Saturday, 18 May 2013 11:00

አገልግሎት ፍለጋና ‘አንታይ አሲድ’…

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታቸሁሳ!

ስሙኝማ…እኔ የምለው…የሸሻችሁት ነገር በየቦታው ሲመጣባችሁ አያናድዳችሁም! በተለይ የህዝብ ትራንስፖርት መኪናዎች ውስጥ… አለ አይደል… ሰላም የማይሰጣችሁን ነገር ስትሰሙ… “የት ብሄድ ነው ሰላሜ የማይረበሽብኝ!” አያሰኛችሁም? የምር…ለምሳሌ መስማት የማትፈልጉት የሬድዮ ፕሮግራም አለ እንበል፡፡ ቤት ውስጥ እሱን ፕሮግራም የከፈተ የቤተሰበ አባል እንደ ‘ፐብሊክ ኤነሚ ነምበር ዋን’ ይቆጠራል፡፡ ታዲያላችሁ…የሆነ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገብታችሁ ቁጭ እንዳላችሁ ያ ፕሮግራም በሰፊው ይለቀቅላችኋል፡፡ “እሱን ፕሮግራም ለውጥ” አትሉት ነገር የሚወዱት ሰዎች እዛው ታክሲ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እናላችሁ በሦስት ብር ከሰባ መንገድ የሠላሳ ሰባት ብር ‘አንታይ አሲድ’ ገዝታችሁ ትገባላችሁ፡፡ ወይ ደግሞ የሆነ የሙዚቃ ካሴት ተከፍቷል፡፡

ታዲያ ካሴቱ ላይ ያሉት ዘፈኖች በሙሉ የሾፌሩ የ‘አገሩ ዘፈኖች’ ይሆናሉ፡፡ እና ሾፌሩ “የአገሬ ለምለም መስክ ታወሰኝ…” ምናምን ታወሰኝ ከሚለው ዘፈን ጋር አብሮ ይዘፍናል፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ያው ሁላችን የትውልድ አካባቢያችንን “ለምለሟ…” “አረንጓዴዋ…” “የምድር ገነት…” ምናምን ማለት እንወዳለን፡፡ ቅልጥ ያለ ‘ሚስኢንፎርሜሽን’ ይላችኋል ይሄ ነው፡፡ አሀ ልክ ነዋ…የአንዳንዶቻችን የትውልድ መንደር ደረቅና አቧራ ከመሆኑ የተነሳ እኮ ዘመዶቻችን አረንጓዴ ቀለምን የሚያወቁት በኢትዮዽያ ባንዲራ ላይ ብቻ ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ…) ገንዘባችሁን ከፍላችሁ በምትንቀሳቀሱበት ታክሲ የማትፈልጓቸውን ነገሮች እያቃራችሁም ለመዋጥ ትገደዳላችሁ፡፡ እናማ… አስቸጋሪ ነው፡፡

እናማ በየቦታው ስትሄዱ የሸሻችሁትን ነገር እንድታዩ ወይም እንድትሰሙ ትገደዳላችሁ፡፡ ኮሚኩ ነገር እነኛ ነገሮች ከስፍራው ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ አንዳንድ ቦታማ ከሌኒን ቤተመንግሥት በስጦታ መጥተው የተረሱ የሚመስሉ መፈክሮች ግድግዳ ሞልተው ያፈጡባችኋል፡፡ የምር ግራ የሚገባኝ ነገር…ዓለም የወዝ አደሮች መሆኗ ሲቀር (እንክት አድርጐ ነዋ!) የመፈክር ለውጥ አይደረግም እንዴ! (በወዲያኛው ዘመን…“ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናውላለን” የሚለውን መፈክር አራት ኪሎ ተሰቅሎ ሲያዩ “ድንቄም!” ያሉት ሰውዬ ሸቤ ገብተው ነበር ይባላል፡፡ ዘንድሮ “ድንቄም!” የሚያስብሉ መአት መፈክሮች አሉ፡፡ “ድንቄም!” ማለቱ…አለ አይደል…“ደግሞ ከእነማን ጋር ያስፈርጀን ይሆን!” እየተባለ ሁሉም ነገር ‘ሆድ ውስጥ’ ተከርችሞበት ቀረ እንጂ! እናላችሁ…ገንዘባችሁን ከፍላችሁ አገልግሎት የምትፈልጉበት ቦታ ሁሉ የሸሻችሁት ነገር አለቦታው መጥቶ ይደነቀርባችኋል፡፡

ቀሺሙ ምግብ ሁሉ የሙሉ ልብስ ዋጋ በሚያወጣበት በዚህ ዘመን ለመመገብ አንዱ ሬስቱራንት ትገባላችሁ፡፡ የቤቱ ባለቤቶች የፈለጉትን ሙዚቃ እስከጥግ ለቀውታል፡፡ እናንተ ምግባችሁን በሰላም፣ ጭቅጭቅ ምናምን በሌለበት ሁኔታ ነው መብላት የምትፈልጉት፡፡ እናላችሁ… የሆነ “ጉድ ስላደረግሽኝ የእጅሽን አትጪ…” ምናምን የሚል ‘ደምፕ’ ያደረገቻችሁን እንትናዬን (ነው የሚባለው… አይደል!) የሚያስታውስ ዘፈን እያምባረቀ ምግቡ እንዴት ብሎ ከጉሮሮ ይወርዳል! አይደለም አጥንቱ ሊጋጥ፣ አጥሚቱም አይወርድ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ‘ደምፕ’ የመደራረግን ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ፡፡ ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ‘ደምፕ’ መደረግ ቀርቷል አሉ፡፡ እናላችሁ…ነገርዬው እንደ አውሮፓ አሰልጣኞች ነገር ሆኗል አሉ፡፡

አለ አይደል…ማንቺኒ ዘንድሮ ማን ሲቲ፣ ለከርሞ ሞናኮ ደግሞ በሌላኛው እንደገና ማን ሲቲ ሊመጡ ይችላሉ፡ እና በዘንድሮ ግንኙነት “የአገሬ ወፍ ጠራችኝ…” ብላ በዛው ሄዳ የምትቀር እንትናዬ የለችም ይላሉ፡፡ ጨዋታው “የወሰደ መንገድ ያመጣል መልሶ…” አይነት ሆኗል፡፡ የእነ እንትናን ኪስ ይጭነቀው እንጂ ምን ችግር አለ! እናላችሁ…ይሄ የሚኒባሶች ነገር…አርጀት ያሉ ሚኒባሶች ወላ ሬዲዮ፣ ወላ ካሴት ማጫወቻ ስለሌላቸው ይመቹኛል፡፡ ሌሎች የሚታዩ ነገሮች ቢኖሩ የማርሹ እጀታ ተነቅሎ እንዳይወድቅ ጠፍንጎ ያሰረው ፕላስቲክ ገመድ፣ ዳሽ ቦርዱን “ወይ ንቅንቅ!” ብሎ አጣብቆ የያዘው ፕላስተር…የተሰነጠቀው የጎን መስታወት “መለያየትማ የለም!” በሚል መሀል ለመሀል ያያዛቸው የሚያብለጨልጨው አሚር ማጣበቂያ፣ የኋላ ማሳያ መስታወቷን ‘በስቅላት እንደተቀጣች’ አይነት አንጠልጥሎ የያዛት ሲባጎ…ምናምን ናቸው፡፡ የማትፈልጉት “አፈር የፈጨሁብሽ፣ እትብቴ የተቀበረብሽ መንደሬ…ናፍቆትሽ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝ…“ምናምን አይነት ‘ሲንቴቲክ’ ዘፈን የለ…(ይሄን የሚዘፍነው ሰው የቅርብ ሞዴሏን ሌከሰስ የሚያሽከረክር እንደሆነ ግንዛቤ ይግባልንማ!) “ሳይከፍል የሚወርድ ባለጌ ነው፣” አይነት ነገር የለ…በቃ ሰላም፡፡ እናላችሁ…በየሄዳችሁበት አካባቢ ሌላ ቦታ የሸሻችሁት ነገር ይገጥማችኋል፡፡

ሠራተኞቹ ከንጉሥነት አልፈው እንደ ንጉሠ ነገሥትነት በሚቃጣቸው መሥሪያ ቤት “ደንበኛ ንጉሥ ነው” የሚል መፈክር ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ስታዩ የፈረንሣይ አብዮት አጀማመር ምክንያትን ለማወቅ ላይብረሪ መሄድ ነው የሚያምራችሁ፡፡ ልክ ነዋ…ምናልባትም ያንን አብዮት ያስነሳው ሰው “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ተብሎ ግድግዳ ላይ በተሰቀለ መፈክር ስለተሾፈበት የተናደደ ሊሆን ይችላላ! እናላችሁ…በሚኒባስ ታክሲዎች መሄድ የመንገድ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ እናማ… የተለያዩ እምነቶችን ‘መልእክቶችን’ በተለያዩ አቀራረቦች ወደ እናንተ ይለቀቁላችኋል፡፡ እናማ… እንደ ሹፌሩ እምነት የሚተላልፋላችሁ ‘መልእክት’ ያንኑ አይነት ይሆናል፡፡ የምር ግን አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ሁሉ ሰው የየራሱ እምነት አለው…መስማት የማይፈልገውን ሊሰማ መገደድ የለበትም፡፡ የምር ግን…ሚኒባስ ታክሲዎችም ሆኑ ሌሎች የህዝብ መጓጓዣዎች የቤተ እምነቶችን ሚና ሲይዙ አሪፍ አይደለም፡፡

(በተደጋጋሚ “እሱን ነገር ዝጋው…” ምናምን በሚባል አተካሮ ችግሮች ሲከሰቱ ተመልክተናል፡፡) እናላችሁ…አንዳንዶቹ በተለያዩ መልኮች የሚቀርቡት መልእክቶች “ወዮልህ! ቀኑ ደርሶልሀል፣ እኛ ዘንድ ካልተጠጋህ…” የሚሉ አይነት ‘ማስፈራሪያዎች’ ናቸው፡፡ የመሥሪያ ቤት የአለቃ “ወዮልህ!…” የቤት ውስጥ የትዳር አጋር “ወዮልህ/ወዮልሽ…” አምልጣችሁ የለየለት “ወዮልህ!... ሚኒባስ ውስጥ ሲገጥማቸሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ…አገልግሎት ፍለጋ በምትሄዱባቸው ቦታዎች የማይመቿችሁን ነገሮች ስታዩ…አለ አይደል…አስቸጋሪ ነው፡፡ ስሙኝማ…ኮንዶሚኒየም የቤት ችግር ለማቃለል አሪፍ ነው፡፡ በርካታ ‘ብሎኮች’ ያሉባቸውን የኮንዶሚኒየም መንደሮች ስታዩ… አለ አይደል… “እነኚህ ባይሠሩ ኖሮ ይሄን ሁሉ ህዝብ ምን ይውጠው ነበር!” የሚያሰኝ ነው፡፡ ግን የኮንዶሚኒየም ኑሮን አስቸጋሪ የሚያደርጉ የእኛ ባህርያት አሉ፡፡ አቅራቢያችሁ ካለው መኖሪያ ወይ የሀይማኖት መዝሙርና ሰበካ፣ ወይ ቅልጥ ያለ የ‘ፖርኖ’ ራፕ ሙዚቃ፣ ወይ በርጫ አፎቻቸውን ‘ወደ አንድ ያዋሃደላቸው’ አሥር ሰዎች በአንድ ጊዜ ሲያወሩ…ብቻ ምን አለፋችሁ የማይሰማ ነገር የለም፡፡

በየኮንዶሚኒየሙ የሚኖሩ ወዳጆቻችን የሚያወሩን ወሬዎች አንዳንዴ የሆነ ተከታታይ የቤተሰብ ‘ሶፕ ኦፔራ’ ታሪክ ይመስላሉ፡፡ እናላችሁ… በየቦታው ውጥረቱ ሲበዛባችሁ…የሸሻችሁት ነገር መገኘት በማይገባው ቦታ ሲገጥማችሁ… አለ አይደል… ጎመን ቀቅል አሉኝ ምን ጊዜ ሊበስል ይኽንን ቀንጥሼ እዘልቀው ይመስል፣ ማለት ይመጣል፡፡ የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አይደለም እኛ ግለሰቦቹ አገር ራሷ እንኳን ይህንን ‘ቀን ጥሳ ታልፍ እንደሁ’ ግራ እየገባን ያለ ጊዜ ላይ እየደረስን ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠፍቶብኝ ብፈልግ አጣሁት ንገሩልኝ ሰዎች ቀን ያገኛችሁት ይሉ ነበር አባቶቻችን ሲቀኙ፡፡ ያን ያገኛችሁ ሰዎች ለእግዚአብሔር ብዙ አቤቱታ አላቸው ብላችሁ ንገሩልንማ! ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የዚች አገር፣ ቀን የወጣልን፣ ቀን ያልወጣልን፣ ቀን የሚወጣልን፣ ‘ዕድላችን’ ሆኖ ቀን የማይወጣልን፣ ቀን እንዳይወጣልን የዓይናችን ቀለም መሰናክል የሆነብን ሰዎች ተብለን ምደባ ሊወጣልን የሚችል ይመስለኛል፡፡ እናማ አገልግሎት እናገኛለን ብለን በምንሄድባቸው ቦታዎች፣ በምንሳፈራቸው የህዝብ ትራንስፖርት መኪናዎች ለተጨማሪ የ‘አንታይ አሲድ’ ወጪ ማውጣት የለብንም! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4245 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.