Saturday, 20 April 2013 12:13

“ዝናብ የለም፤ ደመና ነው፤ ሙቀት የለም…”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(ስለምርጫው የተሰጠ አስተያየት)

እንካ ስላንቲያ?

በምንቲያ?

በረገጣ! ምናለ በረገጣ?

በህዝባዊ አመራር መድበል ካላመጣ እያደር ይፋጃል ያንድ ፓርቲ ጣጣ!! ሰሞኑን እጄ የገባው መፅሃፍ ለየት ያለ ነው፡፡ ከአሁን ቀደም እንዲህ ያለ መፅሃፍ መውጣቱን አላውቅም፡፡ “እንካስላንቲያ” ይላል የመፅሃፉ ርዕስ፡፡ ደራሲው ግን ዝነኛ ነው፡፡ “ጉንጉን” እና “የወዲያነሽ” በተባሉት ወርቅ የልብወለድ ሥራዎቹ ይታወቃል፡፡ አንጋፋው ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል! እኔማ እንዴት አሰበው አስብሎኛል፡፡ ቁጭ ብሎ እንካ ስላንቲያ መፍጠር እኮ ቀልድ አይደለም፡፡ ትዕግስት ይጠይቃል፡፡ በዚያ ላይ የመረጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከበድ የሚሉ ናቸው፡፡ እስኪ አስቡት --- ዕውቀት፣ዲሞክራሲ፣ ህዝብ፣ ፍትህ፣ የህግ የበላይነት፣ ሙስና ወዘተ … ርዕሶች ላይ ያተኮሩ እንካስላንቲያዎቿን ነው ያዘጋጀው፡፡ መፅሃፉን እየኮመኮምኩ ሳለ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ ሃሳቡ ለማን መሰላችሁ የሚጠቅመው? ለኢቴቪ ነው! እናላችሁ --- ኢቴቪ ለምን “የእንካስላንቲያ ውድድር” አያካሂድም ብዬ አሰብኩ፡፡ ፕሮፓጋንዳውንም ቢሆን እኮ በእንካስላንቲያ አጣፍጦ ቢያቀርብልን ይሻለናል!! በዛውም ትንሽ ብንዝናና ምናለበት፡፡ በነገራችሁ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የምርጫ ክርክር ሲያካሂዱ በእንካስላንቲያ ቢያደርጉልን ሳይሻለን አይቀርም (ምርጫው የታለና እንዳትሉኝ ብቻ!) በተለይ እንዳሁኑ ኢህአዴግ ያመዘነበት ምርጫ ሲሆን እንካስላንቲያው ሞቅ ደመቅ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ (ፓርላማውንም ምርጫውንም ተቆጣጠረው አይደል?) ከሁሉም በላይ ደግሞ ከ97 ምርጫ ወዲህ ጥቅልል ብሎ የተኛውን ፖለቲካችንን ከእንቅልፉ ለመቀስቀስም ማለፊያ ዘዴ ይመስለኛል - ፖለቲካን በእንካስላንቲያ ማስኬድ! ወጋችንም እንደ ዘንድሮ ምርጫና ፖለቲካ ጭር እንዳይል … ለምን በጥቂት እንካስላንቲያዎች ሞቅ ደመቅ አናደርገውም - እድሜ ለደራሲ ኃይለመለኮት!

እንካስላንቲያ?

በምንቲያ?

በወለምዘለም!

ምን አለህ በወለምዘለም?

አንጠርጥረህ ምረጥ በምርጫ ቀልድ የለም፡፡ አያችሁልኝ … ምርጥ የምርጫ ማስታወቂያ! ትንሽ ዘገየ እንጂ የአዲስ አበባ መስተዳድር ይጠቀምበት ነበር፡፡ በቅርቡ ሲያቀርበው የነበረው ግን ግግም ያለ ነው - እንድ ድራማቸው! ባይገርማችሁ የመስተዳደሩ ድራማ እኮ ልማታዊ ሳይሆን ፕሮፓጋንዳዊ ነው - በቃ ደረቅ- ችኮ - “እንጨት እንጨት” የሚል፡፡ የእንካስላንቲያው ግን ሌላው ቢቀር ያዝናናል፡፡ ሌላ ደግሞ ይሄውላችሁ - እንካስላንቲያ? በምንቲያ? በአምሮት! ምን አለህ በአምሮት? ሥልጣን ለሰጠህ ህዝብ ይኑርህ አክብሮት፡፡ አሪፍ መልዕክትና ቁም ነገር ይዛለች አይደል? ማንን እንደሚመለከት መግለፅ ግን አስፈላጊ አይመስለኝም (ግልፅ ነዋ!) እስቲ ደግሞ በመልካም አስተዳደር ዙርያ ደራሲው የፈጠረውን እንካ ስላንቲያ እንይ፡- እንካስላንቲያ? በምንቲያ? በመምጠቅ! ምን አለህ በመምጠቅ? መልካም አስተዳደር እንዳለ ለማወቅ ባለሥልጣን ሳይሆን ሕዝብን ነው መጠየቅ፡፡

ልክ ብሏል! በተለይ ኢቴቪ እቺን ቢሰማ ይጠቅመዋል፡፡ በቃ በልኩ የተሰፋች ናት! ራሱ ኢህአዴግ በ9ኛው ጉባኤ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ የተረዳው፣ከህዝቡ ምሬት እንደሆነ በግልፅ ተናግሯል እኮ፡፡ ኢቴቪ ግን ሁሌም ባለስልጣናትን ነው የሚጠይቀው፡፡ ምናልባት ወደፊት ግን ከኢህአዴግ ይማራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን (አበሻ ተስፋ አይቆርጥማ!) እኔ የምላችሁ … የሰሞኑ ምርጫ እንዴት ነው? መረጣችሁ ወይስ ተመረጣችሁ? አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ … “ምርጫ ድሮ ቀረ!” (የፈረደበትን የ97 ምርጫ ማለቱ እኮ ነው) ወዳጄ እርሙን አላወጣ ብሎኝ ነው እንጂ … ነግሬው ነበር እኮ! “እንደዛ ዓይነቱን ምርጫ ኢህአዴግ ዓይኑ እያየ አይደግመውም” ብዬ! (የለየለት ሞኝ አደረገው እንዴ?) ባለፈው ሳምንት የመኢአድ ሊቀመንበር ያሉት ግን ትንሽ ከበድ ይላል፡፡

አሁንም መኢአድ አለ እንዴ? (ይሁና!) እናላችሁ --- ስለምርጫው ተጠይቀው ኢንጂነር ኃይሉ እንዲህ አሉ “ይሄ ምርጫ ሳይሆን ንጥቂያ ነው!” እንዴት ቢማረሩ ነው ባካችሁ! ከምርጫው ራሱን ያገለለው የ33ቱ ፓርቲዎች ቡድን (ስም አልወጣለትም አይደል?) ምን ነበር ያለው? “ኢህአዴግን ለማጀብ ወደምርጫው አንገባም!” ብለው ነበር (ምን ያድርጉ? ምህዳር የለማ!) ባለፈው ሳምንት ከምርጫው በኋላ የምርጫ ቦርድ ሃላፊው ምን አሉ መሰላችሁ? (እኚህ እንኳን ፓርቲዎችን ሁሉ እንደልጆቼ ነው የማየው ያሉት) “እንዳሁኑ ምርጫ ፓርቲዎች ሳይወዛገቡ በሰላም የተጠናቀቀበት ጊዜ የለም” ይሄን የሰማ የቀድሞ የኢህአዴግ ደጋፊ ወዳጄ (አሁን ሃይማኖተኛ ሆኗል) “እውነታቸውን እኮ ነው … በምርጫው አልተሳተፉማ!” ብሎ እርፍ አለ! (ሰው ሁሉ በቀጥታ መናገር ተወ ማለት ነው?) እኔ ደግሞ ያስገረመኝ የአንዳንድ መራጮችና ተመራጮች አስተያየት ነው፡፡

ባለፈው እሁድ አንዱ መራጭ ድምጽ ሰጥቶ ሲወጣ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ያገኘውና “ምርጫው እንዴት ነበር?” ይለዋል፡፡ (ኢንተርቪው በጥቆማ ነው የሚባለው ውሸት ነው አይደል?) መራጩም - “የመብራት ችግር አለ፣ የውሃ ችግር አለ፣ የመሰረተ ልማት ችግር አለ፣ በአጠቃላይ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚፈታልኝን መርጫለሁ” (ማንን ይሆን?) ኢቴቪ ያነጋገራቸውን አስተያየት ሰጪዎች እንደኔ በቅጡ ሰምታችኋቸው እንደሆነ አላውቅም፡፡ “የመረጥኩት ኢህአዴግን ነው” ማለት እኮ ነው የሚቀራቸው፡፡ (ነግረውን ቢለይላቸው ይሻል ነበር!) ሌላ መራጭ ደግሞ እንዲህ አለ - በፈረደበት አንድ ለእናቱ ኢቴቪያችን፡፡ “ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሁም ልማታዊ ነው ማለት ይቻላል” አይገርምም… ልማታዊ ምርጫ! ኢህአዴግ ራሱ እኮ ሌላ ሌላውን እንጂ ምርጫውን ልማታዊ ሲል ሰምቼው አላውቅም (አሁን ይጀምር ይሆናል!) አንዱ ጐልማሳ መራጭ ደግሞ አስተያየታቸውን የጀመሩት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስን በማወደስ ነው፡፡ “የባለራዕዩን መሪ አርአያ ተከትለን…” አሉና እሳቸውም “ይሆነኛል…ይጠቅመኛል” ያሉትን መምረጣቸውን ነገሩን፡፡

አንደኛዋ ወይዘሮ ደግሞ ምን ብትል ጥሩ ነው? “ጫንቃችንን ያቃለለልንን ፓርቲ መርጫለሁ” (ኢህአዴግ ብላ ብትገላገልስ?) ከሁሉም ግን የኢራፓ ሊቀመንበር የሰጡትን አስተያየት የሚያህል የለም (ዊርድ እኮ ነው!) “ዝናብ የለም፤ ደመና ነው፤ ሙቀት የለም…ሁሉ ነገር ኖርማል ነው” (ስለምርጫ እንጂ ስለሜትሮሎጂ ማን ጠየቃቸው?) የሆኖ ሆኖ እስካሁን “የምርጫው ሂደት ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ልማታዊ ነው” ተብሏል፡፡ ግን እኮ ድሮም ቢሆን በጥባጩ ህዝብ ሳይሆን ፓርቲዎቹ ናቸው - ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ! የብጥብጣቸውን ሰበብም አሳምረን እናውቀዋለን - የፈረደበት ሥልጣን ነው!! አሁን ግን የምርጫው ውጤት ቀድሞ የሚታወቅ ስለሆነ (መጨረሻው እንደሚታወቅ ፊልም) ፓርቲዎቹ አልተወዛገቡም (የተሳተፉት ማለቴ ነው!) ለነገሩ ብዙዎቹ ገና የኢህአዴግን ሚሊዮን እጩዎች ሲሰሙ እኮ ነው እጅ የሰጡት (የቤት ሥራቸውን አልሰሩማ!) እነዚህ የጦቢያ ተቃዋሚዎች ግን ሁነኛ መካሪ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም (ቢቻል በዲሞክራሲ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት!) እንዴ…”በምርጫ አንሳተፍም!”፣ “ፓርላማ አንገባም!”፣ “አንደራደርም” ምናምን እየተባለ እስከመቼ ይዘለቃል? እኔ የምጠረጥረው ምን መሰላችሁ? ወይ የፖለቲካ ጨዋታውን አላወቁበትም ወይ ደግሞ ኢህአዴግ አንድ ነገር አስነክቷቸዋል (የምህዳሩ መጥበብ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው!) እንዴ ቢጠብም እኮ ባለችው ዕድል መንፈራገጥ ነው፡፡ ሽሽትማ ለማን በጀ? እንግዲህ ፖለቲካዊ ወጋችንን በእንካስላንቲያ እንደጀመርነው በእንካስላንቲያ እንቋጨው፡፡ (ለደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ምስጋናችን ይድረሰው እያልን!) እንካስላንቲያ? በምንቲያ? በቁርቁስ! ምናለህ በቁርቁስ? አንጠርጥረህ ምረጥ ጥሩን ከልክስክስ ለምክር ቤት ምርጫ ዋሾን አታግበስብስ፡፡ (ወንዳታ ብለናል!!)

Read 4640 times