Saturday, 20 April 2013 12:16

የሕይወት ስንቅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

        ከ1/3ኛ በላይ የህፃናት ሞትን በክትባት መከላከል ይቻላል

የፈንጣጣ በሽታ በኢትዮጵያ መኖሩ በታወቀ ጊዜ ከፓሪስ የህክምና ፋኩሊቲ የተውጣጡ ቡድኖች ህዝቡን ለመከተብ በሚል በ1890 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ያኔ ህብረተሰቡ ስለ ፈንጣጣ በሽታም ሆነ ስለሚሰጠው ክትባት ምንም ግንዛቤ ስላልነበረው፣ ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና ህዝቡን ለመቀስቀስ አጤ ሚኒልክ የፈንጣጣውን ክትባት በፈረንሳዮች እጅ ተከተቡ። ይህ ሁኔታ ግን የክትባትን ጠቀሜታ ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዳና ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ እንዲሆን ባለማድረጉ ንጉሱ አዋጅ አስነገሩ፡፡ “አሁን በከተማው ፈንጣጣ ገብታ ሰውን ሁሉ እንደምትፈጅ ታያላችሁ፡፡

ይህቺንም ክፉ በሽታ ከአገር ለማጥፋት በከተማ ያለው ሰው አዋቂውም ልጁም ከከብት ሃኪም ዘንድ ወይም ከሆስፒታል እየሄደ ይከተብ፡፡ ለመከተብ ዋጋ አያስከፍልም። ጊዜም አያስፈታ፡፡ ከአምስት ደቂቃም ይበልጥ አያቆይ፡፡ አሁንም ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ የምታስቡ ሰዎች ሁሉ ተከተቡ፡፡ ሳትከተቡ ቀርታችሁ ሰው ቢሞትባችሁ በስንፍናችሁ መሆኑን እወቁት” ይህ የአጤ ሚኒሊክ አዋጅ መጋቢት 2ቀን 1904 ዓ.ም በገበያ መሃል እንዲነበብ ተደረገ፡፡ በማግስቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ውርዝ እየተባለ በሚጠራውና በወቅቱ ክትባቱን ይሰጥ በነበረው ሐኪም መኖሪያ ቤትና የሥራ ቦታ ይሰባሰቡ ጀመር፡፡ ስለሁኔታው ውርዝ የተባለው ይኸው ፈረንሳዊ ሐኪም ሲናገር፤ “አዋጁ በተነበበ ማግስት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ ሰዎች ወደ ቤቴ ይመጡ ጀመር፡፡ የአምስትና የስድስት ቀናት ጉዞ አድርገው አዲስ አበባ የሚመጡት ሰዎች ተራ ደርሷቸው እስኪከተቡ ድረስ በቤቴ አካባቢ በመስፈራቸው በራፌ ላይ ዘብ አቆምኩ፡፡ ከየካቲት ወር እስከ ነሐሴ ድረስም 20ሺ 700 ሰዎችን አዲስ አበባ ውስጥ ከተብን” ማለቱን ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ሚኒልክ” በተሰኘው መፅሃፉ ላይ አስፍሮታል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የክትባት ታሪክም በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግሥት የተሰጠው ክትባት የመጀመሪያ ነው፡፡

ክትባቶች በተለያዩ አይነቶች ተዘጋጅተው ወደሰውነታችን እንዲገቡ ከተደረጉ በኋላ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቋም (“Immunity”) የሚያሳድጉ የህክምና ጥበቦች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1769 ዓ.ም ኤድዋርድ ጅነር በተባለ ሰው አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅም ላይ የዋለው ክትባት የተሰራው ከከብት ቫይረስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ከከብት ቫይረስ ተሰርቶ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ክትባት፤ በየጊዜው የተለያዩ ለውጦችንና መሻሻሎችን እያሳየ በመሄድ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ ክትባቶች አይነታቸውም ሆነ መጠናቸው የተለያየ ሲሆን የአሰጣጥ ሂደታቸውም ክትባቱን የሚወስደውን ሰው እድሜ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የአለም ሀገራት ህዝባቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ለክትባት አመራረትም ሆነ አሰጣጥ ፖሊሲዎችን ያረቃሉ፡፡ በተለያዩ ህጐች፣ መመሪያዎችና ደንቦች መሰረትም ሊመሩ ይችላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ግን እነዚህ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች የትኛውንም ህዝብ የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለኩፍኝ፣ ለፖሊዮ፣ ለመንጋጋ ቆልፍና ዘጊ አናዳ የመሳሰሉትን በሽታዎች ለመከላከል የሚሰጡት ክትባቶች፣ የአለም ህዝቦችን አስከፊ ወደሆነ የወረርሽኝ ጥቃት እንዳይገቡ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያ የክትባት አገልግሎትን ለህዝቦቻቸው ለማዳረስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙ የአለም አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በአገሪቱ ከሚከሰቱት የህፃናት ህመምና ሞት መካከል አንድ ሶስተኛው የሚሆኑት በክትባት መከላከል በሚቻል በሽታዎች አማካይነት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ በክትባት ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑና አገልግሎቱም በአስተማማኝና በበቂ መጠን ባለመዳረሱ ምክንያት ዛሬም ድረስ በርካታ ህፃናት በክትባት ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች እየተጠቁ ለህመም፣ ለአካል ጉዳትና ለሞት ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ “ህፃናትን በማስከተብ ከህመም፣ ከአካል ጉዳትና ከሞት እንጠብቃቸው” በሚል መሪ ቃል ከሚያዝያ 14-20 ቀን 2005 ዓ.ም በአገራችን ለሦስተኛ ጊዜ የሚከበረውን የአፍሪካ የክትባት ሳምንት አስመልክቶ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አገሪቱ ክትባትን ለህብረተሰቡ ሁሉ በበቂ መጠን ለማዳረስ ጥረት እያደረገች ነው፡፡

የክትባት ሽፋኑና አገልግሎቱ በአስተማማኝነት ያደገና የጉዳት መጠኑ የቀነሰ ቢሆንም በየደረጃው ያለው የህብረተሰቡ ግንዛቤ ባለማደጉ ምክንያት በክትባት ሊወገዱ የሚችሉ በሽታዎች በርካታ ህፃናትን ለአካል ጉዳትና ለሞት እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡ ሚኒስትር መ/ቤቱ እንደ ኩፍኝ የመሳሰሉ ወረርሽኞችን ለማስቆም፣ በሁሉም የጤና ድርጅቶች ያለምንም ክፍያ ክትባትን ለህፃናት በማዳረስ ላይ መሆኑንም በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል። በአገሪቱ የሚገኙት ከ250 በላይ ሆስፒታሎች፣ 3ሺህ ጤና ጣቢያዎችና 25ሺ ጤና ኬላዎች ክትባትን ለህብረተሰቡ በማዳረሱ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ አህመድ ኢማም ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ የመደበኛ ክትባት ፕሮግራም ሽፋን እ.ኤ.አ በ2003 ከነበረበት 52 በመቶ እድገት አሳይቶ 86 በመቶ መድረሱንም ጋዜጣዊ መግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡ የበሽታዎችን ስርጭት በቀላሉ ለመቆጣጠርና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው የሚባለውን የክትባት አገልግሎት ስርጭትና ጥራት በተመለከተ ለግንዛቤ የሚረዱ አንዳንድ መረጃዎችን በሥራ አጋጣሚ በተዘዋወርንባቸው አካባቢዎች ለማሰባሰብ ሞክረን ነበር፡፡ በሐረርጌ ዞን አፈር ደባ ሶፊ ወረዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያገኘኋት የአምስት ልጆች እናት፣ የ39 አመቷ ዘሀራ የሱፍ የወለደቻቸው አምስቱም ልጆቿ ክትባት አለመከተባቸውንና ልጆቿን ለማስከተብ የሚያስችል ገንዘብ እንደሌላት ነግራኛለች።

ክትባቱ በሁሉም የጤና ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎች ያለክፍያ እንደሚሰጥ የሰማሁትን ብነግራትም በጄ አላለችኝም፡፡ “የእከሌ ልጅ አልተከተበችም፣ እከሌም ልጇን አላስከተበችም፡፡ ግን ምንም አልሆኑባትም፡፡ ለምን አስከትባለሁ” መልሳ ጠየቀችኝ፡፡ ክትባት ለወደፊቱ የልጆቿ ጤናማ ህይወት መሰረት መሆኑንና በወረርሽኝ መልክ ከሚከሰቱ በሽታዎች በቀላሉ መዳን እንደሚቻል ብነግራትም ሃሳቤ ሊዋጥላት አልቻለም፡፡ ይሄ የሚያሳየው በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በበቂ ሁኔታ አለመንቀሳቀሳቸውን ይመስለኛል፡፡ በምዕተ አመቱ የልማት ግብ ተደርገው ከተያዙት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት መቀነስ የሚለውን ጉዳይ ለማሳካት ሁሉም በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክትባቶች በበቂ ሁኔታ መሰራጨታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ህብረተሰቡ ስለ ክትባት ጠቀሜታ በአግባቡ ተረድቶ በጊዜውና በወቅቱ ልጆቹን እንዲያስከትብ ለማድረግ በመጀመርያ ግንዛቤውን ማሳደግ ዋንኛ ተግባር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለህብረተሰቡ እንዲደረሱ በየአካባቢው የሚሰራጩት ክትባቶች ጥራትና ወደ ተጠቃሚው የሚደርሱበት ሁኔታ ምን ያህል አስተማማኝ ነው የሚለውን ማየትም ግድ ይላል፡፡

በጥንቃቄ ጉድለት የተበላሹ ክትባቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናልና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ክትባቶች ከተመረቱበት ቦታ ጀምሮ ወደ ተጠቃሚው እስከሚደርሱበት ጊዜ ድረስ ያለው ሂደት ቀዝቃዛው ሰንሰለት (Cold chain) በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ ክትባቱ ተመርቶ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግም፣ ይህ ሰንሰለት ሂደቱን ጠብቆ በአግባቡ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ቀዝቃዛውን ሰንሰለት መሰረት ባደረገ መልኩ ጥቅም ላይ ያልዋለ ክትባት መድሃኒትነቱ አስተማማኝ አይሆንም፡፡ የማቀዝቀዣ እጦት በድሃ አገራት ክትባትን በበቂ መጠን ለማዳረስ ትልቅ እንቅፋት ሲሆን የሚስተዋለውም ለዚህ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድና ያለፍሪጅ በመቆየትና ከቦታ ቦታ በመዘዋወር አገልግሎት ላይ ለመዋል የሚችሉ ክትባቶችን ለማምረት ሳይንቲስቶች ከመትጋት አልቦዘኑም፡፡ ሔፒታይተስ ቢ የተባለውን ገዳይ በሽታ ለመከላከል ያስችላል የተባለውን ክትባትም በድንች ዘሮች ውስጥ በማስገባትና በማምረት ለምግብነት ማዋል ጀምረዋል፡፡ እነዚህን ድንቾች በተመገቡ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት መሰረትም 60 በመቶ የሚሆኑት የድንቹ ተመጋቢዎች ሔፒታይተስ ቢ የተባለውን በሽታ ለመከላከል የሚያስችላቸው (Anti Bodies) በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶቹ እነዚህን ክትባት የያዙ ድንቾችን በስፋት ለማምረትና ለማሰራጨት እንቅፋት ይሆናሉ የሚሏቸው ችግሮችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የአወሳሰድ መጠኑ (Dosage) አለመመጠን አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ ድንቾቹ ከሌሎች ለምግብነት ከሚውሉ ድንቾች ጋር ተቀላቅለው ለተራ ምግብነት ሊውሉ ይችላሉ የሚለው ስጋት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ በሚበሉ ምግቦች መልክ እየተዘጋጁ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት የክትባት አይነቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ አገራት ውስጥ ክትባትን ለማዳረስ እንቅፋት የሆነውን የፍሪጅ አገልግሎት ለማስቀረት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ አሁን በአገሪቱ እየተሰጡ ያሉትን ዘጠኝ አይነት ክትባቶች በቁጥር ከፍ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ አሁን በአገሪቱ በስፋት እየተሰጡ ከሚገኙ የክትባት አይነቶች መካከል ፖሊዮ፣ ኩፍኝ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ ዘጊ አናዳ፣ ማኔንጃይትስና ሔፒታይተስ ቢ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

Read 3964 times