Saturday, 18 May 2013 10:25

ኮሚሽኑ በሁለት ሳምንት ውስጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሠርት ታዘዘ

Written by 
Rate this item
(32 votes)
  • ክሳት የሚታይባቸው አቶ መላኩ፤ “ያለመከሰስ መብቴን ትቼዋለሁ” አሉ፡፡
  • “ፀሐይና ነፋስ በማይገባበት ክፍል ለብቻዬ ታስሬያለሁ” - አቶ መላኩ
  • “በስርዓቱ መሰረት ችግሮችን ለመፍታት እንጥራለን” - ማረሚያ ቤት
  • የተጠርጣሪዎች ቁጥር 31 ደርሷል፤ ሰኞ ፍ/ቤት ይቀርባሉ

የሚኒስትሮች ካቢኔ አባል የሆኑት የጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተርና ምክትላቸውን ጨምሮ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ታዋቂ ባለሃብቶች ፍ/ቤት ሲቀርቡ የሰነበቱ ሲሆን፤ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሁለት ሳምንት ውስጥ ምርመራውን አጠናቅቆ ክስ እንዲመሰርት ፍ/ቤት አዘዘ፡፡ የዋስ መብት ያልተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎች፣ ከጠበቃ ጋር የመገናኘት መብታችን እንዲከበር ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ማረሚያ ቤት ፈቃደኛ አልሆነም በማለት አማርረዋል፡፡ በሦስት የምርመራ መዝገብ ከፍሎ ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍ/ቤት ያቀረበው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ በአንደኛው መዝገብ ሰባት ተጠርጣሪዎችን አካትቷል፡፡

ከአሁን ቀደም አራጣ በማበደር፣ ታክስ በማጭበርበርና በኮንትሮባንድ ንግድ ከተከሰሱ ሰዎች ጉቦ ተቀብለው ክስ እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል ጭብጥ ዙሪያ የምርመራ መዝገብ የተከፈተባቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡ አቶ መላኩ ፋንታ - የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ እሸቱ ወልደሰማያት - የባለስልጣኑ የአቃቤ ህግ ዳሬክተር አቶ መርክነህ አለማየሁ - የባለስልጣኑ የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም - የቃሊቲ ጉምሩክ ሃላፊ አቶ ከተማ ከበደ - የኬኬ ኩባንያ ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ - የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ - የህክምና ባለሙያ ሰባቱ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት በቀረቡበት የምርመራ መዝገብ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ጋር ያደረጉት የቃል ክርክር፣ በዋስ መብትና መቼ ክስ መቅረብ አለበት በሚል ጥያቄ ዙሪያ ነው። አቶ መላኩ ፋንታ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት መከራከሪያ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

የምክር ቤት አባል እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በቀር ያለመከሰስ መብቱ ሳይነሳ መታሰር የለበትም ብለዋል - የአቶ መላኩ ጠበቃ፡፡ መንግስት የሚያውቀው ህመም እንዳለባቸውና የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን አቶ መላኩ ጠቅሰው፤ ህክምናው በማረሚያ ቤት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጠበቃቸው እና ከአማካሪያቸው ጋር ለመገናኘት እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ፣ የሁሉም ተጠርጣሪዎች ጥያቄ ነው፡፡ ከጠበቃና ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት መብታቸውን በሚመለከት ተጠርጣሪዎቹ አቤቱታ ያቀረቡት በመጀመሪያው እለት ነበር፡፡ ፍ/ቤቱም የተጠርጣሪዎችን ጥያቄ በመቀበል፤ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የተጠርጣሪዎችን መብት እንዲያከብሩ በማሳሰብ ከወዳጅ ቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ ማድረግ እንዳለባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡ የአካል ጉዳተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው አቶ መርክነህ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ግን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ የለም፡፡

የአቶ መላኩ ያለመከሰስ መብትን በሚመለከት ደግሞ፣ ተጠርጣሪው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለአርብ እንዲያቀርቡ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ አርብ ዕለት የቀረቡት አቶ መላኩ የምክር ቤቱ አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካቀረቡ በኋላ ጓደኞቼ እንደሚሆኑት ለመሆን ያለመከሰስ መብቴን ላለመጠቀም ወስኛለሁ ብለዋል - አቶ መላኩ፡፡ የፀረ- ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ወደ ፍ/ቤት ባቀረባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት ሲጠይቅ፣ ተጠርጣሪዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ የቤትና የቢሮ ብርበራ አካሂዶ ስለጨረሰና ምርመራ አጠናቅቄአለሁ ብሎ ስለተናገረ ተጨማሪ ቀን ሊፈቀድለት አይገባም ብለዋል - ተጠርጣሪዎች፡፡ መርማሪው ቡድን በበኩሉ፤ ክስ ለመመስረት በቂ ማስረጃ አሰባስቤያለሁ አልኩ እንጂ ምርመራ ጨርሻለሁ አላልኩም በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

ፍ/ቤቱ የመርማሪውን ቡድን ጥያቄ በመቀበል፣ ከወንጀሉ አዲስነት፣ ውስብስብነትና ስፋት አንፃር 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅጃለሁ ብሏል፡፡ በተመሳሳይ ክስ በሁለተኛው መዝገብ ሰኞ ከሰዓት ፍ/ቤት የቀረቡት የባለስልጣኑ ምክትል ዳሬክተር አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ አስራ አንድ ተጠርጣሪዎች ቢሆኑም፣ በፌደራል ፖሊስና ደህንነት ሃይሎች ክትትል በቁጥጥር ስር የዋሉት የባለስልጣኑ የወንጀል ምርመራ ዳሬክተር አቶ ተወልደ ብስራት 12ኛ ተጠርጣሪ ሆነው በማክሰኞ ችሎት ተካተዋል፡፡ በዚህ መዝገብ የተካተቱት ባለስልጣናትና ባለሃብቶች አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ነጋ ገ/እግዚያብሄር፣ አቶ ምህረትአብ አሰፋ፣ አቶ ሙሴ ጋሻው፣ አቶ አሞኘ ታገሰ እንዲሁም የአቶ ገ/ዋህድ ባለቤት ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋዬ ከነእህታቸው ወ/ሮ ንግስቲ ተስፋዬ ይገኙበታል - ወ/ሮ ንግስቲ ልጅ ሃብታሙ ገ/መድህን ጭምር፡፡ ከአንደኛ እስከ 8ኛ የተጠቀሱት ያልተፈቀደ ሲሚንቶ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች፣ ካሁን ቀደም በኮንትሮባንድ ንግድ የተከሰሱ ሰዎችን ከክስ ነፃ እንዲሆኑ አድርገዋል ተብለዋል፡፡ ቀሪዎቹ ሦስት ታሳሪዎች የአቶ ገ/ዋህድ ባለቤትና ቤተሰብ ናቸው - ሰነድ በማሸሽና በመደበቅ የተጠረጠሩ፡፡

አቶ ገ/ዋህድ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የቃል ክርክር ላይ የመንግስት ሚዲያ ዘገባዎች ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የተጠረጠርኩበት ጉዳይ በፍርድ ሂደቱ የሚጣራና እልባት የሚያገኝ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየእለቱ ስሜን የሚያጎድፍ ዘገባ እያቀረበ ነው በማለት ዘገባዎቹ እንዲታገዱላቸው ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ትዕዛዝ የለም፡፡ ባለቤቴ እና የቤተሰብ አባላት በመታሰራቸው ልጆቼ የት እንዳሉ አላውቅም ያሉት አቶ ገ/ዋህድ፤ ባለቤቴ የፈፀመችው ወንጀል የለም በማለት እንዲለቀቁላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን እሳቸው መከራከር የሚችሉት ለራሳቸው ብቻ መሆኑን በመግለፅ ጥያቄያቸውን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ ይሁንና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በኮ/ል ሃይማኖት ክስ ላይ አስተያየት እንዲሰጥበት ፍ/ቤት አዟል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ በበኩሉ፤ ኮ/ል ሃይማኖት፣ ወ/ሮ ንግስቲ እና ልጃቸው ለምን እንደታሰሩ ለማስረዳት በሰጠው ምላሽ፣ የአቶ ገ/ዋህድ ሰነዶችን የማሸሽና የመደበቅ ድርጊት ፈጽመዋል ብሏል፡፡ በሙስና የተጠረጠረን ግለሰብ ሰነድ ማሸሽና መደበቅ ራሱ፣ በሙስና ክስ የሚታይ ነው ብሏል - መርማሪው ቡድን፡፡

ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲለቀቁና ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ለመርማሪው ቡድን የ14 ቀናት ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ በሶስተኛው መዝገብ የናዝሬት ጉምሩክ ስራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ ኮንትሮባንድ የማስገባትና የመተባበር ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ መርማሪዎችና ባለሃብቶች 6 ናቸው፡፡ ስራ አስኪያጁ አቶ መሃመድ ኢሳ፣ ሰይፈ ንጉሴ፣ ዘሪሁን ዘውዴ፣ ማርሸት ተስፋዬ፣ ሙሉቀን ተስፋዬ እና ዳኜ ስንሻው ሰኞ እለት ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ፤ ከአማካሪ ጠበቆቻቸው ጋር ተወያይተውና ለቃል ክርክር ተዘጋጅተው እንዲመጡ ተነግሯቸው ነበር፡፡ ይሁንና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ስላልተፈቀደላቸው ማረሚያ ቤቱ በፍ/ቤት ትዕዛዝ መሰረት ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ መፍቀድ እንዳለበት ተገልፆለት እንደገና ለሐሙስ ግንቦት 9 ቀን የቃል ክርክሩ እንዲካሄድ ተቀጥሯል፡፡

ሁለተኛ መዝገብ የተከሰሱት በእነ አቶ ገ/ዋህድ ጉዳይም ማረሚያ ቤቱ ጠበቆች እንዲገቡ ባለመፍቀዱ፤ ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር ሳይማከሩ ነበር ፍ/ቤት የቀረቡት፡፡ እዚያው ፍርድ ቤቱ ውስጥ ነው፣ ለ10 ደቂቃ ያህል ተመካክረው የቃል ክርክራቸውን እንዲቀጥሉ የተደረገው፡፡ ጠበቆች ከተጠርጣሪዎች ጋር እንዲገናኙ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ለምን በማረሚያ ቤት ተፈፃሚ እንዳልተደረገ ኮማንደር አበበ ብርሃኔ ወደችሎት ቀርበው እንዲያሰረዱ ታዘዋል፡፡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልነት ማረጋገጫ ይዘው በመቅረብ ያለ መከሠስ መብታቸውን እንዲያስረዱ ለትናንት ተቀጥረው የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ፤ ትናንት ከሰዓት በኋላ ለተሰየመው ችሎት ማስረጃውን አቅርበዋል፡፡ የመክሳትና የመገርጣት ምልክት የሚታይባቸው አቶ መላኩ፤ ያለመከሠስ መብታቸውን መጠቀም እንደማይፈልጉ በመግለፅ ጉዳያቸው ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

“ያለመከሰስ መብቴን ትቼዋለሁ፤ እንደ ጓደኞቼ እሆናለሁ” ብለዋል፡፡ የፀረ ሙስና መርማሪ ቡድን በበኩሉ፤ አቶ መላኩ በ2000 ዓ.ም ምርጫ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ ቢመረጡም ዘንድሮ በሚያዝያ ወር በተካሄደው ምርጫ ስላልተመረጡ ያለመከሰስ መብት የላቸውም ብሎ ተከራክሯል፡፡ ፍ/ቤቱ የመርማሪውን ቡድን መከራከሪያ ባይቀበለውም፤ አቶ መላኩ በራሳቸው ፈቃድ ያለመከሰስ መብታቸውን በመተዋቸው ሂደቱ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ የአቶ መላኩ ጠበቃ ትናንት እንደገና ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ደንበኛቸው በማረሚያ ቤት ጨለማ ቤት እንዲቀመጡ ከመደረጉም በላይ ምግብና መድሃኒት በአግባቡ እየቀረበላቸው አይደለም ብለዋል፡፡ ጠበቃው አክለውም፤ አቶ መላኩ ያጋጠማቸው የህመም አይነት ከኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች አቅም በላይ እንደሆነ በመንግስት የሚታወቅ በመሆኑ የተሻለ ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

ህክምናውን በቶሎ ካላገኙ ለህይወታቸው አስጊ መሆኑን በመግለጽ ጭምር፡፡ ሌላው በጠበቃው የቀረበው ቅሬታ ደንበኛቸው ከቤተሰቦቻቸው፣ ከልጆቻቸው እና ከባለቤታቸው እንዲሁም ከጠበቃቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል የሚል ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች ከጠበቆች ጋር እንዲገናኙ በፍ/ቤት የተላለፈው ማሳሰቢያ ለምን ተፈፃሚ እንዳልሆነ ማረሚያ ቤቱ እንዲያስረዳ በመታዘዙ ኮማንደር ብርሃኑ አበበ ትናንት ፍ/ቤት ፊት ቀርበዋል፡፡ “ጠበቃው ደንበኛቸው በጨለማ ክፍል ተቀምጠዋል ያሉትን እቃወማለሁ በማረሚያ ቤቱ ጭለማ የሚባል ክፍል የለም” ያሉት ኮንደር ብርሃኑ፣ ጤናን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ተጠርጣሪዎችን የሚያክም ክሊኒክ አለ፡፡ ከዚያ ካለፈም ስርአቱ በሚፈቅደው መሠረት ሌላ ቦታ ሊታከሙ ይችላሉ፡፡ እንደተባለው ሣይሆን መድሃኒት ተገዝቶላቸዉ ተጠቅመዋል” ብለዋል፡፡ “ከቤተሠብ ጥየቃ እንዲሁም ከጠበቆችና ደንበኞች ግንኙነት ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሮብኛል ብሎ የጠየቀ የለም፣ እኛም አሠራሩ በሚፈቅደው መሠረት፤ ህገ መንግስቱ በሠጣቸው መብት ተጠቅመው እንዲገናኙ እንፈልጋለን” ብለዋል ኮማንደር ብርሃኑ፡፡ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚጥሩ ኮማንደር ብርሃኑ ለፍርድ ቤቱ ቃል ገብተዋል፡፡

አቶ መላኩ ፈንታ በበኩላቸው፤ ስርአቱ ትክክል ሆኖ ሣለ፣ የአፈፃፀም ችግር በማረሚያ ቤቱ እንዳጋጠማቸው ገልፀው፤ “የህክምና ጉዳይ ጠይቄያለሁ፡፡ መድሃኒቱ ውጪ ይገዛ ቢባልም በተባለው ቀን አይደለም የደረሠልኝ፡፡ የታሠርኩት ጭለማ ቤት ሳይሆን አንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ነው፡፡ ፀሃይና አየር አላገኝም፤ ለሽንት ብቻ እንድወጣ ይፈቀድልኛ” ብለዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ የቀረቡበትን ቅሬታዎች እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ፤ ለግንቦት 19 ቀን ቀጠሮ እንደተያዘ ፍ/ቤቱ ገልጿል፡፡ በተመሣሣይ ከጠበቆቻቸዉ ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡና የቃል ክርክራቸውን ትናንት እንዲያከናውኑ ተቀጥረው የነበሩት በእነ አቶ መሃመድ ኢሣ መዝገብ የተከሠሡት 6 ግለሠቦች፤ በማረሚያ ቤቱ ባለመቅረባቸው አቃቤ ህግ ሠኞ ግንቦት 12 ቀን 4ኛ መዝገብ ከሚከፈትባቸው ከእነ ዳዊት ኢትዮጵያ ጋር እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሠጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ በተጠርጣሪነት 7 ተጨማሪ ግለሠቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ እነሡም አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ ፍፁም ገ/መድህን፣ ማሞ ኪሮስ፣ አለልኝ ተስፋዬ፣ አሸብር ተሠማ፣ ማሞ አብዲ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በተጠርጣሪነት የያዛቸው ግለሠቦች ቁጥርም ከ25 ወደ 32 በማደጉ 4ኛ የምርመራ መዝገብ ይከፈታል ተብሏል፡፡

Read 7234 times