Saturday, 18 May 2013 10:04

ትንሿ በራሪ ሮቦት - “ሮቦንብ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ወርዷ ክንፎቿንም ጨምሮ፣ ከአንድ ጣት ውፍረት ብዙም አይበልጥም። “ንብ የምታክል ሮቦት” ለማለትም ይመስላል፤ ስሟን RoboBee ብለው የሰየሟት። በእርግጥ ባለፉት አስር አመታት በተካሄዱ ጥናቶችና ምርምሮች ጥቃቅን በራሪ ማሽኖች (ሮቦቶች) ተፈጥረዋል። ሁለት ሶስት ግራም የሚመዝኑ ብቻ ሳይሆኑ፤ ከአንድ ግራም በታች ክብደት ያላቸው እንደ ነፍሳት ማንዣበብ ወይም መብረር የሚችሉ ሮቦቶች ተሰርተዋል። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አራት የጥናት አመታትን የጠየቀው RoboBee (ሮቦንብ) ግን፣ ከእስካሁኖቹ ጥቃቅን በራሪዎች ሁሉ እጅጉን ያነሰ ነው። 12 በራሪዎች ቢመዘኑ፣ በድምር አንድ ግራም አይሞሉም።

የተመራማሪዎቹ ጥረት ተሳክቶ ሰሞኑን፣ እንደ ንብ ክንፉን የሚያርገበግብ በራሪ ሮቦት በይፋ አስመርቀዋል። ደግሞም፣ እንደ ንብ መንጋ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ንብ የመሰሉ ሮቦቶችን” ማምረት ቀላል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል። “ድንቅ ፈጠራ” ተብሎ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት የተደነቀው “ሮቦንብ”፣ በብዙዎች ዘንድ ስጋት ማሳደሩ አልቀረም። ትናንሽና ጥቃቅን በራሪ አካላት አሁን አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል። መንግስታት ለወታደራዊ ስለላና ለፖሊስ ቅኝት በራሪ “ሮቦቶችን” መጠቀም ጀምረዋል። ዜጎችን ለመሰለልና የአፈና ቁጥጥር የማካሄድ ጥማት ያለባቸው መንግስታት፤ በየከተማው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትናንሽና ጥቃቅን በራሪ ሮቦቶችን ቀን ከሌት እንዳያዘምቱ ምን ያግዳቸዋል? አሳሳቢው ነገር ይሄ ነው።

Read 3322 times