Saturday, 12 November 2011 08:30

“ታላቅ ዘፋኝ የሚባለው ዝምታችንን የሚያዜምልን ነው”

Written by  ካህሊል ጂብራን - ቢኒያም መለሰ
Rate this item
(0 votes)

ኪነ ጥበብ በንፁሐን ልቦና ውስጥ የምትወለድ፣ ሀገሯም ንፁህ ተፈጥሮ ከተቀዳጀችው ከእውነት ዘንድ ነው፡፡ ኪነ ጥበብ ከተማዋ እውነት ነው ስንል በዝምታ፣ በፀጥታ፣ በእርጋታ ውስጥ ያለን ሃይል ያለፍርሃት መግለጽ ትችላለች እያልን ነው፡፡ የፈጠራ ሰዎች ያዩትንና የተሰማቸውን እውነት ያለ ይሉኝታና ፍርሀት እንደ ሕፃናት ይናገሩታል፡፡
የጥበብ ሰው ከማሕበረሰቡ ጥቂት እርምጃን በሃሳብ ጥልቀት ተራምዶ የማሕበረሰቡን ስሜት ስሜቱ አድርጐ፤ ሲጨነቁ ተጨንቆ፣ ሲደሰቱ ተደስቶ፣ ሲከፋቸው ተከፍቶ፣ ምቾትና ጉስቁልናቸውን፣ ውድቀትና ብልጽግናቸውን፣ ድልና ሽንፈታቸውን፣ ረሃብና ጥጋባቸውን በተለያየ መልኩ ለማህበረሰቡ ይተነፍሰዋል፡፡

በዚህ ጽሑፌ ማንሳት የፈለኩት ስለግጥም ነው፤ ከግጥምም ደግሞ ስለዘፈን ግጥሞች፡፡ ከዛ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር የሆኑት አቶ ዘሪሁን አስፋው (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ስለ ግጥም ያሉትን ላስቀድም፡፡ “ስነ ግጥም አንድ ነገር ወይም ድርጊት አድምቆና አጉልቶ የማሳየት፣ ሃሳብን አክርሮና አግዝፎ የማቅረብ ችሎታ ያለው፤ በጥቂት ምርጥ ቃላት ብዙ ነገሮችን አምቆ በመያዝና በሙዚቃዊ ቃናው የስሜት ሕዋሳትን በቶሎ የሚነካ፣ ለስሜት ቅርብነት ያለው ኪነ ጥበብ ነው፡፡” የምንጽፈው ግጥም በስነ ጽሑፍ ብስለት፣ በቋንቋ ምጥቀት፣ በአገላለጽ ጥራት ስራው ለማሕበረሰቡ በሚሰጠው ግልጋሎት ከይሉኝታና ሀፍረት እንዲሁም ከፍርሃት ነጽቶ በታላቅ የቋንቋ ብልጽግና ስሜት በሚነካና በሚመስጥ ስልት መቅረብ አለበት፡፡ ሥነ ግጥም በተለያየ መንገድ ለተደራሲው (ለማህበረሰቡ) ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከነዚህ መንገዶች አንዱ በዜማ ወይም በዘፈን ነው፡፡ በቀዳሚው ትውልድ የሀገራችን የዘፈን ግጥሞች የማህበረሰባችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አጉልተው አላሳዩም የሚል በጥናት ላይ ያልተመረኮዘ ግምት ቢኖረኝም ባሁኑ ዘመን ፖለቲካዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በዘፈን ግጥሞቻችን ከማንሰማበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ፡፡ ደራሲ የሺጥላ ኮከብ “ወገግታ” በተሰኘ ልብወለድ መጽሐፉ ላይ ስለሙዚቃ ሲጽፍ “ሙዚቃ በስሜት እጃችንን ጭነን የምንምልባት የእምነት መጽሐፍ ናት” ብሏል፡፡ ምክንያቱም እምነት ከእውነት ስለሚቀዳ፣ እውነት ደግሞ የስነ ጽሑፍ ቅድስት ሀገር ስለሆነች ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ እንደአሁኑ ዘመን ግጥም የወረደበት ጊዜ አለመኖሩን አንዳንድ ባለሙያዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የዘፈን አልበሞች ሁሉ ተመሳሳይ ሃሳብ በተለያየ ዜማ ይዘው ይወጣሉ፡፡ ያውም ግጥም ግጥም የማይሸቱ፤ ወዘናቸው ተንጠፍጥፎ ያለቀ፣ ድርቅ ያሉ፣ ሰቅጣጭ ግጥሞች፡፡ አብዛኞቹ የዘፈን ግጥሞቻችን ፍቅር ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ማህበረሰባችን ሌሎች የሚጮሁ ዝምታዎች የሌሉት እስኪመስል ድረስ” ውበትሽ፣ ሽንጥሽ፣ ዳሌሽ፣ አፍንጫሽ፣ ወዘተ የሚሉ ናቸው”፡፡
እውን የእኛ ችግር ይሄ ነው? የማህበረሰባችን ችግር ፍቅር ነው? ታላቁ ፀሐፊ ካህሊል ጂብራን “ታላቅ ዘፋኝ የሚባለው ዝምታችንን የሚያዜምልን ነው” ይለናል፡፡ በእርግጥ የእኛን ዝምታ የዘፈን ግጥም ደራሲዎቻችን ስለማያውቁት አይመስለኝም ዝም ያሉት፡፡ ዝም ያስባላቸው ፍርሃት ነው፡፡ ፍርሃታቸው አንድ ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አደረጋቸው፡፡
ብዙዎቹ ግጥሞች በዜማ ተሸፍነው ስለሚቀርቡ እንጂ ከዜማ ውጪ ማንኛውም ሰው ቢያነባቸው የወረዱ ናቸው፡፡ የዘፈን ግጥሞቻችን ስለወረዱም ይመስላል ዘፋኞቻችን የ 1960ዎቹን ግጥሞች በመውሰድ ዜማውን እያሻሻሉ ማቅረብ የጀመሩት፡፡ በዚህም የዘመናችንን ታላቅ የዘፈን ግጥም እርዛትን አበሰሩን፡፡
አሁን ቆም ብለን የጥበብ ሰዎችን መጠየቅ ያለብን ጥያቄዎች አሉ፡፡ በዘመናችን የሚዘፈኑ ዘፈኖች የማህበረሰባችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሃሳቦች አድምቀውና አጥልቀው አሳይተዋል ወይ? ዘወትር አዲስ ነገር ለመስራት ትጉህ የሆነ ገጣሚና ዘፋኝስ አለን ወይ አርቲስቱ የሚያየውንና የሚሰማውን ታላላቅ የሀገሪቷ እውነቶች በብዕሩ ከትቦ የሕዝብን ስሜት ኮርኩሯል ወይ? የእምነት መጽሐፍ ናት ባልናት ሙዚቃችን ላይ በሙሉ ልብ እንድንምልባት መሰራት ያለበት ነገር ተሰርቷል ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች በጥበብ ሰዎች መመለስ አለባቸው፡፡
የሀገራችንን የዘፈን ዜማ የሚተርቡ ጓደኞቼ ዜማችንን “አምቼ” ነው ይሉታል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ “አምቼ” ሌላ አገር ተሰርቶ የመጣን የመኪና አካል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገጣጥም እንደሆነ ሁሉ የእኛም ዜማ ከሱዳን፣ ከኬኒያ፣ ከአሜሪካ ወዘተ ዘፈኖች በጥቂት በጥቂቱ ተቀድቶ የሚገጣጠም ነው ይላሉ፡፡ እንደ ዜማችን ሁሉ ግጥማችንም ይኸው በሽታ ተጠናውቶታል፡፡ የዘፈን ገጣሚዎቻችን ምን ነካቸው? በፍቅር ታሪክ ላይ ብቻ ተመስጠው ያውም ተመሳሳይ የሆነ የታሪክ ጭብጥ ላይ ሌሎች ዝምታዎቻችንን ማን አንደበት ይሁንላቸው? ማን ይናገርልን? መምህር ዘሪሁን አስፋው “…ደራሲ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ፍቅር ያለውና ከፍቅሩም የተነሳ መስዋዕት የሚከፍል ሐቀኛ ሰው ነው” ብለዋል፡፡ ግጥም የሚጽፍ ሰው ለእውነት የቆመ ጠበቃ ነው፡፡ ማስመሰልንና ውሸትን የማሸነፍ ብርታት ውስጡ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለማህበረሰቡ ባለው ጥልቅ ፍቅር ፍርሃትን አስወግዶ እውነትን የሚሰብክ ታላቅ መምህር ነው፡፡ ደግሜ እጠይቃለሁ:- በእርግጥ ማህበረሰቡ ከፍቅር ውጪ ሌሎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሉበትም? በውስጡ አምቆ የያዘውን የብሶት እሳት ደፍሮ የሚናገርለት ስላጣ እንጂ ማለት የሚፈልገው ብዙ ነገር እንዳለ ደራሲያኑም ሆኑ ዘፋኞቹ በደንብ ያውቁታል፡፡
ሀገራችን የረጅም ዘመን ታሪክና የታላላቅ እውነቶች ባለቤት ብቻ አይደለችም፡፡ ለዘመናት ከችግሩ ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ የሚኖር፣ ቁስሉን በዝምታ የሚያክም ጨዋ ሕዝብ ያለባትም ሀገር ናት፡ ይኸን ማህበረሰቡ በዝምታ የሚያክመውን ቁስል ጮክ ብሎ የሚናገርልንና ከካህሊል ጂብራን ጋር ሆነን በታላቅ ኃይል “ዝምታችንን ያዜመልን ታላቅ ዘፋኝ” ብለን የምናወድሰው ገጣሚና ዘፋኝ በዚህ ወቅት ያስፈልገናል፡፡ እኛም “ታላቅ ዘፋኝ የምንለው ዝምታችንን የሚያዜምልን ነው”!!!

Read 4967 times