Saturday, 27 April 2013 10:26

አቶ ተመስገን ከዳያስፖራ ደጋፊዎች ጋር ለመወያየት አሜሪካ ሄዱ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ከዳያስፖራ ደጋፊዎች የምናገኘው ምላሽ አበረታች ነው”

በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በመድረክ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተመስገን ዘውዴ፤ በሁለቱ ድርጅቶች ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመምከርና በዲፕሎማሲና በፋይናንስ ድጋፍ ዙሪያ ከውጭ ደጋፊዎቻቸው ጋር ለመወያየት ትላንትና ወደ አሜሪካ ተጓዙ፡፡ በአንድነት እቅድና ስትራቴጂ መሠረት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው በጊዜው ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎች በዲፕሎማሲ እና በፋይናንስ ፓርቲውን የሚረዱበትን ሁኔታ ማፈላለግና በሀገራቸው ጉዳይ እንዲደራጁ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበት የገለፁት አቶ ተመስገን፤ ጥረቱ በፊት የተጀመረ እንደሆነና ይህንኑ ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ በፊት እንደተለመደው በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ፣ ስለ አደረጃጀትና የፋይናንስ ድጋፍ ለደጋፊዎች ገለፃ አደርጋለሁ” ያሉት አቶ ተመስገን፤ ጉዟቸው ዋሽንግተን ዲሲ፣ ካናዳና ደቡብ አፍሪካን እንደሚሸፍን ገልፀዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በአሜሪካ 10 ያህል ግዛቶች ተዘዋውረው አባላትን አደራጅተው መመለሳቸውን ገልፀው፤ በአሁኑ ጉዞ በአሜሪካ ውስጥ የሚዘዋወሩባቸው ስቴቶች አሜሪካ በሚገኙ የድርጅት ሃላፊዎች ፕሮግራም እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ በአደረጃጀት፣ በዲፕሎማሲና በፋይናንስ ድጋፍ ለሚሠሩት ሥራ አምስት ወራትን በአሜሪካ በካናዳና ደቡብ አፍሪካ እንደሚቆዩና ነሐሴ መጨረሻ አሊያም መስከረም መጀመሪያ ላይ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ አቶ ተመስገን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

የአንድነትና የመድረክ ደጋፊዎች በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ ሲያትል፣ በካሊፎርኒያ ቦስተን፣ አትላንታ፣ በዴንቨርና በሌሎች በርካታ ግዛቶች እንደሚገኙ ገልፀው የድርጅቱ ሃላፊዎች ባላቸው ፕሮግራም ቢቻል ሁሉንም አዳርሰው፣ አደረጃጀቱንና የፋይናንስ ድጋፉን ለማጠናከር እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ በመቀዛቀዙ የዲያስፖራውም ድጋፍ ተቀዛቅዟል በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ከውጭው ደጋፊ ምን ይጠብቃሉ ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ “ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎቻችንና ወገኖቻችን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ስለገራቸው ያላቸው ስሜት ከፍተኛ ነው” ያሉት አቶ ተመስገን፤ አንድነትም ሲያደራጃቸው በህጋዊና በሠላማዊ መንገድ በመሆኑ ህጋዊ የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲኖር የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በምንም ሁኔታ ከመደራጀትና ከመደገፍ ወደኋላ እንዳላሉ፣ ተቀዛቅዟል የሚባለውም ሀሰት እንደሆነ ተናግረዋል።

“እነዚህ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ የስልጣንና የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲኖር ፍላጐት ያላቸው ስለመሆኑ በደንብ እናውቃለን” ብለዋል። የሀገራቸው የልማትና የደህንነት ጉዳይ፣ የሰብአዊ መብት መከበር፣ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የሚያገባቸው በመሆኑ የሀገር ውስጥ ሠላማዊ ትግልን ከመደገፍ፣ ከመደራጀትና በሠላማዊ መንገድ ከመታገል ቦዝነው እንደማያውቁ በአጽንኦት የገለፁት ሃላፊው፤ በአንድነትና በመድረክ ደጋፊዎች መካከል አንዳችም መቀዛቀዝ እንዳልታየ ተናግረዋል፡፡

“ይህን ጉዳይ ከዚህ ቀደም ወደ እነርሱ እየሄድን ስናደራጅና ስንቀሰቅስ አይተነዋል” ያሉት አቶ ተመስገን፤ ዛሬም እንደተለመደው ሠላማዊና ህጋዊ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን፣ ሰብአዊ መብቱ እንዲጠበቅ፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትና ዴሞክራሲ በዚህች አገር እውን እንዲሆን መታገል እንዳለባቸው እንደሚያስረዱ ገልፀዋል፡፡ በዚህም እንደ በፊቱ ሁሉ ስኬታማና የተዋጣለት የማደራጀትና የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ሰርተው እንደሚመለሱ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ “እንኳን እዚያ ሄደን አገር ውስጥም ሆነን ከዳያስፖራ ደጋፊዎች የምናገኘው ምላሽ አበረታች ነው” ብለዋል - አቶ ተመስገን፡፡

Read 2625 times