Saturday, 04 May 2013 11:25

“…የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁማ! ያው ‘ኔትወርክ’ እንደተለመደው በበዓል ሰሞን እንደልብ ስለማይሠራ ‘መልካም የትንሳኤ በዓል’ የሚል ‘ቴክስ ሜሴጅ’ ለሁሉም መላኬ ይመዝገብልኝማ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንዴ ሳስበው ይሄ ‘ኔትወርክ’ የሚባል ነገር ልክ የሰው ባህሪይ ይዞ የሚያሾፍብን ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ… አጠገብ ለአጠገብ ቆማችሁ ስትደዋወሉ… “ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” ምናምን የሚል ነገር ስትሰሙ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ ነው…ወይስ ይሄ እንደ አንዳንድ ከማዳን ይልቅ በሽታ ያብሳሉ እንደሚባሉት ከውጪ የሚመጡ መድሀኒቶች ለእኛ የሚለቀቀው ቴክኖሎጂ ‘ከማዳን የሚያብስ ነው!’ ልክ ነዋ…ቴክኖሎጂ እንዲህ በተራቀቀበት ዘመን ጎን ለጎን ሆነን እንኳን “…ማግኘት አይችሉም…” ነገር ስንባል…አለ አይደል… የሰዉ አንሶን ቴክኖሎጂም ያሹፍብን ብንል አይበዛብንም! “ኸረ እባክሽ አንቺ ሴትዮ ጎን ለጎን ነው የቆመነው!” ምናምን ለማለት አስቸጋሪ ሆነብንና…አለ አይደል… እንዲሁ ‘የገበጣ ጠጠር’ ሆነን ቀረን፡፡

በቃ…የገበጣ ጠጠር ባንከባለሉት በኩል መንከባለል ነው እንጂ ‘ኮምፕሌይንት’ ‘ፔቲሽን’ ቅብጥርስዮ ምናምን ነገር የለማ! እናላችሁ… አጠገብ ለአጠገብ ሆነን እንኳን “የደወሉላቸውን ማግኘት አይችሉም…” አይነት ነገር እነዚህ አፍ፣ ጆሮዎችና ዓይኖቻቸውን እንደሸፈኑት ጦጣዎች ምስል እየሆንን ነው፡፡ የምንናገረው ነገር እንደየሰዉ አተረጓጎም ሆኖ ‘የተደወለላቸው አልገኝ’ እያሉ ችግር እየሆነ ነው፡፡ “…የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” በሁሉም ነገር እያየነው ነው፡፡ ለምሳሌ “አበበ በሶ በላ…” አለ አይደል…በቃ ጣጣ የለውም፣ “አበበ በሶ በላ…” ማለት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን እያንዳንዳችን የየራሳችንን መዝገበ ቃላት ፈጠርንና ግንኙነታችን ሁሉ ‘የባቤል ግንብ’ ታሪክ አይነት እየሆነ ነው፡፡ የምር… ለምሳሌ አንዱ የእኔ ቢጤ “አበበ በሶ በላ…” የሚለውን የዓረፍተ ነገር አወቃቀር መማሪያ…“አበበ ካልጠፋ ምግብ ለምን በሶ እንዲበላ ተደረገ?” የሚል ሙግት ሊጀምር ይችላል፡፡ “ኧረ እባክህ ይሄ የአረፍተ ነገር አሰካክ መማሪያ እንጂ…” ብላችሁ ሳትጨርሱ “የፈለገ ዓረፍተ ነገር አሰካክ መማሪያ ቢሆንስ! ለምንድንው በሶ የሚሰጡት! ለምን አበበ ብርንዶ በላ አይባልም?” ብሎ አፍ አፋችሁን ሊላችሁ ይችላል፡፡ ደግሞላችሁ… “ጨቡዴ ጩቤ ጨበጠ…” በቃ ጨቡዴ ጩቤ ጨበጠ ማለት ነው — የአረፍተ ነገር አሰካክ መማሪያ፡፡

ዘንድሮ ግን የጨቡዴ ጩቤ መጨበጥ እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ልክ ነዋ…“ካልጠፋ ነገር አበበ በሶ እየበላ፣ ጨቡዴን ጩቤ ማስጨበጥ ጨቡዴ ማፊያ ነው ለማለት ነው!” ምናምን የሚሉት አይነት ‘የደወሉላቸውን’ ሰው የማጣት ነገር አለላችሁ፡፡ ስብሰባ ተቀምጠን (‘ተኝተን’ ላለማለት ነው) የሚያበቃበት ሰዓት እንደ ‘ሚሊኒየሙ ግብ’ ርቆብን እያለ…አለ አይደል… ሰብሳቢው ምን ይላል መሰላችሁ…“በእውነቱ የተካፋዮች ንቃት የሚያስደስት ነው…” ኧረ በህግ አምላክ! (በነገራችን ላይ “በህግ አምላክ” ማለት ትልቅ የመብት ማስከበሪያ የነበረበት ዘመን እዚቹ እኛ አገር ውስጥ ነበር፡፡ የእውነት!) እናላችሁ… እኛ ጠቅላላ ‘ቫሊየም ፋይቭ’ እንደዋጠ ሰው እያንጎላጀጀን እያየ፣ ስለ ‘ንቃታችን’ ሲያወራ…አለ አይደል… አጠገብ ለአጠገብ ሆነን ‘የደወልንላቸውን ሰዎች’ ማግኘት እያቃተን ነው፡፡ ስብሰባ ላይ ከማንጎላጀጅ የባሰ ምን አይነት መደወል ይኖራል፡፡

ይቺን ስሙኝማ…በኮሚኒስት ሩስያ የኬጂቢ ጆሮ ጠቢ የሆነ ሰው ወደ አለቆቹ ይሄድና “ጎረቤቶቼ ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነት አላቸው ብዬ እጠረጥራለሁ” ሲል ሪፖርት ያቀርባል፡፡ አለቃውም “በምን አወቅህ?” ሲል ይጠይቀዋል። ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “በየቀኑ እራታቸውን ይበላሉዋ!” እኔ የምለው…ካነሳነው አይቀር፣ የኮንዶሚኒየም ነዋሪ ወዳጆቼ እንደሚነግሩኝ ከሆነ…“በየቀኑ እራታቸውን ይበላሉዋ!” አይነት ‘ጆሮ በግድግዳ’ ነገር በሽ፣ በሽ ነው አሉ፡፡ እኔ የምለው… ከአኗኗር ጋር እኮ መለወጥ ያለባቸው አንዳንድ ባህሪያት አሉ አይደል እንዴ! የአፓርትማ ኑሮ እኮ… (ኮንዶሚኒየም ማለትም ያው አፓርትማ ማለት ነው…) የ‘ፕራይቬሲ’ ኑሮ ነው፡፡ (ስሙኝማ…ግድግዳ ላይ የተለጠፈ ጆሮ እንዳይሰማን ንግግራችንን በጽሁፍ መለዋወጥ እንችላለን፡፡ ይቺ ቁና፣ ቁና ትንፋሿስ! በቃላት አትጻፍ ነገር! ቂ…ቂ…ቂ… ጥያቄ አለን፣ ቀጥለው በሚሠሩ ኮንዶሚኒየሞች ‘ሳውንድ ፕሩፍ ቤድሩም’ ይሠራልን!) እናላችሁ…ምን ያደርጋል አንዳንድ ነገር…አለ አይደል… ሳያቀስ እንደማይለቀው ያዳቆነ ‘ሉሲፈር’ ነክሶ ይይዝና አይለቅም፡፡

እናላችሁ… ከሳፋና ከድስታችን ጋር የሰፈር አዋዋል ያልተጻፉ ‘ፕሪንሲፕሎቻችንም’ ተከትለውን ፎቅ ላይ ይወጣሉ፡፡ ልክ ነዋ…ቅድመ-ኮንዶሚኒየም እኮ… አለ አይደል… ላይ ሰፈር ያለነው ታች ሰፈር ስላለችው እንትናዬ “ምን አግኝታ ነው ዛሬ እንዲህ ያማረባት!” አይነት ነገር እንላለን፡፡ ታች ሰፈር ያሉት እነእንትና ደግሞ ላይ ሰፈር ያለነውን … “ትናንት ሥጋ ወጥ ሲሸተን ነበር፣ ዛሬ ደግሞ ቋንጣ ፍርፍር…ይሄ ሁሉ ሥጋ ከየት እየመጣ ነው!” ሊሉን ይችላሉ። እናላችሁ…ይሄ ይሄ ተከትሎን ፎቅ ላይ እየወጣ ችግር እየሆነብን ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የኮንዶሚኒየም ነገር ካነሳን አይቀር አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን ስሙኝማ… (ወዳጄ፣ ባለማስፈቀዴ ሂሴን ውጫለሁ…)…እሱና እሷ ኮንዶሚኒየም ሦስተኛ ፎቅ ላይ ይኖራሉ፡፡ እናላችሁ… አየሩ ፀሀያማ ከሆነ መስኮቱን ከፍተው ወደየሥራቸውና ወደየጉዳያቸው ይሄዳሉ፡፡ ታዲያላችሁ… ቴሌቪዥኑ የተቀመጠው መስኮቱ አጠገብ ነው፡፡ አንድ ቀን ታዲያ እነሱ በሌሉበት ዝናብ ይመጣና ወጨፎው ቴሌቪዥኑን ያረጥበዋል፡፡

ሰውየው ተናዶ… “ለምንድነው መስኮቱን ሳትዘጊው የሄድሽው!” ምናምን ብሎ ይጮህባታል፡፡ እሷም ምን ብትል ጥሩ ነው… “እኔ ምን ላድርግ፣ ሬዲዮ ነው ያሳሳተኝ!” ትላለች፡፡ ለምን መሰላችሁ… ለካስ ጠዋት የአየር ጠባይ ትንበያው ላይ “ዛሬ አዲስ አበባ ከፊል ደመናማ ሆና ትውላለች…” ተብሎ ነበር። አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… ቢያንስ በአየር ጠባይ ትንበያ መሠረት የሚንቀሳቀስ ሰው መኖሩን ማወቅም አሪፍ ነው፡፡ እናላችሁ…ዘንድሮ “…የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” ነገር በየቦታው ያልተጻፈ መመሪያ አይነት ነገር ሆኖላችኋል፡፡ ስሙኝማ…ጋብሮቮዎች ሁለት ጊዜ ያልባቸዋል ይባላል፡፡ አንድ ጊዜ ፀሀይ ሲበዛባቸውና ሌላ ጊዜ ደግሞ ገበያ ሄደው ዋጋ ሲከራከሩ፡፡ እኛ አለን እንጂ… ‘እንትን በሚያሳቅፈው’ ብርድ ሁለት መቶ ሁለት ጊዜ የሚያልበን! ለምን አትሉኝም… በየሄድንበት ‘የደወልንላቸውን ማግኘት’ እያቃተን! ለክፉም ለደጉም በዚህ በበዓል ሰሞን የደወልንላቸውን እንዳናገኝ የሚደነቀሩ ደንቃራዎችን አንድዬ ከመንገዳችን ላይ ዘወር ያድርግልንማ! ስሙኝማ…በዛ ሰሞን በበሬ ሥጋ ውስጥ የፈረስ ሥጋ እየቀላቀሉ ሸጡ ምናምን ተብሎ አውሮፓ ታምሶ ነበር፡፡ ለነገሩ ግርግሩ ለምን ቀላቀሉብን ነው እንጂ ፈረሱንም፣ በሬውንም ስልቅጥ አድርገው ነው የሚበሉት፡፡

(እኔ የምለው…እነሱ እኮ የምግብ እጥረት የማይገጥማቸው…አለ አይደል… በመሬት የሚሄደውም፣ በሰማይ የሚበረውም፣ በባህር የሚዋኘውም አንዱም ሳይቀራቸው “እነሆ በረከት” ስለሚሉ ነው! አሀ.. እኛ ‘ቋቅ’ ሲለንስ! አይደለም… የምድር ላይ ተሳቢ ምናምን ‘አውሬ’ ሥጋ፣ አሁንም እኮ ፓስታ ‘ቋቅ’ የሚላቸው የገጠር ሰዎች መአት ናቸው!) እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ይቺን ስሙኝማ…የፈረንጁ ልኳንዳ ነጋዴ የፈረስ ሥጋ ከሌላ ሥጋ ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ ተገኘና ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ዳኛው “ህዝቡ ሳያውቅ የፈረስ ሥጋ በመሸጥ ተከሰሃል፣ ምን መልስ አለህ?” ይሉታል፡፡ እሱ ሆዬም ምን ይላል…“ክቡር ዳኛ፣ ለነገሩ የፈረስ ሥጋ ብቻ አይደለም የሸጥኩት፡፡ ግማሽ የፈረስ ሥጋና ግማሽ የጥንቸል ሥጋ እየቀላቀልኩ ነው የሸጥኩት፡፡” ዳኛውም… “ጥሩ፣ ለመሆኑ ለአንድ ፈረስ ስንት ጥንቸል ቀላቀልክ?” ሲሉት እሱ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ክቡር ዳኛ፤ ግማሸ ለግማሽ አልኩ እኮ፣ ማለት አንድ ፈረስ ለአንድ ጥንቸል፡፡” አሪፍ አይደል! ስሙኝማ… ለነገሩ ጊዜያችን የማይታሰቡ ነገሮች ሁሉ የሚሠሩበት ስለሆነ የምትሸምቱትን ሥጋ በደንብ እያያችሁ ግዙማ! ሁሉም ነገር በልክ ቢሆን አሪፍ ነው፡፡ የሁሉንም ነገሮች ‘ትንሳኤ’ ያፋጥንልንማ! መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6884 times