Monday, 27 May 2013 13:38

አንድነት ፓርቲ በወቅቱ የሙስና ችግር ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“የሙስና ችግር ግለሠቦችን በመያዝ አይቀረፍም፤ ችግሩ ያለው ሲስተሙ ላይ ነው” - የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ “ሙስና፣የመልካም አስተዳደርና የሠብአዊ መብት ጥሠት የግንቦት ሀያ ፍሬዎች ናቸው” - አቶ ዳንኤል ተፈራ

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) የፊታችን ማክሠኞ ግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ.ም በወቅቱ ሙስና ላይ የሚያተኩር ውይይት በጽ/ቤቱ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የኤዲቶሪያል ቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ተፈራ ለአዲስ አድማስ እንዳስታወቁት፤ ፓርቲው የውይይት መድረኩን ያዘጋጀው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገሪቱ ግልፅ ስጋት የሆነው ሙስና ለአንዴና ለመጨረሻ የሚገታበትን ትግል ለማጠናከር የህዝቡ እና የባለሙያዎች ውይይት መነሻ መሆኑን በማመኑ ነው፡፡ “ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የሠብአዊ መብት ጥሠት የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ እነዚህን የሀገር ማነቆዎች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር መወያየት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

“ሙስናና ኢኮኖሚያችን” በሚል ርዕስ የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ በሚያቀርቡት የመነሻ ፅሁፍ ላይ ባለሙያዎችና የትኛውም ኢትዮጵያዊ በመሣተፍ ለሀገሪቱ መፃኢ ዕድል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው በፓርላማ ብቸኛው የመድረክ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሠይፉ፤ “በሙስና ላይ ባለሙያ በመጋበዝ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት የነበረባቸው ሲቪል ማህበራትና ንግድ ምክር ቤቱ እንዲሁም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ነበሩ” በማለት ምላሽ የሠጡት የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ፤ ነገር ግን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የሠራ ባለመኖሩ አንድነት የውይይት መድረኩን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሙስና ችግር የህዝቡ ዋነኛ አጀንዳ እንደመሆኑ አንድነት እንደ ፓርቲ ያለውን አቋምና ህዝቡ በሙስና ዙሪያ እንዲብራራለት የሚፈልገውን ሀሣብ የማብራራትና ከህዝቡም ሀሣቦችን የመውሠድ መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ግንቦት ሀያን ለምን መረጣችሁ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ለመጠቀም እንጂ ከግንቦት 20 ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” ብለዋል - አቶ ግርማ፡፡ በአሁኑ ሠዓት ያለው የሙስና ሁኔታ ብዙ ሠው በሙስና እየተሳተፈ ስለመሆኑ ማሣያ መሆኑን ያብራሩት አቶ ግርማ፤ እዚህ አገር ውስጥ ስለ ዋጋ ንረት፣ ስለ ፍትሀዊ ያልሆነ የገበያ ስርዓት ሥናወራ ሙስና መስፋፋቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ ሙስና በኢኮኖሚው አንፃር ሲታይ ፍትሀዊ የንግድ ሥርዓትን እንደሚያዛባና አንዱን ተጐጂ ሌላውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ አሁን በግልፅ እየታየ ያለው ይሄው ስለሆነ እልባት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

“ለኢህአዴግ ሙስና ሁሉም ነገሩ ነው” ያሉት የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር፣ ከአባላት ምልመላ ጀምሮ ያለው ሂደት ቢመረመር አባላት የኢህአዴግ አባል የሚሆኑት የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ስቧቸዉ ሳይሆን ጥቅም ፍለጋ መሆኑን ገልፀው “እንደውም አብዛኛው ሠው አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ሥለሚባል ርዕዮተ አለም የሚያውቀው ነገር የለም፤ በማለት አብራርተዋል፡፡ ለምሣሌ “የኢህአዴግ ደጋፊ ነጋዴ ፎረም” የሚል ካየሽ እነዚህ ሠዎች አባል የሚሆኑት “እንዴት አድርገን ጥቅም እናገኛለን እንዴት አድርገን ጨረታ እናሸንፋለን አሊያም እንዴት አድርገን ኢህአዴግ እንዳይበላን እንከላከላለን” ብለው እንጂ ለርዕዮተ አለሙ ብለው አይደለም” ያሉት አቶ ግርማ፤ ይሄ በራሱ ሙስና መሆኑን አብራርተዋል፡፡

“ይሄን ብልሹ የሙስና ሥርዓት የዘረጋው ራሱ ኢህአዴግ እያለ አንድ መላኩንና አንድ ገብረዋህድን በማሠር ሙስናን መከላከል አይቻልም” ካሉ በኋላ፣ ዋናው የተበላሸው ነገር ሥርዓቱ እንደሆነና ሥርዓቱን የሚዘውሩት አካላት ላይ መተኮር እንዳለበት አፅንኦት ሠጥተው ተናግረዋል፡፡

Read 1923 times