንድ የምትናፈቅና የምትወደድ እንድትኾን የምታደርገው በፊልም ጥበብ ይመስለኛል፡፡ የአገሪቱ ወጣቶች በብዛት ወደ ሕክምና ሞያ እንዲገቡ ለማድረግ ከፍተኛ በጀት እየተመደበ እንኳ ምርጥ የቴሌቭዥን ተከታታይ ፊልሞች ይሠራሉ፡፡ ከወጣቶቿ የሚበዙት ከዋና ሥራቸው ወይም ሞያቸው ቀጥሎ ትኩረታቸው ለመዝናኛ ወሬ ነው፡፡ ርካሽና ፈጣን የኢንትርኔት ቴክኖሎጂውን አዘውትረው ጆሯቸው ላይ በሚሰኩት ማዳመጫና በስልካቸው ሲከታተሉና መረጃ ሲሰበስቡ ውለው ያድሩበታል፡፡ ከወገኖቻችን እንደ አንዳንዶቹ በምኑም በምኑም ሲያንቧትሩና ሲዳክሩ አይውሉም። የሚመለከታቸውን ነገር ጥንቅቅ አድርገው በጥልቀት ካወቁ ስለተቀረው ጉዳይ እነርሱን አይመለከታቸውም። ለዚህ ዝንባሌያቸው ሚዲያዎቻቸውም ሚና ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡

በአንድ አካባቢ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ቢኖሩም ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ የቶክ ሾውና የመዝናኛ ቻናሎች ናቸው፡፡ ጥቂት የሚባሉት የዜና ቻናሎችም ቢኾኑ ምንም ቢፈጠር ከአካባቢያዊ ጉዳዮች ውጭ ሌላ ነገር አያቀርቡም፡፡ ዜናዎቻቸው በሙሉ ስርጭቱ በሚሸፍነው ግዛት ክልል ስለተከናወኑ ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ስለ ዓለም ወሬ መስማት የፈለገ ዓለም አቀፍ ቻናሎችን መግጠም አሊያም በኢንተርኔቱ ማሠሥ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህ ግን ጊዜ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ቱሪስቶቹ ሌላ አገር ለመጎብኘት የሚነሡት በጡረታ ጊዜያቸው ላይ ነው። ወጣቶቹ የዕረፍት ጉብኝት ማድረግ የሚጀምሩት በዚያው በአሜሪካ ሌሎች ግዛቶች ነው፡፡ ከአሜሪካ የሚወጡ ወጣቶች ካሉ ጥቂቶች ናቸው፤ እነርሱም የቤተሰቦቻው ፈቃድና ፍላጎት መሠረት ያደርጋሉ፡፡ አሜሪካውያን በቤታቸው የሚያደርጉትን እንግዳ አቀባበልና ኑሯቸውን እንድንመለከት በየተመደብንበት ቤት ለአንድ ቀን ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ እኔ፣ ናይጄሪያዋ ቲሚ እና ኬኒያዊው ታሩስ አስማ አንዋር ወደተባለች ወጣት አሜሪካዊት መኖሪያ ቤት ተመራን፡፡

አስማ የዐረብ ዝርያ ካላቸው ቤተሰብ የተወለደች ብትኾንም ተወልዳ ያደገችው ግን አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡ በደቡብ ምሥራቅ ኤስያ አገሮች ጋዜጠኛና የንግግር ጸሐፊ ኾና ሠርታለች፡፡ አሁን የሕግ ባለሞያ በመኾኗ ፍሎሪዳ - ፔንሳኮላ ውስጥ በወንጀል መከላከል ጥብቅና ትሠራለች፡፡ ዐሥራ ሦስት የዓለም አገሮችን ተዘዋውራ ጎብኝታለች፤ አፍሪካ ውስጥም ግብጽን ጎብኝታለች፡፡ አስማ ዘንድ የተመደብነው ስለ አፍሪካ ታውቃለች ከሚል እንደኾነ ገምቻለኁ፡፡ እውነትም የአስማ ዓለም አቀፋዊ ዕውቀት ሰፋ ያለ ነው፡፡ ከየት እንደመጣኹ ጠይቃ ‹‹ከኢትዮጵያ›› ስላት ‹‹እርሷ ደሞ የት ነው የምትገኘው?›› ብላ እንደሌሎቹ አላሸማቀቀችኝም፡፡ አገሬን ታውቃታለች፡፡ መቼም ኢትዮጵያውያን ወደ ባሕር ማዶ ሲጓዙ አገራቸው በብዙ መልኩ በዓለም ሕዝብ ፊት ታዋቂ እንደኾነች ያስባሉ፡፡ ጥንታዊቷና የዘመናት ታሪክ ያላት አገራችን የት እንደኾነች መጠየቅ ምን ያህል ግርታ እንደሚፈጥር የሚታወቃቸው ግን ከአገር ሲወጡና መልክአ ምድራዊ መገኛዋን የመጠየቅ ‹ድፍረት› ሲገጥማቸው ነው፡፡ በአንድ አፓርትመንት ውስጥ በሚገኘው የአስማ መኖሪያ አብረናት አመሸን፡፡ ስለ ሥራዋ፣ ኑሮዋ አጫወተችን፡፡

ብዙውን ጊዜ እንደምታደርገው የነገረችንን ፓርቲ መሰል ዝግጅት ለምሽቱ አዘጋጅታለች፡፡ ቀለል ካለ ራት ጋራ ወይን እየተጎነጩ መጨዋወት እንደምትወድ ነገረችን፡፡ በዕለቱም ከተለያዩ ሰዎች ጋራ ብንወያይ እንደማይገደንና እንደማይደብረን በማሰብ በርካታ ጓደኞቿን መጋበዟን ነገረችን፡፡ ራት አዘጋጅታ ስታጠናቅቅ ተጋግዘን አቀራረብነው፡፡ ማምሻውን የተጠሩት ጓደኞቿ መጠጥ እየያዙ በሰዓቱ ተገኙ፡፡ አንድ ወጣት ፕሮፌሰርን ጨምሮ ሁሉም የአስማ ጓደኞች ምሁራን ናቸው፡፡ ከአስማ በቀር አንዳቸውም በስም እንኳ አገሬን አያውቋትም፡፡ ታሪክና ጂኦግራፊ ያበቃ መሰለኝ። ለእነርሱ ኢትዮጵያን ለማስረዳት ያልፈነቀልኁት ደንጊያ የለም፡፡ ሰሚ ባገኝ ብዬ በዝነኛው ቡና መሸጫቸው ውስጥ የሚገኘው የሲዳማ ቡና መገኛ እናት አገር ኢትዮጵያ መኾኗን ተናገርኁ፡፡ ቀደም እንዳልኋችኹ ከአገሬ ስነሣ ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር ዓለም ኹሉ እንደሚያውቃት የነበረኝን ሐሳብ ድራሹን አጠፉብኝ፡፡ ከራት በኋላ በነበረን የሞቀ ጨዋታ ስለ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ ለማስረዳትም ጊዜ ወስዶብን ነበር። ሁላችንም በየፊናችን ስለ አገራችን ለማስረዳት እንሻማለን፡፡ በሽሚያችን፣ የናይጄሪያዋ ቲም ወትሮውንም ስታወራ በጣም ትፈጥናለችና ያን ዕለት ስለ አገሯ እየተሽቀዳደመች ስታስረዳ÷ ‹‹እንዴት የሰው አገር ቋንቋ እንዲህ ፈጥነሽ ልታወሪ ቻልሽ?›› ብለው አሸማቀቋት፡፡

የየራሳችን ቋንቋ ያለን ሕዝቦች በእነርሱ ቋንቋ ማውራታችን በራሱ አስገርሟቸዋል፡፡ እኔና ኬንያዊው ጋዜጠኛ ስለየራሳችን አገር ስንገልጽ፣ ‹‹አትሌቶቻችን ከዓለም አንደኛ ናቸው›› በማለታችን የተካረረ ክርክር ተነሥቶ ነበር፡፡ ኬንያዊው ታሩስ በክርክሩ መሀል፣ ‹‹እናንተ ያላችኹ ኀይሌ ገብረ ሥላሴ ብቻ ነው›› ሲል የመምጫዬ አገር ታሪክና ጆግራፊያዊ አቀማመጥ ግራ አጋብቶት የነበረው አንዱ ወጣት አሜሪካዊ፣ ‹‹ገብረ ሥላሴ እናንተ አገር ነው እንዴ?›› ብሎ የመረጃ ክፍተቱን ስላሰፋልኝ ደስ አለኝ፡፡ ይህን ያህል ግዙፍ የመረጃ ክፍተት በማግኘቴም ስለቀሪዎቹ አትሌቶች ኮራ ብዬ አስረዳኹ፡፡ አሜሪካኖቹ የታሪክና ጂኦግራፊ ዕውቀታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ይህ የኾነው ደግሞ አይጠቅመንም ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ እነርሱን የሚጠቅመው የሚመለከታቸውን ጉዳይ አጥብቆ ይዞ ዕውቀታቸውን ማጎልበት፣ በዚያም ላይ መሥራትና በዕረፍት ጊዜያቸው መዝናናት ብቻ ነው፡፡ በእነርሱ አገር የጠቅላላ ዕውቀት የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጥያቄና መልስ ውድድር የለም፡፡ በጨዎታችን ያግባባን የጋራ ጉዳይ ቢኖር የአሜሪካ ምርጫና ሙዚቃ ነበር፡፡ ስለ ዘፋኞቻቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህን ስመለከት ቻርልስ ኦያንጎ የተባለ ዑጋንዳዊ ደራሲና ጋዜጠኛ፣ ‹‹ ቢራና የአውሮፓ እግር ኳስ ባይኖር ኖሮ የአፍሪካ መሪዎችን ምን ይውጣቸው ነበር?›› ያለውን አስታውሼ ‹‹ለመዝናኛው ኢንደስትሪ እንዲህ ትኩረት ባትሰጥ ኖሮ አሜሪካን ምን ይውጣት ነበር?›› ብዬ አሰብኁላት፡፡ አስተሳሰቤ ግን የሞኝነት መኾኑን ቆየት ብዬ ተረዳኁት፡፡ አሜሪካኖች በኹሉም ጉዳዮች ላይ ስለሚመለከታቸው ነገር ለማወቅ የሚቀድማቸው የለም፡፡

የታሪክና የጂኦግራፊው ጉዳይም ከሚመለከታቸው ጋራ ስላልተገናኹ ይኾናል፡፡ ይህን የተረዳኁት ደግሞ የኮንግረስ ሠራተኛውን ማትን ዋሽንግተን ዲሲ ባገኘኁት ጊዜ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመመለሻ ጥቂት ቀናት ሲቀሩኝ ሌላ ከተማ በሚኖሩ ጓደኞቼ አማካይነት ያገኘኁት ማት አሜሪካዊ መኾኑን እስክረሳ ድረስ ሐበሻ መስሎኛል፤ ሐበሻ ኾኖብኛል፡፡ ስለ አገሬ የማያውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ እንደርሱ አገሬን አላውቃትም ብል አልተሳሳትኁም። ስለ ብዙኀን መገናኛውና ጋዜጠኞቻችን፣ ስለ ፖሊቲካውና ፖሊተከኞቻችን አንዲትም ሳትቀረው ያውቃል፡፡ ስለ ፖሊቲከኞቻችን ማንነት፣ ጠባይዕና የዕውቀት ይዞታ ጨምሮ ጥቃቅን ነገራቸውን ያወራል። በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የፖሊቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ያውቃል፡፡ ታዋቂዎቹን የተቃውሞ ፖሊቲካ ፓርቲ አመራሮች በስምና በመልክ ለይቶ የሚገኙበትን ቦታና ኹኔታ ጭምር ጠንቅቆ ይናገራል፡፡ ፖሊቲካዊ ጉዳዮችን በሚመለከት በተለያዩ መድረኮች በሚካሄድ ውይይት ላይ የትኛው ፖሊቲከኛ ማስታወሻ እንደሚይዝና ማንኛው ፖለቲከኛ ተኮፍሶ እንደሚያወራ ሳይቀር አጥንቷል፡፡ ስለ ገዥው ፓርቲ ሹማምንትማ በሚገባ ያውቃል፡፡ በኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት ጥሬ ክትፎ አብሮኝ የበላው ማት ሻይ ውስጥ ስለምንጨምረው ቀረፋና ቁርንፉድ (ጣዕማችን) ኹሉ ያውቃል፡፡ ስለ ማት ያለኝን ምስክርነት በእኔ የመረጃ ክትትልና የዕውቀት ዳርቻ ለማረጋገጥ ልድፈርና፣ ማት ስለ እኔ አገር ያለውን ዕውቀት ስሰማ አሜሪካውያን ሥራዬ ብለው በሚከታተሉት ጉዳይ ላይ ያላቸውን የመረጃና ዕውቀት መልክና ልክ በወጉ አሳይቶኛል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4138 times