Saturday, 27 April 2013 10:46

የ‘አንድ ሰሞን’ አብሾ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ሰላም ነው? ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“እንደው ለጤናሽ እንደምን ከረምሽ…” “ጨጓራህ ሰሞኑን ትንሽ ሻል አላለህም…” “አገሩ ከብቱ ደህና ከረመ…” አይነት ሰላምታዎች እኮ የ‘ድሮ ታሪክ’ አይነት ሆነዋል፡፡ የምር እኮ…አለ አይደል… እንደዚህ አይነት ሰላምታዎች ቢሆንም፣ ባይሆንም ለሰው ደህንነትና ጤንነት ከመጨነቅ የሚመጡ ነበሩ፡፡ አሁን በ‘ሰለጠነው’ ዘመን ግን “ሰላም ነው?” የሚል ሰላምታ ይሁን...መረጃ ጥየቃ ይሁን…የማይለይ ድፍንፍን ያለ አባባል ዋናው ሰላምታችን ሆኖ ቀርቷል፡፡ እንደ ብዙ የ‘ድሮ ነገሮች’ የድሮ ሰላምታም እየናፈቀን ነው፡፡ እኔ የምለው… ‘አንድ ሰሞን እንዲህ የሚያደርገን ሰዎች እየበዛን’ ግራ የሚገባ ነገር ሆኗል፡፡ ተጠባባቂ የመምሪያ ሀላፊነት ደብዳቤ በደረሰው በሦስተኛው ቀን ትከሻው ስፋት ላይ ሀያ አምስት ሳንቲሜትር የሚጨምር ሰው አይገርማችሁም! ምን አለፋችሁ… በመሥሪያ ቤቱ ‘ኮሪደሮች’ እሱ በሚያልፍበት ጊዜ ሌሎቹ ሠራተኞች የሁለትና የሦስት ሜትር ርቀት እንዲኖራቸው ይጠብቃል፡፡ ለሥራ ባልደረቦቹ ሰላምታ የመስጠት ነገርንማ እርሱት፡፡

‘እሱም አንድ ሰሞን እንደዛ እያደረገው’ ነዋ! በተራ ሠራተኝነት ዘመን ጆፌ ተጥሎብሽ እምቢ ያልሽ እንትናዬ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ አንቺን አያድርገኝ፡፡ እናላችሁ… ያውም ዘንድሮ ስልጣን የ‘ብቃት’ ጉዳይ ብቻ ባልሆነበት ዘመን (ልክ ነዋ!) …ትከሻ ማስፋት ቀሺም ነው፡፡ ሳይታሰብ የተቀመጡበት የድሀ ቤት ግድግዳ የሚያክል ወንበር እኮ ከስር የሚንሸራተተውም ሳይታሰብ መሆኑን ነገሬ አለማለት የለየለት ቅሽምና ይሆናል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በዛኛው ዘመን “ጓድ…” ካልተባሉ ድፍን አገር ቢንጫጫ የማይሰሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ “ጓድ…” ማለቱ የቀረ ቢሆንም ‘አንድ ሰሞን እንደዛ እያደረገን’…አለ አይደል… “እግሬ ስር ሀር አንጥፉልኝ…” ማለት የሚዳዳን መአት ነን፡፡ የጓድ ነገርን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ ጊዜ አንድ አሜሪካዊ ባለስልጣን ንግግር ሊያደርጉ መድረኩ ላይ ይወጣሉ፡፡ “የእለቱ የክብር እንግዳ፣ የትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ሀላፊዎች፣ የቢዝነስ ሀላፊዎች…” ምናም እያሉ መሀል ላይ ቆም አደረጉ፡፡ ከዛ ምን አሉ መሰላችሁ…“ሩስያዎች ይሻላሉ፣ በቃ ጓድ ብለው ይገላገላሉ፡፡

” የእኛን አገር ባዩ…ከሁለት ገጽ ንግግር ግማሹ እኮ የተሰብሳቢዎች ዝርዝር ነው። እናላችሁ…የአንድ ሰሞን ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሥራዎች ሁሉ የ‘አንድ ሰሞን’ እየሆኑ ዘላቂ የሚባል ነገር እየተመናመነ ነው፡፡ ድርጀቶች በጊዜ መሥራት ያለባቸው ሥራዎች ሳይሠሩ ይቀሩና አንድ ሰሞን በቴሌቪዥን ካሜራ ፊት “ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፣” ይባላል፡፡ ‘አንድ ሰሞን እንዲህ የመሆን ነገር’ ይሄ ነው፡፡ “እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አድርጎን ነበር…” አይነት አስተሳሰብ ከግለሰብ ወደ ተቋም ሲለወጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲሀ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ነገሬ ብላችሁልኝ ከሆነ… ከ‘ባለጊዜ’ ጋር መለጠፍን… አለ አይደል…የጥንት ጊዜ ንግርት እንደተፈጸመ አድርገው የሚያዩት አሉ፡፡ ‘ባለጊዜዎቹ’ ሳይሆኑ እነሱ በሰው ልጅ ላይ ‘ሊነሰነሱበት’ ከአንድዬ ሙሉ ስልጣን ያገኙ ይመስላቸዋል፡፡ ደግሞላችሁ… ራሳቸውን ከፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ችግራቸው እግረ መንገዳቸውን ሌላውን ‘ዝቅ ለማድረግ’ መሞከራቸው፡፡ እነሱ ከ‘ባለጊዜ’ እግር ስር ‘ቱስ፣ ቱስ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) እያሉ የእንትና ባህል ቤት በርን ስላዘጉ “ሰው ምን ይላል…” ማለትን ይረሳሉ፡፡

(እግረ መንገዴን…‘ቦተሊከኞች’ም ብትሆኑ ራሳችሁን ብቻ ማዳመጥ ሳይሆን “ሰው ምን ይላል?” ማለት ብትለምዱ አሪፍ ይሆናል፡፡ ዕድለኛ በሆኑት አገሮች እኮ ‘ፐብሊክ ኦፒኒየን’ ከዙፋን ወደ በርጩማ ሊያወርድ ይችላል፡፡) እናላችሁ…ዘንድሮ መቼም የፊልም ነገር ያው እንደምናየው ነው፡፡ መአት ፊልሞች ይወጣሉ፣ መአት ሰዎችም በአንድ ጊዜ ከ‘ተራ ሰውነት’ ወደ ‘ፊልም ተዋናይነት’ እየተለወጡ ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ ታዲያላችሁ…እንደው ከባዶ አየር ዱብ ብለው አንዳንዶቹ የሚያሳዩት ችሎታ “በርቱ!” የሚያሰኝ ነው፡፡ እናማ… በዚሀ መሀል እንትን ፊልም ላይ የአንድ ደቂቃ ተኩል የባሬስታነት ገፀ ባህሪይ የተጫወተው ሰው ፊልሙ በተመረቀ በማግስቱ የፊቱን ሦስት አምስተኛ የሚሸፍን መነፅር ያደርጋል፡ የፀጉር አበጣጠር ይለውጣል፣ የሱሪው ቀበቶ ማረፊያ ዝቅ ይላል…ምን አለፋችሁ ብቻ… ‘አንድ ሰሞን እንደዛ የሚያደርጋቸው’ ሰዎችን ይቀላቀላል፡፡ አንድ ሰሞን…አለ አይደል… ‘አንድ ሰሞን’ ብቻ ይረሳና ድንገት ከህልሙ ሲነቃ ሁሉ ነገር ይደበላለቅበታል፡፡ ህልም ደግሞ አሪፍ አይደለም፡፡ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የህልምን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ጋብሮቮያዊው ልጅ አባቱን “አባዬ ዛሬ በህልሜ ቸኮላት ስትገዛልኝ አየሁ” ይለዋል፡፡ አባቱ እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፡፡

“ጥሩ ልጅ ከሆንክና ጠባይህን ካሳመርክ ለገና ደግሞ አንድ ኪሎ ቸኮላት ስገዛልህ በህልምህ ታያለህ፡፡” ስሙኝማ…ዘንድሮ መቼም ከዘመን መለዋወጥ ጋር እዚህ አገር ስረ መሠረቱ የጠፋ ነገር ቢኖር እውነተኛ ጓደኝነት ነው፡፡ ጓደኝነት የሰብአዊነት ባህሪይ ሳይሆን የቢዝነስ አዋጪነት ስትራቴጂ አይነት ሆኗል፡፡ ለዚህ ነው ጓደኝነቶች የሚፈጠሩትም የሚፈርሱትም የብርሀንን በሚያስንቅ ፍጥነት የሚሆኑት፡፡ አዲስ አበባን በ‘ዎክ ለብ ለብ’ ሲያካልሉ አንድም ቀን ቅር ብሏቸው የማያውቁ ጓደኛሞች አንደኛው ድንገት ‘አንድ ሰሞን እንዲህ ያደርገውና’ ነገሮች ሁሉ ይለዋወጣሉ፡፡ ተዉት ጥርስ የነቀሉበት… ‘ዎክ ለብለብ’…ጭርሱን “ሰው እንዴት እኮ በሚኒባስ እንደሚሄድ ይገርመኛል…” ማለት ይጀመራል፡፡ ለምን መሰላችሁ… በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ ካላቸው ከሞላቸው ተጠግቷላ፡፡ እሱም “አንድ ሰሞን እንደዛ እያደረገው ነዋ!” ኮሚኩ ነገር እኮ…አለ አይደል…ካላቸው ከሞላቸው ጋር ያለው ግንኙነት ከመልእክት አመላላሽነት ያልዘለለ ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እንደ ‘ሰውዬዎቻቸው’ የኪስ ውፍረት ‘አንድ ሰሞን እንዲህ እንዲህ የሚያደርጋቸው’ እንትናዬዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የውጪ ጫማ ከተገዛላቸው በኋላ…ምን አለፋችሁ ይለወጣሉ፡፡

ደግሞላችሁ…ዘንድሮ እንትናዬን የማግኘት ዋናው መለኪያ ፈራንካ እየሆነ ነው፡፡ ይሄ በቦሌ መንገድ በእግር እየሄደ “በእናትሽ፣ ይሄ ህንጻ ደስ አይልም!” የሚለው ‘አማተር ሰርቪየር’ ምናምን (ቂ…ቂ…ቂ…) ጊዜ አልፎበታል፡፡ አሁን ቅድሚያ የሚያገኘው ህንጻውን ከውጪ ሆኖ በጣቱ እየጠነቆለ የሚያሳይ ሳይሆን ህንጻ ውስጥ ገብቶ የሚያንበሸብሸውን ነው፡፡ እናላችሁ…እንትናዬ “አጅሪት ዶላርና ፓውንድ የሚያስነጥሰውን ይዛለች…” እየተባለ ሲቪዋ ላይ አዳዲስ ገጾች ይጨመሩላታል፡፡ ከዛ ምን ይሆናል መሰላችሁ…የልብ ጓደኛ ትመጣና “አንቺ… ዘውድነሽ ጋ ሄደን ጸጉራችንን የምንሠራው መቼ ነው? ብታዪው ጸጉሬ በርኖስ ሊሆን ምንም አልቀረው…” ትላለች፡፡ ‘አንድ ሰሞን እንደዛ ያደረጋት’ ምን ትል መሰላችሁ…“ዘውድነሽ! ያቺ እዛ መንደር ውስጥ ያለችው! ኸረ ለጠላቴም አያሳየው!” ‘አንድ ሰሞን እንደዛ ሲያደርግ’ ውጤቱ ይሄ ነዋ! “ዘውድዬ… ሀያ አምስት ብሩን በሚቀጥለው ወር እከፍልሻለሁ… አሁን እንዲሁ አትሠሪኝም!” ምናምን እያለች ስትለማመጥ የነበረችው ሁሉ ይረሳል፡፡ የ‘አንድ ሰሞን’ ነገር ሰውን ብቻ ሳይሆን ራስንም ያስረሳል፡፡ እናላችሁ…“እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር…” የሚለው ትዝ የሚለው መቼ መሰላችሁ…የተወጣጣንበት የመሰለን መሰላል በሀሳብ እንጂ በአካል እንደሌለ የነቃን ጊዜ፡፡ ዶላርና ፓውንድ የሚያስነጥሰው እንትናም እኮ “ማነሽ ባለ ሳምንት…” ብሎ ይሄዳል፣ “በተጠባባቂነት የመምሪያ ሀላፊ ሆነው እንዲሠሩ…” የሚለው ደብዳቤ…አለ አይደል… “ቀደም ሲል በነበሩበት ክፍል ሆነው ሀላፊነትዎን በአግባቡ እንዲወጡ…” ምናምን በሚል ደብዳቤ ሲተካ፣ …..ብቻ ምን አለፋችሁ… የ‘ፌሽታው ጊዜ’ ዘላለም መሆኑ ቀርቶ በአጭሩ ሲቀጭ ያን ጊዜ ‘አንድ ሰሞን’ የሚባል ነገር እንዳለ ትዝ ይላል፡፡ ከ‘አንድ ሰሞን’ አብሾ ይገላግለንማ! ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 4705 times