Monday, 27 May 2013 13:46

የአያት ሪል እስቴት ባለቤት የ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

ከሶስት ዓመት በፊት በቫት ማጭበርበር የባንክን ስራ በመስራት፣ ለግለሠቦች በዱቤ ቤት በመሸጥና በበርካታ ወንጀሎች በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ክስ የተመሠረተባቸውና እስካሁንም በእስር ላይ የሚገኙት የአያት አክሲዮን ማህበር መስራችና ባለቤት አቶ አያሌው ተሠማ የ12 ዓመት ፅኑ እስራትና 3.2 ሚሊዮን የገንዘብ ቅጣት ተፈረደባቸው፡፡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት በተጠቀሱት ወንጀሎች ጉዳያቸው ሲታይ የከረሙት 1ኛ ተከሣሽ አያት አክሲዮን ማህበርና ባለቤቱን ጨምሮ በዚሁ መዝገብ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ሁለት ግለሠቦችም ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2005 በዋለው ችሎት ተፈርዶባቸዋል፡፡

ከአያት አክሲዮን ማህበር ቀጥሎ በሁለተኛነት የተከሠሡትና የማህበሩ መስራች የሆኑት አቶ አያሌው ተሠማ እጃቸው ከተያዘበት ጀምሮ የሚታሠብ የ12 ዓመት ፅኑ እስራትና 3 ሚሊዮን 235ሺህ 543ብር ከሀምሳ ሳንቲም፣ ሶስተኛ ተከሣሽ ዶ/ር መሀሪ መኮንን አካሉ የ12 ዓመት ፅኑ እስራትና 436ሺህ 969 ብር ከ60 ሣንቲም ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን አራተኛው ተከሣሽ አቶ ጌታቸው አጐናፍር ደግሞ የ10 ዓመት ፅኑ እስራትና የ411 ሺህ 969 ብር ከ60 ሳንቲም ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

እነዚህ ተከሣሾች በበርካታ ወንጀሎች ተከሠው ሲከራከሩ የቆዩ ሲሆን በተወሠኑት ክሶች ነፃ መባላቸውም ታውቋል፡፡ ከትላንት በስቲያ በከፍተኛው ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ተከሣሾቹ ጥፋተኛ ከተባሉባቸዉ ጉዳዮች መካከል የባንክና የብድር አዋጅን በመተላለፍ፣ ሠዎች የመኖሪያ ቤት በዱቤ እንዲያገኙ በማድረግና የባንክን ሥራ በመስራት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከላይ የተገለፀው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

Read 3375 times