Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 November 2011 08:04

ሁለት ጉድጓድ ያለው አይጥ አይሞትም (ሁዌት ጐጆ ያነን ፉር ኤሞት) - የጉራጊኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በሰሜን ነፋስና በፀሐይ መካከል ጠብ ይፈጠራል፡፡ 
የሰሜን ነፋስ፡- “ፀሐይ ሆይ! በከንቱ አትድከሚ፡፡ በጉልበት ከእኔ የሚበልጥ ማንም የለም” ይላታል፡፡
ፀሐይም፡- “በተግባር እንፈታተሽ እንጂ በአፍ በማውራትማ ማንም ኃያል ነኝ ማለት ይችላል” ብላ መለሰችለት፡፡
የሰሜን ነፋስ፡- “በፈለግሺው ዓይነት መንገድ እንጋጠም ጉልበቴን አሳይሻለሁ” ይላል፡፡
ፀሐይ፡- “እንግዲያው ከእዚያ ወደዚህ የሚመጣው ሰውዬ ላይ ኃይላችንን እንፈትሽ፡፡ እንደምታየው ትልቅ ካፖርት ለብሷል፡፡ ከሁለታችን ጉልበት ያለው ካፖርቱን ያስወልቀው” ብሏል፡፡
የሰሜን ነፋስ፡- “መጀመሪያ የእኔ ተራ ይሁን” ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ በፉክክሩ ተስማሙ፡፡

የሰሜን ነፋስ ኃይለኛ አውሎ ንፋሱን ለቀቀው፡፡ ሰውዬውን ከግራ ወደ ቀኝ ያላትመው ጀመር፡፡ የካፖርቱን ዚፕ አጥብቆ ዘጋ፡፡ ቁልፎቹን ቆለፈ፡፡ በተቻለው ሁሉ ካፖርቱ ከላዩ ላይ እንዳይወልቅ ተከላከለ፡፡ የሰሜን ንፋስ ምንም ለማድረግ አልቻለም፡፡ 
ቀጥሎ የፀሐይ ተራ ሆነ፡፡
ፀሐይ በመጀመሪያ ቀስ ብላ ሰውዬውን አሞቀችው፡፡ ሰውዬው ዚፑን ከፈተ፡፡ ቁልፎቹን አንድ በአንድ መፍታት ጀመረ፡፡ ፀሐይ ሙቀቷን እያበረታች መጣች፡፡ ሰውዬው ካፖርቱን አወለቀና ትከሻው ላይ አደረገው፡፡ የፀሐይ ሙቀት አልቀነሰም፡፡ እንዲያውም የመጨረሻውን ፍላት ሙቀት ለቀቀችበት፡፡ ሰውዬው ካፖርቱን መያዝ እንኳን ከማይችልበት ደረጃ ደረሰ፡፡ በጣም ወበቁ ሲብስበት ካፖርቱን ወረወረው፡፡
ቀጥሎ ኮቱንም አወለቀው፡፡
በላብ የሾቀውን ሸሚዙንም አውልቆ ለመወርወር ተገደደ፡፡ ካኒተራውንም አውጥቶ ጣለ፡፡ በመጨረሻም ራቁቱን ቀረ፡፡ እንዲህ አድርጋ ፀሐይ የሰሜን ነፋስን ድል መታችው፡፡
* * *
በጉልበት ከመመካት ብልሃት ማወቅ ምንጊዜም የተሻለ መንገድ ነው፡፡ ከመደንፋትና ከመፎከር በውይይትና በምክክር ችግርን መፍታት ተመራጭ መንገድ ነው፡፡ በከንቱ ኃይልን ከማባከን፣ አቅምን ከመፈረካከስ በጥበብና በመላ ውጥረትን መቀነስ ወደ መፍትሔ ያደርሳል፡፡ ቀስ በቀስ ለውጥን ማምጣት እንጂ በአንድ ጀንበር ዘመቻ ሁሉን ካልቀየርኩ ብሎ ዘራፍ ማለት ከሌላ ብቻ ሳይሆን ከራስም ጋር ያጋጫል፡፡ ግሥላ ራሱን የሚያጠፋው ሁሉን በጉልበት እጨብጣለሁ ብሎ ሲገሥል ነው!
ሐይቲያውያን የሚተርቱት ተረት ከላይ የዘረዘርነውን ይሰበስብልናል፡- ወንዙን አቋርጠህ ሳትጨርስ እናትየዋን አዞ አትሳደብ፡፡
በሥራቸው አጋጣሚ፣ በፖለቲካ ሰበብ ወይም ይሆነኝ ተብሎ በተፈጠረ ሌላ ሁኔታ፤ ሲያዩዋቸው ባላንጣ የሚመስሉ ወገኖች የተወዳጁ ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን አገራዊ ጥፋት መገመት አያዳግትም፡፡
ፐርሺያውያን ገጣሚያን
“አይጥና ድመት የተስማሙ ለታ
አለቀላት ሱቁ ፍታቱ ተፈታ”
የሚል ግጥም ገጥመዋል፡፡ ሙሰኛና ቢሮክራት የተቆራኙ ቀን ካዝናው ወዮለት እንደማለት ነው፡፡ አገራችን ታልባ የማታበቃ ጥገት ሆና ከድህነት ትላቀቃለች ብሎ ማሰብ ቢያንስ ጅልነት ነው፡፡ ከድህነት መላቀቅ አንዱ ዓይነተኛ ገፅታው የሌባን እጅ ማሳጠር ነው፡፡ ሌብነት የሚበረታው ግርግር ሲበዛ ነው፡፡ ሌብነት የሚሸፈነው አፈና ሲበዛ ነው፡፡ ፈረንጆች They shout at most against the vices they themselves are guilty of. ይላሉ፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” እንደማለት ነው፡፡
ሥፋት ያላቸውን ህጎች አውጣ እንጂ ጠባብ ጥቅሞች ላይ አታተኩር፡፡ የሚለውን የብልሆች ምክር ማዳመጥ አገርንም ህዝብንም ለማሳደግ ይጠቅማል፡፡ ጥቃቅን ጥቅሞች ላይ ማተኮር ትልቁን ስዕል እንዳናይ ዐይናችንን ይጋርደናል፡፡ ትልቁ ስዕል ከኢፍትሐዊነት የፀዳ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ትልቁ ስዕል የለበጣ ወይም በቅድመ-ሁኔታዎች የታጠረ ሳይሆን ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ትልቁ ስዕል አርቆ-አስተዋይ ትውልድ ለመፍጠር መትጋት ነው፡፡ ትልቁ ስዕል የእከክልኝ-ልከክልህ አካሄድን ማስወገድ ነው፡፡
ሰው መሳደብ የሚጀምረው ጥበብ ሲያልቅበት ነው ይላሉ አበው፡፡ ትክክለኛ ሂስ ማቅረብ ከዘለፋና ከስድብ ጋር ከቶም አይገናኝም፡፡ ከማግባባት ይልቅ ማስፈራራትም ሀራምባና ቆቦ ናቸው፡፡ ሀገርን የማዳንም ሆነ የማሳደግ ተልዕኮ ያለው ዜጋ ሆደ-ሠፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዕድሜና ተመክሮ ሊያበስለን ይገባል፡፡ ባንዱ ሰበብ ሌላውን ማጥቃት በምንም መለኪያ አግባብነት አይኖረውም፡፡ “ሚስቱን ፈርቶ ደበሎዋን ደበደበ” እንደተባለው ይሆናል፡፡
ሁኔታዎችን እንዳመጣጣቸው መመለስ ተገቢ ቢሆንም ከሚዛናዊነትና ከመቻቻል ውጪ አይደለም፡፡ አንዲትን ቅፅበት መታገሥ አቅቶን ዘላለማዊ የሀገር ስህተት ልንፈፅም እንችላለን፡፡ ፀፀቱ የሀገርም፣ የህዝብም ነው፡፡
“ቀሪውን ዕድሜህን ሙት ከመሆን ለደቂቃ “ፈሪ” መሆን ይሻላል” እንደሚሉም እናስታውስ፡፡ ትክክለኛ ማፈግፈግ ከማጥቃት አንድ ነው የሚሉ ስትራቴጂስቶች እንዳሉም አንርሳ፡፡ ግትርነት ያለጊዜና ቦታ ከንቱ መታበይ ነው፡፡ ካፈርኩ አይመልሰኝ ማለትም ግብዝነት ነው፡፡ ለሀገር ሲባል ብርቱ መስዋዕትነት መክፈል ተገቢ የሚሆነውን ያህል ለሀገር ሲባል “ከእኔ ይቅር” ማለትም የመስዋዕትነቱ አካል ነው፡፡
ከትላንት የተሻለ ዛሬ እንዲኖረን እንትጋ፡፡ ለዚህ ወሳኙ ነገን ጨለማ አድርጎ አለማየት ነው፡፡ በትላንት ችካል አለመቸከል ነው፡፡ የማንመልሰውን ለይተን ማወቅ ነው፡፡
ጃፓኖች “ግልባጩም ሌላ ግልባጭ አለው” የሚሉት ተረት አላቸው፡፡ አንድ ዓይነት ለውጥ ብቻ አናስብ፡፡ አማራጮችን እንይ፡፡ “ኩሉ አመክሩ ወዘሠናየ አፅንዑ” ይለናል ግዕዙ፡፡ ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን አፅኑ እንደ ማለት ነው፡፡ ምንጊዜውም አማራጭ ለማየት ልባችን ብሩህ፣ ዐይናችን ክፍት ይሁን፡፡ ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል የሚለውም አብሮ ይሄዳል፡፡ ሁለት ጉድጓድ ያለው አይጥ አይሞትም የሚለው የጉራጊኛ ተረትም ዞሮ ዞሮ አማራጭ ያለው ወድቆ አይወድቅም የሚለውን ቁም ነገር ነው የሚያስገነዝበን፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን ማለት ያባት ነው!

 

Read 5404 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:07