Saturday, 01 June 2013 12:42

የአይፎን እና የጋላክሲ ጦርነት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በወር 140 ሚ. ሞባይል ስልኮች ተሽጠዋል - ግማሾቹ (70 ሚ) እንደ አይፎንና ጋላግክሲ የመሳሰሉ ‘ስማርትፎን’ ናቸው። በስማርትፎን ሽያጭ ዘንድሮ መሪነቱን ከአፕል የተረከበው ሳምሰንግ፣ ከጋላክሲ ሞባይሎች ሽያጭ በየወሩ በአማካይ 8 ቢ. ዶላር ገደማ ገቢ እያገኘ ነው። የአፕልም ገቢ ተቀራራቢ ነው፤ ወደ ስምንት ቢ. ዶላር የሚጠጋ ገቢ ከአይፎን ሞባይሎቹ ሽያጭ በማስገባት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የሳምሰንግ ሩጫ የሳምሰንግ ስኬት ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ በእርግጠኛነት የሚገልፁ ዘገባዎች ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ አዲሱ ‘ጋላግሲ ኤስ4’ ከፍተኛ ተወዳጅነት ማግኘቱን ይጠቅሳሉ። በእርግጥ ነባሩ ጋላግክሲ ኤስ3 ሞባይልም፣ ዋነኛ የአይፎን ተቀናቃኝ ለመሆን በመቻሉ፣ ሳምሰንግ በሞባይል ምርት የመሪነቱን ደረጃ እንዲቆናጠጥ ረድቶታል።

ከወር በፊት ለገበያ የቀረበው ኤስ4 ግን፣ ገና ካሁኑ ሪከርድ ሰብሯል። ኤስ3 ለገበያ የቀረበ ጊዜ፣ አስር ሚሊዮን ሞባይሎችን ለመሸጥ ሁለት ወራት ፈጅቶበት ነበር። ኤስ4 ግን በአንድ ወር ውስጥ ነው አስር ሚሊዮን የተቸበቸበው። በሽያጭ መጠን መሪነቱን መያዝ ግን፣ በአትራፊነትም አንደኛ መሆን ማለት አይደለም። ሳምሰን በየወሩ ከ2 ቢ. ዶላር በላይ ትርፍ እያገኘ እንደሆነ የገለፁ የሰሞኑ ዘገባዎች፣ አፕል በየወሩ የሚያገኘው ትርፍ ከ3 ቢ. ዶላር በላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሳምሰንግና የአፕል ኩባንያዎች ስኬት፣ ወደፊትም እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል - የስማርትፎኖች ገበያ እየተስፋፋ ነውና።

ከመደበኛ ሞባይል ወደ ስማርትፎን ላለፉት አምስት አመታት በአይፎን መሪነት በፍጥነት እያደገ የመጣው የስማርትፎን ገበያ፣ ዘንድሮ ከሌላው መደበኛ ሞባይል ጋር በቁጥር ለመስተካከል እንደበቃ ጋርተር የተሰኘ የጥናት ተቋም ገልጿል። ካለፈው የጥር ወር ወዲህ፣ በመላው አለም በየወሩ 140 ሚ. ገደማ ሞባይሎች ለተጠቃሚ እንደተሸጡ ጋርተር ጠቅሶ፣ ከእነዚህም መካከል ሰባ ሚ. ያህሉ መደበኛ ሞባይሎች ሲሆኑ ሰባ ሚ. ያህሉ ደግሞ ስማርትፎን ናቸው ብሏል። በመደበኛ ሞባይልና በስማርትፎን ገበያ፣ በጥቅሉ ሳምሰንግ በየወሩ 35 ሚ. ገደማ ሞባይሎችን ሲሸጥ፣ ከመሪነት የወረደው ኖኪያ በወር 21 ሚ. ሞባይሎችን ሸጧል። አፕል 13ሚ.፣ ኤልጂ 5ሚ.፣ ከቀድሞ ቦታው አንድ ደረጃ የወረደው ዜድቲኢ ከ4.5 ሚ በላይ፣ ደረጃውን እያሻሻለ የመጣው ሁዋዌ ደግሞ ወደ 4 ሚ. ገደማ ሞባይሎችን ለገበያተኛ አድርሰዋል። የኩባንያዎቹ ስኬታማነት የሚለካው ግን በጥቅል የሞባይል ሽያጭ ሳይሆን በስማርትፎን ሽያጭ ነው - ስማርትፎን ከፍተኛ ገቢ ያስገኛልና። የስማርትፎን ፉክክር በስማትፎን ገበያውን የሚመሩት፣ የጋላክሲ አምራቹ ሳምሰንግ እና የአይፎን አምራቹ አፕል ናቸው። ሳምሰንግ፣ የጋላግሲ ኤስ ሞባይል ምርቱን ባለፈው አመት በሃምሳ በመቶ በማሳደግ፣ አሁን በየወሩ 23 ሚ. ገደማ ሞባይሎችን እየሸጠ መሆኑን ጋርተር ገልጿል።

አፕልም እንዲሁ፣ ምርቱን በማስፋት በየወሩ 13 ሚ. አይፎኖችን ለተጠቃሚዎች ሸጧል። የስማርትፎን ምርታቸውን በእጥፍ ያሳደጉት ኤልጂ እና ሁዋዌ ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን የተዘጋጁ ይመስላሉ። ኤልጂ በወር ከ3 ሚ. በላይ፣ ሁዋዌ ደግሞ ወደ 3 ሚ. የሚጠጉ ሞባይሎችን ገበያ ላይ እያዋሉ ነው። በየእለቱ የሚሰራጩ መረጃዎችና ዘገባዎች ሲታዩ፣ የስማርትፎን ውድድር እየበረታ እንደሚሄድ ያመለክታሉ። የካናዳው ብላክቤሪ እና የታይዋኑ ኤችቲሲ፣ በያዝነው ወር የስማርትፎን ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ የአለምን ትኩረት ስበዋል። ኖኪያና ሶኒም እንዲሁ በአዳዲስ ምርቶች ገበያውን ለመጋራት እየጣሩ ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ በቅናሽ ዋጋ ስማርትፎን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ከየአገሩ ወደ ፉክክሩ መግባት ጀምረዋል። ሳምሰንግና አፕል፣ ለዚህ ውድድር ተዘጋጅተዋል። ሳምሰንግ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው፣ ከጋላክሲ ኤስ4 በዋጋ ግማሽ ያህል የሚቀንስ ሚኒ ኤስ4 ለገበያ አዘጋጅቷል። አፕልም እንዲሁ፣ ሚኒ አይፎን5 ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከህዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል ሞባይል በመላው አለም በአጠቃላይ ወደ 7 ቢሊዮን የሚጠጉ የሞባይል ስልክ መስመሮች አገልግሎት ላይ ውለዋል። በአፍሪካም 550 ሚ. ያህል ሞባይሎች ለተጠቃሚዎች ደርሰዋል - በአማካይ ለሶስት ሰዎች ሁለት ሞባይል እንደማለት ነው (64%)። የኢትዮጵያ፣ ገና የዚህን ግማሽ ያህል እንኳን አልደረሰም። በየአመቱ 1.7 ቢሊዮን ያህል ሞባይሎች ለገበያ እንደሚቀርቡ የገለፀው ጋርተር፣ የስማርትፎን ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ዘንድሮ ከ800ሺ በላይ እንደሚደርስ ጠቁሟል። ግማሽ ሞባይል፣ ግማሽ ላፕቶፕ (ታብሌት) ሳምሰንግ በስማርትፎን ሽያጭ ገበያውን መምራት ቢጀምርም፣ በ‘ታብሌት’ ገበያ ግን የአፕል አይፓድ አልተቻለም። አፕል፤ በወር ውስጥ ወደ ከ6 ሚ. ላይ አይፓዶችን በመሸጥ የአምናውን ሪከርድ ሰብሯል። ሳምሰንግ ወደ 3 ሚ. ገደማ እየሸጠ ይገኛል።

Read 5251 times