Saturday, 11 May 2013 14:32

የዝንጀሮ ቆንጆ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ምዕራፍ አንድ - “በጣም እርቦኛል፤ ባገኝ እበላለሁ” ገና መንጋቱ ነው፡፡ ገና መንቃቴ ነው፡፡ እናት እና አባቴም ነቅተዋል፤ ሲያወሩ ይሰማኛል፡፡ “አንተ ምን ሆነህ ነው?” ትላለች እናቴ፡፡ “ምን ሆንኩ?” አላት አባቴ፡፡ “ሌሊት እራስህን አታውቅም ነበር፡፡” “አይደለምና በሌሊት እና በእንቅልፋቸው፣ በቀኑ እና በእውናቸው፣ እራሳቸውን የሚያውቁ ጥቂት ናቸው፡፡” እንዲህ ነው አባቴ፣ በግጥም ነው የሚያወራው፡፡ “መዘላበዱ ጀመረህ ደግሞ ገና ሳይነጋ፡፡” “ማዘንጊያ ይቅርታ፤ ሳልስምሽ ነጋ፡፡” “ከአለቃ ገብረሃና ጋር እኮ የሚያመሳስላችሁ ድንክነታችሁ ብቻ ነው፡፡” “ሊቃንነታችንስ?” “ድንቄም እቴ!” “እንትናችንስ?” “አፈር ብላ፤ አፈር ያስበላህ፡፡” “በጣም እርቦኛል፤ ባገኝ እበላለሁ፡፡” “ሳታቅፈኝ አድረህ አታውቅም ነበር፡፡” አፈርኩ፡፡ እናቴ ድምጽ ውስጥ የጋለ ስሜት አለ።

ቤታችን አንድ ክፍል ናት፡፡ ወዲያ ጥግ እና ወዲህ ጥግ ሁለት ፍራሾች አሉ፡፡ ወዲያ ጥግ ያለው ፍራሽ የእናትና አባቴ መኝታ ቤት ነው፤ ወዲህ ጥግ ያለው ፍራሽ የኔ መኝታ ቤት ነው፡፡ “አንተ ልጅ ሰዓት አልደረሰብህም?” እናቴ ናት፤ እኔን ነው፡፡ እንድሄድላቸው ፈልጋለች መሰለኝ፡፡ “ልክነሽ፤ ደርሷል፡፡” የትምህርት ቤት ሰዓት መድረሱን ነው የጠቆመችኝ፡፡ ምዕራፍ ሁለት - ምፅዋት አቆለቆልሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ፡፡ ረዥም ነኝ፡፡ በቁመት በማን እንደወጣሁ አላውቅም፡፡ አባቴ ድንክ ነው። ጥርሴ የናቴ፣ ከርዳዳ ፀጉሬ ደግሞ ያባቴ ውርስ ናቸው። አፍንጫዬ እንደ እናቴ ሰልካካ፣ እንደ አባቴም ጥፍጥፍ አይደለም፡፡ ትንንሾቹ አይኖቼ የራሴ ናቸው፡፡ ስሄድ አንገቴን በጣም ከመድፋቴ የተነሣ አገጬ ደረቴን ይነካል፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰው ጋር የምጋጭበት ጊዜ ትንሽ አይደለም፡፡ ይቅርታ አልጠይቅም፡፡

ስንጋጭ ይቅርታ የሚጠይቅ ጠይቆኝ፣ የሚሳደብ ሰድቦኝ ያልፋል፡፡ ስንጋጭ ይቅርታ የማልጠይቀው ሲሰድቡኝም መልስ የማልሰጠው፤ ትዕቢተኛ ወይም ትዕግስተኛ ሆኜ አይደለም፤ በሃሣብ ስለምዋጥ ነው፡፡ ዛሬ የማስበው ስለኢኮኖሚክስ መምህሬ ነው፡፡ በቀደም እለት አለቅጥ አናዶኝ ነበር፡፡ የኔ የተግባር መልስ ብድሬን ይመልስ አይመልስ ግን እንጃ፡፡ አስተምሮ ሊወጣ ሲል፣ በቀደም እለት “የትምህርት ሰዓት ሲያበቃ እፈልግሃለሁ፡፡” ብሎ ቢሮ እንደሚጠብቀኝ ተናግሮ ወጣ፡፡ በእርጋታ ነው ቀጣዩን ትምህርት የተከታተልሁት፡፡ እንዲያውም ቀጠሮውን ረስቼ ልወጣ የግቢው በር ጋ ከደረስኩ በኋላ ነበር አስታውሼ ወደ ቢሮው ያመራሁት። አልፎ አልፎ እንደሚያደርገው በቅርቡ ባነበበው መጽሐፍ ላይ እንድንወያይ ይሆናል የፈለገኝ ብዬ ነበር የገመትኩት፡፡ በቋቋቲያም ጣቶቼ ለአመል ያህል የቢሮውን በር ነካክቼ ገባሁ፡፡ ወንበሩ ላይ ወደኋላ ተለጥጦ አይኑን ፊት ለፊት ካለው ግድግዳ ላይ ተክሏል፡፡ ፊት ካለው ጠረጴዛ ላይ ተደራርበው የተቀመጡ ሱሪ፤ ሸሚዝና ጫማ ይታያሉ፤ አዲሶች አይደሉም፤ ስለዚህ ሌላ ምንም ስያሜ ሊሰጣቸው አይችልም፤ ከአሮጌ በቀር። ገብቼ ትንሽ እንደቆምኩ ከሃሳቡ ነቃ፡፡ “እስኪ እነኚህን ልብሶች ለካቸው፤ ጫማውንም እየው፡፡”

አለኝ በረዥሙ ተንፍሶ፡፡ በወቅቱ የጠራ ስሜት አልተሰማኝም፤ ራሴን ነው ያየሁት፡፡ ሱሪዬ ሁለቱም ጉልበቶቼ ላይ ተቀዷል፡፡ ነጠላ ጫማ ነው እግሬ ላይ የሰካሁት፤ እርሱም አንድ እግሩ ተበጥሶ በሽቦ አያይዤዋለሁ፤ ክንዶቹ፣ አንገቱ ላይና ጠርዞቹ ላይ የተበላ የክር ሹራብ ከላይ ለብሼአለሁ፤ እናቴ ናት የሰራችልኝ፡፡ ይኼን ብሎኝ ሳለ ከበስተውጭ ተጠራ፡፡ “ውሰዳቸው ልክህ ከሆኑ ትለብሳቸዋለህ። ካልሆነም…” እየሄደ ስለሆነ የተናገረው የመጨረሻዎቹን ቃላት አልሰማኋቸውም፤ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡ ልክ እርሱ እንደወጣ ጥርት ያለ ስሜት ተሰማኝ። ንዴት፡፡ የተናቅሁ መሰለኝ፡፡ እርዳታ፣ ምጽዋት ለእኔ?! እንዲህ ነኝና ፍቃዱ ይህን ነገር ገብቼ ለእናቴ ብነግራት “ለምን በጥፊ አላልከውም ነበር?!” ነው የምትለኝ፡፡ እውን ለምን በጥፊ አላልኩትም? ነደደኝ፡፡ ጆሮዎቼ ጋሙ፡፡ ቢሆንም ልብሶቹንም ጫማውንም ይዤ ወጣሁ። የትምህርት ተቋሙ ግንብ ስር የሚያድር አንድ ወጣት አለ፡፡ በቀጥታ ወደ እርሱ አመራሁ። ኩርምት ብሎ ተኝቷል፤ እንቅልፍ ወስዶታል፤ ቀሰቀስኩት፤ ነቃ፡፡ “ውሰዳቸው፡፡” አልኩት፤ የያዝኳቸውን ልብሶችና ጫማ ከፊቱ እያደረግሁ፡፡ “ልክህ ከሆኑ ትለብሳቸዋለህ፣ ካልሆነም…ትሸጣቸዋለህ፡፡” “እ…ምን…” ባለማመን ዓይነት ከላይ እስከታች እያየኝ፡፡ “ውሰዳቸው፤ ልክህ ከሆኑ ትለብሳቸዋለህ፣ ካልሆነም…ትሸጣቸዋለህ፡፡” ብዬ የሰፈሬን መንገድ ተያያዝኩት፤ ሽቅብ ወደ ሽሮ ሜዳ፡፡

***

መምህሩ ላይ የጠበቅሁትን ያህል ለውጥ አላየሁበትም፤ ብቻ እኔን ሲያይ የመገረም፣ የንቀትና ሌላ ሊገባኝ ያልቻለ አንድ ስሜት አየሁበት፡፡ ልብሱንና ጫማውን ያ ወጣት ጐዳና አዳሪ አድርጐት እንዳየው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ልጁ ከዩኒቨርሲቲው በር አካባቢ አይጠፋም፡፡ መምህሩ አቶ አባ መስጠት አሁን ስለ ተመጽዋቾች ጥሩ የሆነ ሃሳብ እንደሚጨብጥ ሙሉ እምነት አደረብኝ፡፡ ራቁቴን በቡቱቶ፣ ሌጣዬን ያለጫማ እሄዳለሁ እንጂ የምጽዋት ልብስ ልለብስ?! ከተመጽዋችነት ጋር ስለማልተዋወቅ አይደል እንዴ ለዚህ የበቃሁት?! ማለት መኪና እያጠብኩ ያለ ምንም እረዳት ዩኒቨርሲቲ ድረስ ልማር የበቃሁት?! ዋ አለማወቅ፡፡ ምዕራፍ ሶስት፡- ኑሮ እናቴ ሹራብ ትሠራለች፤ ስፌት ትሰፋለች፣ ሰዎች ትነቅሣለች (በነገራችን ላይ ንቅሳት በጣም ያበላል፡፡ ብዙ ሰዎች የሚታይ ቦታ ላይ ብቻ ሰዎች የሚነቀሱ ይመስላቸዋል፤ ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ወጣት ሴቶች፣ አንዳንድ ባለትዳሮችና በጠንቋይ ትዕዛዝ… አዎ በጠንቋይ ትዕዛዝ … ጡታቸው ላይ፣ ጭናቸው ላይ፣ መቀመጫቸው ላይ፣ የተለያየ ነገር ይነቀሳሉ፡፡

የሚነቀሱት ነገር ደግሞ ማስረገሙ፣ የሰው ስም፣ ሸረሪት፣ ቢራቢሮ፣ እንዝርት፣ አበባ፣ ጀበና፣ የኮከብ ቅርፅ፣ የሶስት ማእዘን ቅርፅ … በጠንቋዩ ትእዛዝ እና በራሳቸው ምርጫ ይነቀሳሉ፡፡ አብዛኞቹ ጠንቋዮች እናቴን በሙያዋ አውቀዋታል፤ እና አብዛኞቹን ሴቶች የሚልኳቸው ወደ እኛ ቤት ነው፡፡ የእኔ መኖር ራሱ ለገበያው አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ (ጠንቋዮቹ ሴቶቹ እንዲነቀሱ የሚያዟቸውን ነገሮች በሙሉ ልቅም ባለ ዲዛይን የምሰራው እኔ ነኝ፤ እና እኔ እና እናቴ ስንት ጡቶች፣ ስንት ጭኖች፣ ስንት መቀመጫዎች እንዳየን መገመት ትችላላችሁ፡፡) አባቴ ቀን ቀን ለሀብታም ውሾች ከሆቴል የኮንትራት ምግብ ያመላልሳል፤ ማታ ማታ ቡና ቤት በዘበኝነት ያድራል፡፡ እኔ መኪና አጥባለሁ፤ አቅሜ የፈቀደውን ያህል እሸከማለሁ፤ ሌላ ድንገተኛ ሥራም እሰራለሁ፤ እንዲህ ነው የምንኖረው፡፡ ሶስታችንም ራሳችንን መቻል ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ማንም የማንንም እጅ አያይም። እኔም ምፅዋትን፣ ተረጂነትን፣ እንድጠላ ያደረጉኝ እነርሱ ናቸው፡፡ መክረውኝ አይደለም፣ ያደግሁበት ስለሆነ ብቻ ተዋሃደኝ፡፡ እራሳችንን መቻል እንችልበታለን፡፡ ሽሮ ሜዳ ውስጥ የተከበርን ቤተሰብ ነን፡፡ አባቴ አንድ እለት እርቦት አንጀቱ ታጥፏል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም እኔም፣ እናቴም ተርበናል፡፡

ሰውዬው ከሚያመላልሰው የውሾቹ ምግብ ላይ ተደብቆ ትልልቅ ጉርሻዎችን ውጦ ረሃቡን አስታገሰ፡፡ ከሰዓት በፊት ግን ጎረቤት ገበታ ላይ ደርሶ ምግብ ብላ ተብሎ ሲለመንና እምቢ ሲል በአይኔ አይቼዋለሁ፡፡ ለእኔና ለእማዬም ደህና የሚጋጡ አጥንቶችን አምጥቶልን በእነርሱው ውለን አድረናል፡፡ ምዕራፍ አራት፡- ተረት እና ሌብነት የትምህርት ሰዓት አብቅቶ ወደ ቤቴ ስሄድ አንጀቴ አንድ ላይ ጥብቅ አለብኝ፡፡ ከነጋ የአሥር ሣንቲም ቆሎ ብቻ ነው አፌ ያደረግሁት፡፡ ከቤት ከመውጣቴ በፊት አባቴ “በጣም እርቦኛል፤ ባገኝ እበላለሁ።” ሲል ሰምቼ ነበር፡፡ እናቴ ከየትም አምጥታ ልትበላ አትችልም፡፡ እዚህ ጋ አንድ ኢትዮጵያዊ ግጥም ፀሐፊ እንዳለው “ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል” ሊባል ይችላል፡፡ ይህንን የሰማ አንድ ብፁእ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ “ለምን ሞክረህ አታየውም” ብሏል። (ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው) አንዱ ጥጋበኛ ኢትዮጵያዊ ደግሞ “ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል” ብሎ ጥያቄ የጥጋበኛ ጥያቄ ነው” ብሏል፡፡ ይህን ብልም በቀጥታ ወደ ቤቴ ነው ያመራሁት። የሠፈራችን መግቢያ ላይ አንዲት ፍራፍሬ መሸጫ መደብር አለች፡፡ ባለ መደብሩ ያቀርበኛል፡፡ እኔ ግን ባልጠላውም ልቀርበው አልፈልግም፡፡ ቀርቤ ሳወራው ቶሎ ብሎ አፉን ይከፍታል፡፡

ለሰው ሳወራ ፊትን ትኩር ብሎ የመመልከት ልማድ ስላለኝ የእርሱን የተከፈተ አፍ ማየት ያስጠላኛል፤ የበሰበሱ ጥርሶች፤ ምናምን የተለጠፈበት ምላስ … ቅፅበታዊ ሃሣብ ብልጭ አለልኝና ከመንገዴ ወጥቼ ወደ እርሱ ሄድኩኝ፡፡ በፈገግታ ተቀበለኝ፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ለትንሽ ጊዜ የሚስብ ወሬ ፍለጋ ዝም አልኩና ጀመርኩለት፡፡ “በመጀመሪያ አዲስ አበባን የረገጠውን ጉራጌ ታውቀዋለህ?” “ኧረ አላውቀውም” “ይኸውልህ ያኔ የጉራጌ ምድር እንዲህ እንደ አሁኑ ሰው አልበዛበትም ነበር፤ የሚታረስ መሬት፣ የሚያርስ በሬ፣ የምትታለብ ላም በሽ በሽ ነበር። መሬቱ ያለ ብዙ ልፋት ብዙ ይለግስ ነበር፡፡ እንዲያውም አብዛኛው ነገር ከዱር የሚገኝ ነበር፡፡” “ኧረ ባክህ?!” “እውነቴ ነው የምልህ፣ እና አሁን የምልህ ሰውዬ በመጀመሪያ አዲስ አበባን የረገጠው ጉራጌ ሁሌ ጠግቦ ይበላና፣ ሚስቱ የምታወጣውን ጨሌ አረቄ በኮዳ ይይዝና፣ ከቤቱ በላይ ያለችው ጉብታ ላይ ቁጭ ብሎ ያብሰለስል ነበር፡፡ ይፈላሠፍ ነበር፡፡” “ኧረ ባክህ?!” “እውነቴን ነው የምልህ እና አሁን የምልህ ሰውዬ፣ በመጀመሪያ አዲስ አበባን የረገጠው ፈላስፋ ጉራጌ ጉብታው ላይ ቁጭ ብሎ፣ አረቄውን እየተጎነጨ ድንገት ቀና ቢል አድማስ ታየው፡፡ ሁሌም በአድማስ ይገረም ነበር፡፡ “ከዚያ በኋላ ምን ይሆን ያለው” እያለ ያብሰለስል ነበር፡፡ እና የዚያን እለት አረቄውን እየተጎነጨ በጣም በአድማስ ተመሰጠ፡፡

“ከዚያ በኋላ ምን ይሆን ያለው፣ እያልኩ እስከመቼ እኖራለሁ፤ ለምን ሄጄ አላየውም” ብሎ መንገድ ጀመረ፡፡” “ኧረ ባክህ?!” “እውነቴን ነው፤ እና አሁን የምልህ ሰውዬ፣ በመጀመሪያ አዲስ አበባን የረገጠው አብሰልሳይ ጉራጌ ከአድማስ ወዲያ ማዶ ምን እንዳለ ለማየት ጉዞ ጀመረ፡፡ አስብ ለማንም አልተናገረም፡፡ የሚወዳትን ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን ወደ ኋላ ትቶ አድማስን ወደፊት እያየ ገሰገሰ፡፡ አስብ ስንቅ አልያዘም፤ በጁ ያለው የአረቄ ኮዳው ብቻ ነው፡፡” ዝም አልኩ፡፡ “እና ከዛስ?!” “ከዚያማ ሲሄድ፣ ሲሄድ፣ ሲሄድ፣ … ከአንድ ወንዝ ደረሰ፡፡ በጣም ተጠምቶ ነበር፡፡ ውሃ ጠጣ፤ ብዙ ጠጣ፡፡ እና ውሃውን መጠጣት በቅቶት በውሃ እየተጫወተ እያለ አንድ የሚያብለጨልጭ ነገር አየ፤ ከውሃው ውስጥ አውጥቶ አየው፤ የንጉሱ ምስል ያለበት የወርቅ ገንዘብ ነበር፡፡

እንደገና ጎንበስ ብሎ ቢያይ ያንኑ የሚመስሉ ብዙ የወርቅ ሳንቲሞች አየ፡፡ እየለቀመ ኪሶቹን ሞላ፡፡” “እና ከዛስ?!” “ከዚያማ ኪሶቹን በሙሉ በወርቅ ሳንቲም ሞልቶ ሳንቲሞቹን ለንጉሱ ሊያስረክብ መንገድ ቀጠለ … መንገድ ላይም አንዲት መልአክ የምትመስል ሴት አግኝታው ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀችው … ነገራት…” “ኧረ ባክህ?!” አየሁት “አአአ” ብሏል፤ አፏን ከፍቷል፡፡ የፍራፍሬ መደርደሪያውን ተደግፌ ነው የቆምሁት፡፡ ረዥሙ የፍራፍሬ መደርደሪያ በርብራብ ተከፋፍሎ ብርቱካኑ በአንድ ወገን፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ በሌላ ወገን ተቀምጦበታል፡፡ ከእነዚህ በላይ ደግሞ በስስ ላስቲክ የታሠሩ መጠነኛ ክብ ቢጫ ዳቦዎች ጣል ጣል ተደርጎባቸዋል፡፡ እጄን ሰድጄ አንዱን ቢጫ ዳቦ ያዝኩት፤ ዳቦውን ጀርባዬ ውስጥ ወሸቅሁት፡፡ የጀመርሁለትን አጓጊ ወሬ በውል ሳልቋጭ ጥዬው ወደ ቤቴ፡፡ ፊቱ ላይ ቅሬታ ይነበብ ነበር፡፡ ነገ እንደምቀጥልለት ቃል ገብቼለታለሁ፡፡ ስለየው እንኳ አፉን አልከደነም ነበር፡፡ ዳቦውን ይዤ ስገባ የእናቴ ጠባብ ሰልካካ ፊት በነጫጭ ችምችም ጥርሶቿ ታግዞ ሲፈካ ታየኝ፡፡ አሁን ከየትም ላምጣው አትጠይቀኝም። በጣም የተራብን እለት አባዬ የውሾችን ምግብ ሠርቆ እንደአመጣ እያወቅን ያለ ጥያቄ ተቀብለነው እንበላለን፤ እና እኔም ዛሬ … ግን የቱ ይሻላል? ምፅዋት መቀበል? መስረቅ? ወይስ ምን?

Read 3242 times