Wednesday, 12 June 2013 13:55

እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

Written by  አብደላ ዕዝራ abdiezra@yahoo.com
Rate this item
(7 votes)

ሂሳዊ ንባብ
የአማርኛ ግጥም ህትመት ቢበራከትም፣ ዘመን ተሻግሮ የሚፈካዉ በቁጥር ነዉ:: እየዘገበ ቤት የሚመታ፣ ቋንቋዉ የማይናደፍ፣ እሳቦቱ ወድያዉኑ የሚነጥፍ ግጥም አቅም ያንሰዋል:: አሰልቺና ደነዝ በመሆኑም የጥሞናን ጊዜ ሲያመክን ለገጣሚዉ አይሰቅቀዉም:: በአንፃሩ ጥቂቶች የሚመስጥ፣ የሚያባንን፣ እያደረ ከአዕምሯችን የሚንቀለቀል ግጥም ለኩሰዋል:: የነብይ መኮንን ስዉር-ስፌት እየተነበበ የሚነዝር፣ ስሜትና እሳቦት የሚያደራ በመሆኑ አይለቀንም::

ባዶ ስንኝ ቅቤ አይወጣዉ፣ በስሜት አልባ ወግ
ቢናጥ
ከዉበት ጋር ካልተቃኘ፣ ልብን ነዉ የሚሰቀጥጥ
[ስዉር-ስፌት ፥ 133 ]

ሥነግጥም መስጦን፣ ቆይቶ ቆይቶ እንደ ብርቅ ወዳጅ የሚታወሰን አለ፤ ዳግም ሲነበብ አዲስነቱ የሚፈካ፣ ምስሉ እንደ ፀናፅል ሲወዛወዝ ድብርት አያፍነዉም:: ነብይ መኮንን ሁለት ስብስብ ግጥሞች አሉት፤ ዉጭ አገር የታተመለት ጥቁር ነጭ ግራጫ እና የአገር ቤቱ ስዉር-ስፌት :: ይህ ሂሳዊ ንባብ ስዉር-ስፌት ትኩረቱ ነዉ፤ የግድ ሲሆን የመጀመሪያ መፅሐፉ ላይ እየነጠረ ይመለሳል:: ትርጉምና ኢልቦለድ መፅሐፍ አሳትሟል፤ ትያትርም ደርሷል:: የአዲስ አድማስ ርዕሰ አንቀፅ መነሻዉ ሥነቃል፣ ጅማሬዉ ተረት ሆኖ ከአንድ ድርጊት-ሁነት ጋር ይላወሳል፤ ተላዉሶም ጥቂት መስመሮቹ እንደ ዝርግ ግጥም ይፀድቃሉ:: በጋዜጣ፣ በንባብ ምሽት- በመፅሐፍ ያልተሰበሰቡ - ግጥሞቹ ጥራትም ብዛትም ይስተዋልባቸዋል:: እንድያዉም አንዳንዶቹ የታተሙትን ያደናግዛሉ:: ይህ ሂሳዊ ንባብ በሶስት ክፍሎች ተመድቧል:: መጀመሪያ፥ አጠቃላይ ግምገማ:: ለጥቆ፥ አራት ነጠላ ግጥሞቹ ተበጥረዉ በጥሞና ይነበባሉ:: መቋጫዉ፥ የነብይ ገሃድ-ዘለል surrealistic ግጥሞች ዳሰሳ ይሆናል::

አንድ፥
ስዉር-ስፌት : አጠቃላይ ግምገማ
የሰማይን ህብረ-ቀለም፣ የቀስተ ደመናዉን ዳስ
ባዲስ ልብ እንደመጐብኘት፣ ባዲስ አይን እንደመዳሰስ
ያለ ነዉ የግጥም ጥንስስ:: [ገፅ 117]
ግጥም ሲወለድ የሚቀርብለት ስጦታ ምንድነዉ? የጌትነት እንየዉ መፅሐፍ ሲመረቅ ነብይ ያነበበዉ፤ ባዲስ ልብና አይን የሆነ
ህብረ-ቀለም ሲዳሰስ ግጥም ይጠነሰሳል:: ለሥነግጥም የሰጠዉን ድንጋጌ ያጐላለታል:: ነብይ ለአንድ ስንኝና ለረጅም ግጥም እኩል ይመሰጣል:: ትኩስ ምስል የመከሰት ትሰጥኦዉ አንዳንዴ ይደራረብና አንድን እሳቦት በግልፅነት ያሳሰዋል:: እንደ <የአራስ ጥሪ> እና <የግልብጥ ሩጫ> ግጥሞች:: ሲፈልግ ደሞ እጅጉን ያጠበዉና በሁለት ስንኝ ሙሉ ግጥም ይቀኛል::

ክፉ ሰዉ ሞተ አሉ፣ ኑ እናልቅስ እንቅበር
ደሞ ከደጐቹ፣ ክፉ እንዳይፈጠር
<ስላቅ ቁጥር አንድ> መንቶ ግጥም ነዉ:: ተናጋሪዉ አፈር ለለበሰ አይደልም ጭንቀቱ:: የሚያሳስበዉ የዋህነቱን አወላልቆ ክፋት ለሚከናነበዉ ነዉ:: የዋሲሁን በላይ <ከቻልሽ> አጭር ግጥም ይታወሰል “ሀገሬ አትዉለጂ ያሉት የበቃሉ / ሌላ የሚከዳ እነርሱ ይወልዳሉ” ክህደት አንድ የክፋት ገፅ ነዉ፤ ነብይ የተወለዱት -ገና ቅኖቹ- እኩይነት ህልማቸዉን እንዳይጐረብጠዉ ነዉ ስጋቱ:: ይህ ቀጭን መስመር በነብይ ጠቅላላ ግጥሞች ተዛምቷል:: የነብይ ግጥሞች በአመዛኙ ከክፋት ተላትመዉ ለሰብአዊነት፣ ለተስፋ፣ ለሀገር ፍቅር፣ ለጥበብ ... ይዘምራሉ::

ጊዜ አራቀዉና
ቦታ ለየዉና
እትብትሽ ሰዉ አገር ተቀበረም ቢባል
የእኔ እትብት አለልሽ ለሁለት ይበቃል !
ባገር የበቀለ
ባገር ላይ ያበበ
እልፍ ይዘረዝራል::
እንደነገሩ ሳይሆን፣ የእትብት ተምሳሌት በባህላችን ጥልቅ ነዉ:: አለማየሁ ገላጋይ በአጥብያ ልቦለድ እንደሚለዉ < አገር ... የመንደር ነፀብራቅ ነች:: ... ሰዉ ሁሉ ለአገሩ የሚሞተዉ መንደሩን እያለመ ነዉ:: > አንድ አንጓዉ የተዳሰሰዉ ግጥም ተናጋሪዋ መንደሯን፣ ሰፈሯን፣ ባዕድ አገር ላለች የወዳጅ ልጅ ስትቀኝ ጥቃቅኑ እንደ ዕንቁ ተወልዉሎ በሀገር መኩራት ተጨማሪ ስንቅ ሆናት:: ሌላዉ ቢቀር የቄስ ትምህርት ቤት “በኔታ ጉሮሮ እሰይ ጠጅ ይንቆርቆር” የመሰለ ትዝታ ከልጅነት ዘመን ሲፈልቅ ለምናብም ጠበል ነዉ:: ሃይሌ ገሪማ 92 ላይ በ120 ፕሮግራም ሲቀርብ አድምጠነዋል፤ እኛ ዝምታ፣ ነብይ ግን የጥሞና ግጥሙ ጠነፈፈ::

ተመለስኩ አገሬ
ከአያቴ ሽበት ዉስጥ ታሪኬን ልፈልግ
እንደዶቅማ ልልቀም የህይወቴን ፈለግ ::
ተራ ቃላት ሳይሆን በዘይቤ የራሰ ስንኝ ነዉ፤ ከአገር መመለስ፣ ማንነትን እርጅና ዉስጥ መበርበር፣ አገር በስደት እንዳልሟሟ ያበስራል:: ህፃንም አዋቂም ጀርባቸዉ የሚጐብጠዉ አገርን ከአፍላነት እስከ አረጋዊነት ተሽክመዉት ነዉ::
ነብይ ከአያሌ ገጣሚያን የሚለይበት፣ የደመቀበት አንድ ጠገግ አለ:: ክቡር ስም ለተሰጣቸዉ ኢትዮጵያዉያን - በተለይም ድንገት በሞት የተቀማናቸዉን- ስሜቱ ተሸረካክቶ፣ ምናቡ ትፍታቶ ወደ ህይወት ይጠራቸዋል፤ ያቆያቸዋል:: የሀዘን መግለጫ ሳይሆን የግለሰቡ እሴትና ብርቅነት እንዲሁም ስራዉንና ባህሪዉን ከመገንዘብ የሚፈልቅ የስሜት የፀፀት ዉጤት እንጂ... ገና 1976 ነብይ ማዕከላዊ እስር ቤት እያለ ነበር ለክቡር ስም መቆርቆር የጀመረዉ:: በትግል ወቅት ከበደ ሚካኤል እንደ ህዝባዊ ገጣሚ ሳይሆን ለሌላዉ ወገን መዝመሙ ነበር የተሰመረበት:: ሆኖም ነብይ እየቆየ ያጤነዉን በሶስት ስንኝ የተዋቀረ እምቅ ግጥም በሚያሻማ ፍካሬ አስነብቦናል::

ያኔማ ልጅ ነበርኩ እድሜዬ ገራገር
ያኔማ ልጅ ነበርኩ ህይወቴ ግርግር
ሳድግ ነዉ የገባኝ የከበደ ነገር:: [ጥቁር ነጭ
ግራጫ ፥ 6]
ተናጋሪዉ ምንድን ገባዉ ? ከበደ ሊቅ አስተዋይ ወይስ ገለልተኛ፣ አስተኔ? ነቢይ በከበደ ሚካኤል የአፃፃፍ ዘዬ <ሁለት ጠበኞች> ስለ ምላሰኛና ቀናተኛ ሴቶች ግጥም ፅፏል:: መታሰቢያነቱ <ለከበደ ሚካኤል ተማሪዎች > በማለት:: [ጥቁር ነጭ ግራጫ፥ 27] እንዲሁም
አያ ሳቅ እሳቱ፣ ፍሙን አክስሞታል
ኮሜዲዉ አርጅቶ ትራጀዲ ሆኖል በማለት ለመንግስቱ ለማ ተቀኝቷል::
የገብረ ክርስቶስ ደስታ ህልፈት የገጣሚዉን ስሜት ግራና ቀኝ ተቀባበሉት፤ ሶስት ገፅ በፈጀ ግጥሙ ሊያገኘዉ፣ ሊያወያየዉ ታከተ::

ሙያህም ነገህም ገብሬ፣ እንዳንተዉ እሩቅ በራሪ
እንዳንተዉ ስደተኛ ነዉ፣ ባህር ማዶ ተሻጋሪ
አደህይቶን አገር ዟሪ::
ለማይሞተዉ ወዳጁ ፀጋዬ ገ/መድህን በስድስት ገፅ ጊዜን ለመግታት ቻለ::

“ጐህ ሳይቀድ አረፈ!” ሲሉ
አይዋጥልኝም ቃሉ
የህይወትህ ዉጣ ዉረድ፣ ከማን ሆነና ነዉ
ትግሉ ?
ሰማይ በጮራ ተነድሎ ፣ ጐህ እንዲቀድ አደል
ዉሉ ?
አንድ ግለሰብ “ጉቶ የሸፈነዉ፣ ያገር ግዙፍ ዋርካ ”ቢያክልም ሳይዘመርለት፣ ጠበል ሳይደርሰዉ ሊቀዝዝ ሲችል ነብይ በግጥም ብርሃን ያጥለቀልቃዋል:: <... ነቢይ አንድ ዘዉግ የሆነዉ ሌሪክ ግጥም ስር የሚመደበዉን “ሙሾ” እንደ አንድ ኪናዊ ቅርፅ በአፃፃፍ ብልሃትና በድምፀት በማራመድ ረገድ ለአማርኛ ሥነግጥም ያበረከተዉ አስተዋፅኦ> ገና የሚጠና መሆኑና <... እጅግ በርካታ በሆኑ ማህበራዊ ሁነቶችና አጋጣሚዎች ላይ በአጭር ጊዜ የተዋጣላቸዉን ማራኪ ግጥሞችን እንዲሁም ድንቅ የዉዳሴ መዝሙሮችና የሃዘን እንጉርጉሮዎችን የሚፅፍ ምናበ ሰፊ> መሆኑን ብርሃኑ ገበየሁ አስምሮበታል:: [መድበለ ጉባኤ ፥ ገፅ 198-200]
ነቢይ ግጥሞቹን ርዕሰ ጉዳይ እየመረጠላቸዉ ይቀነበባሉ:: አንድ ግጥም ከቋፍ ያዘለቀዉ ጭብጥ ተስተዉሎ ነዉ የተቀነበበዉ፣ ሁለት- ሶስት ቦታ ቢመደብም ለፍሬ ይበቃል:: በግጥሞቹ ለኑሮ፣ ለጥበብ፣ ለትዝታ፣ ለብርቅ ግለሰብ፣ ለተስፋ፣ ለአገር ተቆርቋሪነት... ይመሰጣል:: በወሲብ የመተሻሸት ጉዳይ ሲያደባ ግን ቁጥብ ነዉ:: <ኮከብ ቆጠራ> እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል:: ተባዕትና እንስት የመስክ ሣር ላይ በጀርባቸዉ ተንጋለዉ ኮከብ ይቆጥራሉ ....

ድንገት ዞር ስትይ፣ ዞር ብል በድንገት
በዐይን ንጥቀት ፍጥነት
የቆጠርናቸዉም፣ ያልቆጠርናቸዉም
ትንሹ... ትልቁ
ከዋክብቱ ሁሉ ተደበላለቁ
ከንፈሮቻችን ላይ፣ እሳት አፈለቁ
ከዚያ የሆነዉን፣
እኛም አላወቅን፣ እነሱም አልነቁ
እንዲሁም <የኮከብ ቡና > ግጥሙ ወሲብን እያደራ ይረግባል::
ቋንቋዉ እንደ ዮሐንስ አድማሱና ዳኛቸዉ ወርቁ ጠነን ባሉ ቃላት (ፍች በሚለማመጡ) አልተጋመደም:: በዉብ አዲስ ምስል የተቀረፀ፣ የሀገር ቤት ፈሊጥ ሆነ የንግግር ፅላሎት የሚታወስበት፣ አንድ ግልፅ እሳቦት የፈረጠበት ግጥም ነዉ - በአመዛኙ:: ብርሃኑ ገበየሁ እንዳለዉ <ነብይ ሁሉን የህይወት ገጠመኝ መተረትና ቅርፅ ማስያዝ ይሆንለታል> ሙሉ ግጥም የሚወጣቸዉ አጭር ወይም መንቶ ስንኞች በየግጥሙ ተጠልለዋል፤ ብቻቸዉን ዕምቅ ግጥም ይወጣቸዋል:: እንደ ከበደ ሚካኤል ተራኪ ግጥሙን የሚቋጭብት ሳይሆን እሳቦቱን ሲቀባባ ይደራረቡባታል:: ለምሳሌ <ከበቀሉ መፅደቅ> ሶስትዮሽ ግጥሙ

በጥላ በጣዩ ረክቶ በጥሞና ለሚኖረዉ
እያንዳንዱ ማታና ቀን የየራሱ ዘላለም ነዉ [በዚህ ግጥሙ ብቻ ጥቂት እንጐቻ ግጥሞች አቆጥቁጠዋል::]
በብዙ የነብይ ግጥሞች እሳቦት ወይም ገጠመኝ ግልፅ ስለሆነ በአንድ አረፍተ ነገር ሊሰበሰብ ይችላል:: ሆኖም የሚጥም ቋንቁና ለጋ ምስል ያከርማቸዋል:: ለጥላሁን ገሰሰ በሶስት ገፅ የተቀኘዉ በአራት ስንኝ ፍንጭ ሆኖ ይፍታታል::

ወድያ ከወደ ወሊሶ
አንድ አራስ ድምፅ ተፀንሶ
እናት ልጅ ወለድኩ ብላ
አንቅልባ ሙሉ ድምፅ አዝላ
“አንቅልባ ሙሉ ድምፅ ” የመዝገበ ቃላት ፍች አይደለም - ረቂቅ ነዉ:: ሰዉን ሳይሆን ድምፅን ወተት ማጥባት፣ ወፌ ቆመች ማለት፣ ድምፅን ማሳደግ እንጂ:: ያ ድምፅ ፀድቆ ስሜት ሊሰዉር:: ግልፅነት ግጥምን አንድምታ ይነፍገዉና ያሳሰዋል፤ ነቢይ በሚያባንን ምስል ትንፋሽ ስለለገሰዉ አይሰለችም እንጂ::

ህይወት መልኳ ሁለት ነዉ
አንድ ፊቷ ሙቀት ዉበት፣ ላንጨብጠዉ
የምናየዉ
እንደ ምድጃ ዳር ተረት፣ በፈገግታ
የምንለዉጠዉ፤
ሌላ ፊቷ ፈጣን ቀለም፣ ከሩቅ ከቅርብ
የምንወደዉ
በረርን-ለፍተን፣ጨንቆን-ጠቦን፣ተሯሩጠን
የምንይዘዉ
ህይወት እንደ ህልም፣ ህይወት እንደ ዉጣ ዉረድ በደረቁ የተዘረገፈ ሳይሆን በምስል የተወጠረ ነዉ:: ቅዠትና ጥረት ይፈራረቃሉ::
አንድ-ሁለት ግጥሙ ግን ግልፅነቱ ፈክቶ ከማሳሳቱ የተነሳ ዘይቤም አያሻግረዉም:: <የአህጉሬ የምርጫ ዜማ> አጭር ግጥም ቢሆንም የምርጫ ዉጤት የተጭበረበረ ነዉ የሚል ዘገባ ፈረጠ እንጂ አልተጦቀመም:: <ወይ ጠበል> የሚለዉም የነቢይን ብዕር አይመጥንም :: <የዕድሜ ዕቁብ ቢኖር > የተሻለ ግጥም ቢሆንም ርዕሱ ጭብጡ ነዉ:: በአንድ አንጓ ሊታመቅ ሲችል በሶስት ገፅ መነመነ:: ምናልባት ገጣሚዉ ሲቀኘዉ በበቂ ዉስብስብ ስሱነት አልተያዘ ይሆናል:: ግን <አገርክን ፍለጋ > በአንፃሩ የእሳቦቱ ስፋት፣ የጉዞዉ ቅርበት ርቀት መላተም ድንቅ ነዉ:: የቋንቋ ዉበት ያቀናዉ ግልፅ እሳቦት ብቻ አይደለም፤ ገጠመኙ ብዙ ጓዳ አለዉ:: ሁለቱም ግጥሞች የሰዉ ዕድሜ ማጠር ቢያጠልባቸዉም ተበላልጠዋል::
ግጥም ጭብጥ ብቻ አይደለም፤ እምቅነት፣ ዜማ፣ የቋንቋ ዉበት፣ ምናበ ሰፊነት... ነብይ በእነዚህ ሁሉ የተካነ ነዉ:: ሆኖም ግጥም ግልፅ ወይስ አሻሚ መሆን አለበት? <አሻሚነት፣ ከአንድ ፍቺ ባላይ ትርጓሜ መያዝ፣ ከግጥሙ ዐዉደንባብ በመነሳት ቁርጥ ያለ ትሩጓሜ ለመስጠት (እንዲህ ነዉ ብሎ ለመወሰን አለመቻል) [የአማርኛ ሥነግጥም ፥ 411] አንባቢ ገለልተኛ አይደለም፤ ሎሬት ፀጋዬን፣ ደበበን፣ ሰለሞን ደሬሳን፣ በድሉ ዋቅጅራን፣ በዕዉቀቱን... አንብቦ ይሆናል ወደ ስዉር-ስፌት የመጣዉ:: ንባቡን ይጫጫኑታል:: አንባቢ ጀማሪም ቢሆን ያደመጠዉ የቃል ግጥም፣ ዕንቆቅልሽ፣ ተረትና ምሳሌ ... ዉስጡ መሽገዋል:: Barthes በዝነኛ መፃፅፉ <The Death of the Author> የአንባቢ መወለድ የደራሲን ህልፈት ይጠራል ባይ ነዉ:: ፅሁፍ ከደራሲ ተላቆ የአንባቢ ጣጣ ሆኗል እንደማለት፤ የደራሲዉ ግለህይወት ሳይሆን ፅሁፉ ነዉ ወሳኝ:: ምንባብ፥ ሁለት ዐይነት ነዉ ይላል፤ ‘readerly text’ አንባቢዉ ገለልተኛ ሆኖ በዝምታ የሚያነበዉ:: ‘writerly text’ የአንባቢን ንቁ ተሳትፎ የሚያደፋፍረዉ:: ግጥምን ለማጣጣም ግልፅም ድፍንፍንም ሲሆን ይገፈትራል፤ አሻሚነቱ -ambiguity-ደግመን አንድም እያልን እንድናነበዉ ይፈታተናል:: መዝገበ ቃላት “ገለጠ”ን ሲፈታ ብርሃን ሆነ፣ አሳየ፣ አስረዳ ብቻ አይልም:: <ሳሳ፣ መመለጥ ጀመረ> ብሎ ይተረጉማል:: ይህ የግጥም መመለጥ፣የግጥም መሳሳት ነዉ ለአሻሚ ስንኞች የሚያስገበግብ:: ፀጋዬ ገ/መድህን እና ሰለሞን ደሬሳ አያሌ ግጥሞቻቸዉ እየቆየ ሲነበብ ለጋ ፍካሬ ይፈርጣቸዋል - አያበቁም:: “የዕዉነተኛ ግጥም ማራኪነት እንደ ዐይን ፍቅር በዝያችዉ የንባብ ቅፅበት ይወለዳል” ይላል ነብይ [ ጥቁር ነጭ ግራጫ ፥ 36] ልክ ነዉ፤ በተጨማሪ የግጥም መሸሸግ እያደር ይመስጣል:: ነብይ ጥቂት ቶሎ ጓዳቸዉን የማይገልጡ ግጥሞች አሉት:: <ገዋ..ሰዉ...ገዋ>፣ <ላማባዲናም የለኝ...>፣ <ክታቤን ልሰብስብ>፣ <እስረኛዉና የሰጠመችዉ ፀሐይ> ... የመሳሰሉት:: <ስላቅ ቁጥር ሁለት> ዕምቅ ግጥሙ በተነበበ መጠን የተለያየ ፍካሬ ያፈልቃል::

ብቻዋን ነጭ ናት ይች የጥቁር አገር
ጉዷም አይደበቅ ጉዷም አይነገር::
ልማዷን፣
ባህሏን ለማክበር፣
እንደፈረደብኝ እኔዉ ጭሬ ልደር::
ዜማዉ፣ ምናቡ፣ መመሰጡ… ብቻ ሳይሆን ማዉጠንጠንን የሚቀሰቅስ ያልፈረጠ እሳቦት አስቀርቷል:: በተለይም ግጥሙ የተበረከተዉ ለአንድ ያነበበዉ መፅሀፍ - የሥልጣኔዎች ግጭትና የአዲስ ዓለም ሥርዓት - መሆኑን አወሳስቦታል:: አንባቢዉ እንደ ዕዉቀቱ፣ ገጠመኙ... ከአንድ በላይ ትርጓሜ ያከርበታል:: በተለይም የርዑየቱ ስፋትና የተናጋሪዉ <እንደፈረደብኝ እኔዉ ጭሬ ልደር> ብቸኝነት፣ ምርኩዝ መነፈግ ወይም በራስ መተማመን የመሰለ አሻሚነት እንድናስብ ያነቃቃል:: ምስሉ የተለመደዉን ፍች ተሻግሮ ያዉካል:: ይህ አይነት ግጥም ነዉ ለአንባቢ ትንፋሽ፣ እሳቦት... ጓዳ የሚያስተርፈዉ::
ግጥሙና መፅሐፉ ምን ያክል ተነካክተዋል ? የግጥሞች ዝምድና -intertext- ምርጥ ገጣምያን ዘንድ የተለመደ ነዉ:: እንዳለ መገልበጥ ሳይሆን በርቀት ማጥቀስ አዲሱን ግጥም ያደነድነዋል፤ ለአንባቢም የሁለቱ ዝምድና ሊመስጥ ይችላል:: መንግስቱ ለማ ሶስት ገፅ የፈጀ “ሕይወት” በሚለዉ ግጥሙ አዉጠንጥኗል :: “ማን ያዉቃል ? / የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ / ቀጠሮ እንዳላቸዉ መስከረም ሲጠባ” ይህ ጥያቄ ከነቢይ ምናብ ደብዝዞ በ<የመስከረም ፍቅር> መገቻዉን አገኘና ፈካ:: ዐዉዳመትና ፍቅር ተደጋገፉ::

ልብሽ ለመዝፈኑ፣ ልቤ ለማዜሙ
ምን ያሻል ምስክር፣ ለዓለም ዘልዓለሙ
መስቀል-ወፍና ፀደይ፣ ከተፈፃፀሙ !
እነ Barthes ደራሲ ከመፍጠርም፣ ከመቀኘቱም በፊት በሌላ ምንባቦች፣ገጠመኝ፣ ስሜት... የተሞላ ስለሆነ ፅሁፉ ከምንም ከገዋ አያጐነቁልም፤ ከሌላ ፅሑፎች ጋር ይነካካል:: ገጣሚዉ አስቦበት ወይም ሳያዉቀዉ ይሆናል:: የደበበ ሰይፉ <ዘመዴን ስስመዉ> በነቢይ <ይድረስ ለወዳጄ> እንደስንኝ ተዛመደ::

ዘመዴን ስስመዉ
ጐንጬ ቢሻክረዉ
እኔንም ሻከረኝ፤
ዕድሜ መለስለሱ ማብቃቱ ታወቀኝ::
አንድም እርጅና ፣ የዕድሜ መንጠፍ ነዉ:: አንድም የዋህነት፣ ለጋነት አብቅቶ ግለሰብ መሻከሩን መብሰሉን፣ ለዘመድ መረማመጃ አለመሆኑን ያበሰረበት አርነት ይሆናል:: በተለይ ተናጋሪዋ ሴት ከሆነች ደግሞ ተጨማሪ ጓዳ ያበጃል። ነብይ -ለዘመኑ ወጣትና ለነገዉ ጐህ- ያበረከተዉ ረዘም ያለ ግጥም <ይድረስ ለወዳጄ> ወጣቱን፣ ወራሹን ቀድሞ እንዲገኝ “ ነብስህ እንደ ሱፍ አበባ፣ ለነገ ፀሐይ ትከፈት” እያለ ነዉ ከታህተ ንቃቱ ያንቀላፋ የደበበ ግጥም የተወራጨዉ::

ፂሙ ቢሻክረህ እንኳ፣ እያንዳንዱን ቀን ሳመዉ
በፍቅርህም በሞትህም፣ ቀርበህ ስታዉቀዉ፣
ዘመድ ነዉ
የደበበ ግጥም በሁለት ስንኝ ተመሳስሎት ተለቃለቀና የሚመስጥ የዘመን ዐዉድ አበጀ::
ነቢይ እያንዳንዱን ግጥም ሲቋጭ ለግለሰብ፣ ለገጠመኝ፣ለሁነት... ማበርከቱ ትርፍ አይደለም:: - ለማትጠገብ ሀገርና ለልብ አዉልቆች - ክንፋቸዉ ለተሰበረ ወፎች - የራስጌ ማስታወሻ ለሌላቸዉ ... ጥሬ ትርጋፅ ወይም ለግጥሙ ልጣጭ ሳይሆን ተጨማሪ ንዝረት ነዉ፤ ዳር ተቀምጦ ይተነፍሳል::
< የታየዉን ነገር ባልታየበት በኩል፣ ድንግል በሆነበት ገፁ ማሳየትና ህጉን መግሰስ የግጥም መሰረታዊ ነገር ነዉ> ይላል ነብይ በስብስቡ መግቢያ፤ ተሳክቶለታል::

ሁላችን አሳብ እኮ ነን
ጅምር ሀሳብ የሰዉ ዉጥን፣
ከሰዓሊ ቀለም እኩል
ከፀሐፊ ጭረት እኩል
በጠብታ ተጀምረን፣ ጐርፍ ለመሆን የምንችል
በቃል በሆሄ ተነጥበን፣ ህይወት አክለን
የምንዉል:: [ገፅ 125]
አይደናበርም፤ ግጥም ለመሰብሰብ፣ ከሩቅ ጭል ጭል የሚለዉን ፍም ይከተላል:: ከወንዝ ስምጣ ተስፋ ላጠራት ፀሐይ ሳይሆን፣ ከሰዉ ለፈለቀ ብርሃን ነዉ የተቀኘዉ::

ዉበትን ሰዉ፣ ሰዉን ዉበት፣ ሲፈልግ ይኖራል
ገና
አዲስ ጣዕም ለማጣጣም፣ ዝንተ-ዓለም
ይራባልና [ ገፅ 132]
ዉጥን፣ ጭረት፣ ሆሄ ... በነቢይ ሶስተኛ ስብስብ ለመድፍረስ ተጠራርተዉ በግጥም ለመቀረፅ ይቀላዉጣሉ:: የተራበም አንባቢ የባለቅኔዉን ብዕር ለክፉ ቀን እንዲሆነዉ ሳይታክት ያንኳኳል:
ይቀጥላል

Read 5372 times