Wednesday, 12 June 2013 13:50

የዕድሜ ልክ ጥሪት የማይገዛው ዕድሜ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

ለአንድ ዓመት የኩላሊት እጥበት 240ሺ ብር! በእርዳታ የተገኙ 10 ማሽኖች በቦታ እጥረት ወደ አገር ውስጥ አልገቡም

             ህመሙ እንደጀመራት እንዲህ የከፋና የዕድሜ ልክ ችግርና ሥቃይን ሊያስከትል ይችላል ብላ ፈፅሞ አልገመተችም፡፡ እጅ እግሯን እያሣበጠና ሰውነቷን እያቃጠለ ከፍተኛ ራስ ምታት ለሚያስከትልባት ችግር መፍትሔ ለማግኘት የተለያዩ ሃኪሞች ጋ ሄዳለች። ሁሉም የከፋ የጤና ችግር እንደሌለባት እየነገሩ፣ ለህመሟ ማስታገሻ ጥቂት ክኒኖች በመስጠት አሰናበቷት እንጂ የረባ እርዳታ አላደረጉላትም። ህመሟ እየባሰ፣ ሥቃይዋ እየጨመረ ሲሄድ ቤተሰቦቿ ግራ ተጋቡ፡፡

ባለቤቷ የአስራ አምስት ዓመት የትዳር አጋሩና የአራት ልጆቹ እናት የሆነችው ባለቤቱ የገጠማት ችግር ምን እንደሆነ ሊያውቅላት የሚችል የህክምና ባለሙያ መጥፋቱ ግራ አጋባው። ስቃይዋ እየበዛና የሰውነቷ እብጠት እየጨመረ ሲሄድ፣ ዓይኔ እያየ ለሞት አሣልፌ አልሰጣትም ያለው ባለቤቷ፤ ወደ ቤቴል ሆስፒታል ይዟት ሔደ። በሆስፒታሉ በተደረገላት ምርመራ ሁለቱም ኩላሊቶቿ ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ በአስቸኳይ አርቴፊሻል የኩላሊት እጥበት (ዳያሊስስ) እንደሚያስፈልጋት፤ ያለበለዚያ ግን በህይወት የምትቆየው ለጥቂት ቀናት ብቻ እንደሆነ ተነገራት።

በሰውነቷ ውስጥ የተከማቸው ፈሣሽ (ሽንት) በመሣሪያ ተመጥጦ ካልወጣላት በስተቀር አሲዱ ሰውነቷን እያቃጠለ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡት ጉበት፣ ሣንባና መሰል የሰውነት ክፍሎቿ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ሃኪሞቹ ገለፁ፡፡ ህክምናው የዕድሜ ልክ ነው፡፡ ኩላሊት ለማስቀየር የሚያስችል አቅምና ኩላሊት ካገኘች ጤናዋ ሊመለስ ይችላል፡፡ ሁሉንም ለባል በዝርዝር አስረዱት - ሃኪሞቹ፡፡ የሰማው ነገር እጅግ አስደነገጠው፡፡ የቤቱ ሙቀት ሲቀዘቅዝ፣ ልጆቹ ያለ እናት ሲቀሩ፣ ተስፋው ሁሉ ሲጨላልም ታየው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት እንኳን ማወቅ አልቻለም፡፡

በአንድ የውጪ ድርጅት በሂሣብ ሥራ ሙያ ተቀጥሮ የሚያገኘው ደመወዝ፣ አራቱን ልጆቹን በግል ትምህርት ቤት እየከፈለ ለማስተማርና ቤቱን ለማስተዳደር ቢያስችለውም ለእንዲህ ያለ ክፉ ጊዜ የሚሆን ባንክ የተቀመጠ ገንዘብ አልነበረውም። ግራ ገባው፡፡ ባለቤቱ በየጊዜው ጤናዋ እየተጓደለ፣ ሥራዋን በአግባቡ ማከናወን ባለመቻሏ ከምትሰራበት የግል ድርጅት ከተሰናበተች ቆይታለች፡፡ ባል ከቤተሰቦቹ በውርስ ያገኘው ቤት የመኖሪያ ቤት ችግሩን በማቃለሉ ኑሮው ሰላማዊና የተረጋጋ ነበር፡፡ ያን የመሰለ ሰላማዊ ህይወትና የሞቀ ትዳር እንዲህ በድንገት አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ሃሣብ ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ ስለ ጉዳዩ ከሃኪሞቹ ጋር በስፋት ተወያየ፡፡ ሠናይት የተባለውን ህክምና ከመጀመር ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌላት ነገሩት፡፡ ለዳያሊስስ ህክምናው ማስጀመሪያና ለካቴተር ማስገቢያ በቅድሚያ 15ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅበትም አረዱት፡፡ ጊዜ ማጥፋት አልፈለገም፡፡ ማድረግ ያለበትን ሁሉ ከራሱ ጋር መክሮ ጨርሷልና፡፡ ወያኔ ዲኤክስ መኪናውን በአንድ የመኪና መሸጫ ሥፍራ በመያዣነት አቁሞ 20ሺህ ብር ተበደረ፡፡

ሠናይት ህክምውን ጀመረች፡፡ ህክምናው ሰውነቷን ሁሉ አሣብጦ አቅሏን ካሣታት ህመምና ስቃይ እፎይታን ሰጣት፡፡ በሣምንት ለሶስት ቀናት ዳይሊስሱ መቀጠል እንደሚገባው የተነገረው ባለቤቷ፤ መኪናውን ባወጣችው ዋጋ ሸጣት፡፡ ከመኪና መሸጫው ሥፍራ የተበደረውን ሃያ ሺህ ብር ከፍሎ 190ሺህ ብር እጁ ገባ፡፡ በሣምንት ለሦስት ቀናት ለሚደረገው የዳይላሲስ ህክምና፣ በወር 20ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ እያደረገ የመኪናው ሽያጭ ገንዘብ እስከሚያልቅ አስታመማት፡፡ ከዚህ በኋላስ ምን አደርጋታለሁ የሚል ጭንቀት የያዘው ጌትነት፤ ከቤተሰቦቹ በውርስ ያገኘውን ቤት ለመሸጥ ተነሳ፡፡ ባለቤቱ ግን ተቃወመች፡፡ “እግዜር እንዳለልኝ እሆናለሁ እንጂ አንተን ከእነልጆችህ ሜዳ ላይ ጥዬ አልሄድም” አለችው፡፡ ቤቱ ግን ተሸጠ - 630ሺህ ብር፡፡ ከነልጆቹም ኪራይ ቤት ገባ፡፡ ከዚህ የሽያጭ ገንዘብ ውስጥ 240ሺህ ብር ከአንድ ዓመት የዳይሊሲስ ክፍያ አላለፈም፡፡

የቤት ኪራይ ወጪ፣ የልጆች ቀለብ፣ የሰራተኛ ደመወዝ እየተባለ ገንዘቡ ተመናመነ፡፡ ልጆቹን ይማሩበት ከነበረው የግል ትምህርት ቤት አስወጥቶ፣ በመንግስት ትምህርት ቤቶች አስገብቷል፡፡ በሦስተኛው ዓመት ላይ ጌታነህ የቀረው 30ሺህ ብር የማይሞላ ገንዘብ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ መንገላታትና የባለቤቱን ሕይወት ማቆየት እንደማይሆንለት ሲረዳ በጣም አዘነ፡፡ አንዱን ኩላሊቱን ሰጥቶ የሚስቱን ሕይወት ለመታደግ እንደሚችል ያሰበው ዘግይቶ ነበር፡፡ ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የሚችልበት ምንም አማራጭ አልነበረውም፡፡ ለቀናት አስቦበት ምንም መፍትሔ አላገኘም፡፡ የዳያሊሲስ ህክምናውን ከሦስት ቀናት ወደ ሁለት እንዲቀንስ አደረገ፡፡ ሁለቱን ቀናትም ማድረግ የማይችልበት ደረጃ እየቀረበ መምጣቱን ሲረዳም በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እንድታደርግ ወሰነ፡፡ ይሄም በሠናይት ጤና ላይ ትልቅ ችግር ማስከተል ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታም ብዙ ቀናት መቆየት አልቻለችም፡፡ ከሦስት ዓመት ከሁለት ወራት የዳያሊሲስ ህክምና በኋላ እጅግ ከምትወደው ባለቤቷና ልጆቿ ተለይታ ህይወቷ አለፈ፡፡ ጌታነህ የባለቤቱን ታሪክ ሲያጫውተኝ ዓይኖቹ በእንባ እየታጠቡ ነበር፡፡ ከአራት ወራት በፊት ህይወቷ ያለፈው ባለቤቱን ለማስታመም ንብረቱን በሙሉ ሸጦ ጨርሷል፡፡

አራት ህፃናት ልጆቹን ይዞ በግለሰብ ቤት ውስጥ በኪራይ መኖር እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ተረድቷል፡፡ ግን አማራጭ የለውም፡፡ … የዳያሊስስ ህክምና የፈጠረውን የህይወት ፈተና ተቀብሎ እየተፈተነ ይገኛል፡፡ የተጨበጠ እጅን ያህል መጠንና የአደንጓሬ ቅርፅ ያለው ኩላሊታችን፣ በአራት ክፍሎች የተከፈለ ነው። እነዚህም ጥቃቅን ቱቦዎች፣ በአይን የማይታዩ የደም ስሮች፣ ወንፊት መሰል ነገሮችና ጡንቻዎች ናቸው። እነዚህ የኩላሊት ክፍሎች የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የፈሳሽ መጠን የማስተካከል፣ ትርፍ ሆኖ ሲገኝ በሽንት መልክ ወደ ውጪ እንዲወጣ ማድረግ፣ በሰውነታችን ውስጥ የፈሳሽ መጠን ሲቀንስ የሽንት መጠንን በመቀነስ ከሰውነታችን ብዙ ፈሣሽ እንዳይወገድ ማድረግ፣ የደም ግፊት ሚዛንን መጠበቅ ከኩላሊት ተግባራቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ኩላሊት እነዚህን ተግባራት በአግባቡ መከወን ሲሣነው የኩላሊት ህመም ተከስቷል ይባላል፡፡ ሁለት አይነት የኩላሊት ህመሞች አሉ፡፡ እነዚህም አጣዳፊ የኩላሊት ህመምና የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰ ህመም የተባሉት ናቸው፡፡

አጣዳፊ የኩላሊት ህመም በህክምና ሊሻሻል ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ረጅም ጊዜ ሣይታወቅ ቆይቶ ደረጃ በደረጃ እየተባባሰ አደጋ ላይ የሚጥለው የኩላሊት ህመም ነው፡፡ የኩላሊት ጤና ተቃወሰ ማለት አጠቃላይ የሰውነታችን ሥርዓት ተናጋ ማለት ነው፡፡ የኩላሊት እክል በተለይ በልብ፣ በጨጓራ፣ በአንጀት፣ በቆዳና በነርቭ፣ በጉበትና በአጠቃላይ በሰውነት ክፍሎቻችን ላይ የሚያስከትለው የጤና ችግር እጅግ የከፋ ነው። የኩላሊት ጤና ሲታወቅ ታማሚው የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ምልክቶቹ መካከል የሰውነት ማበጥ፣ በተለይም የፊትና የእግር ማበጥ፣ የሽንት መጠንና ቀለም መቀየር፣ የአይን መቅላት የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ራስ ምታት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የኩላሊት ጤናን በማይመለስ ደረጃ የሚያውኩ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል የደም ግፊት በሽታ ቀዳሚው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስኳር፣ ኢንፌክሽኖች፣ ተመላልሶ የሚመጣ ቶንሲላይት፣ በፈንገስ፣ በቫይረስና በባክቴሪያ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች (በሽንት ቱቦና በደም ስሮች ላይ) ኩላሊት በማይመለስ ደረጃ እንዲታመም ያደርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች፣ ለተለያዩ የጤና ችግሮች እየተባሉ የሚሰጡ መድሃኒቶች እንዲሁም ለኩላሊት፤ ለጉበትና ለአንጀት ቁስለት እየተባሉ የሚሰጡ መድሃኒቶች የኩላሊት ጤናን ያውካሉ፡፡ በአገራችን የኩላሊት ጤና መታወክ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በርካታ የችግሩ ተጠቂዎችም ለህልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ስለበሽታው የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም በአሁኑ ወቅት የኩላሊት ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ጠቋሚ መረጃዎች አሉ፡፡ ህክምናው በክልሎችና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ስለማይገኝ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚመጡትን የኩላሊት ህሙማን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡

በሽታው ሥር የሰደደና ቀጣይነት ያለው የሚሰጡ መድሃኒቶች የኩላሊት ጤናን ያውካሉ፡፡ በአገራችን የኩላሊት ጤና መታወክ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በርካታ የችግሩ ተቂዎችም ለእልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ስለበሽታው የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም በአሁኑ ወቅት የኩላሊት ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ጠቋሚ መጃዎች አሉ፡፡ ህክምናው በክልሎችና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሊገኝ የማይችል በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ከልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚመጡትን የኩላሊት ህሙማን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ በሽታው ሥር የሰደደና ቀጣይነት ያለው ህክምና የሚያስፈልገው ከሆነም በጣት በሚቆጠሩ ጥቂት የህክምና ተቋማት ውስጥ ህክምናውን ለማግኘት ህሙማኑ ተራ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኩላሊት እጥበት ሕክምና (ዳያሊሲስ) የሚሰጠው በግል የህክምና ተቋማት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ውስጥ ህክምናው ይሰጥ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት መሣሪያው በመበላሸቱ ምክንያት አገልግሎት መስጠቱን አቋርጧል፡፡ በግል ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ሕክምናውን ለማግኘት አቅም ያጡ ህሙማን እጅግ በከፋ ስቃይ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ዳዊት ተከስተ እንደሚናገሩት፤ የኩላሊት ጤና ሲቃወስ መላው የሰውነታችን ክፍሎች ሥርዓት ይናጋል። ይህም ታማሚውን ለከፍተኛ ስቃይና ትንፋሽ ለሚያሳጣ ህመም ይዳርገዋል፡፡ አቶ የሱፍ አብዱል ኦማድ በኢትዮጵያ የኩላሊት ህሙማን ማህበር መሥራችና ፕሬዚዳንት ናቸው። በማህበሩ ውስጥ ታቅፈው የሚገኙ ከ180 በላይ አባላት አሉ፡፡ በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ካሉ ለጋ ወጣቶች ጀምሮ በዕድሜ የገፉ የኩላሊት ህሙማን የማህበሩ አባላት ናቸው፡፡

ህሙማኑ በየጊዜው ለሚያከናውኑት የኩላሊት እጥበት አቅም ሲያጥራቸውና ችግር ሲያጋጥማቸው ማህበሩ በገንዘብ እየደገፈ ህክምናው እንዳይቋረጥባቸው ያደርጋል፡፡ ማህበሩ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ተቋማት የሚያገኘውን የገንዘብ እርዳታ የማህበሩን አባላት ለመደገፍ ያውለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ የሱፍ እንደሚናገሩት፤ የማህበሩ አባል የሆኑ በርካታ የኩላሊት ህሙማን ሀብትና ንብረታቸውን፣ ቤታቸውን፣ መኪናና ጌጣቸውን ሁሉ ሸጠው ለህክምና አውለውታል፡፡ ህሙማኑን ከበሽታው የበለጠ የሚጐዳቸው የህሊና ስቃዩ ነው፡፡ ህሙማኑ እጥበቱ ለአንድ ጊዜ ያህል እንኳን ከተቋረጠባቸው ውስጣዊ የሰውነታቸው ክፍል ስለሚበላሽ ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ፡፡ ይህ ችግር እንዳይከሰት ማህበሩ የተቻለውን ያህል ድጋፍ እያደረገ ሕሙማኑ ህክምናውን እንዳያቋርጡ ያግዛቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የማህበሩ አባል ለመሆን የሚያመለክቱ ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ የሱፍ፤ በወር ከ20 እስከ 25 የሚሆኑ አዳዲስ አባላትን ማህበሩ በአባልነት እንደሚቀበል ይናገራሉ፡፡

ከማህበሩ አባላት መካከልም በወር ስምንት ያህል ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡም አቶ የሱፍ፤ ገልፀዋል፡፡ ይህንን የህሙማኑን አጣዳፊ ችግር በማስመልከት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን የሚገልፁት አቶ የሱፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ መንገዶች ማህበራቸውን እያገዘ እንደሚገኝና መድሃኒት በማስመጣት፣ የህክምናና የመሳሪያ እርዳታዎች እንዲገኙ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ የማህበሩ አባላት፣ ለኩላሊት እጥበት ሕክምናው የሚያወጡት ከፍተኛ ወጪ ፈጽሞ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነና መዳን የሚችሉ በርካታ ህሙማን በአቅም ማጣት ብቻ ሕይወታቸው ሲያልፍ መመልከቱ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡ ማህበሩ ከጃፓን አገር በእርዳታ ያገኛቸው 10 የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና የሚሰጡ መሣሪያዎች በቦታ ማጣት ሰበብ እስከ አሁንም ድረስ ወደአገር ውስጥ ሊገቡ አለመቻላቸውን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ችግር ፈጽሞ ሊገባቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ በየቀኑና በየሰዓቱ እጅግ በርካታ ዜጐች በዚህ በሽታ እየተሰቃዩና በርካቶች እየሞቱ ጉዳዩ፣ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በቸልታ መመልከታቸው ግራ እንዳጋባቸው ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሣሪያዎቹ ወደ አገር ውስጥ ገብተው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ፈቅዶ በጀት ቢመድብም፣ መሣሪያው ወደ አገር ውስጥ ገብቶ የሚቀመጥበትና አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ ሊገኝ አለመቻሉንም ይገልፃሉ፡፡ ከብዙ ጊዜ እንግልትና ድካም በኋላ በአሁኑ ወቅት የዘውዲቱ ሆስፒታል ቦታውን ሊሰጥ ፈቃደኛ መሆኑን የገለፁላቸው ቢሆንም ሆስፒታሉ ቃሉን ተግባራዊ በማድረግ ለህሙማኑ እፎይታን ሊያስገኝ የሚያስችል እንቅስቃሴ አለመጀመሩን ተናግረዋል፡፡ አገራችን እጅግ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች በርካታ ህንፃዎችና ፎቆች እየተገነቡ እንደሆነ እንሰማለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ፎቅና ህንፃ ግን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ያለውንና በየሰዓቱ የሚሞተውን የኩላሊት ታማሚ ህይወት የሚታደግ አንዲት ጐጆ ማግኘት ተሣነን፡፡ እኛስ ማን አለን? ኢትዮጵያውያን አይደለንምን? አቶ የሱፍ ይጠይቃሉ፡፡ ህሙማኑ የዳያሊሲስ ህክምናውን ለማስጀመር የሚያስችላቸውን ካቴተርና ፌስቱላ የተባሉ ህክምናዎችን ለማድረግ ከ15ሺህ በላይ እየተጠየቁ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ የሱፍ፤ የህክምና ባለሙያዎቹ በወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽሙት በደል እጅግ አሳዛኝ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የዘውዲቱ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ፍሬውን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፤ የኩላሊት ህሙማኑ ችግር እንደተባለው አጣዳፊና ፋታ የማይሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጤና ጥበቃ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ህክምናው ከተጀመረ በኋላ መቋረጥ የሌለበት በመሆኑ ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የሚናገሩት ዶ/ር አያሌው፤ ሆስፒታላቸው ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ በቀጣዮቹ አራትና አምስት ወራት ውስጥ አገልግሎቱንን ለመጀመር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ የኩላሊት ህሙማን ማህበሩን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቅፎና ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በጀት መድቦለት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ነገሮች እንዲሟሉ እያደረገ መሆኑንም እኚሁ ዶክተር ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ያስገነባውና በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኤችአይቪ የምርመራ ማዕከል ተመርቆ ሲከፈት፣ የኩላሊት እጥበት ሕክምናው በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ በቅርቡ ሊጀመር መታቀዱም ተገልፆ ነበር፡፡ የህክምናውን መጀመር እጅግ በታላቅ ጉጉት ከሚጠብቁት ህሙማን መካከል አብዛኛዎቹ ቤትና ንብረታቸውን ሸጠው የጨረሱ፣ ምንም ቀሪ ተስፋና ዕድል የሌላቸው ናቸው፡፡ የእነዚህን ህሙማን ህይወት ለመታደግ ሆስፒታሉም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ቅድሚያ ሰጥተው አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡

Read 4125 times