Saturday, 18 May 2013 10:23

ተቃዋሚዎች የሙስና እርምጃው ፖለቲካዊ እንዳይሆን ሰግተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)
  • ኢህአዴግም እንደ ድርጅት ሙሰኛ ነው - ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
  • ገቢዎች ከመንግስትም በላይ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው - አቶ ሙሼ ሰሙ
  • ማጥመጃው ትላልቅ ዓሳዎችን ካጠመደ እንተባበራለን - ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም
  • የእርምጃውን አቅጣጫ ለማወቅ ቀጣዩን ማየት ያስፈልጋል - ዶ/ር መረራ ጉዲና

በፌዴራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳይ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ እንዳይሆን ስጋት አለን የሚሉ ተቃዋሚዎች፤ እውነቱን የምናውቀው በእርምጃው ቀጣይነት ነው ብለዋል፡፡ መንግስት አላማው ሙስናን ማጥፋት ከሆነ ግን የሚደነቅና የሚበረታታ ተግባር ነው ሲሉ አወድሰዋል፡፡ አሁን የተወሠደው እርምጃ ግዙፉን የሙስና ችግር ዝም ብሎ መነካካት ነው ያሉት የመድረክ አመራር አባል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል ማለት አይቻልም፤ አሁንም ትልልቅ አሳዎች አልተነኩም ብለዋል፡፡ በመላ ሃገሪቱ ሙስና መስፋፋቱን የሚናገሩት ፕ/ር በየነ፤ ራሱ ገዢው ፓርቲ የሚያንቀሣቅሣቸው የንግድ ድርጅቶች ከሙስና የፀዱ አይደሉም በማለት ተችተዋል፡፡

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሠሙ በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣኖችና ባለሃብቶች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን ቢደግፉም ዋነኛ የችግሩ ምንጭ ግለሰቦች ሳይሆኑ ስርአቱ ነው ይላሉ፡፡ ስርአቱ ለእነዚህ ባለስልጣናት የመደራደርያ በር ስለከፈተላቸው የፈለጉትን ነጋዴ በፈለጉት ጊዜ ጠርተው እያሸማቀቁና ስሙን እያጠፉ በጠላትነት የሚያዩበት ሁኔታ ካልተቀየረ ሙስናን ማጥፋት አይቻልም ብለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ማሰር ሙስናን የመዋጋት አካል መሆኑን ጠቁመው፤ ዋናው ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ነው ባይ ናቸው - አቶ ሙሼ፡፡ የቀድሞው የቅንጅት አመራር አባልና አለማቀፍ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም በሰጡት አስተያየት፤ እርምጃው የሚቀጥል ከሆነ የሚመሠገን ነው፤ ካልሆነ ግን በፖለቲካ ግጭት ምክንያት የተፈጠረ ያስመስለዋል ብለዋል፡፡

“ከተያዙት የበለጡ ትላልቅ አሳዎች መኖራቸውም መዘንጋት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል፡፡ በሙስና ተጠርጥረው የተያዙት ሠዎች ጉዳይ ፖለቲካዊ ይመስላል ያሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ሃይሉ ሻውል፤ የተያዙት በእርግጥም በሙስና የተጠረጠሩበት ጉዳይ እውነት ከሆነ ግን እርምጃው ቀጣይ እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል፡፡ የመድረክ አባል የሆኑት ዶ/ር መራራ ጉዲናም እርምጃውን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት፡፡ የእርምጃውን አቅጣጫ ለማወቅ ቀጣዩን ሂደት ማየት ያስፈልጋል ይላሉ - ዶ/ር መረራ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሙስናን ጉዳይ በግሌ እከታተላለሁ ማለታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር መረራ፤ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊም “አንድ እጃችንን በመንግስትና በግል ሌቦች ታስረን ነው የምንሰራው” እያሉ ለውጥ ሳያመጡ ነው ያረፉት በማለት “ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያምስ አቅም አላቸው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን እስካሁን ብቃት አልነበረውም፤ አሁንም ሁለት ባለስልጣናትን ስላሰረ ብቃት አለው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል ብለዋልም፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ የተወሠደው እርምጃ መላውን ህብረተሠብ ያግባባና የህዝቡ ፖለቲካዊ ድጋፍ የታየበት ነው በማለት እርምጃውን ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኙ ወገኖችን ኮንነዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች የህብረተሠቡንና የመንግስትን ጥረት የማክሸፍና የማምከን ሙከራ እያደረጉ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ይህን አይነቱን እርምጃ ፖለቲካዊ ነው ማለት ለኪራይ ሠብሣቢነት አሠራር ድጋፍ መስጠት ነው ብለዋል፡፡ የፌደራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነምግባር ትምህርት ዳሬክተር አቶ ብርሃኑ፤ ኮሚሽኑ ግንዱን ትቶ ቅርንጫፉ ላይ አተኩሯል የሚለውን አስተያየት አይቀበሉም፡፡ ከ“ሚኒስትር በላይ ግንድ ካለ ይንገሩን” ሲሉ ይሟገታሉ - ዳሬክተሩ፡፡ በሙስና የተጠረጠሩ ባለስልጣናትን ለመያዝ የማንንም ፈቃድ እንደማይፈልጉ ሲያስረዱም፤ እስካሁን በነፃነት እየሰሩ እንደሆነና በምርመራቸው ጣልቃ የገባባቸዉ እንደሌለ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልፀዋል፡፡

Read 4057 times Last modified on Saturday, 18 May 2013 10:39