Saturday, 04 May 2013 13:48

ባቡሩ ሲመጣ

Written by  ፊያሜታ
Rate this item
(2 votes)

አይነ ስውሩ ለማኝ የሰሙትን ነገር ለማመን ቸግሯቸዋል፡፡ በቀኝ መዳፋቸው የያዟቸውን ሳንቲሞች በቀስታ እያሻሹ ጥቂት ሲያስቡ ቆይተው፣ ከበስተቀኛቸው ቁጭ ወዳሉት ወደ እማማ እቴናት ዘወር አሉ፡፡ “የማነው ስሙ …የጌትዬ ሱቅስ?” በጉጉት ተውጠው ጠየቁ፡፡ “የእሱም ፈርሷል” እማማ እቴናት ከፊታቸው የዘረጉትን የነተበ የምጽዋት ምንጣፍ እያስተካከሉ መልስ ሰጡ፡፡ “ተውራየል ግርጌ ያለው…የዚያች የጐንደሬይቱ ውቴልስ?” ቀጠሉ ሰውዬው፡፡ “ኤዲያ!.. ‘ተላይ እስተታች አፍርሰውታል’ እያልሁዎት አይሰሙኝም እንዴ?” በተሰላቸ ድምጽ መለሱላቸው፡፡ አይነ ስውሩ በሀዘኔታ አናታቸውን እያወዛወዙ በሃሳብ ተዋጡ፡፡ ስጋት ገብቷቸዋል፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ “እንዲያው ግን…ምን ይሁን ብለው ነው አሉ አንቺዬ?” አይነስውሩ አገጫቸውን ሽቅብ ሰቅለው ጠየቁ። እማማ እቴናት በአይነስውሩ ጥያቄ በመሰላቸት፣ በረጅሙ ተንፍሰው ፊታቸውን ወደ ባምቢስ አቅጣጫ አዞሩ፡፡

“ሰማሽ ወይ?” ሰውዬው በጥርጣሬ ወደ እማማ እቴናት ዞረው ጠየቁ፡፡ “ሴትዬዋ መልስ አልሰጡም፡፡ ከኡራኤል አቅጣጫ የሚመጡ ጋቢ የለበሱ አዛውንት የተመለከቱና ጉሮሮዋቸውን አጽድተው መለመን ቀጠሉ፡፡ “ስለአዛኝቷ…ስለ ኪዳነ ምህረት…” አሉ በሚያሳዝን ዜማ፡፡ አዛውንቱ ኪሳቸውን ፈትሸው ያገኟቸውን ዝርዝር ሳንቲሞች የእማማ እቴናት ጨርቅ ላይ ጣል አድርገው አለፉ፡፡ “ኪዳነምህረት ትስጥልኝ… የነፍስ ዋጋ ያርግልኝ!” ዜማ ቀይረው መመረቅ ጀመሩ - እማማ እቴናት፡፡ አይነስውሩ የባልቴቷን ምርቃት ለማስጨረስ የሚሆን ትዕግስት አልነበራቸውም፡፡ “እኔ እምልሽ…ምን ይሁን ብለው አሉ…እንዲህ አገር ምድሩን ያፈራረሱት?” ጣልቃ ገብተው ጠየቁ፡፡ “ባቡር ሊተክሉ ነው አሉ!” ሲሉ መለሱ እማማ እቴናት፤ ጨርቁ ላይ የተዘሩትን ሳንቲሞች በአይናቸው እየደመሩ፡፡ “ኧረ አንዳች ውጋት ይትከልባቸው!” ቆጣ ብለው ተናገሩ አይነ ስውሩ፡፡ እማማ እቴናት በሰውዬው ንግግር በድንጋጤ ክው ብለው በስጋት ዙሪያቸውን ተገላምጠው ተመለከቱ፡፡ አለፍ ብለው ታክሲ እየጠበቁ ከቆሙት ሰዎች በስተቀር፣ የአይነስውሩን ንግግር ሊሰማ የሚችል ሰው በዙሪያቸው አለመኖሩን ሲያረጋግጡ ስጋቱ ቀለል አለላቸው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የአይነ ስውሩን አጉል ንግግር ዝም ብለው ማለፍ አልፈለጉም፡፡ “እስዎ ሰውዬ…ይሄን አጉል ንግግር ቢተው መልካም ነው፡፡ ምን ባረጉ ነው እሚረገሙ? አገር ላልማ ባሉ አጉል መናገር ምንድነው? …” ብለው ጀመሩ፡፡ አይነስውሩ በቁጣ ቱግ ብለው አቋረጧቸው፡፡ “ኤዲያ!...አንቺ ደሞ እምኑ ላይ ነው ንግግሬ አጉል እሚሆነው?...” ሳንቲሞቻቸውን ወደ ኮት ኪሳቸው እየጨመሩ ኮስተር ብለው ተናገሩ፡፡ እማማ እቴናት አለፍ ብሎ የቆመ የታክሲ ወያላ ዝርዝር ሳንቲም ፍለጋ ላይ መሆኑን አይተው በፍጥነት ከተቀመጡበት ተነሱ፡፡ በአይናቸው የደመሯቸውን ዝርዝር ሳንቲሞች ይዘው ሄደው፣ አራት ድፍን ብሮች ይዘው ሲመለሱ የአይነስውሩ ዝርዝር ወግ ጠበቃቸው፡፡ “ውነቴን እኮ ነው?...ምን እንዳይመጣ ነው?” አይነስውሩ ንግግራቸውን ገታ አድርገው የእማማ እቴናትን መልስ መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ “የሚመጣውንማ ያዩታል! ምን ማለትዎ ነው?…ልማት እኮ ነው! ስንቱ ባለሱቅ ሸቀጡን ሸካክፎ ያንን የመሳሰለውን ህንጣ “እሺ” ብሎ ያፈረሰው፣ የሚመጣበትን ቢያውቅ አይደለ እንዴ?” የባልቴቷ ንግግር በአይነስውሩ ድንገተኛ ሳቅ ተሸፈነ። “አይ አንቺ… ‘ተናት ትበልጥ ሞግዚት፣ ታንቃ ትሞት’” አሉ… ሳቃቸውን ገታ አድርገው፡፡

እማማ እቴናት በአይነስውሩ ሳቅ ክፉኛ ተበሳጩ። ከሳቁ ውስጥ እንደ ንቀትም፣ እንደ ሽሙጥም፣ እንደ ስላቅም የሚመስል ነገር ሰምተዋል። “ሰማሽ ወይ…እኔና አንቺ ተዚህ የባሰ ምን ይመጣብን ብለሽ ነው እንዲህ እምትባትቺው… እንጥፍጣፊ ሳቅ ፊታቸው ላይ ይታያል፡፡ …እንኳን እኛ፣ ስንቱ ባለጠጋ ከቦታው ተነስቶ የለ እንዴ?...ደሞስ “ለልማት ተሆነ…” ባልቴቷ መቀጠል አልቻሉም፡፡ አይነስውሩ በቁጣ ቱግ ብለው የተቀመጡበትን ቅዳጅ ካርቶን እየነካኩ ወደ ባልቴቷ ዘወር አሉ፡፡ “ያነዜማ ይለይልናል..በገዛ አገሬ “ለምነህ አትበላም” ተባልኩማ ጉድ ይፈላል” እንደ መፎከር አደረጋቸው፡፡ ባልቴቷ በተራቸው የአይነስውሩን የሚመስል እንደ ንቀትም፣ እንደሽሙጥም ያለ ሳቅ አመለጣቸው። “እንዴት?” የሰውዬው ንዴት ከመንግስት ወደ ባልቴቷ ዞረ፡፡ “ተናግሬያለሁ!…እነሱ እንደሆኑ በልማቱ ለመጣባቸው ፊት አይሰጡም…አጉል አጉል ሲናገሩ ጉድ እንዳያፈሉ” ከወያላው የተቀበሉትን ብር ወደ ከረጢታቸው እየከተቱ ተናገሩ፡፡ “በይሆት ይሆኑ እያለሁ ተዚች ቦታ የሚያስነሳኝ ሰው ተተገኘ እውነትም እናቱ ወልደዋለይ” ይኸው እሱ ይታዘበኝ… ወደ ኡራኤል ቤተክርስቲያን አቅጣጫ እየጠቆሙ በእልህ ተናገሩ፡፡ “ኧረ ይተው፣ እንደ አፍ አይቀናም” ባልቴቷ የከረጢታቸውን ሸምቀቆ አጠበቁ፡፡ አይነ ስውሩ የባልቴቷ ንግግር ንቀት እንዳለበት ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ጊዜ የፈጀባቸው፣ ምን ብለው መልስ እንደሚሰጡ ማሰቡ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ የሴትዬዋ ንቀት ደማቸውን አፍልቶታል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ “ደሜ ፈላ” ብሎ በግልፍተኝነት አጉል መልስ መስጠት የሴትዬዋን ውለታ ብቻ ሳይሆን፣ ንግግሩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋም መዘንጋት ይሆናል፡፡

አይነስውሩ የባልቴቷ ውለታ አለባቸው፡፡ ከዋናው አስፓልት ዳር የሚገኘው ይህ የተቀመጡበት ቦታ፣ ለእማማ እቴናት እንጂ ለሌላ “የኔ ቢጤ” የተከለከለ ነበር። እርግጥ ማን እንደከለከለ በውል አይታወቅም፡፡ እማማ እቴናት እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጦ ለመለመን የሞከረን የኔ ቢጤ፣ በግልምጫም በፍጥጫም ነዝንዘውና አስፈራርተው በማባረር ለረጅም ጊዜያት ቦታውን የራሳቸው ግዛት አድርገውት ኖረዋል፡፡ አንዳንድ የኔ ቢጤዎች “እሷ እኮ የመንግስት ጆሮ ጠቢ ናት” በማለት ያስወሩባቸዋል፡፡ እርግጥ ሃሜቱን የፈጠረው የራሳቸው የእማማ እቴናት ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደ ፖለቲከኛ ያረጋቸዋል፡፡ “እድሜ ለእነሱ…ይሄው ሰላም ውለን እንገባለን!!...አዳሜ አይንሽ በቅናት ይቅላ እንጂ እነሱ እንደሆኑ ማልማታቸውን አይተውም” ይላሉ፣ “እነሱ” እነማን መሆናቸውን ሳይገልፁ በደፈናው፡፡ እንዲህ ያለው “ልማታዊ” ንግግራቸው ነው፣ “ነገር አላቸው” ብሎ የሚያሳማቸውም፣ የሚያስፈራቸውም፡፡ አንድ ወቅት ግን አይነ ስውሩ ለማኝ ድንገት ከካንቺስ አቅጣጫ መጡና ከእማማ እቴናት ጋር ወግ ጀመሩ፡፡ እማማ እቴናት ስለ ልማቱ ያወሯቸውን በጐ በጐ ነገር ሁሉ እየተቀበሉ “ልክ ነሽ” ሲሏቸው ቆዩ፡፡ እንደዋዛ ከጐናቸው ቁጭ ብለው እያወሩ እግረ መንገዳቸውን ሲለምኑ ዋሉ። እማማ እቴናት አይነስውሩን ወደዷቸው፡፡ በነጋታውም እዚያው ቦታ ላይ እንዲለምኑ ፈቀዱላቸው፡፡ አይነስውሩ ይህን ውለታ አፍርሰው “ለምን ናቅሽኝ” ብለው ፀብ መግጠም አልፈለጉም፡፡ ከእማማ እቴናት ጋር መጋጨት፣ ከባቡሩ ጋር መጋጨት እንደሆነ ገብቷቸዋል፡፡ ከባቡሩ ጋር መጋጨት ደግሞ ከልማቱ ጋር መጋጨት ነው፡፡ አይነስውሩ በሃሳብ ተውጠው መተከዝ ጀመሩ፡፡

“እኔ እምልሽ እቴናት…?” አሉ አይነስውሩ በውስጣቸው ሲመላለስ ለቆየው ጥያቄ መልስ ባገኝ ብለው በማሰብ፡፡ “አቤት” እማማ እቴናት በሰለለ ድምጽ መለሱ፡፡ “ምን ይሁን ብለው ነው፣ ይኸን ሁሉ ቤት ያፈራረሱት አሉ?” “ዘነጉት እንዴት? ‘ባቡር ሊተክሉ ነው አሉ’ ብየዎትም አልነበር?” የተሰላቸ ምላሽ ሰጡ፡፡ “እ…እሱስ አልዘንግቼውም እንዲያው ብቻ…ላንድ ባቡር ይሄን ታህል አገር መፍረሱ ገርሞኝ ነው… እስተ ላይ ድረስ ነው አሉ ያፈራርሰውት” በመገረም መልሰው ጠየቁ፡፡ “እህሳ” አረጋገጡላቸው፡፡ አይነስውሩ ግራ በመጋባት ጥቂት ሲያስቡ ቆዩ። ዋናውን አስፓልት ተከትሎ ግራና ቀኝ የነበሩ በርካታ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች “ለባቡር ግንባታ” በሚል የመፍረሳቸው ነገር እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡ “ቆይ…አንድ ባቡር ለመትከል ይኸን ሁሉ ቤት ማፍረሳቸው ምን ባይ ነው?” በማለት ወደ እማማ እቴናት ጥያቄያቸውን ሰነዘሩ፡፡ “እኔ ምኑን አውቄ ብለው ነው” አሉ እማማ እቴናት ከበስተጀርባቸው ያሉትን ፍርስራሾች ዘወር ብለው እየተመለከቱ፡፡ “ደሞስ …እህል እንጅ ባቡር መች ቸገረን?…ያንድ የወንዳፍራሽ ባቡር አይደለ እንዴት፣ ይህን ያህል ዘበን የውራየልንና የካዛንቺስን ህዝብ ቀጥ አርጐ ያኖረው?” አይነስውሩ በመገረም ተናገሩ፡፡ እማማ እቴናት የአይነስውሩን አባባል ከፀረ -ልማት ትችት ቆጥረው ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ሲዘጋጁ ቆይተው፣ ድንገት በሳቅ ፍርስ አሉ፡፡ “እንዴት?” የድንገተኛው ሳቅ ሰበብ ያልተገለጠላቸው አይነስውሩ ፈጠን ብለው ጠየቁ፡፡ “አይ እስዎ… ‘ባቡር’ ብልዎት፣ የህል ወፍጮ መስሎዎት ነው ለካ?” ያቋረጡትን ሳቅ ቀጠሉ፡፡ “እህሳ?…‘ባቡር ሊተክሉ ነው’ አላልሽኝም?” ግራተጋቡ ሰውዬው፡፡ “እሱስ ብዬዎት ነበር…” አሉና በእንጥልጥል ትተውት የቀረ ሳቃቸውን አሟጠጡ፡፡ “እና ምንድነው እሚያስቅሽ?” የተናደዱ ይመስላሉ፡፡

“አይ…ባቡር ስልዎት እኮ…የህል ወፍጮ ሳይሆን…” ብለው ጀመሩና አሁንም በእንጥልጥል ተውት፡፡ ምክንያቱም ይተከላል የተባለው “ባቡር” የእህል ወፍጮ አለመሆኑን እንጂ፣ “ምን” መሆኑን እርሳቸውም ቢሆኑ በእርግጠኝነት አያውቁም፡፡ ከእሳቸው አለፍ ብለው ጫማ ሲጠርጉ የሚውሉት ወጣቶች ሲያወሩ የሰሙት፣ ‘ባቡር’ የሚባል ተሽከርካሪ” ሊመጣ መሆኑን ብቻ ነው። እርግጥ እማማ እቴናት በወሬም ቢሆን ከሰውዬው የተሻለ ስለጋቡር ግንዛቤ አላቸው፡፡ ባቡር የመሳፈር እድል ባያገኙም፣ ሀዲድ የመሻገር አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ የቂርቆስን በአል ጠብቀው ስራ ፍለጋ ሲያቀኑ የሚሻገሩትን ሀዲድ ‘የምን እንቅፋት ነው?’ ሲሉት ኖረው፣ አንድ እለት የባቡር መንገድ መሆኑን ሰው ነግሯቸዋል፡፡ “እህ…እንዴት ያለ ባቡር ነው ዛዲያ?” ግራ ተጋብተው ጠየቁ ሰውየው፡፡ እርግጥም ግራ መጋባት ሲያንሳቸው ነው፡፡ ለእሳቸው “ባቡር”፣ የእህል ወፍጮ ነው፡፡ ከእህል ወፍጮ በቀር “ባቡር” የሚባል ነገር ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር የለም። ገጠር ተወልደው ገጠር ያደጉ ገበሬ ናቸው (ይቅርታ ‘ነበሩ’)፡፡

ግብርናው አልሆን ብሏቸው ከ2 አመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም በኤነትሬ እንጂ በባቡር ተሳፍረው አልነበረም፡፡ “እንጃ እኔ…ብቻ እንዲያው…’እንደ መሂና ያለ ነው’ አሉ… ሰው እሚያመላልስ” አሉ እማማ እቴናት፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዳይጠየቁ በመስጋት ነገሩን አድበስብሰው ለማለፍ፡፡ የፈሩት ደረሰ፡፡ የአይነስውሩ ጥያቄ ከጆሯቸው ደረሰ፡፡ “ወይ ታምረ ነገር…ይኸ ሁሉ መሂና ሞልቶ፣ ምን እሚሉት “ባቡር” ነው እሚተክሉ?” በመገረም ጠየቁ አይነስውሩ፡፡ እማማ እቴናት ከጥያቄው ለመሸሽ አይኖቻቸውን ወደ መንገደኛው መለሱ፡፡ “አትለፉኝ ወገኖቼ…ተዘከሩኝ…ባዛኝቷ!...” ሳንቲሞቻቸውን እያንቃጨሉ በሚያሳዝን ዜማ ልመና ጀመሩ፡፡ አይነስውሩ በሰያፍ ይዘው በጥርሳቸው ሲሞርዷት የቆዩዋት ሳንቲም ሽልንግ መሆኗን ካረጋገጡ በኋላ ወደ እማማ እቴናት ዞር አሉ፡፡ ‘እንደ መሂና ያለ ነው’ አልሽኝ?” በመገረም፡፡ “ሊስትሮዎይ እንዲያ ሲሉ ነበር” በመሰላቸት፡፡ “የሆነውስ ሆኖ…እንዲያው ግን…ይኸ ባቡሩ ምን ያህላል አሉ? አሉ ሰውዬው ጥቂት ሲያስቡ ቆይተው፡፡ እማማ እቴናት በስም እንጂ በአካል የማያውቁትን ባቡር መጠን ለመገመት ተቸግረው ጥቂት ሲያሰላስሉ ቆዩና፣ ከዋናው አስፓልት ማዶ የፈረሱ ቤቶችን እያዩ መለሱ፡፡

“መቸም ተዚህ ተትልቁ አውቱቢስ ሳይበልጥ አይቀርም” የራሳቸውን ግምት ሰጡ፡፡ “ውራየል አውጣኝ!” በማጋነን ጮህ ብለው ተናገሩ፤ ሰውዬው፡፡ “እንዴት?” ሴትዬዋ በግምታቸው እንደማፈር አሉ፡ “ያንት ያለህ?” አይነስውሩ አናታቸውን በግርምት እየወዘወዙ ለራሳቸው አወሩ፡፡ “መቼም…ታውቱቢሱ ባይተልቅ ይኸን ያህል መንደር አፍርሰው መንገድ አይጠርጉለትም ነበር” ግምታቸውን በመረጃ ለማስደገፍ ሞከሩ፡፡ “ጉዳችን ሊፈላ ነዋ?” ድምፃቸው ውስጥ ስጋት አለ፡፡ “ኤዲያ!...ይኸን መቀባጠር ሞያ ብለውት!...አገር ሲለማ ጉድ የሚፈላው ተመቼ ወዲህ ነው?” ባልቴቷ ልማታዊ ቁጣ ተቆጡ፡፡፡ “ይኸ ባቡሩ ታውቶቢሱ ተተለቀማ ጉድ ፈላ” የባልቴቷን ምላሽ ለመስማት ጓጉተዋል፡፡ “እስዎ ደሞ እድሜ ልክዎን ልማቱን እንዳሽሟጠጡ ነው!...እናታለም አትለፊኝ…የኔናት ለነፍስሽ ብለሽ ተዘከሪኝ…” ከሰውዬው ወደ ወጣቷ ዞሩ - ወደ ታክሲ ፌርማታው ስትጓዝ ወዳዩዋት፡፡ ወጣቷ ምላሽ ሳትሰጣቸው አለፍ ብለው ታክሲ ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር ሰልፍ ያዘች፡፡ “ሰማሽ ወይ?...ይኸ ባቡሩ ትልቅ ተሆነማ ሺ ተምንተሺ ሰው ማሳፈሩ አይቀርም?...” በስጋት ተውጠው ጠየቁ አይነስውሩ፡፡ “አንቱዬ…ዛሬስ ደናም አይደሉ መሰል? አጉል ወግ ሲጠርቁ ስንቱ መንገደኛ አለፈ!...ምናለ ልማቱን ማሽሟጠጥ ትተው ስራዎን ቢሰሩ?” ቆጣ ብለው፡፡ አይነስውሩ የፌዝ ሳቅ አሰሙ፡፡

“አይ እቴናት… ‘አጉል ወግ’ አልሽው?...አንቺ መቼ ነገሩ ገብቶሽ? ‘መንገደኛው ሳይሰጠኝ አለፈ’ ብለሽ ትብከነከኛለሽ?...አይ ሞኚት…ይኸ ባቡር እሚሉት ነገር መጥቶ አዳሜን ጠራርጐ እያጐረ ይዞት ሲነጉድ፣ ኸትኛው መንገደኛ እንደሚዘከርሽ ታያለሽ!” ብለው ጆሯቸውን ወደ መንገዱ ቀሰሩ፡፡ እማማ እቴናት ይሄን ንግግር ሲሰሙ ድንገተኛ ስጋት ተፈጠረባቸው፡፡ የአይነስውሩ ንግግር እሳቸው እንዳሰቡት “አጉል ወግ” አለመሆኑ ተሰማቸው። “ይመጣል” የተባለው ባቡር የእለት እንጀራቸውን ከፊታቸው ጠራርጐ ይዞ ወደ ሩቅ መንደር የሚሄድ ጠላታቸው ሆኖ ታያቸው፡፡ መንግስት በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የሚተክለው ባቡር፣ መንገደኛውን በሙሉ አጭቆ ይዞ ሲከንፍ፣ እዚህ ቦታ ላይ ታክሲ ጠባቂ ሰው አይኖርም፡፡ የታክሲ ፌርማታው ጭር ይላል፡፡ “ለነፍሴ” ብሎ እሚመፀውት ሰው ይጠፋል፡፡ ከበስተቀኛቸው አለፍ ብሎ ተሰልፎ ታክሲ የሚጠብቀው ይሄ ሁሉ መንገደኛ፣ ባቡሩ ሲመጣ እዚህ ቦታ ላይ ላይኖር ይችላል፡፡ ታክሲ ጠባቂ መንገደኛ ከሌለ ደግሞ መጽዋች አይኖርም…እሳቸው የሚኖሩት ደግሞ መፅዋች ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እማማ እቴናት ስጋት ገባቸው፡፡ የህልውና ስጋት!

Read 3997 times