Saturday, 12 November 2011 08:29

የፈጠራ ሰዎችና ውስጣዊ ፍርሃታቸው የመጽሐፌ ስኬት ፍርሃት ፈጠረብኝ የምትለው ደራሲ

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(0 votes)

በዚህች አጭር ጽሑፌ የማወጋችሁ ኤልዛቤት ጊልበርት ከተባለች አሜሪካዊት ደራሲ የሰማሁትን ንግግር ነው፡፡ ከደራሲዋ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የማውራት ዕድል አልገጠመኝም፡፡ በዲቪዲ የተቀረፀውን ንግግሯን የሰማና የተመለከተ ደራሲዋን አግኝቶ ለማውራት ቢቋምጥ ግን አትፍረዱበት፡፡ ንግግሯ ይጥማል፡፡ ሌክቸር የምታደርግ ሳይሆን አጠገባችን ተቀምጣ የሚጣፍጥ ወግ የምታወጋ ነው የምትመስለው፡፡ የንግግሯ አጀንዳ ደግሞ ቀለል ያለ አይደለም፡፡ የከረረ ርዕሰ ጉዳይ ነበር ያነሳችው - Ted talk በተባለ ፕሮግራም ላይ ንግግሯን ያቀረበችው ኤልዛቤት ጊልበርት፡፡ ደራሲዋን ለማታውቋት ትንሽ ማብራሪያ ላስቀድም፡፡

የ40 ዓመቷ ደራሲ ኤልዛቤት ጊልበርት ላለፉት 20 ዓመታት በፀሐፊነት ዘልቃለች፡፡ የታተሙ መፃሕፍትም አላት፡፡ ነገር ግን ደራሲዋ ከፍተኛ ዓለምአቀፍ ዝና የተቀዳጀችው በቅርቡ ነው - “Eat, Pray, love” በተሰኘውና ከፍተኛ የሽያጭ ሪከርድ ባስመዘገበው መጽሐፍዋ፡፡ ይሄ መጽሐፍ በፊልምም ተሰርቷል፡፡
እንደ መጽሐፉ ሁሉ ፊልሙም ተወዳጅነት እንዳገኘላት ይነገራል፡፡ መቼም ይሄ ስኬት ለደራሲዋ ልዩ ደስታና የእርካታ ስሜት እንደሚፈጥርላት የሚጠበቅ ነው፡፡ በሥራው ውጤታማ ሲሆንና አድናቆት ሲጐርፍለት ማን የማይደሰት አለ? ኤልዛቤት ጊልበርትን በተመለከተ ግን የመጽሐፉ ታላቅ ስኬት ደስታን አይደለም ያጐናፀፉት፤ ፍርሃትን እንጂ፡፡ ግን ምን ዓይነት ፍርሃት? ከየት የመጣ? ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡
በ2009 እ.ኤ.አ በካሊፎርኒያ ለሴሚናር ተካፋዮቿ ያቀረበችው ንግግር በዚህ ፍርሃቷ ላይ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ በእርግጥ ነገሩ ትንሽ ግራ መጋባት የሚፈጥር ዓይነት ነው፡፡
አንድ ደራሲ ተጨንቆ ተጠቦ ያዘጋጀው መጽሐፉ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ሲያገኝለት፣ ሞቅ ያለ ገቢ ሲያመጣለት ፍርሃት የሚባለው ነገር እንዴት ደፍሮ አጠገቡ ድርሽ ሊል ይችላል? ጊልበርት የፍርሃቱን ምንጭ ትናገራለች፡፡ “ፀሐፊ ነኝ፤ መጽሐፍ መፃፍ ሙያዬ ነው፤ ግን ከዚያም ይልቃል፡፡ የህይወት ዘመን ፍቅሬና ቀልቤን የሚማርከኝ ነገር ነው፡፡ ይሄ እውነት መቼም ይለወጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡ በቅርቡ ግን አንድ ለየት ያለ ነገር በህይወቴ ላይ ተከሰተ፡፡
የመጨረሻ መጽሐፌ በሽያጭ ከተተኮሰና ተወዳጅነት ከተቀዳጀ ወዲህ በየሄድኩበት የሰዎች አቀባበል “በቃ አከተመልሽ!” የሚል ይመስላል - “ ትላለች ደራሲዋ፡፡ ምናልባት አብደው ይሆናል እንጂ በመጽሐፉዋ ዓለምን የናጠች ደራሲ፤ በምን ተዓምር ነው የሚያከትምላት? ጭራሽ እንደገና ኮከብ ሆና ትበራለች እንጂ፡፡ ኤልዛቤት ጊልበርት ነገሩ ወዲህ ነው ትለናለች፡፡
ሰዎች ገና ሲያዩዋት የሚያቀርቡላት ጥያቄ “ከአሁኑ ሥራ የላቀ መጽሐፍ መፃፍ ቢያቅተኝስ ብለሽ አትጨነቂም?” የሚል እንደነበር ትናገራለች፡፡
የሚገርመው ግን የዛሬ 20 ዓመትም ገና በወጣትነት ዕድሜዬ፣ ፀሐፊ ለመሆን ሳኮበኩብ ተመሳሳይ ፍርሃት የሚፈጥር ጥያቄ እጠየቅ ነበር ብላለች -ደራሲዋ፡፡
“በፀሐፊነትሽ ተቀባይነት ባላገኝስ ብለሽ አትፈሪም ወይ? ተብያለሁ” የምትለን ደራሲዋ፤ እንዲህ ዓይነቱ ነገር የአዕምሮ አለመረጋጋት ይፈጥራል ባይ ናት፡፡
የፈጠራ ሰዎች በተለይ ፀሐፊዎች አዕምሮአቸው ያልተረጋጋ መሆኑን ለማየት የ20ኛውን ክ/ዘመን የፈጠራ ሰዎች አስደንጋጭ የሞት ቁጥር መመልከት በቂ ነው፡፡ ብዙዎቹ የዘመኑ ድንቅ የፈጠራ ሰዎች በለጋ ዕድሜያቸው የተቀጩ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው እጅ ራሳቸውን ያጠፉ ነበሩ የምትለው ደራሲዋ፤ በለጋ ዕድሜያቸው ያልተቀጩትም ቢሆኑ በተፈጥሮአዊ ተሰጥኦዋቸው በቅጡ ሳይረኩ የባከኑ ናቸው ትለናለች፡፡ ኖሚ ሚለር የተባለ የኪነጥበብ ሰው “እያንዳንዱ መጽሐፌ የበለጠ ገድሎኛል” ሲል መናገሩን ደራሲዋ በምሳሌነት ትጠቅሳለች፡፡
ይሄ ዓይነቱ ፍርሃትና ስጋት በፈጠራ ሰዎች ላይ አይሎ እንደሚታይ የተናገረችው ጊልበርት፤ አባቴ ለ40 ዓመት በኬሚካል ኢንጂነርነት ሲሰራ ቆይቷል፤ ሆኖም ግን ማንም ኬሚካል ኢንጂነር መሆን አያስፈራህም ወይ ብሎ ሲጠይቀው ሰምቼ አላውቅም ብላለች፡፡ እሱስ ይፈራ ነበር? በፍፁም ትላለች - ጊልበርት፡፡
ደራሲዎቻችንን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ጂን መገልበጥ እንዲጀምሩ የሚያደርጋቸው እንዲህ ያለው የፍርሃትና የስጋት ስሜት ነው፤ እኔ ግን በማለዳ ጂን መገልበጥ አልሻም፤ የምወደውን የፀሐፊነት ሙያ መቀጠል ነው የምፈልገው ብላለች፡፡
በፈጠራ ሰዎች ላይ የሚፈጠረው “ይሄ ባይሳካልኝስ?” የሚል የፍርሃት ስሜት ምንጩ ከወዴት ይሆን?
ፈጠራና ፍርሃት ቁርኝት የሚፈጥሩት የፈጠራ ሂደቱ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በተዓምራዊ ሃይል የሚከሰት ነው ብለን ስናስብ ነው ትላለች - ጊልበርት፡፡
ኤልዛቤት ጊልበርት ራሷ የፈጠራ ሃሳቦቿ ከራሷ ውስጥ የሚመነጩ ሳይሆን ከሩቅ ቦታ ሲያሰኛቸው ብቅ የሚሉ ናቸው ብላ ታምን እንደነበር ትናገራለች፡፡
አሁንም ድረስ ብዙ የጥበብ ሰዎች፤ ፈጠራ ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ እንደሆነና ከማያውቁት ምንጭ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ ይሄም ነው በጥበብ ስራቸው ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥርባቸው፡፡ ሃሳብ አልመጣ ሲላቸውና ብዕራቸው ሲደንዝ የፈጠራ ቆሌ አልታረቀችኝም ወደሚል ድምዳሜ ይገባሉ፡፡ ደራሲዋ የዘመናችን ሙዚቀኛ ቶም ዌይ የነገራትን ትጠቅሳለች፤
“…በሎስ አንጀለስ ጐዳና ላይ መኪና እያሽከረከርኩ ነበር፡፡ ትናንሽ የዜማ ቁርጥራጮች ወደ አዕምሮዬ ሲመጡ ይሰማኛል፡፡ የምጽፍበት ብዕርና ወረቀት የለኝም፡፡ መቅረፀ ድምጽ አልያዝኩም፡፡ ዜማዎቹ ሊያመልጡኝ ሆነ ወዲያው “ይቅርታ እየነዳሁ መሆኔን አታይም እንዴ? አሁን እኔ መፃፍ የምችል ይመስልሻል? ከፈለግሽ በሌላ ምቹ ሰዓት ተመልሰሽ ነይ፤ አሁን ሌላ ሰውን ሄደሽ ነዝንዢ” ማለቱን በመጥቀስ፡፡
አሁን የ90 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ አሜሪካዊት ገጣሚ ፈጠራን አስመልክቶ የነገሯትን አስቂኝ ገጠመኞችም ጊልበርት ታስታውሳለች፡፡
“ግጥሞች ከመልክአ ምድሩ ወደኔ ሲመጡ እሰማቸዋለሁ፡፡ ያኔ ሮጬ ቤቴ እገባና ወረቀት ላይ አሰፍራቸዋለሁ” ሁሌ ግን አይሳካም፡፡ ቤት ደርሰው እስኪጽፉት እሳቸው ላይ ነጥሮ ወደ መጣበት መልክአምድር ይመለሳል - ግጥሙ፡፡ ገጣሚዋ ያኔ አይጨነቁም፡፡ ግጥሙ ወደሌላ ገጣሚ ጋ እንደተላከ አስበው ይጽናናሉ - ጊልበርት እንደምትለው፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ግጥሙ በሳቸው ውስጥ ያልፍና ከማምለጡ በፊት ጭራውን ይይዙታል፡፡ ከዚያም ጭራውን ወደራሳቸው እየሳቡ ግጥሙን ወረቀት ላይ ይገለብጡታል፡፡ ወረቀቱ ላይ ሲሰፍር ታዲያ ከመጨረሻው የግጥሙ ቃል ይጀምርና በመጀመሪያው ቃል ያልቃል - ከኋላ ወደፊት ማለት ነው፡፡
አንዳንዴ ጊልበርትም ሃሳብ እምቢ ሲላት ሙዚቀኛው ቶም ዌይ እንዳደረገው እንደምታደርግ ትናግራለች፡፡ “በምጽፍበት ባዶ ክፍል ውስጥ ባዶውን አየር እያየሁ “ስማ አንተ፤ ይሄ መጽሐፍ አሪፍ ባይሆን የእኔ ጥፋት አይደለም፤ መጽሐፉ ምርጥ እንዲሆን የምትሻ ከሆነ ናና የድርሻህን አዋጣ፡፡ ያለዚያ እኔ መፃፌን እቀጥላለሁ፡፡ ምክንያቱም መፃፍ ሥራዬ ነው” እላለሁ፤ ለፈጠራ ሰዎች የሚያዋጣውና ትክክለኛው አካሄድም ይሄ ነው ትላለች - ደራሲዋ፡፡
ኤልዛቤት ጊልበርት እንደምትለው እያንዳንዳችን እዚህች ምድር ላይ እንድንሰራው የተፈጠርንለት ሥራ አለ፤ ለአንዳንዱ ደራሲነት፣ ለሌላው ዳንስ፤ ለግማሹ ቢዝነስ ለሌላው ደግሞ የቴክኒክ ሙያ ሊሆን ይችላል፡፡
ለምንድነው እኒህን ስራዎች ለመስራት የምንፈራው? አሁን ጊልበርት “ቀጣዩ ሥራዬ ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? ከተወዳጁ መጽሐፌ የተሻለ ሥራ መፍጠር ይቻለኛል?” የሚለው አያስጨንቀኝም ትላለች፡፡
“ከቀድሞው የላቀም ይሁን ያነሰ ጽሑፍ መፃፌን እቀጥላለሁ፤ ምክንያቱም መፃፍ ሥራዬ ስለሆነ፡፡ “ትልቁ ስኬቴ ከዝነኛው መጽሐፌ ጋር ትላንት አልፏል የሚለውን ግን አልቀበለውም፤ ለምን ቢሉ? ገና የ40 ዓመት የሥራ ዘመን ይቀረኛልና”
ኤልዛቤት ጊልበርት ንግግሯን ስትቋጭ፣ “ደራሲ ከሆንክ ምንም ሳትፈራ ፃፍ፤ ሥራህንም ለተደራስያን አቅርብ፤ ሊወዱትም ላይወዱትም ይችላሉ፡፡ አንተ ግን ሥራህ መፃፍ መሆኑን አትዘንጋ! ስኬትህ ያለው ወደፊት በሚመጣው ዘመን ነው” ብላለች፡፡
ለአገራችን የፈጠራ ሰዎች አንዳች ቁምነገር ያስጨብጥ ይሆን? ርዕሰ ጉዳዩ ለውይይት የሚነሽጥ ይመስላል፡፡ መልካም ጊዜ!

 

Read 2967 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:35