Print this page
Saturday, 01 June 2013 13:47

ክዋሜ ንክሩማህ - ከነፃነትና ከአንድነት ትግሉ በስተጀርባ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ የነፃነት፣ የህብረትና የአንድነት የትግል ታሪክ ውስጥ አንፀባራቂ ቦታ ከያዙት የአፍሪካ አንድነት መስራች አባት መሪዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ናቸው ስለሚባሉት የጋናው የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የክዋሜ ንክሩማህን ግለ ስብዕና የሚያስተዋውቅ ጽሑፍ ማቅረቤ ይታወሳል። የአሁኑ ጽሑፌ የክዋሜ ንክሩማህን ከነፃነትና ከአንድነት ትግሉ በስተጀርባ የነበረ ማንነታቸውን በመጠኑ ያስቃኛል፡፡ ክዋሜ ንክሩማህ፤ አፍዝ አደንግዝ የሆነ ግርማ ሞገስና ከማንኛውም ሰው ጋር በቀላሉ የመግባባት አስደናቂ ችሎታ ቢኖራቸውም ያለ አንድ የቅርብ ጓደኛና ሚስጥረኛ አጋር እንደ በረዶ በሚቀዘቅዝ ብቸኝነት የሚኖሩ ሰው ነበሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በስልጣን ላይ በነበሩበትም ሆነ ከዚያም በፊት ባሳለፉት ህይወታቸው ጥቂት የእረፍት ጊዜያቸውን ማሳለፍ የሚፈልጉት ከቅርብ የስራና የትግል ጓዶቻቸው ጋር ሳይሆን ከሴቶችና ከኮረዶች ጋር ብቻ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ዋነኛ መዝናኛቸው ከነበረው ስራቸው ውጪ የንክሩማህ ልብ ስስ የነበረው ለሴቶች ብቻ ነው፡፡ በእርግጥም ንክሩማህ ከሴቶችና የደረሱ አፍላ ኮረዶች ጋር መቃበጥ ነፍሳቸው ነበር። እንዲህም ሆኖ ግን አለመጠን ተጠራጣሪ ሰው ከመሆናቸው የተነሳ፣ እንዲያ ከሚወዷቸው ሴቶችና ኮረዶች ጋር ጠበቅ ያለ የምር ወዳጅነት ለመመስረት እጅግ ይፈሩና ይጠነቀቁ ነበር፡፡ ትዳር ለመያዝ የሚሆን የአንዲት ደቂቃም እንኳ ጊዜ የለኝም በማለት በግልጽ ያወጁበት ዋነኛው ምክንያትም ይሄው ተጠራጣሪነታቸውና ፍርሃታቸው ነበር፡፡

ክዋሜ ንክሩማህ፣ ያኔ አብረዋቸው ይቃበጡ ከነበሩት በርካታ ሴቶችና ኮረዶች መካከል የተለየ ወዳጅነት መመስረት የቻሉት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የጋና አገረ ገዢ የነበሩት የሰር ቻርለስ አርደን ክላርክ ፀሐፊ ከነበረችው ወጣት እንግሊዛዊት ኤሪካ ፓወል ጋር ብቻ ነበር፡፡ ንክሩማህ ከሴቶች ጋር ዋዛ ፈዛዛ መውደዳቸውን አሳምራ የምታውቀው ኤሪካ ፓወል፣ ባልገመተችው ሁኔታና ጨርሶ ባልጠበቀችው ቀን በመኖሪያ ቤታቸው በክርስቲያንቦርግ ግንብ ራት ሲጋብዟት ግራ ከመጋባቷ የተነሳ ምን ብላ መመለስ እንዳለባት መወሰን አቅቷት ተቸግራና ተጨንቃ ነበር፡፡ በመጨረሻ ለአለቃዋ ለሰር ቻርለስ አርደን ክላርክ ስታማክራቸው፣ እርሳቸውም የንክሩማህን ሰብዕና ብጥርጥር አድርገው ስለሚያውቁት “ታውቂያለሽ ኤሪካ … ንክሩማህ እኮ ብቸኛ ሰው ነው፤ በጣም ብቸኛ ሰው” በማለት የቀረበላትን ግብዣ እንድትቀበል በዘወርዋሬ መክረው እንዳግባቧት የህይወት ዘመን ትዝታዋን ባሰፈረችበት መጽሐፏ ውስጥ ገልፃዋለች፡፡

በእራት ግብዣው የተጀመረው የኤሪካና የንክሩማህ ወዳጅነት፣ ቀስ በቀስ እየጠበቀ ስር መስደድ ሲጀምር ኤሪካ የሰር ቻርለስ የፀሐፊነት ስራዋን በመልቀቅ የንክሩማህ የግል ፀሐፊ ሆና ተቀጠረች፡፡ ይህንን ያየውና የሰማው ድፍን የአክራ ከተማ ነዋሪ፣ ኤሪካን የንክሩማህ ቅምጥ እንደሆነች ቢያወራባትም እርሷ ግን ግንኙነታቸው እስከተቋረጠበት እስከመጨረሻው ቀን ድረስ ሽምጥጥ አድርጋ ክዳዋለች፡፡ በሌላ በኩል፣ ደግሞ ኤሪካ ፓወል ከንክሩማህ ጋር የነበራትን ጠበቅ ያለ ግንኙነትና አብሮ ወጣ ገባ ማለት የተመለከቱ ጋናውያንና የውጭ ሀገር ዜጐች፣ ትዳር ሊመሠርቱ ይችላሉ ብለው በሰፊው ቢገምቱም ጉዳዩ ከግምት ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ የሆኖ ሆኖ አብረው ባሳለፉት የፍቅር ጊዜያት ውስጥ ንክሩማህ ፀባያቸው እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ጨርሶ የማይጨበጥ፣ ትዕግስት የለሽና፣ ግንፍልተኛ ሰው እንደሆኑ፣ አልፎ አልፎም የሚያፈቅሩትና የሚያፈቅራቸው ሰው እንደሌለ በመናገር ይነጫነጩ እንደነበር የገለፀችው ኤሪካ፤ አብረው እየተዝናኑ በነበረበት አንድ ምሽት ግን ንክሩማህ በምድር ላይ ከልባቸው የሚተማመኑባትና ለሁነኛ ምክር የሚመርጧት ብቸኛዋ ሰው እርሷ ብቻ እንደሆነች በደንብ እንደነገሯት በመጽሐፏ ይፋ አድርጋዋለች፡፡

ክዋሜ ንክሩማህ የማታ ማታም ቢሆን ትዳር ለመያዝ የሞከሩት በግማሽ ልባቸው ነበር። ለዚያውም ለትዳር የምትሆናቸውን ሴት ፍለጋ አይናቸው ያማተረው በሀገራቸው በጋና አልነበረም። የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን ጨብጠው ጥቂት ወራቶችን እንዳሳለፉ፣ አንድ ቀን ድንገት የቢሮአቸውን ስልክ አንስተው ሽርካቸው ለነበሩትና የፀረ ኮሎኒያሊዝምና ኒዎ ኮሎኒያሊዝም የትግል አጋሬ ለሚሏቸው የግብፁ መሪ ጋማል አብደል ናስር ደወሉላቸው፡፡ አጭር የወዳጅነት ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ናስር ጨርሰው ያልገመቱት፣ ያልጠበቁትና ዱብእዳ የሆነባቸውን ጥያቄ አወረዱባቸው፡፡ “ጓድ ናስር፤ እባክዎ በሀገርዎ በግብጽ ከሚገኙት ደማም ሸጋ ኮረዳዎች ውስጥ አንዷን ቆንጆ ይምረጡልኝና አግብቼ ጐጆ ልውጣ? እባክዎ ወዳጄ፤ እባክዎ ጓድ ፕሬዚዳንት፤ አንዷን ያገርዎን ልጅ ያጋቡኝና ለወግ ለማዕረግ ልብቃ” በማለት ለግብፁ ፕሬዚዳንት ጋል አብደል ናስር ተማጽኖአቸውን አቀረቡላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ይህን የትዳር ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የቅርብ የትግልና የስራ ባልደረቦቻቸው ለነበሩት ጋናውያን ባለስልጣናት ትንፍሽ አላሉም ነበር፡፡ በአፍሪካ የነፃነት ትግል ውስጥ ስመጥርና የአንድ ሀገር መሪ ከሆነ ሰው በመቶ አመታት ጊዜ ውስጥ እንኳ ቢሆን ሊቀርብልኝ ይችላል ብለው ያልገመቱት ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዚዳንት ናስር፣ ነገሩ በእጅጉ ቢያስገርማቸውም ንከሩህማን አላሳፈሯቸውም፡፡

የምንተ እፍረታቸውን የቅርብ አማካሪያቸውና የማስታወቂያ ምኒስትራቸው ከነበሩት ታዋቂው ግብጻዊ ጋዜጠኛ ሞሐመድ ሃይካል ጋር በመመካከር ፋቲያ ሪዝቅ የተባለች ቆንጆ ግብጻዊት አፈላልገው አጩላቸው። በጣት የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ብቻ በተገኙበት በመኖሪያ ቤታቸው ክርስቲያንቦርግ ግንብ በተዘጋጀ እጥር ምጥን ያለ ድግስም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ተሞሽረው ጐጆ ወጡ - ግንቦት 30 ቀን 1957 ዓ.ም፡፡ የሰርጋቸው እለትም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ምን ሊያደርጉ እንዳሰቡ ለቢሮ ፀሐፊዎቻቸውም ሆነ ረዳቶቻቸው ምንም አይነት ፍንጭ አላሳዩም። ያለወትሮአቸው በሙሉ ጥቁር ሱፍ ልብስ፣ በነጭ ሸሚዝና ቀይ የቢራቢሮ ክራቫት ሽክ ብለው ዘንጠው ያያቸው የመቶ አለቃ ሃሚልተን የተባለ ልዩ ረዳታቸው “የክርስቶስ ያለህ! ፕሬዚዳንት ልክ እንደ ሙሽራ እኮ ነው ሽክ ዝንጥ ያሉት!” ሲላቸው፣ ንክሩማህ እንኳን መልስ ሊመልሱለትና ሙሽርነታቸውን ሊነግሩት ቀርቶ፣ የወትሮ ፈገግታቸውን እንኳ ሊያሳዩት አልፈለጉም፡፡ የመዳራቸውን ዜና የሰማው እንደተቀረው ጋናዊ በብሔራዊ ራዲዮ ጣቢያው የቀትር ዜና እወጃ ላይ ነበር፡፡

ክዋሜ ንክሩማህ ከፋቲያ ሪዝቅ ጋር የፈፀሙት የጋብቻ ህይወት አብዛኛውን ጊዜ በከፍተኛ ዝምታ የተሞላ ሲሆን አልፎ አልፎ ባልና ሚስቱ ለመግባባት የሚሞክሩት በአይንና በእጅ ምልክት ብቻ ነበር። ለምን ቢሉ … ጥንዶቹ የሚግባቡት የጋራ ቋንቋ ስላልነበራቸው ነው፡፡ ባለቤታቸው ፋቲያ ሪዝቅ፣ ከአረብኛና እጅና እግሩ ከማይያዝ የተሰባበረ የፈረንሳይኛ ቋንቋ በቀር ጆሮዋን ቢቆርጧት እንግሊዝኛ የማትሰማም የማትናገርም ነበረች፡፡ ንክሩማህም “ሽኩረን” (አመሠግናለሁ) ከሚለው የአረብኛ ቃል በቀር ሌላ ነገር አይሰሙም አይናገሩም ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ፣ ከፋቲያ ሪዝቅ ጋር የመሠረቱት ጋብቻ ሶስት ልጆችን ቢያስገኝላቸውም በ1965 ዓ.ም ለቀድሞ ወዳጃቸው ኤሪካ ፓወል በፃፉት ደብዳቤ፣ የያዙት ትዳር ከብቸኝነት ስሜታቸው ጨርሶ እንዳላላቀቃቸው እውነቱን ተናዘውላታል፡፡ “ኤሪካ ሚስት ማግባት ፈጽሞ እንደማልፈልግ ታውቂያለሽ፡፡ ለእኔ ብዬ ሳይሆን ለፕሬዚዳንትነቴ ስል ብቻ ሚስት እንዳገባሁ ነግሬሽ ነበርን?” በማለት ለኤሪካ ጽፈውላታል፡፡

እንዳሉትም ከሰርጋቸው ቀን በፊት ስሟን ሰምተውትም ሆነ አይኗን አይተውት ከማያውቁት ፋቲያ ሪዝቅ ጋር የመሠረቱትን ጋብቻ ለፕሬዚዳንትነታቸው ሲሉ ብቻ አክብረውት ኖረዋል፡፡ ብቃትንና ክህሎትን በተመለከተ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ፣ የሰልፍ ረድፋቸው ልበ ብርሀንና አዕምሮ ብሩህ ከሚባሉት ተርታ ነበር፡፡ በፖለቲካ ብቃትና ክህሎታቸው በመጠቀም ፈጽሞ አይነኬና ተገዳዳሪ አልባ ይባል የነበረውን የእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ሀይል ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ የነፃነት ትግሉን በግንባር ቀደምትነት በማስተባበርና በመምራት አገራቸውን በ1957 ዓ.ም ማርች 6 ቀን ነፃነቷን እንድትጐናፀፍ አስችለዋታል፡፡ በክዋሜ ንክሩማህ የተመራው የጋና የነፃነት ትግልና ያስገኘው ውጤትም በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ይማቅቁ ለነበሩት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት መንገዱን ከፍቶላቸዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በ1960ዎቹ አመታት ጋናን ተከትለው ሀያ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓ የቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅና ነፃነታቸውን ዳግመኛ ለመቀዳጀት በቅተዋል፡፡ ይህም ለፕሬዚዳንት ንክሩማህ በወቅቱ ነፃ የወጡ የበርካታ የአፍሪካ መሪዎችን ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮትን አስገኝቶላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አክብሮትና አድናቆት በግል ከነበራቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ፍላጐትና ምኞት ጋር ተዳምሮ፣ ከሌሎች የወቅቱ የአፍሪካ መሪዎች በአስተሣሠብም ሆነ በመሪነት ችሎታ የላቁና ከሁሉም የተለየ ሚና ለመጫወት በመለኮት ተመርጠው የተቀቡ መሲህ መሪ እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ አደረጋቸው፡፡

በዚህ የተነሳም የሚመሯትን ሀገራቸውን ጋናን ከድሀና ኋላቀር ሀገርነት ወደ ኢንዱስትሪ ሀይልነት፤ የትምህርት ማዕከልና ሌሎች ሀገራት እንደርሷ ለመሆን የሚመኟት የሶሻሊስት ህብረተሠብና ሀገር ሞዴልነት ለመቀየር ቆርጠው ተነሱ፡፡ ከሀገራቸው ውጭም አፍሪካን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና፣ በወታደራዊ ሀይል ረገድ ታላቅ የሆነች፤ እንደ አሜሪካ አሊያም እንደያኔዋ ሶቪየት ህብረት የተባበረችና አንድ የሆነች ለማድረግና በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ሌት ተቀን ማለም ጀመሩ፡፡ ማርክስና ኤንግልስ ለአውሮፓ፣ ማኦ ዜዱንግ ደግሞ ለቻይና እንዳበረከተው አይነት ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ ለአፍሪካ ማበርከት የሚያስችል ልዩ ችሎታ አለኝ ብለው በእርግጠኛነት በማመናቸው “ንክሩማኒዝም” የተሰኘ የራሳቸውን ልዩ ርዕዮተ አለም በመቅረጽ በጋና በይፋ አወጁ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ወጪ በማድረግም ይህን ርዕዮተ አለማቸውን የሚያጠናና የሚያስፋፋ ትልቅ የምርምር ተቋም በስማቸው በመሠየም አቋቋሙ፡፡ ከፓርቲያቸው ቢሮዎች አንስቶ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሰራተኞች፣ የሙያና ሌሎች የሲቪል ማህበራት “ንክሩኒዝም” የተሰኘውን ርዕዮተ አለማቸውን በከፍተኛ ንክሩማሀዊ ስሜትና ተነሳሽነት በመላው የጋና ምድርና የጋና ህብረተሠብ ዘንድ በሚገባ እንዲያሰርፁ ቀጭን ትዕዛዛ አስተላለፉ፡፡ ይህን ትዕዛዛቸውን ያለ አንዳች ማንገራገርና ተቃውሞ ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን እንዳረጋገጡ፣ በፕሬዚዳንትነት ሊመሯት የቋመጡላትን የተባበረች አፍሪካን ወደ መፍጠሩ ህልማቸው ፊታቸውን አዞሩ፡፡

የሳምንት ሰው ይበለን!! “የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት (United States of Africa) አሁኑኑ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ አሁኑኑ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ለነገ ካልን እጅግ እንዘገያለን፡፡” በማለት የአፍሪካ ህብረት ወይም አንድነት ሳይሆን እንደ አሜሪካ ወይም እንደያኔዋ ሶቭየት ህብረት የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት አሁኑኑ መፍጠር አለብን በለት በሙሉ ሃይላቸው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የዛሬ 50 አመት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይም ይህን አቋማቸውን በማንሳት የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት መመስረቱን ጉባኤው እንዲያውጅ በእጅጉ ወትውተው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ይህን አቋማቸውንና ጥሪያቸውን በወቅቱ በጉባኤው ላይ ከነበሩት የአፍሪካ መሪዎች አንዳቸውም ስላልደገፉላቸው በብሽቀት ጨሰው ነበር፡፡ ያኔ ታንጋኒካ ትባል የነበረችው የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጁለየስ ኔሬሬ የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት ከመመስረታችን በፊት ለምን የምስራቅ አፍሪካ መንግስታት ፌዴሬሽን አናቋቁምም የሚለውን ሃሳብ ሲያቀርቡማ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በከፍተኛ ብስጭት ፀጉራቸውን ሊነጩ ደረሱ፡፡

በዚህ ብቻም አላበቁም፡፡ ሃሳባቸውን የተቃወሟቸውን መሪዎች በተይም ፕሬዚዳንት ኔሬሬን “የማትረባ፣ ቀለም ያልዘለቀህ ገጠሬ” በማለት በቀጥታና በግልጽ ንቀት ወርፈቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ የነበራቸው ዲካ የለሽ የበላይነት ስሜት እርሳቸው ያቀረቡትን ማናቸውም አይነት ሃሳብ የየትኛውም የአፍሪካ ሀገር መሪ ያጣጥልብኛል ብለው እንዳያስቡ አድርጓቸው ነበር፡፡ እናም ያኔ በመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የገጠማቸውን ተቃውሞ በልበ ሰፊነት ለመቀበል አቅምና ቀልባቸውን ነሳቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ የተጠናወታቸው ወደር የሌለው የበላይነት ስሜት እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ልታይ ልታይ ባይነት ልክፍት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ እናም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከሁሉም የበለጡና የላቁ መስለው ለመታየትና የሚመለከታቸውን ሰው ሁሉ ቀልብ ለመማረክ የማያደርጉት ነገር አልነበረም፡፡ ይህንን የበላይነትና ልታይ ባይነት ከፍተኛ ስሜታቸውን በሚገባ የተረዳው የፓርቲያቸውና የመንግስታቸው የፕሮፖጋንዳ ማሽንም የዋና አለቃውን ስሜትና ፍላጐት ለማርካት ያልተጓዘው ርቀት ያልፈነቀለው ድንጋይ ጨርሶ አይገኝም፡፡

ለምሳሌ በንክሩማህ የሚመራህ Convention People’s Party ልሳን የሆነው evening News የተሰኘው ጋዜጣ በሰኔ 19 ቀን 1954 ዓ.ም እትሙ ንክሩማህን የገለፃቸው “ንክሩማህ ማለት መለኮታዊ ሃይል ያለው፣ ነብይ፣ ህዝቡን ወደ ተቀደሰችው የነፃነት መሬት የሚመራ አዲሱ ሙሴ፣ የአፍሪካ ኮከብ፣ ድሀና ጐስቋላ የሆኑ በሚሊወን የሚቆጠሩ ጥቁሮች ተስፋ፣ የገና መሲህ፣ ብረቱ ልጅና፣ የጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ታላቁ መሪ” በማለት ነበር፡፡ በየእለቱ እየታተሙ የሚወጡ የመንግስት ጋዜጦችም ከርዕሰ አንቀጽ እስከ ተራ የዜና ዘገባቸው ድረስ ዋነኛ ትኩረታቸው የክዋሜ ንክሩማህን የአዕምሮ ምጡቅነትና አርቆ አሳቢነት በተቻላቸው አቅም ሁሉ ማራገብ ብቻ ነበር፡፡ በ1961 ዓ.ም ንክሩማህን አስመልክቶ የጋና መንግስት በይፋ ያወጣው መግለጫ እንዲህ ይላል “በሚሊወን ለሚቆጠሩ በአፍሪካ አህጉር ውስጥና ከአፍሪካ አህጉር ውጪ ለሚኖሩ ህዝቦች ክዋሜ ንክሩማህ ማለት አፍሪካ ማለት ነው፡፡

አፍሪካ ማለት ደግሞ ክዋሜ ንክሩማህ ማለት ነው፡፡ በአፍሪካ ምን እየተካሄደ ነው የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ሁሉም ሰው መልሱን ለማግኘት የሚሮጠው ወደ አንድ ሰው ብቻ ነው ወደ ክዋሜ ንክሩማህ፡፡ ለኢምፔሪያሊስቶችና ቅኝ ገዢዎች የንክሩማህ ስም ከንፈራቸው ላይ ያለ እርግማን ማለት ነው፡፡ ለመጤ ሰፋሪ ነጮች ደግሞ በአፍሪካውያን ኪሳራ ያሳለፉት የምቾትና የድሎት ጊዜ ማክተሙን የሚጠቁም የማስጠንቀቂያ ደወል ማለት ነው፡፡ በውጭ የበላይነት ለሚማቅቁት አፍሪካውያን ግን የንክሩማህ ስም የተስፋ እስትንፋስና ነፃነት ማለት ነው፡፡ ክዋሜ ንክሩህ ማለት መላ ህይወታችን ማለት ነው፡፡ ያለእርሱ በህይወት መቆየት ጨረሶ አንቺልም፡፡” አሁን አንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ ለመሆኑ እንዲህ የተባለላቸው የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩህ የአመራር ብቃትና ክህሎታቸው እንዴት ያለ ነበረ? የሳምንት ሰው ይበለን፡፡

Read 3455 times