Saturday, 11 May 2013 14:21

የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍትህና የእንክብካቤ ማእከል...

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ እኔ ወደጋንዲ ሆስፒታል የመጣሁት ሁለት ሴት ልጆች የመደፈር ጥቃት ስለደረሰባቸው ነው፡፡ ልጆቹ የጎረቤት እና የራሴ ሲሆኑ የጎረቤ ልጅ የዘጠኝ አመት ስትሆን የእራሴ ግን የሰባት አመት ናት፡፡ ልጆቹ ለእኛ እንደነገሩን ከሆነ የመደፈር ጥቃት የተፈጸመባቸው አንድ ጊቢ አብሮን በሚኖር ሰው ነው፡፡ በእርግጥ ገና በህግ እስኪረጋገጥ እንዲህ ነው ማለት ባይቻልም የልጆቹ አንደበት የመሰከረው ይህንኑ ነው፡፡ አሁን በሕክምናው ታይተዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በፖሊስ መዝገብ ላይ ሁኔታው ሰፍሮ ወደ ፍትሕ እንሄዳለን፡፡ ጉዳዩ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ እኛም ተከራዮች ነን...እሱም ተከራይቶ የሚኖር ነው፡፡ ወደፊት እንዴት እንደምናደርግ አላውቅም” አሳካሚ እናት... የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍትህና የእንክብካቤ ማአከል በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ከተቋቋመ ሚያዝያ 2005 ዓ/ም ልክ አንድ አመት ሆኖታል፡፡

ማእከሉ በዩኒሴፍ የገንዘብ እርዳታ እና በፍትህ ሚኒስር የበላይነት የተቋቋመው የዛሬ አመት ሚያዝያ 22/2004 ዓ/ም ነበር እንደ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር መረጃ ፡፡ይህ ማእከል ከመቋቋሙ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ያሉበት አንድ ኮሚ ተቋቁሞ ልምድ ለመቅሰም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሄድ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በዚያ መሰረት ማእከሉ ተቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ የሴቶችና ሕጻናት የፍትህና የእንክብካቤ ማእከል አገልግሎት የሚሰጠው ከፈቃዳቸው ውጭ በሆነ መንገድ የግዳጅ ወሲብ ለተፈጸመባቸው ሴቶች ሲሆን በዚህ አንድ አመት ውስጥ ወደ 1100/አንድ ሺህ አንድ መቶ የሚሆኑ ባለጉዳዮች ተስተናግደዋል፡፡ በእድሜም ከአንድ አመት ከአራት ወር ሕጻን እስከ 80/ሰማንያ አመት የእድሜ ባለጸጋ የሚሆኑ ሴቶች የአስገዳጅ ወሲብ ተፈጽሞባቸዋል፡፡

የዚህን ማእከል የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት በጋንዲ ሆስፒታል በተገኘንበት ወቅት የሁለት አመት ከስድስት ወር ሴት ሕጻን በዚሁ ጉዳይ በሐኪም እየታየች ነበር፡፡ አስተባባሪ ነርስ የሆነችው ሲስተር ሙሉነሽ ወልደመስቀል በማእከሉ ከአስተባባሪነት በተጨማሪ ከስነአእምሮ ጋር በተገናኘ ችግር ያለባቸውን እንዲሁም ከመደፈር ጋር ተያይዞ ጭንቀት የደረሰባቸውን ማረጋጋት እንዲሁም ሕክምና መስጠት የመሳሰለውን ሁሉ ትሰራለች፡፡ ሲስተር ሙሉነሽ እንደገለጸችው ሴቶች በቤታቸው፣ በስራ ቦታ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ሊደፈሩ ስለሚችሉ አገልግሎቱ የሚሰጠው የእድሜ ገደብ ሳይኖረው ለሁሉም ሴቶች ነው፡፡ የመደፈር ጥቃት በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶች ላይም እንደሚከሰት የታወቅ ሲሆን ማእከሉም እንደ ተከፈተ ብዙ ወንዶች የሐኪም መረጃ ለማግኘት ወደማእከሉ ቢመጡም ሊሟሉ የሚገባቸው ብዙ የህክምና አሰራሮች ስላሉ በአሁኑ ወቅት ግን የወንዶቹ ተቋርጦአል። ስለዚህ ወንዶቹ የሚሄዱት ወደሌሎች ሆስፒታሎች ሲሆን ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሴቶች እንደመሆኑ መጠን ሴቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሕክምናው ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

በማእከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ከሆነ ሕጻናቱ የሚጫወቱባቸው ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤተሰብ የሌላቸው ለተወሰኑ ቀናት የሚያርፉበት መኝታ ክፍል እና በተሟላ የምግብ አቅርቦት እንደሚስተናገዱ ለመመልከት ተችሎአል፡፡ ሲ/ር ሙሉነሽ ወልደመስቀል እንደተናገሩት ከሆነ ሕጻናቱን እና የተጎዱትን በማስተናገዱ ረገድ በክፍሉ ውስጥ ያሉት ነርሶች በሙሉ ፈቃደኝነት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ለመረዳት ተችሎአል፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ ታከለ የማእከሉ አስተባባሪ ናቸው፡፡ ዶር ስንታየሁ እንደገለጹት ተጠቂዎቹ ሕጻናት ከሆኑ በቤተሰባቸው አማካኝነት አዋቂዎቹ ደግሞ እራሳቸው ወደማእከሉ ይቀርባሉ። ማንኛዋም ሴት ተደፍሬአለሁ ስትል ቃሉዋ ታማኝነት አለው። ስለዚህ ተጠቂዋ ካርድ በማውጣት የህክምናውን አገልግሎት ለላቦራቶሪ ፣ለመድሀኒት፣ ተኝቶ ለመታከም ...ወዘተ ሁሉንም ሙሉ በሙሉ በነጻ ታገኛለች፡፡ በተለይም ሴትዋ ጥቃቱ በተፈጸመ በቅርብ ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ...ማለትም ፡- ጥቃቱ ከተፈጸመባት እስከ ሶስት ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ወደማእከሉ ከመጣች ከኤችአይቪ ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችለውን መድሀኒት እንድታገኝ ይደረጋል፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመ እስከ አምስት ቀን ድረስ ወደ ሕክምናው ማአከል ከመጣች ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችል መድሀኒት ይሰጣታል፡፡ ጥቃቱ ከተፈጸመባት እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ ከመጣች የአባላዘር በሽታ እንዳይይዛት የሚከላከል መድሀኒት ይሰጣታል፡፡

ዶ/ር ስንታየሁ እንደችግር የገለጹት ተጠቂዎቹ ሁሉም በቅርብ ቀን ውስጥ ወደህክምና ማእከሉ አለመምጣታቸውን ነው፡፡ ማእከሉ ከተከፈተ ጀምሮ እንደታየው ልምድ ከሆነ ሴቶች የሚመጡት ጥቃቱ በተፈጸመ ከሶስት እስከ ስድስት ወር እና ከዚያም ካለፈ በሁዋላ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ወደማእከሉ የሚደርሱት ያልተፈለገ እርግዝና ከተከሰተባቸው በሁዋላ ሲሆን በአገሪቱ የውርጃ ሕግ መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ ቢሆንም በከፊል ይህንን እርዳታ ሊያገኙ የማይችሉ ይሆናሉ። ለምሳሌም እርግዝናው ከ28/ሀያ ስምንት ሳምንት በላይ ከሆነው ተንከባክበናት እንድትወልደው ከማድረግ ውጭ ሌላ እርዳታ ማድረግ አይቻልም፡፡ከዚያም ውጭ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ሲባል ሊያገኙ የሚገባቸውን እርዳታ እንዳያገኙ ይሆናሉ እንደዶክተር ስንታየሁ ማብራሪያ፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ አክለውም ይህ ማእከል ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የህክምና ማስረጃ መስጠት ይገኝበታል፡፡ ይህ የህክምና ማስረጃ እንደቀድሞው በእንግሊዝኛ ሳይሆን በአማርኛ የሚጻፍ ነው፡፡ እንደቀድሞው በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ ወደትርጉም ቤት የሚያስኬድ እና የሚያስቸግር ሳይሆን በወቅቱ በሴትዋ አካል ላይ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ወደፖሊስ የሚላበት ነው ፡፡

በእርግጥ ይህ ወንጀል ነው አይደለም የሚለውን የሚወስነው የፍትህ አካሉ እንጂ ሕክምናው አይደለም፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምናገረው አሉ ዶ/ር ስንታየሁ ...ማንኛዋም ጥቃቱ የደረሰባት ሴት ችግሩ በደረሰ ውስን ቀናት ውስጥ ወደማእከሉ መቅረብ ብትችል መረጃውን በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የቆሰለው አካላቸው ድኖ ገላቸውን ፣ልብሳቸውን ታጥበው እና ከቀናትም ባለፈ ወራት ፈጅተው ስለሚመጡ ምንም መረጃ የማይገኝበት አጋጣሚ ብዙ ነው ብለዋል ዶ/ር ስንታየሁ ታከለ የማእከሉ አስተባባሪ፡፡ በማእከሉ ያገኘናት የፖሊስ ባልደረባ ም/ሳይጅን ጽጌ ደግፌ ትባላለች፡፡ ም/ሳጅን ጽጌ ቢሮ ውስጥ አንድ ጥሩ አሻንጉሊት ፊት ለፊት ተቀምጦአል፡፡ እሱዋም እንደገለጸችው ይህ አሻንጉ ሊት ሴቶቹ በተለይም ህጻናቱ የደረሰባቸውን ችግር ለማስረዳት እፍረት ቢሰማቸውና ድብቅ ቢሆኑ እንዲናገሩ ለማጫወቻነት የተቀመጠ ነው፡፡

እንደ ምክትል ሳይጅን ጽጌ መግለጫ ቀደም ሲል በፖሊስ ጣቢያ ይህ ስራ በሚሰራበት ጊዜ መረጃው በፍጥነት ስለማይደርስና ባለጉዳ ዮቹም ከቦታ ቦታ በመዘዋወር እንግልት ስለሚደርስባቸው ጉዳዩ ፍትህ ሳያገኝ መዝገብ የሚዘጋበት እና ተከሳሾች ነጻ የሚወጡበት አጋጣሚ ይስተዋል ነበር፡፡ አሁን ግን ከአንድ አመት ወዲህ ይህ የፖሊስ ስራ ከህክምናው ጋር ተጣምሮ በአንድ ማእከል ውስጥ ሐኪም፣ አቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በመሆን መስራት በመቻሉ ውጤቱን በፍጥነት በመቀባበል ተጎጂዎቹም ሳይንገላቱ መረጃው ለፍትህ አካላቱ እንዲደርስ አስችሎአል፡፡ ም/ሳይጅን ጽጌ የተጠቂዎችን የእለት ሁኔታ ስትገልጽ ከአስሩም ክፍለ ከተማ አንዳንድ ጊዜ ምንም ተጎጂ ላይመጣ ሲችል አንዳንዴ ደግሞ በቀን እስከ አስር እና ከዚያም በላይ ሴቶች ተጎጅዎች ወደ ማከሉ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በእድሜ ደረጃም በአብዛኛው ሕጻናት በተለይም እስከ አስራ አምስት አመት ድረስ ያሉት ተጎጂዎች ናቸው፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል በተቀቋቋመው ማእከል ውስጥ አገልግሎት የሚያገኙ ተጎጂዎች ሕክምናውን ካገኙና የደረሰውን ችግር ካስረዱ በሁዋላ ወደመጡበት ክፍለ ከተማ በመሄድ የፖሊስ ሪፖርቱን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ጉዳት ያደረሱት ሰዎች ተገቢውን የፍትህ እርምጃ እንዲያገኙና ተጎጂዎቹም በዚህ ፍትሕ እንዲረኩ ለማድረግ ዋናው የህክምናው ማስረጃ ሲሆን ለዚህም ተጎጂዎች በጊዜ ወደህክምና ማእከሉ በመቅረብ ተገቢውን ክትትል ቢያደርጉ ለአሰራር ይበልጥ አመቺ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍትሕ አካሉና ከህክምና ማእከሉ ጋር በመጣመር ይህንን ስራ ከጀመረ ወዲህ በሴቶችና በቤተሰብ ላይ የነበረው መንገላታት በእጅጉ መቀነሱን መመስከር ይቻላል ብላለች ም/ሳጅን ጽጌ ደግፌ፡፡ የሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ እንደሚሉት ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና የህክምናው ዘርፍ በጋራ የሚሰሩበት ይህ የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍትህና የእንክብካቤ ማእከል በሀገራችን የመጀመሪያው ሞዴል ማእከል ነው፡፡ የጋንዲ ሆስፒታል የተመረጠበትም ምክንያት የሴቶች ሆስፒታል ስለሆነ እና አገልግሎቱን ከዚያ በፊትም ስለሚሰጥ ነው፡፡ በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስርና በጤና ቢሮ አማካኝነት ጥያቄው ሲቀርብ የህብረተሰቡ ትልቅ ችግር እና ሴት ሕጻ ናቱ የሚጎዱበት እንደመሆኑ ጋንዲ ሆስፒታልም የራሱን ግልጋሎት ሊሰጥ ይገባል በሚል ከስም ምነት ተደርሶ እነሆ ስራው ከተጀመረ አንድ አመትን አስቆጥሮአል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራ ችን ከፍላጎታቸው ውጭ የወሲብ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የህክምና ማስረጃን ለፍትህ አካል የማ ቅረብ ስራን የሚሰራው ይህ በጋንዲ ሆስፒታል የሚገኘው የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍት ህና የእንክብካቤ ማእከል ብቻ ነው፡፡ ወንዶቹን በሚመለከት ግን የህክምናውን ማስረጃ በትክክል ከሚመለከተው ሐኪም የማግኘትን አሰራር በመከተል ወደ ጥቁር አንበሳ እና ዘውዲቱ ሆስፒታል እንዲሄዱ ይደረጋል ብለዋል ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጋንዲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፡፡

Read 3966 times