Saturday, 27 April 2013 11:15

ትዳር አፍራሹ መካንነት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(15 votes)

በዓለም ላይ ካሉ ጥንዶች 15 በመቶ ያህሉ መካኖች ናቸው ሴቶች ለመካንነት 50% ድርሻ ሲኖራቸው፤ ወንዶች 20% ድርሻ አላቸው ሳውና ባዝ አዘውትሮ መጠቀምና በሙቅ ውሃ መዘፍዘፍ ለመካንነት ይዳርጋል

 ከአምስት ዓመታት በፊት በገቢዎችና ጉምሩክ መ/ቤት ውስጥ በሥራ ላይ ሣለች ነበር የዛሬውን ነጋዴ ባለቤቷን የተዋወቀችው- በወቅቱ ከውጭ አገር ያስመጣቸውን ዕቃዎች ቀረጥ ከፍሎ ለመረከብ ሲመላለስ፡፡ የተስተካከለ የሰውነት አቋሟና ጥርት ያለው የፊት ገፅታዋ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮዋ ብቅ ያለውን ነጋዴ አስደነገጠው፡፡ የራሱም ሊያደርጋት እጅግ ተመኘ። ቁጥብ ባህርይዋና ከሰዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት አለመቻልዋ ብዙ ፈተነው፡፡ ይህ ደግሞ ይበልጥ እንዲወዳት የበለጠ እንዲመኛት አደረገው እንጂ አላሸሸውም፡፡ በውበቷ የደነገጠው ስሜቱ ሲረግብ ስለ አብሮ መዝለቅ፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ጥልቅ ጓደኝነትና ፍቅር ማሰብ ጀመረ፡፡ ሁሉንም ነገር በገንዘብ አቅምና በጉልበት ማድረግ እንደማይቻል ያስተማረችውን ይህቺን ወጣት ሊያገባት ወሰነ፡፡

በአስመጪነት ንግድ ፈቃዱ ከተለያዩ አገራት የሚያስመጣቸዉን ዕቃዎች (ልብሶች) ለጅምላ ነጋዴዎች የሚያከፋፍል ሲሆን በችርቻሮ የሚሸጥባቸውም ሁለት ትላልቅ ሱቆች መርካቶ ውስጥ አሉት፡፡ ዘመናዊ መኪኖችን እንደልቡ እያቀያየረ መያዙ፣ ሀብትና ንብረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ቢያስደስተውም ሁልጊዜ የሚያስጨንቀውና አጥብቆ የሚያሣስበው ጉዳይ አለ፡፡ በተለይ የስኳር ህመምና እርጅና የተጫጫናቸው ወላጅ እናቱን ባገኘ ቁጥር ሃሳቡ ጭንቅ ይሆንበታል፡፡ “ልጄ ትዳር ይዘህ ውለድና ልጅህን አሣየኝ፤ ሞት ሣያቀድመኝ ልቅደመው” ነጋ ጠባ ይወተውቱታል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያገኛቸው ሴቶች ሁሉ ከእሱ ይልቅ ገንዘቡን ሲያስቡ እያገኛቸው ተስፋ ቆርጧል፡፡ ይህቺ በጉምሩክ ቢሮ ውስጥ ያገኛት ወጣት ግን የተለየች ነች፡፡

ረጋ ያለ ባህርይዋና በሣል አስተሣሰቧ ስለ እሷ ደጋግሞ እንዲያስብና ከተራ ስሜት በዘለለ ዘላቂ በሆነ የፍቅር አይን እንዲመለከታት አድርገውታል። ትውውቃቸው አድጐ ለፍቅር ጓደኝነትና ለትዳር ሲበቃም ቤተሰቦቹ እጅግ ደስተኞች ነበሩ፡፡ በተለይም ወላጅ እናቱ የዓመታት ህልማቸው እውን ሲሆንና የልጅ ልጃቸውን ታቅፈው ሲስሙ ከወዲሁ ታይቷቸው ደስታቸው ወሰን አልባ ነበር፡፡ የሁለቱ ጥንዶች የጋብቻ ዘመን ጅማሬም እጅግ የሚያስቀናና ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ለስምንት ዓመታት ካገለገለችበት መ/ቤት የለቀቀችው ጋብቻዋን እንደፈፀመች ሲሆን መርካቶ የሚገኙትን የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ተረክባ መሥራት ጀመረች። ትዳራቸው ከአይን ያውጣው በተባለለት ፍቅር ጠንክሮ ሁለተኛ ዓመቱን አጋመሰ፡፡

ቀስ በቀስ የእነዚህ ጥንዶች ትዳር እንደ ጅማሬው መዝለቅ የማይችልባቸው ሁኔታዎች መከሰት ጀመሩ፡፡ ለዚህ እንቅፋት መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ደግሞ እንደ ምኞታቸው ልጅ መውለድ አለመቻላቸው ነበር። ሚስት ተጨነቀች፡፡ በእንግድነት ወደ ቤታቸው የሚመጡት የባሏ እናት በነገር ይሸነቁጧት ያዙ፡፡ “ቪላ ቢሠራ ምን ዋጋ አለው፡፡ ቤት ያለ ልጅ በረት …” እያሉ አሳቀቋት፡፡ የሚሏትን ሁሉ በአንድ ጆሮዋ እየሰማች በሌላው እያፈሰሰች ውስጧ በሰቀቀን እየተሰቃየ ኑሮዋን ትገፋው ጀመር፡፡ ሦስተኛው የጋብቻ ዓመትም ያለ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡ ይህን ጊዜ እሷም ጥርጣሬ ገባት፡፡ ችግሯን የምታወያየው ሰው አጣች፡፡ የህክምና ባለሙያዎችን ለማማከርና ምርመራ ለማካሄድ ወስና፣ ብራስ የእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከል ሄደች፡፡

ምርመራውን ያደረገላት ሃኪም የማህፀን መጣበቅ ችግር እንዳለባትና ይህም በቀዶ ጥገና ህክምና ሊስተካከል እንደሚችል ነገራት። ደነገጠች፡፡ ምን ብዬ ነው ለእሱ የምነግረው? ተደብቄስ ህክምናውን እንዴት ማከናወን እችላለሁ? የሚሉት ሞጋች ጥያቄዎች ሰላም ነሷት፡፡ ግን የተከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍላ ለማፍረስ ያጋደለውን ትዳሯን ለመታደግና የባሏን ፍቅር መልሳ ለማግኘት እንዲሁም የልጅ እናት የመሆን ፀጋን የማግኘት ጠንካራ ፍላጐት ነበራት፡ “የእናትነት ፀጋን እንደታደላቸው ሴቶች ማህፀኔ የተሰጠውን ዘር ለፍሬ ለማብቃት ባለመቻሉ ምክንያት ትዳሬ ሲፈርስ ዝም ብዬ ማየት አልችልም፤ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍዬ ህልሜን እውን አደርገዋለሁ” ቁርጥ ውሳኔ ነበር፡፡ የዚህችን ወጣት ታሪክ ለፅሁፌ መግቢያ እንዲሆን የመረጥኩት የብዙዎች ትዳር መፍረስ መንስኤ ስለ ሆነው መካንነት ጥቂት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡

ዘገባውን ለማዘጋጀት መረጃዎች ለማሰባሰብ በተዘዋወርኩባቸው የግልና የመንግስት የህክምና ተቋማትና የመዝናኛ ሥፍራዎች ውስጥ ካገኘኋቸው ባለትዳር ወንዶችና ሴቶች ጋር ውይይት አድርጌ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ጥንዶች በትዳር ውስጥ ልጅ መውለድን ለትዳር ዘላቂነትና አስተማማኝነት ዋንኛ መሠረት ነው ይላሉ፡፡ አብዛኛዎቹም መካንነቱ የሴቷ ችግር ብቻ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ፡፡ የማህፀንና የጽንስ ሃኪሙ ዶ/ር ስንታየሁ ተስፋ እንደሚናገሩት ግን፤ ሴቶች ለመካንነት ክስተት የሃምሣ በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ወንዶች የሃያ በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማርገዝና ለማስረገዝ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ተሟልተው በማይገኙበት ሁኔታ ውስጥ ጽንስ ሊፈጠር አይችልም፡፡ እርግዝና እንዲፈጠር መሟላት አለባቸው የሚባሉትን መሠረታዊ ነገሮች ዶክተር ስንታየሁ እንዲህ ይዘረዝሯቸዋል፡፡ ጤናማ የሴት እንቁላል፣ በአግባቡ ተግባሩን የሚያከናውን የማህፀን ቱቦ፣ የወንድን የዘር ፍሬ ወደሚፈለገው ቦታ የሚያደርስ ውህድ፣ ጤናማ የወንድ ዘር ፍሬ፣ ጤናማ የወንድ ውህድ ቅመምና ወሲብን በአግባቡ ለመፈፀም የሚያስችል ብቃት ወሳኞቹ ናቸው፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ተሟልተውና በአግባቡ ተከናውነው ጽንሱ ካልተፈጠረ መካንነት አለ ሊባል ይችላል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ሃኪም የሆኑት ዶክተር መስፍን አስቻለው፤ መካንነትን ሲገልፁ “የትኛውንም አይነት የወሊድ መከላከያ መድሃኒት ሳይጠቀሙ እና ለመውለድ የተሟላ ፍላጐትና ዝግጅት ኖሮአቸው በሣምንት ሶስት እና አራት ቀናት ያህል የግብረሥጋ ግንኙነት እየፈፀሙ ሴቷ ማርገዝ ካልቻለች፣ ያለመውለድ ችግር አለ ሊያሰኝ ያስችላል፡፡ በተለይ ችግሩ የተከሰተው ጥሩ የመውለጃ ጊዜ ተብሎ በሚገለፀው ማለትም ከ20 እስከ 26 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ እያለች ከሆነ መካንነቱ አለ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል” ይላሉ። መካንነቱ የተፈጠረው ምንም ዓይነት የእርግዝና ክስተትን ባላየች ሴት ላይ ከሆነ ችግሩ primary fertility ወይንም የመጀመያ ደረጃ መካንነት ሲባል፣ ቀደም ሲል ውርጃ አጋጥሟት በነበረች ሴት ላይ የተከሰተ ችግር ከሆነ secondary fertility ወይንም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ መካንነት ተብሎ ይጠራል፡፡ ለማስረገዝ ወይንም ለመውለድ ፍፁም አቅም ማጣት ሲከሰት ደግሞ sterility ተብሎ እንደሚጠራም ዶክተር መስፍን ይናገራሉ፡፡ በዓለማችን ካሉ ጥንዶች 15 በመቶ የሚሆኑት መካኖች ሲሆን መካን ከሆኑ ጥንዶች መካከል መፍትሔ ፍለጋ የጤና ተቋማትን በራፍ የሚያንኳኩት 35 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውንም ዶክተሩ ይገልፃሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ አገራት ደግሞ ችግሩ የበለጠ እንደሚስተዋልና በርካታ መካን ጥንዶች መካንነቱን ከእምነት ጋር በማያያዝ ወደጤና ተቋማት የመሄድ ልማድ እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡ መካንነት የሚከሰተው በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን ዶ/ር ስንታየሁ ገልፀዋቸዋል፡፡ በእንቁላል ማምረቻና ማስተላለፊያ ቱቦዎች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ በሴትም ሆነ በወንድ መራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ቁስለቶች፣ ስፐርምን የሚያመርቱ አካላት አለመኖር፣ የወንድ ብልት ደም ዝውውር መዛባት፣ የብልት ቀዳዳ በተገቢው ቦታ አለመኖር፣ እንቅርት፣ የማህፀን ቲቢና እጢ፣ የስኳር በሽታ፣ ስርዓተ ወሲብን በአግባቡ አለመፈፀም፣ ስፐርምን ከውጪ ማፍሰስ፣ እንቁላልን በተገቢው መጠን የማፍራት ብቃት፣ (ይህ ሁኔታ ዕድሜ በጨመር ቁጥር እየቀነሰ ይመጣል) የእንቁላል መጠን መቀነስ፣ የውህድ ቅመሞች እጥረት፣ የወር አበባ አለመስተካከል - ዕድሜ በገፋ መጠን - እየጨመረ የመሄድ ችግር ነው፡፡ የመካንነት ችግር የሴቶች ብቻ ሳይሆን የሁለቱም ወገኖች ችግር መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ስንታየሁ፤ ሁለቱም ጥንዶች በጋራ የሚያከናውኑት ምርምራና ሕክምና ለውጤታማነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ፡፡

ጥንዶቹ የመካንነት ምርመራ ለማድረግ ወስነው ወደ ጤና ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት የህክምና ባለሙያው አጠቃላይ የመራቢያ አካላት ምርመራ፣ የወንድ ዘር ፍሬ ምርመራ፣ የወር አበባ ሂደት ትክክለኛነት ምርመራና የእንቁላል ማምረቻና ማስተላለፊያ ቱቦዎች ምርመራ ያከናውናል፡፡ በመራቢያ አካላት ምርመራ ወቅትም በሴቶች ላይ የማህፀን መጣበቅ፣ የእጢ መኖር፣ የማህፀን አፈጣጠር ችግር ሊገኝ ይችላል፡፡ በመካንነት ምርመራ ወቅት ከተገኙ ችግሮች በመነሳትም ህክምናውን ማከናወን እንደሚቻል የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፤ የመድሃኒት ህክምናና ቀዶ ህክምና ዋነኞቹ መፍትሔዎች መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡ በሴቷ የእንቁላል ማምረቻና ማስተላለፊያ ቱቦዎች ላይ፣ በመራቢያ አካላት የአፈጣጠር ችግር፣ በማህፀን ውስጥ በሚፈጠር እጢ አማካኝነት የተከሰተውን የመካንነት ችግር በቀዶ ህክምና ማስተካከል ሲቻል፣ በወንዶች የዘር ፍሬና በውህድ ቅመሞች ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ደግሞ በመድሃኒትና በሆርሞን ህክምና አማካኝነት ለማስወገድ እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

ህክምናው ትዕግስትን፤ ገንዘብንና ውጣ ውረዶችን እንደሚጠይቅም በማከል፡፡ መካንነትን የሚያስከትሉ ችግሮችን ለመከላከል እንደሚቻል የገለፁት ዶ/ር መስፍን፤ ከተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ራስን መጠበቅ፣ ጤናማ የወሲብ ባህርይን ማዳበር፣ ለማህፀን ቁስለት ከሚያጋልጡ ችግሮች መጠበቅ፣ ማንኛውንም የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች አለመጠቀም፣ ከጨረር አመንጪ ቁሳቁሶችና ከተባይ ማጥፊያ መድሃኒቶች ራስን መጠበቅ፣ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረትን ማስወገድ፣ ከሱሶች መጠበቅ፣ ከጥጥ የተሰሩ ሰፋፊ ልብሶችን አዘውትሮ መልበስ፤ ለሴቶች ከወሲብ በኋላ ከመታጠብ መቆጠብና በሙቅ ውሃ ውስጥ በየጊዜው አለመዘፍዘፍና ሳውና ባዝን አዘውትሮ አለመጠቀም - እርግዝና እንዳይፈጠር ከሚያደርጉ ችግሮች ለመከላከል እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ መካንነት (ልጅ ያለመውለድ ችግር) በግለሰብ፣ በጥንዶች፣ በህብረተሰብና በአገር ደረጃ የሚያስከትለው ሥነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ችግር ነው፡፡ በፍቅር የተመሠረቱ በርካታ ትዳሮች በልጅ ማጣት ሳቢያ የእንቧይ ካብ ሲሆኑ ማየቱ ምንኛ አሳዛኛ ጉዳይ ነው፡፡

የሰለጠኑት አገራት በህክምና ሊወገድ ለሚችለው የመካንነት ችግር መፍትሔ ማግኘት ባይከብዳቸውም ተፈጥሮአዊ ለሆነው መካንነትም መፍትሔ አላጡለትም፡፡ ጥንዶች በትዳር ህይወታቸው የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ልጅ ለመውለድ ባይታደሉም በጉዲፈቻነት ልጆችን እየወሰዱ በማሳደግ የልጅ አምሮታቸውን ይወጣሉ። በአገራችንም ይህ ባህል በስፋት ቢለመድና በልጅ ማጣት ሳቢያ የሚፈርሱትን ትዳሮች ቢታደግ መልካም ነው፡፡

Read 9093 times