Saturday, 20 April 2013 13:20

ማይክል ክሩገር ምን ይላሉ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ የ58 አመቱ ማይክል ክሩገር ጀርመናዊ ናቸው፡፡ እግር ኳስን በ1970ዎቹ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ተወዳዳሪ በሆነው ሃኖቨር 96 በአጥቂ መስመር ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡ የአሰልጣኝነት ሙያቸውን ከጀመሩ ደግሞ ከ23 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ በሚወዳደረው ሻልካ 04 ረዳት አሰልጣኝነት በ1989 እኤአ ላይ ስራቸውን የጀመሩት ማይክል ክሩገር በሌሎች አምስት የጀርመን ክለቦችም ሰርተዋል፡፡ ሁለት የግብፅ ክለቦችንም አሰልጥነዋል፡፡ አረብ ኮንትራክተርስን ሲያሰለጥኑ በ1996 የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ዋንጫን ሲያሸንፉ ከሌላው የግብፅ ክለብ ኤልመስሪ ጋር ደግሞ በ1998 ደግሞ የግብፅ ጥሎ ማለፍ ዋንጫንም አግኝተዋል፡፡ በ2008 እና በ2010 እኤአ ላይ በሁለት የተለያዩ የውድድር ዘመናት አልሜሪክን በማሰልጠን የሱዳን ፕሪሚዬር ሊግ እና ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን አንስተዋል፡፡

ማይክል ክሩገር ከእግር ኳስ አሰልጣኝነት ባሻገር መምህርነትም ሙያቸው ነበር፡፡ በታዋቂው ሃኖቨር ዩኒቨርስቲ በጆግራፊ እና ስፖርት ተመርቀዋል፡፡ የህግ ሙያ ለማጥናት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ሙያቸው በጣም ስራ ስላበዛባቸው የጀመሩትን ሳይጨርሱ ቀሩ እንጅ ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዛማሌክ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ስለነበረው ዝግጅት፤ በአሰልጣኝነት ልምዳቸው፤ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ደረጃ፤ በኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጨዋቾች ብቃት እና የፕሮፌሽናልነት ተስፋ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ አሰልጣኝ ማይክል ክሩገር ከስፖርት አድማስ ጋር የሚከተለውን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዛማሌክ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ምን ውጤት ይጠብቃል? ዝግጅታችንን በሚያረካ መንገድ ሰርተናል ለማለት ባንደፍርም በካይሮ ከዛማሌክ ጋር በሚኖረን ጨዋታ በተቻለን መንገድ ውጤት ለማጥበብ የምንችልበትን አቋም ግን ከቡድኔ እጠብቃለሁ፡፡ በእርግጥ በተጨዋቾች ላይ የተመለከትኩት የልምምድ መንፈስ መዳከም ያሳስበኛል፡፡

የግብፅ ክለቦች ለዚህ አይነቱ መዘናጋት ቅጣት እንዳላቸው ማሰቤም አስጨንቆኛል፡፡ አንድ ቡድን ለማንኛውም ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት በከፍተኛ ዲሲፕሊንና ትኩረት መስራት አለበት፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋቾች ለጨዋታው በሚደረግ ዝግጅት አስፈላጊውን ዲስፒሊንና ትጋት እኔ በምፈልገው ደረጃ አላሳዩም፡፡ እንግዲህ የክለቡን ተጨዋቾች ልመክራቸው ሞክሪያለሁ፡፡ በካይሮ ከዛማሌክ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ምንም አይነት መዘናጋት እንዳይኖር አስጠንቅቂያቸዋለሁ፡፡ ተጨዋቾች ወደ ልምምድ ሜዳ ሲመጡ በብሩህ መንፈስ፤ በንቃት እና በከፍተኛ የትጋት መንፈስ ለመስራት መሆን አለበት፡፡ ተጨዋቾች በዚህ ረገድ ድክመት ይታይባቸዋል፡፡ አንዳንዴ ልምምዶችን የማሰራው በልመና ነው፡፡ በልምምምድ ሜዳ ተገቢውን እንቅስቃሴ አለማድረግ እና መሳነፍ ተገቢ አለመሆኑን ያለመሰልቸት እያስተማርኩ ቆይቻለሁ፡፡ እዚህ አገር ማንንም ተጨዋች ዲስፕሊን አጉድለሃል፤ ልምምድ በደንብ አትሰራም፤ ብቃትህ ወርዷል ብሎ መቅጣት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ተጨዋች ስትቀጣ ምትክ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ግን አማራጮች ስለሌሉ ከቅጣት ይልቅ ተጨዋቾችን ብቃታቸውን እንዲያሻሽሉ ምክር በመስጠት ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጥረት ማድረጉን አተኩሬበታለሁ፡፡ የግብፅ ክለቦችን በማሰልጠን ከነበረዎት ልምድ በመነሳት ዛማሌክ እንዴት ይገመግሙታል? በግብፅ ለሁለት ክለቦች ሰርቻለሁ፡፡ አረብ ኮንትራክተርስ እና ኤል ማስሪ ይባላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከ15 አመት በፊት ነው፡፡ ሁለቱም ክለቦች በወቅቱ ጥሩ ደረጃ ነበራቸው፡፡

አረብ ኮንትራክትስን ሳሰለጥን አሁን ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚባለውንና ያኔ ካፕ ዊነርስ ካፕ የተባለውን ውድድር ማሸነፍ ችለናል፡፡ ኤልማስሪን ሳሰለጥን ደግሞ በታሪኩ በየትኛውም ውድድር ዋንጫ አሸንፎ የማያውቀው ክለብ የግብፅ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ለማድረግ ችዬ ነበር፡፡ ያን ጊዜ የነበረው ዛማሌክ ከታላቁ የግብፅ ክለብ አልሃሊ አንፃር ሲታይ ያን ያህል ጥንካሬ አልነበረውም፡፡ ክለብ ኮንትራክትስን እያሰለጥንኩ በግብፅ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከዛማሌክ ጋር ስንገናኝ የተሸነፍነው በመለያ ምቶች ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ባለፉት 15 አመታት በኋላ ዛማሌክ እጅግ ተለውጧል፡፡ በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ከአልሃሊ እኩል የሚፎካከርበትና በአህጉራዊ ውድድሮችም ከፍተኛ ስኬት የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ዛማሌክ ዛሬ በአፍሪካ ደረጃ ከአልሃሊ ቀጥሎ በጥንካሬው 2ኛ ደረጃ የሚሰጠው በመሆኑ ከባድ ፈተና ይገጥመናል፡፡ የአሁኑ ዛማሌክ በወጣት እና ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ምርጥ ተጨዋቾች ስብስብ የተገነባ ነው፡፡ ለግብፅ ብሄራዊ ቡድንም ወሳኝ ተጨዋቾች አስመርጧል፡፡ ከዛማሌክ የምታደርጉት ጨዋታ በዝግ ስታድዬም ሊሆን ይችላል፡፡ ለጊዮርጊስ ይጠቅመዋል? ጨዋታው በዝግ ስታድዬም ሊደረግ እንደሚችል መረጃው አለኝ ፡፡ ለእኔ በዝግ ስታድዬም የሚደረግ ጨዋታ አይመችኝም፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በሚያህል ትልቅ ውድድር ያለተመልካች መጫወት አያስደስትም፡፡

በእርግጥ ከግብፅ ክለብ ደጋፊዎች አስፈሪ የድጋፍ አሰጣጥና ነውጠኛነት አንፃር ሲታይ ጨዋታው በዝግ ስታድዬም መካሄዱ ለእኛ ተጨዋቾች ተረጋግቶ መጫወት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደእኔ አስተሳሰብ ግን ከዝግ ስታድዬም ይልቅ በተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ፊት ከሜዳ ውጭ መጫወት እና ውጤት ማግኘት የአንድ ቡድን ምርጥ ብቃት ለመለካት ያግዛል ነው፡፡ ከዝግ ስታድዬም ይልቅ የትኛውም ግጥሚያ በተመልካች ፊት መደረጉ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝነት እየተሳካልዎት ነው? እቅድዎስ ምንድነው? የመጀመርያው ትኩረቴ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከባለፉት አመታት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነው፡፡ በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ጊዮርጊስ ከሞላ ጎደል ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ክለቡ ለሁለተኛ ዙር ከሚደርሱት 16 ቡድኖች አንዱ እንዲሆን እቅዴ ነበር፡፡ ይህን ማሳካት ተችሏል፡፡ በዚያ ላይ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድል የሚገባበትን ጥሩ እድል ይዞ ይገኛል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ፡፡ ዛማሌክን ጥሎ ለማለፍ ባይሳካለት እንኳን ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የሚገባበት ተጨማሪ እድል አለው፡፡ በአገር ውስጥ ውድድር ግን ብዙ የሚያበረታታ ሁኔታ ላይ አንገኝም፡፡ ዋናው ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአህጉራዊው ውድድር መሳተፉ እና ለብሄራዊ ቡድን በተመረጡ ወሳኝ ተጨዋቾቹ በበቂ ሁኔታ አለመጠቀሙ በሊግ ውድድሩ ለዋንጫ ፉክክር ያለውን አቅም ፈትኖታል፡፡ ይሁንና በሊጉ ስኬታማ ለመሆን እስከመጨረሻ እንታገላለን፡፡ የዛማሌክ አሰልጣኝ ብሄራዊ ቡድኖችን አሰልጥነዋል፡፡ በእርስዎ ግን ይህ ልምድ የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር ከክለብ አሰልጣኝነት ይልቅ የብሄራዊ ቡድን ስራ የሚቀል ይመስለኛል፡፡

በክለብ ደረጃ ማንኛውም አሰልጣኝ የእለት እለት ስራ ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህ ብቃት ማነፃፀር ስትፈልግ በክለብ አሰልጣኝነት ያለንን ልምድ ብታነፃፅር ይሻላል፡፡ በክለብ አሰልጣኝነት የዛማሌኩ ዮርቫን በሰሜን አፍሪካ በቂ ልምድ ቢያካብቱም እኔ በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ባለው የጀርመኑ ቦንደስሊጋ እስከ 2010 እኤአ መስራቴ ያለኝን ጥሩ ብቃት ይመሰክራል፡፡ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ምርጥ የሚባለው ለምንድነው? የቦንደስ ሊጋ ትልልቅ ክለቦች በሆኑት ሻልካ 04 ፤ ሃኖቨር 96 እና ሌሎች ክለቦች ውስጥ በአሰልጣኝነት በመስራት ከፍተኛ ልምድ አካብቻለሁ፡፡ ቦንደስ ሊጋ የዓለማችን ትልቅ ውድድር ነው፡፡ ሊጉ ላገኘው ከፍተኛ ስኬት የውድድሩ ፓኬጅ በሁሉም አቅጣጫ የተሟላ እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው፡፡ የክለቦች አደረጃጀት እና ጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው ለሊጉ ጥንካሬ በቅድሚያ ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የቦንደስ ሊጋ ውድድሮች በየስታድዬሙ በርካታ ተመልካች አላቸው፡፡ ክለቦች በምርጥ አጨዋወት የተሳካላቸውና ተመጣጣኝ ፉክክር የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የቦንደስ ሊጋ ውድደሮች ከፍተኛ ተመልካች ለማግኘት የበቁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ የየክለቡ ስታድዬሞች ዘመናዊ እና የተሟሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ውድድርን ለማሻሻል ምን ይደረግ? የመጀመርያው የለውጥ አቅጣጫ በሊግ ደረጃ የሚወዳደሩ ሁሉም ክለቦች የተሟላ እና በቂ የልምምድ ሜዳ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምትመለከተው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ በአገሪቱ ካሉት ክለቦች አንፃር የተሻለ ቢሆንም ምቹ እና ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል የሊግ ግጥሚያዎች የሚደርጉባቸው ስታድዬሞች ደረጃም ማደግ አለበት፡፡ አሁን ያሉት ስታድዬሞች ለሊግ ውድድር አይመጥኑም፡፡ ከስምንት በላይ ክለቦች በሜዳነት የሚገለገሉበት የአዲስ አበባ ስታድዬም እንኳን በቂ ደረጃ የለውም፡፡ በክለቦች አደረጃጀትም ከኋላ ቀር አሰራሮች መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በውድድር አመራር ያሉ የተለያዩ ችግሮችም መቀረፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የሊግ ውድድር ፕሮግራሞች በየጊዜው የማይዘበራረቁ፤ ከኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች ጋር የማይጋጩ ሆነው መቀረፅ አለባቸው፡፡ በክለቦች እና በብሄራዊ ቡድን የተጨዋቾች አገልግሎትም የተጠና እና በእቅድ የሚሄድ አሰራርም ያስፈልጋል፡፡ የገቢ ምንጭን በሚያሰፉ ሁኔታዎች መስራትም ተገቢ ነው፡፡ በሊግ ደረጃ የሚወዳደሩ ክለቦች በስልጠና እና በፕሮፌሽናል የክለብ አደረጃጀቶች ወጥ በሆነ ስትራቴጂ መመራት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን ኳስ ተጨዋቾች የፕሮፌሽናልነት ተስፋን እንዴት ይመለከቱታል? ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብሄራዊ ቡድን በሚያስመርጣቸው ተጨዋቾች በአስፋላጊው መንገድ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የውድድር መደራረብ የሚፈጥረው ተፅእኖ እንዳለ ሆኖ በተጨዋቾች የአካል ብቃት ላይ ያለው ድክመትም መጥፎ ደረጃ ላይ መገኘቱ ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች በሳምንት ሶስት ጨዋታዎች በተሟላ አቅምና ዝግጅት የሚያደርጉበት ብቃት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ጥሩ የእግር ኳስ ችሎታ እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ በተደራራቢ ግጥሚያዎች በተሟላ ብቃት የሚያገለግሉበት የአካል ብቃት እና የልምምድ አቅም አለማዳበራቸው ግን ይህን ችሎታ ጥቅም አልባ የሚያደርገው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በተለይ በአካል ብቃት እና ጥንካሬ ፤ በስፖርታዊ የአስተሳሰብ ባህርይና ቅልጥፍና፤ በፍጥነት፤ በስራ ትጋት እና የዲስፕሊን ደረጃ ብዙ እየሰሩ አይደለም፡፡ ተጨዋቾች ለልምምድ በቂ ትኩረት ሲያደርጉ አልመለከትም፡፡ በሚያስፈልገው የፕሮፌሽናል ተጨዋች ደረጃ በትጋት የመስራት እና በየጊዜው ብቃትን የማሻሻል ጥረት ይጎድላቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ተጨዋቾች በየጨዋታው በሚኖራቸው የፉክክር ባህርይም እገረማለሁ፡፡

አንዱ ጨዋታ ላይ ምርጥ ብቃት ያሳየ ተጨዋች በሌላ ጨዋታ ሳይጠበቅ ተዳክሞ እና ብቃቱ ወርዶ ያጋጥምሃል፡፡ እነዚህ ችግሮች አንድም በፕሮፌሽናል ደረጃ የመስራት ባህል ባለመዳበሩ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በተገቢው ሁኔታ ልምምድ ካለመስራት እና ዲስፕሊን ካለማክበርም ይፈጥራሉ፡፡ የተጨዋቾች ብቃት መውረድና መዋዠቅ በቅዱስ ጊዮርጊስም ክለብም ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ በክለቡ አሰልጣኝነት ይህን ችግር ለመረዳት እና ለማጥናት ጥረት እያደረግኩ ነው፡፡ ቢሆንም አሁን ባለው ትውልድ የጎላ ለውጥ ለመፍጠር የሚከብድ ነው፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ አንድ ተጨዋች ሊያሟላቸው ከሚገቡ ነገሮች አንፃር የኳስ ቁጥጥር እና ችሎታ በቂ አይደሉም፡፡ የተሟላ የአካል ብቃት፤ ተመሳሳይ ደረጃ ባላቸው ውድድሮች የማይዋዥቅ አቋም ማሳየት፤ ፍጥነት፤ ጉልበት እና የታክቲክ ብስለትን በሚያስፈልገው ደረጃ ማዳበር ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በቂ ስልጠና አለማግኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም አስፋላጊው ትኩረት እና ጥረት ሲያደርጉ አልመለከትም፡፡

ይህ ከባድ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች አሁን ባላቸው የብቃት ደረጃ አይደለም በአውሮፓ በአፍሪካ ለሚገኙ ክለቦች እንኳን በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እነዚህ ችግሮች ለመቅረፍ ኢትዮጵያውያን ኳስ ተጨዋቾች በፕሮፌሽናል ደረጃ ስፖርቱን ለመስራት እንቅፋት የሚሆነውን ደካማ አስተሳሰብ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁኔታ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀየር በቂ ጊዜ ሰጥቶ ሰፊ ስራዎችን ማከናወን ይጠይቃል፡፡ በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ማንም ተጨዋች አቋሙን ማሳየት ያለበት በተሟላ ብቃት ውጤታማ ለመሆን እንጅ በስፖርቱ ለመዝናናት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በተሟላ ዲስፕሊን፤ በከፍተኛ ትጋት ልምምድን በመስራት እና ብቃትን በማሻሻል የመስራት ባህርይን ሁሉም ተጨዋቾች መከተል አለባቸው፡፡ አሁን በጥሩ ደረጃ የፕሮፌሽናል ጉዞውን በአውሮፓ በመጀመር ፈርቀዳጅ የሆነውን ሳላሃዲን ሰኢድ ብቻ ነው፡፡ ሳላሃዲንን ብትመለከት ከብዙ ተጨዋቾች የተለየ ስብእና እንዳለው ትገነዘባለህ፡፡ በተፈጥሮው ካለው ተሰጥኦ ባሻገር የራሱን ትጋት በመጨመር አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል፡፡ የጊዮርጊስ ኡጋንዳዊያን ተጨዋቾች አስተዋፅኦን በተመለከተስ… በቡድናችን የሚገኙት ኡጋንዳውያን በጣም እየጠቀሙን ናቸው፡፡ ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዱንጋካራ ያለበት የብቃት ደረጃ ለአውሮፓ እግር ኳስ እንደሚመጥን የምመሰክረው በሙሉ መተማመን ነው፡፡ በግብ ጠባቂ ደረጃ በኢትዮጵያ እግር ኳስ መሰረታዊ ችግር መኖሩን አውቃለሁ፡፡ ለግብ ጠባቂነት ብቁ ደረጃ ያላቸውን ተጨዋቾች ለማግኘት ብቸኛው መፍትሄ ከታዳጊ ስልጠና መነሳት ነው፡፡ሌላው ኡጋንዳዊ የጊዮርጊስ ተጨዋች የመሃል አጥቂው ሮበርት ሴሴቴንጎም እጅግ ምርጥ ብቃት እና አቋም በማሳየት ክለቡን ያጠናከረ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጊዮርጊስ የሚገኙት ኡጋንዳውያን በየትኛው የአውሮፓ ክለብ ለመግባት የሚያስችል የአካል ብቃት፤ ብስለት እና ሌሎች ለፕሮፌሽናል ተጨዋች የሚያስፈልጉ አቅሞችን በማሳየት ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

Read 3494 times