Saturday, 27 April 2013 11:27

“ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማንኛውም ወገን የማያዳላ ተቋም ነው”

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(0 votes)

አምባሳደር ቲና ኢንቴልማን ፤ የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት “አሴምብሊ ኦፍ ስቴት ፓርቲስ” ፕሬዚደንት ከመሆናቸው በፊት የኢስቶኒያ የወጪ ጉዳይ መሥሪያቤት ሰራተኛ እንዲሁም በመንግስታቱ ድርጅት የኢስቶኒያ ቋሚ ተወካይ የነበሩ ሲሆን በእስራኤል እና በሞንቴኔግሮ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ፕሬዚደንቷ ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት አለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ከአፍሪካ ጋር በተያያዘ ስለሚነሱበት አከራካሪ ጉዳዮች ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ጋር ተነጋግረዋል፡፡

የሮም ስታቹት ፈራሚዎችና አባል አገሮች ስብጥር እንዴት ነው? አባል አገሮቹ ከመቶ ሀያ በላይ ናቸው፡፡ በአህጉር ደረጃ ካየነው አፍሪካ ብዙ አባል አገሮችን የያዘ አህጉር ነው፡፡ አውሮፓ እና ላቲን አሜሪካ አገሮችም በበቂ ሁኔታ አባል አገሮቸ አሏቸው፡፡ እስያ በተወሰነ መልኩ ሲሆን አሜሪካን አባልም ፈራሚም አይደለችም፡፡ አፍሪካ በአህጉር ደረጃ ብዙ አባሎች ያሉባት አህጉር ብትሆንም የአለምአቀፉ ፍርድቤት አፍሪካውያንን ለማጥመድ የተቋቋመ ነው ከማለትም አልፎ “አለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ከሚባል የአፍሪካ የወንጀለኞች ፍርድቤት” ቢባል ጥሩ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህ መነሻ የሚያደርጉት ደግሞ በፍርድ ሂደት ላይ ያሉት ወንጀሎች የአፍሪካውያን ብቻ መሆናቸውን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? እኔ በፕሬዚደንትነት የምመራው “አሴምብሊኦፍ ስቴት ፓርቲስ” በፍርድ ቤቱ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ፍርድቤቱ ነፃ እና ገለልተኛ አካል ነው፡፡ ነገር ግን እንደፕሬዚዳንትነቴ እና በግል እምነቴ የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የመጨረሻ ነው ማለት አይደለም፡፡

ጉዳዮች ወደ ፍርድቤቱ የሚመጡት በአገር ውስጥ ያሉ የፍትህ ተቋሞች ተፈፀሙ ለሚባሉ ወንጀሎች ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀሩ ነው። ዩጋንዳ፣ ማሊ፣ ሴንትራል አፍሪካ እና ኮትዲቯር ተጠያቂ መሆን አለባቸው የሚባሉ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለፍርድቤቱ እንዲታይ ያቀረቡት ራሳቸው አገራቱ ናቸው፡፡ ጉዳዮች በአለምአቀፉ ፍርድቤት እንዲመረመሩ ከአፍሪካ የሚመጡ ጥያቄዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በጥያቄውም መሰረት ይስተናገዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዚህ ላይ በዋነኛነት መታየት ያለበት አፍሪካ ላይ አተኮረ የሚለው ሳይሆን ተከሳሾች ባሉበት አካባቢ የተጎዱ አሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ዩጋንዳ ውስጥ በሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ ምክንያት የብዙዎች ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። አሁንም በፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው የቀረበውና እስከአሁን ያልተያዙት የሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ መሪ ጆሴፍ ኮኒ እና ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቢታይ በተለይ የጥቃቱ ሰለባ ለሆነው ህዝብ እፎይታን ይሰጣል፡፡ በቅርቡ የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ፤ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ላይ ባደረጉት ንግግር ፣“ሄግ የሚገኘው አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በአንዳንድ ወገኖች የተሰራ ወንጀልን የሚያወግዝ ፣የአንዳንዶችን ደግሞ እንዳላየ የሚያልፍ ነው” በሚል አፍሪካውያን አለምአቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዳይተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህን ጥሪ እንዴት ያዩታል? አለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ሁሉንም በእኩል አይን የሚያይ ነው፡፡ ሁሉንም ተፈፅመዋል የሚባሉ ወንጀሎችንም ይዳኛል ማለት አይደለም። ቅድም እንዳልኩት ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ተፈፅሟል ለሚባል ወንጀል በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ያሉ የፍትህ ተቋሞች ናቸው ምላሽ መስጠት የሚችሉት፡፡ ካጋሜ ይህን ንግግር እስከተናገሩበት ቀን ድረስ፣ ሩዋንዳ በአለምአቀፉ ፍርድ ቤት አሰራር ሙሉ በሙሉ ደስተኛ አለመሆኗን አላውቅም ነበር፡፡ አሁንም ደግሜ የምናገረው ግን የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ለማንኛውም ወገን የማያዳላ ሁሉን አቀፍ ተቋም ነው፡፡ የቀድሞው የብሪታኒያ የውጪጉዳይ ሀላፊ ሮቢን ኩክ ደግሞ “የአለምአቀፉ ፍርድቤት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ወይም የአሜሪካን ፕሬዚደንቶችን ለመዳኘት የተቋቋመ ፍርድ ቤት አይደለም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ስለዚህ አስተያየትስ ምን ይላሉ ?

የአለምአቀፉ ፍርድ ቤት የመጨረሻ አይደለም። አገሮች የፍትህ ስርአታቸውን አጠናክረው የውስጥ ጉዳያቸውን በራሳቸው መጨረስ ከቻሉ፣ ወደ አለምአቀፉ ፍርድ ቤቱ የሚያመጣ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ባለፈው አመት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ማላዊ ከአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸውን የሱዳኑን ፕሬዚደንት አልበሽርን አልቀበልም በማለቷ የህብረቱ ጉባኤ አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በ2009 ዓ.ም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማም፤ አልበሽር በበአለ ሲመታቸው ላይ እንዳይገኙ አድርገዋል፡፡ ዛምቢያም አልበሽር ወደ አገሯ እንዳይመጡ በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች፡፡ በተቃራኒው የአፍሪካ ህብረት አባለ አገሮች የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት እንዳይተባበሩ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡

ይህን ሁለት ጫፍ የያዘ አቋም እንዴት ያዩታል?

የአፍሪካ ህብረት፣ በአባል አገሮች የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የህብረቱ አገሮች የሮም ስታቹት ፈራሚዎች ናቸው፡፡ ህብረቱ አባል አገሮቹ ከፍርድቤቱ ጋር እንዳይተባበሩ ጥሪ ያቀረበው በፕሬዚደንቶች ላይ የተላለፈውን የእስር ማዘዣ ተከትሎ ነው፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ፖለቲካ እና የህግ ጉዳይ ስለሆነ ማስታረቁ ቀላል አይሆንም።

የተጠቀሱት አገሮች ፈራሚዎች በመሆናቸው ለውሳኔው ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡ አባል ያልሆኑ አገሮች ግን እንዲተባበሩ ጥሪ ይቀርብላቸዋል እንጂ አይገደዱም፡፡ በፍርድቤቱ ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች በምሳሌ የሚያነሱት የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚደንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ኢራቅ ላይ ለተፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎቸ ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ለምን አፍሪካ ላይ ብቻ ያተኩራል የሚል ነው፡፡ አፍሪካን አስመልክቶ የሚነሳው ጉዳይ ሁልጊዜም ጥያቄ ያስነሳል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩት አራት የአፍሪካ አገሮች ራሳቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው ያሏቸውን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ለፍርድቤቱ አቅርበዋል፡፡ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ባለው ግንኙነት ላይም ትልቅ ጉዳይ ሆኖ የተነሳው የአልበሽር እና አሁን በህይወት የሌሉት የጋዳፊ ጉዳይ ነበር፡፡ የሁለቱ መሪዎች ጉዳይ በፍርድቤቱ እንዲታይ ውሳኔ የተሰጠው ደግሞ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ነው፡፡ በጥያቄው ላይ የተነሳው የኢራቅ እና የአሜሪካን ጉዳይ ከዚህ ጋር አይያያዝም። ሁለቱም የሮም ስታቹት አባል አገሮች አይደሉም፡፡ አሁን ሶሪያ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን የፀጥታው ምክር ቤት የፖለቲካ ተቋም ነው፡፡

የአባል አገሮቹ ፖለቲካ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት እስከአሁን ውሳኔ አላገኘም፡፡ በ2008 የተካሄደውን የኬኒያ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ ለነበረው ግጭት እጃቸው አለበት በሚል የአለምአቀፉ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረተባቸው ኡሁሩ ኬኒያታ፣ በቅርቡ የአገሪቱ ፕሬዚደንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡ የእሳቸው ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ የአለምአቀፉ ፍርድቤት ከአፍሪካውያን ላይ እጁን እንዲያነሳ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑን የሚገልፁ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ? በፍፁም አልስማማም፡፡ የኬኒያ ህዝብ ይመራኛል የሚለውን የመምረጥ መብት አለው። ይህንን ውሳኔ መቃወም አንችልም፡፡ ነገር ግን ፕሬዚደንት አሁሩ ኬኒያታ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በወቅቱ ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል። ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት መዳኘት አለበት፡፡ ፕሬዚደንት መሆናቸው የሚለውጠው ነገር አይኖርም፡፡ እሳቸውም ከፍርድቤቱ ጋር እተባበራለሁ ብለዋል፡፡ ቃላቸውን እንደሚያከብሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኡሁሩ ኬኒያታ በአለምአቀፉ ፍርድ ቤት መከሰሳቸው በምርጫው አሸናፊ እንዲሆኑ አስተዋፅኦ አድርጓል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህን አስተያየት ይቀበሉታል?

የአሁሩ በፍርድቤቱ የመከሰስ ጉዳይ ለምርጫ ፍጆታ ውሎ እንደነበር ሰምቼያለሁ፡፡ አዲስ አበባ ስለመጡበት ጉዳይ ይግለፁልኝ---- በአባል አገራት ውስጥ ባሉት ተቋማት ዙርያ ለመወያየት በተለያዩ ጊዜያት የስራ ጉብኝት አድርጌያለሁ፡፡ ይህ አንዱ የጉብኝት አካል ነው፡፡ በቆይታዬ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ዲላሚኒ ዙማን አግኝቼ ተወያይቼያለሁ፡፡ ከሌሎች ኮሚሽነሮች እና ተወካዮች ጋር በየአገሩ ያሉ የፍትህ ተቋማት በሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይ ተነጋግሬያለሁ፡፡ በተለይ በአፍሪካ ህብረት እና በአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ግንኙነት ዙርያ ተወያይቼያለሁ፡፡ በሁለቱ መሀል ያለው ግንኙነት ረጋ ባለ የመግባባት መንፈስ መካሄድ እንዳለበት ሀሳቤን አጋርቻለሁ፡፡

Read 4015 times