Monday, 27 May 2013 13:37

12 ሰዎችን የገደለው ፖሊስ፣ በባህርዳር ተቀበረ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(6 votes)

በዲሲፕሊን ጉድለት የጦር መሳሪያ እንዳይታጠቅ ተከልክሎ ነበር ከ15 በላይ አመራሮችና የፖሊስ አባላት ምርመራ እየተደረገባቸው ነው በርካታ የግድያ ዛቻ የደረሰባት የፖሊሱ የቀድሞ ፍቅረኛ ታስራለች በባህርዳር የፍቅረኛውን እናት ጨምሮ በ12 ሰዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ከፈፀመ በኋላ የአባይ ወንዝ ውስጥ ገብቶ የሞተው ኮንስታብል ፍቃዱ ናሻ በባህርዳር ማዘጋጃ ቤት በኩል የቀብሩ ስነስርዓት እንደተፈፀመ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኛው ገልፀዋል፡፡ የሟቹ የፖሊስ አባል አስከሬን ውሃ ውስጥ በመቆየቱ ይበላሻል በሚል እዚያው ባህርዳር የአገር ሽማግሌዎችና የፖሊስ አባላት በተገኙበት በመድኒያለም ቤ/ክርስቲያን ተቀብሯል፡፡ ከግድያ ያመለጠችው የፖሊሱ የቀድሞ ፍቅረኛ ወ/ት ዘቢደር ፍቃዱ ሰሞኑን ከበርካታ ሰዎች የግድያ ዛቻ እንደተሰነዘረባትና በፖሊስ እንደታሰረች ታውቋል፡፡ ወ/ት ዘቢደር የታሰረችው በሁለት ምክንያት ነው ይላል - ፖሊስ፡፡

ለ12 ሰዎች መገደል ሰበቧ እሷ ናት በሚል ስሜት የግድያ ዛቻ እየሰነዘረባት በመሆኑ ለደህንነቷ ሲባል መታሰሯን የጠቆመው ፖሊስ፤ ከዚህ ውጭ ግለሰቧ ላይ ምርመራ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡ የ24 አመቱ ኮንስታብል ፍቃዱ ናሻ፣ የፖሊስ አባል በመሆን የተቀጠረው ከአምስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ በደቡብ ክልል ሲያገለግል ከቆየ በኋላ፤ ከአንድ አመት በፊት ወደ ባህርዳር ተዛውሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የጥምቀት እለት በአንድ መጠጥ ቤት ለመዝናናት በገባበት ወቅት ነበር ከወ/ት ዘቢደር ወርቁ ጋር ተዋውቆ ፍቅር የጀመሩት፡፡ ከሦስት ወራት የፍቅር ግንኙነት በኋላ ወ/ት ዘቢደር በምትሠራበት ቦታ የወንዶች ድብደባ እንደሰለቻት በመግለጽ እንዲያገባት ለኮንስታብል ፍቃዱ ናሻ ጥያቄ እንዳቀረበች ትናገራለች፡፡

ኮንስታብል ፍቃዱ “አሁን አቅሜ አይፈቅድም” በማለቱ ተነጋግረውና ተማምነው ለመለያየት እንደወሰኑም ታወሳለች - ዘቢደር፡፡ ከተለያዩ በኋላ፤ ከሌላ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር ታርቃ ግንኙነት እንደጀመረች ወሬ ሲሰማ ግን ኮንስታብል ፍቃዱ፣ እየመጣ አብራው እንድታድር ማስገደድና መደብደብ እንደጀመረ የምትናገረው ዘቢደር፣ በተደጋጋሚ ለፖሊስ ብታመለክትም፣ ብትታረቁ ይሻላል እየተባለ መቀጠላቸውን ገልጻለች፡፡ የኮንስታብሉ ዛቻና ድብደባ እንዲቆም ባለመደረጉ ነው ግንቦት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ወደባሰ አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊት የተሸጋገረው፡፡ ኮንስታብል ፍቃዱ፣ ዘቢደር የተከራየችበት ቤት ሄዶ ከፍቅረኛዋ ጋር መሆኗን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ካምፕ ሄደ፡፡ ከአስር ደቂቃ በኋላ ተመልሶ ሲመጣ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከሶስት ካዝና ጥይት ጋር ታጥቆ የመጣው ኮንስታብል ፍቃዱ፤ ተኩስ ሲጀምር ጐረቤት መሰብሰቡን ዘቢደር ትገልፃለች፡፡

“ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?

አንተ ህግ አስከባሪ አይደለህም ወይ?” ሲሉት ኮንስታብሉ በጓሮ በኩል ያመለጡትን ዘቢደር እና ፍቅረኛዋን ጫካ ድረስ ያሳድዳቸዋል፡፡ ግን አላገኛቸውም፡፡ በቀጥታ ያመራው ወደ እናቷ ቤት ነበር፡፡ ፊትለፊት ያገኛቸውን የዘቢደርን እናት ተኩሶ ከገደለ በኋላም የሚያስቆመው አልተገኘም፡፡ ከእናቷ ቤት ሲወጣ ከፊልድ የመጣና ቤተሰቦቹን ለማየት የጓጓ አባወራ መንገድ ላይ ያገኛል፡፡ በአንድ ጥይት መትቶ ሲጥለው አባወራው መለመን ይጀምራል፡፡ “አትግደለኝ፡፡ አንተዋወቅ፣ ቂም የለን” ቢለውም ደጋግሞ በመተኮስ ገደለው፡፡ እንዲህ ህፃን ልጅን ጨምሮ 12 ሰዎችን ሲገድል 83 ጥይቶችን ተኩሷል፡፡ ህግ አስከባሪዎች ግድያውን ለማስቆምና በወንጀለኛው ላይም እርምጃ ለመውሰድ በቂ ሙከራ አላደረጉም በማለት ትችት የሚሰነዝሩ ነዋሪዎች፣ ያን ሁሉ ጥይት ይዞ ከካምፕ እንዲወጣ መፈቀዱንም ክፉኛ ይተቻሉ፡፡ በዲሲፒሊን ጉድለት መሳሪያ እንዳይታጠቅ ተከልክሎ የነበረው ኮንስታብል ፍቃዱ ላይ በርካታ አቤቱታዎች ቀርበውበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ወንጀለኛው ያለርህራሄ ያደረሰውን ጭፍጨፋ የሰሙ የአካባቢው ፖሊሶች ሊይዙት እንዲሞክሩና ወንጀለኛው እንዳመለጣቸው ተጠቁሟል፡፡

ራቅ ያለ አካባቢም ሌሎች የፖሊስ አባሎች አግኝተውታል፡፡ ስለተፈፀመው ወንጀል ባያውቁም፤ ኮንስታብሉ የሚያሳየው ያልተለመደ ሁኔታ ጥርጣሬ ውስጥ ስለከተታቸው፣ የያዘውን መሣሪያ እንዲያስረክባቸው ጠይቀውታል፡፡ ይሄኔ ነው ለማምለጥ ብሎ አባይ ወንዝ ውስጥ የገባው ይላል ፖሊስ፡፡ የ12 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ኮንስታብል ፍቃዱ፤ በዋናተኞች ሲፈለግ ቆይቶ ከአንድ ቀን አዳር በኋላ የአባይ ውሃ ላይ ተንሳፎ የተገኘ ሲሆን፣ አፍንጫው በአሳዎች ተበልቶ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል፡፡ ለጥንቃቄ ሲባልና የፖሊሱን አስከሬን እዚያው እንዳለ ህዝቡ እንዲያየው ለባህርዳር ነዋሪ ጥሪ እንዳደረገ ፖሊስ ገልፆ፤ ግንቦት 6 ቀን ጠዋት አስክሬኑ በህዝብ ከታየ በኋላ ከአካባቢው እንደተነሳ ያወሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት የቀብር ስነስርዓቱ እዚያው ባህርዳር በመድሃኒያለም ቤ/ክርስትያን እንደተፈፀመም ታውቋል፡፡ ማንኛውም የፖሊስ አባላት ግዳጅ ከሌለባቸው ወይም ለስራ ካልተሠማሩ በቀር መሳሪያ መያዝ እንደማይችሉ የገለፁት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኛው፤ ሟቹ መሳሪያ ይዞ ሲወጣ ያልከለከሉ እና ለድርጊቱ መፈፀም አስተዋጽኦ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ከ15 በላይ አመራሮችና የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

Read 3552 times