Wednesday, 12 June 2013 15:47

የመሲሁ መሪ አመራርና ፍፃሜአቸው

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

ጋናውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ “የእኛ መሪ ክዋሜ ንክሩማህ፤ ተራ መሪ ሳይሆን “ኦሳጊይፎ” (ድል አድራጊ) እና የመላ አፍሪካ ተምሳሌት ወደምትሆን ነፃና የበለፀገች ጋና የሚወስደን መሲህ መሪ ነው” ብለው በከፍተኛ አድናቆትና ፍቅር እልል ብለውላቸዋል፡፡ እሳቸውም “አዎ! እኔ ተራ መሪ ሳልሆን ለተለየ ተልዕኮ የመጣሁ ልዩ መሪ ነኝ” ብለው በአደባባይ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ይህ የፕሬዚዳንት ንክሩማህ የአደባባይ ላይ ንግግር እንዲሁ በንግግር ብቻ ቀርቶ ቢሆን ኖሮ ለእርሳቸውም ሆነ ለጋናውያን መልካም ነገር በሆነ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰባቸው፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አመራራቸው እጅግ የተዋጣላቸውና የተሳካላቸው መሪ እንደሆኑ በእርግጠኝነት እንዲያምኑ አደረጋቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ይበልጡኑ ብቸኛና እንኳን ሰው ጥላቸውንም የማያምኑ ክፉኛ ተጠራጣሪ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ከእለት ወደ እለት ከህዝቡ እየራቁ መሄድ ጀመሩ፡፡

በ1957 ዓ.ም ጋና ነፃነቷን የተቀዳጀችበትን ቀን አስመልክቶ በተካሄደው ታላቅ የራት ግብዣ ላይ ከተዋወቁ በኋላ፣ የአንድ ሰሞን አንሶላ ተጋፋፊ ወዳጃቸው የነበረችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ቆንጆ ጀኖቪቫ ማሪያስ በፃፈችው የህይወት ትዝታ መጽሐፏ፤ “ንክሩማህ በፖለቲካ ረገድ እየተሳካለት በሄደ ቁጥር፣ የቅርብ ወዳጆቹንና የስራ ባልደረቦቹን የፈለገውን ያህል ለእሱ ታማኞች ቢሆኑም እንኳ ይበልጥ እየጠራጠራቸውና እያራቃቸው መሄድ ጀመረ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም በራሱ ብቸኝነት ውስጥ እየሰጠመና ከአብዛኛው ህዝብ ራሱን እያገለለ መሄድ ጀመረ፡፡ ከህዝቡ ይልቅም ሊሰማው ይፈልጋል ብለው የሚገምቱትንና ከፍተኛ የበላይነት ስሜቱን የሚያጠናክርለትን ነገር ብቻ እየመረጡ የሚነግሩትን የፓርቲ ካድሬዎችን ድጋፍ ብቻ ማግኘት ቻለ፡፡” በማለት ፅፋለች፡፡

ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ በዚህ የብቸኝነት አለማቸው ውስጥ እየኖሩም ቢሆን ታዲያ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ግንብ መገንባት ችለዋል፡፡ ጋና ሪፐብሊካዊ ሀገር እንደሆነች የሚደነግገውና በ1960 ዓ.ም የፀደቀው አዲሱ የአገሪቱ ህገመንግስት፤ ለፕሬዚዳንት ንክሩማህ በፈለጉ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እንዲመሩ፤ ፓርላማው የሚያወጣቸውን ህጐችና ውሳኔዎች እንዲሽሩና ማንኛውንም የመንግስት ባለስልጣን በፈለጉበት ጊዜ ማባረር እንዲችሉ ከፍተኛ ስልጣን አጐናጽፎአቸዋል፡፡ ፓርላማው ጨርሶ የማይቆጣጠረውና ኦዲት የማይደረግ የፕሬዚዳንቱ የመጠባበቂያ ፈንድም አቋቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑም፣ የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሀን ማለትም ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ቻሉ። በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ በመጠቀምም፣ ከፍተኛና መሠረተ ሰፊ የቁጥጥር መረብ በመዘርጋት ስልጣናቸውን በብቸኝነት አጠናከሩ፡፡

የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ፤ ግንባር ቀደምና የበላይ ገዥ ፓርቲ መሆኑን በማወጅ፣ ጠቅላላ የጋና የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የሰራተኛ፣ የገበሬና የወጣት ማህበራት ሁሉ በፓርቲው ስር እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ ከፓርቲው ቢሮዎች ጀምሮ እንደጋና ሴቶች ካውንስል፣ የግንባር ቀደም ታጋዮች ድርጅት፣ የጋና የሰራተኛ ብርጌዶች፣ የጋና ወጣት ታጋዮች ማህበር ወዘተ እስካሉት የሲቪልና የፖለቲካ ድርጅቶች ድረስ የንክሩማሂዝም ርዕዮተ አለምንና የንክሩማህን መመሪያዎችና ትዕዛዞች በመላው የጋና ምድርና ህብረተሰብ ዘንድ ሌት ተቀን እንዲያስፋፉ ትዕዛዝና ሃላፊነት ሰጧቸው፡፡ “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም።” የሚለው እድሜ የጠገበ የአፍሪካውያን አባባል አፍሪካውያን መሪዎች ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ “የስልጣንን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” በሚል ቀይረውታል፡፡ በአፍሪካ ሀምሳ የነፃነት አመታት ውስጥ በተደጋጋሚ እንደታዘብነው፣ ለአብዛኞቹ የአፍሪካ መሪዎች ስልጣን ማለት የነብር ጅራት ማለት ነው።

አስቀድመው የሚይዙት፡፡ ከያዙት ግን ጨርሰው የማይለቁት፡፡ በዚህ የተነሳም ለእነዚህ መሪዎች የተቃዋሚዎቻቸውና ተቀናቃኞቻቸው ህልውና ማለት የነብሩ ጥርስና ጥፍሮች ማለት ናቸው። እናም በማናቸውም አይነት ዘዴ ቢሆን መወገድ አለባቸው፡፡ ለእነዚህ መሪዎች፣ ተቃዋሚቻቸውንና ተቀናቃኞቻቸውን ቸል ማለት ወይም ንቆ መተው፣ ካምሱሩ ከተፈታ ቦንብ ላይ ሃሳብን ጥሎ ተደላድሎ እንደመቀመጥ ማለት ነው፡፡ ከሞላ ጐደል በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ስልጣን በያዙት መሪዎች የሚገደሉት፣ የሚታሰሩትና ከፍተኛ መንፈሳዊና አካላዊ እንግልት የሚቀበሉበት ዋነኛ ምክንያትም ይሄው ነው፡፡ የጋናና የአፍሪካ ነፃነት መሲሁ መሪ ክዋሜ ንክሩማህም ከእነዚህ የተለዩ መሪ አልነበሩም፡፡ ይህን ሁሉ ስልጣን ይዘውና መፈናፈኛ የሌለው ከፍተኛ የቁጥጥር መረብ ዘርግተውም ቢሆን የስልጣን የቁጥጥርና የበላይነት ጥማታቸው ቅም ሊለው አልቻለም፡፡ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚዎቻቸው በነፃነት ሲዘዋወሩ ማየት ጨርሰው ሊቋቋሙት የሚችሉት ነገር አልነበረም፡፡ ለፕሬዚዳንት ንክሩማህ የተቃዋሚዎቻቸው ህልውና እንደአይናቸው ብሌን የሚሳሱለትን ስልጣናቸውን መገዳደር ብቻ ሳይሆን እኩያ የሌለውን የበላይነት ስሜታቸውን መንካትና የመሲህነት ክብራቸውን ዝቅ ማድረግ ማለት ነበር፡፡ እናም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ለዚህ ዝግጁ የሆነ ልብም ሆነ ትዕግስት ፈጽሞ አልነበራቸውም፡፡

ይሁን እንጂ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የተማሩት ትምህርትና ልባቸውን አለቅጥ ጢም አድርጐ የሞላው የታላቅነት መንፈሳቸው፤ የጊኒው ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ፣ የማላዊው ፕሬዚዳንት ካሙዙ ባንዳና ሌሎች በወቅቱ የነበሩ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች ተቀናቃኞቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን ለማስወገድ እንዳደረጉት አይነት በጠራራ ፀሐይና በአደባባይ በጥይት ግንባራቸውን እየቀነደቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በጄ አላላቸውም፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ይህንን ከማድረግ ይልቅ ተቃዋሚዎቻቸውን የማስወገድ ቀጣዩን እርምጃቸውን ዘመናዊና ህጋዊ መሠረት ለማስያዝና ሽፋን ለመስጠት በመወሰን ከ1958 ዓ.ም የቅድሚያ መከላከል እስር ህግን አወጁ፡፡ ይህ አዋጅ መንግስት የፈለገውን ማንኛውንም ጋናዊ ያለአንዳች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማሰርና ያለአንዳች ፍርድ እስከ አምስት አመት ድረስ አስሮ የማቆየት ስልጣን አጐናጽፎታል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህም ይህንን አዋጅ በመጠቀም አንዳች አይነት የህግም ሆነ የፖለቲካ አቧራ ሳያስነሱ የልባቸውን መስራት ችለዋል፡፡ ንክሩማህ፣ ይህንን አዋጅ ለፓርላማው አቅርበው ሲያፀድቁ አስራ ሁለት ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ቀድሞ ነገር አዋጁ ለማንና ለምን እንደተረቀቀ ስለማያውቁ፣ ፓርላማው ውድቅ እንዲያደርገው ተማጽነውም ተቃውመውም ነበር፡፡

አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የማታ ማታ የፈሩት አልቀረላቸውም፡፡ አዋጁ በፀደቀበት አመት በቁጥጥር ስር ውለው ወህኒ ከተወረወሩት ሰላሳ ስምንት ተቃዋሚዎች ውስጥ አስራ አንዱ እነዚሁ ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ፓርላማውን ተቃዋሚ አልባ ለማድረግ የነበራቸውን እቅድ በዚህ አይነት ካሳኩ በኋላ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ተቃዋሚዎቻቸው ላይ አዞሩ፡፡ ይህንን አዋጅ በመጠቀምም፣ በ1961 ዓ.ም ሶስት መቶ አስራ አንድ፣ በ1963 ዓ.ም አምስት መቶ ሰማኒያ ስድስት፣ በ1965 ዓ.ም ደግሞ አንድ ሺ ሁለት መቶ የሚሆኑ ተቃዋሚዎቻቸውን ከያሉበት አሳፍሰው ወህኒ በመወርወር፣ አንዳንዶቹ በደህንነት ሀይል በደረሰባቸው ከፍተኛ አካላዊ ጉዳትና በእስር ቤቱ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ የተነሳ ህይወታቸውን እንዲያጡ አስደርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ለንደን በስደትና በትምህርት ሳሉ ጀምሮ የቅርብ ጓደኛና የፀረ ኮሎኒያሊዝም የትግል አጋራቸው የነበሩትና በደረሰባቸው ኢሰብአዊ እንግልትና የህክምና እጦት በእስር ቤት እንዳሉ በ1965 ዓ.ም ህይወታቸው ያለፈው ዶክተር ዳንቃህ ይገኙበታል፡፡ በ1964 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ጋናን ከብዙሀን ፓርቲ ስርአት አራማጅ አገርነት ወደ ባለ አንድ ፓርቲ አገርነት ለመቀየር በግላቸው ወሰኑና ህዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ ቀን ቆርጠው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከመካሄዱ በፊት ታዲያ እሳቸው በዋናነነት የሚቆጣጠሩት የመንግስት ብዙሀን መገናኛዎች፣ በህዝብ ውሳኔው የማይሳተፍና የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በመቃወም ድምፅን የሚሰጥ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚቀጣ ማስፈራራታቸውን አጧጧፉት፡፡ ለምሳሌ “ጋናያን ታይምስ” የተባለው መንግስታዊ ጋዜጣ ህዝቡን ያስፈራራው “የሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ የሚባለውን አሠራር መከታ በማድረግ ልታታልሉን የምትፈልጉ ሰዎች ሁሉ በደንብ ማወቅ ያለባችሁ ትልቅ ቁምነገር፣ እኛን ማታለል የምትችሉበት ጊዜ ያከተመ መሆኑን ነው፡፡” በማለት ነበር፡፡ ጋናን ወደ አንድ ፓርቲ አገርነት የመቀየሩ ውሳኔ እሳቸውን በምድረ ጋና ያሉ ብቸኛው የፓርቲ መሪ ከማድረግ ውጪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ረገድ ለንክሩማህ የፈየደላቸው ነገር አልነበረም፡፡

ምነው ቢባል ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ፕሬዚደንቱ ቀደም ብለው በወሰዷቸው የአፈናና የማስወገድ እርምጃዎች ጨርሰው ከጋና የፖለቲካ ጨዋታ ውጭ ሆነው ነበርና። ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ በ1965 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ስማቸውን በክፉ እያነሱ በሀሜት ሲቦጭቋቸው ተገኝተዋል ተብለው በቢሮአቸው የቀረቡላቸውን ሁለት ጋናውያን ፍላግ ስታፍ ህንፃ እየተባለ በሚጠራው ፕሬዚደንታዊ ፅህፈት ቤት ግቢ ባቋቋሙት የዱር አራዊት መጠበቂያ ፓርክ ውስጥ እንዲገቡ በማስገደድ፣ በአንበሳ ተበልተው እንዲሞቱ አስደርገዋል እየተባሉ በቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ሲታሙ ኖረዋል፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ ይህን ፓርክ ያቋቋሙት ወዳጆቻቸው የሆኑ የአፍሪካና የሌሎች ሀገራት መሪዎች በስጦታ ባበረከቱላቸው የዱር አራዊቶች ነበር፡፡ ለምሳሌ ሰዎቹን የበላውን አንበሳ ያበረከቱላቸው አባባ ጃንሆይ ሲሆኑ ጉማሬውን የሰጧቸው ደግሞ የላይቤርያው ፕሬዚደንት ቶልበርት ተብማን ነበሩ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኘውን ምን የሚያህል ዘንዶ ያበረከቱላቸው ደግሞ የኩባው ፕሬዚደንት ጓድ ፊደል ካስትሮ ነበሩ፡፡ ጋናን በብቸኝነት የመምራት ኃላፊነት የተሸከመው የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ፣ በሊቀመንበሩ በንክሩማህ ፈላጭ ቆራጭ አመራር ስር በመውደቁ ብዙም ሳይቆይ ለመበስበስና ለሙስና አደጋ በእጅጉ ተጋለጠ፡፡ የፓርቲው አባላት የሆኑ ሚኒስትሮችና የፓርላማ አባላት መደበኛ ስራቸው የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውን፣ የጐሳና የብሔር አባሎቻቸውን ጥቅም ማሳደድና ከፍተኛ የግል ሀብት ማከማቸት ብቻ ሆነ፡፡ ሚኒስትሮች ከእያንዳንዱ የመንግሥት ፕሮጀክት አስር በመቶ ሲቦጭቁ፣ ሌሎች የበታች ሹሞች ደግሞ እንደየደረጃቸው የመንግሥትን ሀብት መቀራመት ስራዬ ብለው ያዙት፡፡ በሙስናና የግል ሀብት በማካበት በኩል የማይታሙት ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ጉዳዩ በጣም ሲያሳስባቸው በ1961 ዓ.ም ሙስናን ለመዋጋት ቃል በመግባት፣ በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥትና የፓርቲ ባለስልጣኖችን አጥብቀው አወገዙ፡፡

የተወሰኑ ባለስልጣኖቻቸውንም ከስራ አባረሩ፡፡ የሙስናን ጉዳይ የሚያጣራና የባለስልጣኖቻቸውን ሀብት፣ ቤት፣ መኪናና ውሽሞቻቸውን ሁሉ የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ አቋቋሙ፡፡ ይሁን እንጂ የተቋቋመው ኮሚቴ ስለአከናወነው ተግባር አንዲትም ነገር ትንፍሽ ሳይልና ይኑር ይፍረስ ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ ቀረ፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ጋናን ወደ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ አገርነት ለመለወጥ ያወጡትን እቅድ በተግባር ለመለወጥ ያደረጉት ጥረት በመጀመሪያው ሁለትና ሦስት አመታት ደህና ይመስል ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና መንገዶች በብዛት መገንባት ችለዋል፡፡ ለተጠቃሚው በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ ያስቻለውና በቮልታ ወንዝ ላይ የተገነባው የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ጣቢያ የተጠናቀቀውም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ታላላቅ የልማት ውጤቶችን በፍጥነት ለማየት ትእግስት ያጡት ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአናት በአናቱ ማዘዝ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሮች ሁለ ካቅሟ በላይ የሆኑባት ጋና፣ በኢኮኖሚ ውጥረት ውስጥ ወደቀች፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1961 ዓ.ም የአለም የኮካዋ ምርት ገበያ ዋጋ በመውደቁ፣ መንግሥት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ታክስና ግብር እንዲጥል አስገደደው፡፡ ይህም በበኩሉ ከፍተኛ የሆነ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ መናርንና ሊቋቋሙት ያልተቻለ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን አስከተለ፡፡ ይህንን በመቃወምም የወደብና የባቡር ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ መቱ፡፡ የአድማው ዜና የተነገራቸው ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ እንዴት ተደፈርኩ ብለው በንዴት ጧ ፍርጥ አሉ፡፡ የጦፈው ንዴታቸው ወደ እርሱ እንዳይዞር የፈራው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትራቸው፣ በጋና ብሔራዊ ሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት በመግባት፣ የስራ ማቆም አድማውን የመቱት የወደብና የባቡር ሠራተኞች “አሳፋሪ አይጦች ናቸው” በማለት በስድብ አጥረገረጋቸው፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ ግን እንደሚኒስትሩ አልተሳደቡም፣ የደህንነትና ልዩ የፖሊስ ኮማንዶዎቻቸውን በመላክ አድማውን ሰጥ አደረጉት፡፡

ተመሳሳይ አድማና አመፅ እንዳይነሳም ይግባኝ የማይባልበት ፍርድ የሚሰጥ ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ዳኞችንም ራሳቸው መርጠው ሾሙ፡፡ ይህ እርምጃ ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ እንዳይከሰት በሚገባ ረድቷቸዋል፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ማጥ ውስጥ ለመግባት እየተንሸራተተች የነበረችውን ጋናን ለመታደግ ግን ምንም አይነት አቅም አልነበረውም፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ በመላው አፍሪካ ብቸኛው አንፀባራቂ ኮከብ መሪ ለመሆን የወጠኑት ውጥን በእግሩ ቆሞ መሄድ እንዳቃተው በግልፅ ታየ፡፡ የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥትን በማቋቋም፣ በፕሬዚደንትነት ለመምራት የነደፉትን እቅድ፣ ተግባራዊ ለማድረግ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሽንጣቸውን ገትረው ቢወተውቱም እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው የአፍሪካ መሪ ማግኘት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ህልምና እቅዳቸው እንደጉም በኖ በመጥፋቱ ስሜታቸው ክፉኛ የተጐዳው ፕሬዚደንት ንክሩማህ፤ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በተለይ ደግሞ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የፊት ለፊት ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡ የእነዚህን ሀገራት መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ “የፈረንሳይ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አሻንጉሊቶች” እያሉ መዝለፍና በነገር መወረፍ ስራዬ ብለው ተያያዙት፡፡ ከሁሉም ሀገራት ይልቅ ግን ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ጐረቤቶቻቸው ከሆኑት ከቶጐ፣ ከኮትዲቭዋር፣ ከናይጄሪያ፣ ከቡርኪናፋሶና ከኒጀር ጋር አይንና ናጫ ሆኑ፡፡ ንክሩማህ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የጀመሩት በነገር መናቆር ብቻውን አላጠገባቸውም፡፡

እናም የእነዚህን ሀገራት መሪዎች ከስልጣን በማስወገድ በሌላ አሻንጉሊት መሪ ለመተካት በመወሰን፣ ተቃዋሚ ቡድኖችን ማደራጀት፣ ማሰልጠንና ማስታጠቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስልጡን ነፍሰ ገዳዮችን በማሰማራት መሪዎችን ለማስገደል የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ቀጠሉ፡፡ የቶጐውን ፕሬዚደንት ሲልቫነስ ኦሊምፒዬን ለማስገደል ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ፣ ሙከራውን ያደረጉት የጋና የደህንንት ኮማንዶዎች ማንነት እንደታወቀ፣ ሰባት የአፍሪካ ሀገራት ፕሬዚደንት ንክሩማህን በማውገዝ፣ ከጋና ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወዲያውኑ አቋረጡ፡፡ የአገራቱ እርምጃ ግን ፕሬዚደንት ንክሩማህን በሰው ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና ከጠብ አጫሪነት ድርጊታቸው ሊገታቸው አልቻለም፡፡ በፕሬዚዳንት ንክሩማህ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሰው የጋና የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ፣ በቻይናና በምስራቅ ጀርመን ባለሙያዎች የሚታገዝ በርካታ የፀረ መንግስት ሽምቅ ተዋጊዎች ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ በዘጠኝ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ፀረ መንግስት እንቅስቃሴዎችን ይመራ ነበር፡፡ በ1965 ዓ.ም በእነዚህ ካምፖች የሰለጠነ አንድ አፍሪካዊ፣ የኒጀር ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሃማኒ ዲዬሪን ለመግደል ያደረገው ሙከራ ከሽፎ በቁጥጥር ስር እንደዋለ፣ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ለደረሰባቸው መሰጠነ ሰፊ ውግዘትና ወቀሳ ኮሚክ የሆነ መልስ ሰጥተዋል፡፡ “የተባበሩት የአፍሪካ መንግስት ተቋቁሞ ቢሆን እኮ እንዲህ ያለ የግድያ ሙከራ አይካሄድም ነበር!” በ1962 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ግን ፕሬዚደንት ንክሩማህ፣ ፈጽሞ ያልገመቱት ነገር ደረሰባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን “በሰፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርም” እያሉ እንደሚተርቱት፣ በራሳቸው ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ ወዲያውኑም የህዝብ ጉባኤ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩትን ታዊያ አዳማፊዬና ሁለት ሚኒስትሮቻቸውን ለግድያ ሙከራው ዋና ተጠያቂ በማድረግ፣ ፍርድ ቤት አቀረቧቸው፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ግን ወንጀሉን ለመፈፀማቸው በቂ ማስረጃ አላገኘሁም በማለት ተከሳሾቹን በነፃ አሰናበቷቸው፡፡

በዚህ እጅግ የተበሳጩት ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ ዳኛውን በማባረር በአንድ ጀንበር ውስጥ ለመንግስቱ አደጋ ነው ያሉትን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ የመሻር መብት የሚያጐናጽፋቸውን ህግ አስረቅቀው በፓርላማ ማስፀደቅ ቻሉ፡፡ ከዚያም ራሳቸው በመረጧቸው ዳኞች፣ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አዲስ ችሎት አስችለው፣ ተከሳሾቹን በሞት ፍርድ እንዲቀጡ አስደረጉ፡፡ ከወራት በኋላ ግን ምህረት አድርጌላቸዋለሁ በማለት፣ የሞት ቅጣቱን በእድሜልክ እስራት ቀየሩላቸው፡፡ ይህ ከሆነ ከሁለት አመት በኋላ፣ በ1964 ዓ.ም እንደገና ሁለተኛው የግድያ ሙከራ በአንድ የጋና ፖሊስ ኮንስታብል አማካኝነት ተሞከረባቸው። እንግሊዝ ሀገር በሚገኘው በዝነኛው የሳንድኸርስት ወታደራዊ አካዳሚ በሰለጠኑ መኮንኖች ይመራ የነበረው የጋና የጦር ሃይል፣ በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጦር ሃይል በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ ዲሲፕሊን የነበረውና በእለት ተዕለት የመንግስት እንቅስቃሴ ውስጥ እጁን የማያስገባ የጦር ሃይል ነበር። የተንኮታኮተው የጋና ኢኮኖሚ የፈጠረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የጦር ሀይሉን እንደተቀረው የጋና ህዝብ በቁንጥጫው ቢመዘልገውም ቃሉን ጠብቆ መዝለቅ ችሏል፡፡ በ1965 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ግን ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በህይወት ዘመናቸው ሙሉ ሠርተውት የማያውቁትን ትልቅና እጅግ አደገኛ ስህተት ፈፀሙ። የጋናን መንግስታዊና የሲቪል ተቋማት እንዳሉ በፓርቲው ቁጥጥር ስር ለማድረግ የጀመሩትን እንቅስቃሴ በጦር ሃይሉ ላይም ለመፈፀም በማሰብ፣ የጦር ሀይሉን ዋና ዋና ተቋማት በፓርቲው ካድሬዎች ለማስያዝና የፓርቲውን ሰላዮችም በጦር ሀይሉ ውስጥ አስርገው ለማስገባት ተንቀሳቀሱ፡፡

ይህን ጊዜ ለወትሮው ድምፁ ተሰምቶ የማያውቀው የጋና ጦር ሃይል ከዳር እስከዳር በመንቀሳቀስ፣ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በፀባይ አሳሰበ፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ ግን የጦር ሀይሉ ማሳሰቢያ የተለሳለሰ በመሆኑ ይመስላል ንቀው አጣጣሉት፡፡ የጦር ሀይሉ ከበፊቱ ያልተለየ ማሳሰቢያ ለሁለተኛ ጊዜ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜም ፕሬዚዳንት ንክሩህማ፤ የጦር ሀይሉን ማሳሰቢያ መናቅና ማጣጣል ብቻ ሳይሆን “ለመሆኑ ለእኔ ማሳሰቢያ የምትሠጡኝ እናንተ ማን ሆናችሁ ነው!” ብለው በጦር ሀይሉ መሪዎች ላይ በቁጣ ቱግ አሉ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሀይለኛ ቁጣ ያረፈበት የጋና ጦር ሃይል፣ በዚህ ጊዜ ፕሬዚዳንቱን “እባክዎ አደብ ይግዙልን” የሚል ማሳሰቢያውን ለሶስተኛ ጊዜ ለማውጣት አልፈለገም፡፡ የደረሰበትን ቁጣ ዋጥ አድርጐ ብቻ ፀጥ አለ፡፡ ይህ ከሆነ አራት ቀን በኋላ ግን ሶስት ጀነራሎች በጋና ጦር ሀይሎች ዋና ኤታማጆር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከረፋዱ እስከ ተሲያት የደረሰ ረጅም ስብሰባ አካሂደው ተለያዩ፡፡

ከሶስቱ ጀነራሎች አንዱ “የቤተመንግስት ቅልብ ጦር” እየተባለ የሚጠራው የፕሬዚዳንቱ የክብር ዘበኛ ሬጂመንት አዛዥ የነበሩት ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ ነበሩ፡፡ የካቲት 24 ቀን 1966 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ንክሩማህ፤ የቬየትናም ጦርነትን እሸመግላለሁ ብለው ወደ ቬየትናም ዋና ከተማ ሃኖይ ለመሄድ፣ በጠዋቱ አውሮፕላን ተሳፍረው ቻይና ቤይጂንግ ከተማ ገቡ። ከፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት ጋር አንድ ትልቅ አጥር ተጋርቶ በተሰራው ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ውስጥ ባለው ቢሮአቸው ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲንጐራደዱ የነበሩት ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ ይህን እንዳረጋገጡ፣ ከማን እንደሆነ ያልታወቀ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ ስልኩን አነጋግረው ከዘጉት በኋላ፣ ከጠረጴዛቸው መሳቢያ ኡዚ ጠመንጃቸውን ይዘው ከቢሮአቸው ወጡ፡፡ ከአንድ ሰአት በኋላም የጋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ከስልጣን እንደተባረሩና አዲሱ መሪ ጀነራል ኢግናቲየስ አቺምፓንግ መሆናቸውን አወጀ፡፡ በአክራና በኩማሲ ከተሞች ህዝቡ በነቂስ ግልብጥ ብሎ በመውጣት “ንክሩማህ መሲሁ መሪያችን አይደለህም!” እያለ በደስታ ጨፈረ፡፡ እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ በጊኒ በጥገኝነት የኖሩት ንክሩማህም ሚያዚያ 27 ቀን 1972 ዓ.ም ቡካሬስት ውስጥ በህክምና ላይ እንዳሉ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡

Read 3493 times