Saturday, 15 June 2013 10:59

“ፌስቱላ” ያለ ዕድሜ ጋብቻ ያስከተለው መዘዝ!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(5 votes)

በአገራችን በየዓመቱ 9ሺ ሴቶች የፌስቱላ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ህክምና የሚያገኙት ግን 1200 ብቻ ናቸው

              “ለባል የተሰጠሁት ገና ከእናቴ ጀርባ ላይ በአንቀልባ እያለሁ ነው፡፡ ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲሄድ ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤት አስገቡኝ ለትምህርት ግጥም ሆንኩ፡፡ ጐበዝ ተማሪ ስለነበርኩ መምህራኖቼ በጣም ይወዱኝ ነበር፡፡ 3ኛ ክፍል ላይ ስደርስ ትምህርቴን አቋርጬ ትዳር እንድይዝ በቤተሰቦቼ ተገደድኩ፡፡ አሻፈረኝ ብልም የሚሰማኝ አጣሁ። በደረቁ እየላጩ በእግር ብረት እያሰሩ ትዳር አስያዙኝ፡፡ በዕድሜ እጅግ ከሚበልጠኝ ባለቤቴ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የጀመርኩት የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው፡፡ ከዛም አረገዝኩ፡፡ ስለ እርግዝና ምንም የማውቀው ነገር ባለመኖሩ ተጨነቅሁ፡፡

ልጁን ከሆዴ አውጥቼ መጣል ተመኘሁ፡፡ ግራሩን በደረቴ አድርጌ ወገቤን አርቄ ይዤ ዝም ብዬ አምጣለሁ፡፡ ልጁ ሊወጣልኝ አልቻለም፡፡ ቀኔ ደርሶ ምጤ ሲጀምረኝ የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡ ለአራት ቀንና ሌሊት ሳምጥ ቆየሁና ወለድኩ፡፡ ልጁ ከነህይወቱ ቢወጣም እኔ ግን ተበላሸሁ፡፡ አጥንቴ ተፈረከሰ፡፡ የሽንት ቆባዬ ፈነዳ። ሽንቴ ሲወርድ አልሰማውም፡፡ ሰውነቴ በሽንት ሲዘፈቅ ይታወቀኛል እንጂ ሲወርድ አላውቀውም ነበር፡፡ ግራ ቢገባኝ እናቴን ጠየኳት፡፡ እናንተ ከወለዳችሁ በኋላ ሽንታችሁን ስትሸኑ ይታወቃችኋል ወይ አልኳት፡፡ አዎ እኛ ይታወቀናል አለችኝ፡፡ ታዲያ እኔ ምን ሆኜ ነው ስላት ቆሌው ተጣልቶሽ ነው አለችኝ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ሰገራዬና ሽንቴ ተቀላቅሎ እየወረደ እስከ ፀጉሬ ድረስ ይነክረኛል፡፡

ቤቱና አካባቢው ሁሉ በመጥፎ ሽታ በመታጠኑ ሰው ሁሉ ተጠየፈኝ፡፡ እናቴ ጠፈሩን አልጋ ጀንዲዉን ቀዳ ይንጠፍጠፍ ብላ እዚያ ላይ ሰቀለችኝ፡፡ ሠገራ እንዳይመጣኝ ምግብ አልበላም፡፡ የአጓት ውሃ እየጠጣሁ ህይወቴን አቆየኋት፡፡ እናቴ በሁኔታዬ በጣም ታዝን ነበር፡፡ ድሮውንም እብድ ነበርሽ በቃ ሆጭ ብለሽ አረፍሽው ትለኛለች፡፡ ባለቤቴ በየአዋቂው ቤት ይዞኝ መዞር ጀመረ ግን ምንም መፍትሔ አላገኘሁም፡፡ የወለድኩትን ህፃን ሣየው እነቂው እነቂው ይለኛል፡፡ እንዲህ የተበላሸሁት በሱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ቤተሰቦቼም ቆሌው ተጣልቷት ማህፀኗን አፍርሶ ጣለው ይሉኛል እንጂ ምንም መፍትሔ ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ እንዲህ እያልኩ ለሃያ ስምንት አመታት ኖርኩ፡፡ ከዕድሜዬ ግማሽ የሚበልጠውን ያሣለፍኩት መኝታ ላይ ነው፡፡ እዛው አልጋዬ ላይ ሆኜ ከበኸር ልጄ ሌላ አስራ አንድ ልጆችን ወልጃለሁ። ባለቤቴ ገንዘቤን ሁሉ ባንቺ ጨረስኩ፡፡

እኔም ባንቺ ስንከራተት ደከመኝ ይለኛል። እዛው መኝታዬ ላይ ሆኜ ግንኙነት እንድናደርግ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ እንኳንስ እንደዚህ ሆኜ ፊቱንም ፍላጐት የለኝም፡፡ እናም እምቢኝ እለዋለሁ፡፡ ግን ያስገድደኛል፡፡ ሁለት ቀን ባቸንፍ አንድ ቀን እገኛለሁ፡፡ ምን ላድርግ የሰው እህል እየበላሁ ሰው ቤት ተቀምጬ እንቢ ብዬ የት እደርሳለሁ። እያስገደደ ይገናኘኛል፡፡ እንዲህ እያልኩ እዛው መኝታ ላይ ሆኜ በሙት አካሌ አስራ ሁለት ወለድኩ፡፡ ይህን ሁሉ ልጅ ወልጄ እንኳን ፈርምልኝና ላዛውር ብለው ፈቃደኛ አልሆነልኝም። የአካባቢዬ ሰዎች ዝም ብለሽ ስትወልጂበት ይተውሻል ይሉኛል። እርግዝናዬን እንጂ ምጤን አላውቀውም። እያማጥኩም አልወለድኩም፤ በቃ በዛው በተከፈተው ውልቅ እያሉ ይወጣሉ። ይህንን ሁሉ ልጅ በመውለዴ እኔ ብጐዳም በሽታው እየጠናብኝ እየተበላሸሁ ስሄድ መቼም ልጅ ልጅ ነውና ከዝንብ ይከላከሉኛል ይከውኑኛል የሚል ተስፋ አድርጌ ነው፡፡ አገር ምድሩ ተጠይፎኝ ሽንትና ሰገራዬ ዝም ብሎ እየወረደ፣ ለሃያ ስምንት ዓመታት ከኖርኩ በኋላ፣ ለበሽታዬ መድሃኒት አለ መባሉን ሰምቼ ጐንደር መጣሁ፡፡ ወደ ጐንደር ስመጣ ቤተሰቦቼ ፍቃደኞች አልነበሩም፤ የነበረው በሽታሽ ይሻልሻል። አፈራርሰው ነው የሚገድሉሽ እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር። ግን ወሰንኩ። በቃ ከሞትኩም ሐኪም አይቶኝ ልሙት አልኩና መጣሁ፡፡ መርፌና ኪኒና ጀመርኩ። ብዙም ሣይቆይ ህመሙ እየታገሰልኝ ሄደ፡፡

የወር አበባዬም ቆመ። በ2003 ዓ.ም ህክምናው ተሠራልኝና ዳንኩ፡፡ ማመን አቃተኝ፡፡ ለካ በሽታው አብሮኝ የተፈጠረ አይደለም። ለካ ይድናል ብዬ በጣም ተገረምኩ። ከሰው ተገልዬ ሰው ሣይቀርበኝ ለሃያ ስምንት አመታት የኖርኩት ሴትዮ፣ ሰው ማግኘት ከሰው መዋል ጀመርኩ፡፡ ተመስገን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡” ይህንን አሳዛኝ ታሪካቸውን ያጫወቱኝ በአማራ ክልል በጐንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኚት ፅዮን ስኳች ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ነገሥ መስፍን ናቸው። የአርባ አራት አመቷ ወ/ሮ፣ በህመምና በሥቃይ የቆዩባቸው ሃያ ስምንት አመታት በቃላት ሊገለፅ በማይችል መጠን እጅግ ከባድ እንደነበሩ ይናገራሉ። በሆስፒታሉ ከአካላዊ ሕክምና በተጨማሪ የሥነ ልቡና ሕክምና ተደርጐላቸው ዛሬ ሙሉ በሙሉ ጤናቸው ተመልሷል፡፡ የእኚህ እናት ታሪክ በአገራችን በአብዛኛው የተለመደና የብዙ ሴቶች ታሪክ የሆነ ጉዳይ ነው። በተለይ በአማራው ክልል አካባቢ የወ/ሮ ነገሥ መስፍን አይነት ታሪክ ያላቸውን ሴቶች ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ለዚህ ዋንኛ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው የሚካሄደው ሴት ልጆችን ያለ ዕድሜ መዳር ያስከተለው ተፅዕኖ ነው፡፡ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አለም አቀፍ የፌስቱላ ስልጠና ማዕከል በአለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የፌስቱላ ቀን ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም “To End obstetric Fistula” በሚል መሪ ቃል አክብሮ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በሐምሌ 2011 ዓ.ም ተመርቆ ሥራውን የጀመረው ማዕከሉ፣ እስከ አሁን ድረስ 550 ለሚደርሱ የፌስቱላ ህሙማን ህክምና ሰጥቷል፡፡

በማዕከሉ ለህክምና ከሚመጡት ህሙማን አብዛኛዎቹ የሚመጡት ከአማራው ክልል ገጠርማ አካባቢዎች ነው፡፡ ከህሙማኑ በርካታዎቹ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሲሆን የሰባት ዓመት የፌስቱላ ተጠቂ ሕፃንም በማዕከሉ በህክምና ላይ እያለች አግኝተናታል፡፡ በማዕከሉ ተኝተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙት ህሙማን ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት ህመሙ ያጋጠማቸው ያለ ዕድሜያቸው በሚፈፅሙት ወሊድ ምክንያት ሲሆን ችግሩ የመጀመሪያ ልጃቸውን በሚወልዱበት ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ የአስራ ሶስት አመት ዕድሜ ያላት ታዳጊ ለዓለም፣ ከጠለምት አድርቃይ ወረዳ ጐንደር ሆስፒታል አለም አቀፍ የፌስቱላ ስልጠና ማዕከል የመጣችው በወሊድ ሰበብ የደረሰባትን የፌስቱላ ችግር ለመታከም ነው፡፡ ታዳጊዋ ያለ ዕድሜዋ ተድራ ያለ ጊዜዋ በመውለዷ ሳቢያ የፌስቱላ ችግር ሲያጋጥማት ባሏ ጥሏት ሄዷል። በጐንደር ዙሪያ የደብረ አምባ ዳንጐሬ ወረዳ ነዋሪዋ ፍሩንስ መንጌም የዚህ ችግር ሰለባ የሆነችው በወሊድ ሣቢያ ነው፡፡ ፍሩንስ ለባል የተሰጠችበትን ወይም የታጨችበትን ዘመን አታውቀውም፡፡

በእናቴ ጀርባ ላይ በአንቀልባ ሆኜ ነው የታጨሁት ትላለች። ዕድሜዋ ትንሽ ከፍ ሲል ያጫት ሰው ወደቤቱ አስገባት፡፡ በሁለቱ ተጋቢዎች መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት የአባትና የልጅ ያህል ይራራቃል። ገና ቦርቃ ያልጠገበችው ህፃን፣ ጐጆ ወጣሽ ስትባል ትርጉሙም አልገባት፡፡ ከእናት ከአባቷ ቤት አስወጥቶ ቤቱ ያስገባት ጐልማሣም ባሏ እንደሆነ ጨርሶውንም አታውቅም፡፡ ኧረ እንደውም ባል ማለት ምን እንደሆነ የምታውቀው ነገር አልነበራትም። ጐልማሳው ባል ከቤቱ ያስገባትን ታዳጊ እንደ ልጁ ሣይሆን እንደ ሚስቱ ሊያስተዳድራት ከቤተሰቦቿ ፈቃድ አግኝቷልና ገና ያልጠነከረ ሰውነቷን ተገናኝቶ በአስራ አራት አመቷ አረገዘች፡፡ እርግዝናዋ ከአቅሟ በላይ ነበረና እጅግ ፈተና ሆነባት፡፡ ምንም አይነት የህክምና እርዳታ ለማግኘት በማትችልበት ሁኔታ ለአራት ቀንና ሌሊት አምጣ ህይወት የሌለው ልጅ ወለደች፡፡ በምጥ ያሳለፈችባቸው አራት ቀናት እጅግ ከባድ ከመሆናቸው የተነሣም ፅንሱ በማህፀኗ ላይ ጉዳት አድርሶ የሽንት ፊኛዋንና የሰገራ መውጫዋን አቀላቀላቸው፡፡

በዚህም ሽንትና ሠገራዋን መቆጣጠር ፈፅሞ ተሣናት፡፡ በሽታው ከሰው አራራቃት፡፡ በለጋ ዕድሜዋ ከቤተሰቦቿ እቅፍ ወስዶ ለዚህ ችግር የዳረጋት ባለቤቷም ተጠየፋት፡፡ በሽተኛ ምን ያደርግልኛል፤ እኔ ወደ ጤናማዋ መሄዴ ነው ብሎ ጥሎአት እብስ አለ፡፡ በዚህ የስቃይና የመከራ ጊዜዋ የደረሰባትን መገለልና ችግር ስታወራ እምባና ሣግ ያቋርጣታል፡፡ የወሬ ወሬ የሰማችው ጉዳይ ልቧን አሸፈተውና አዲስ አበባ በመከራ መጣች፡፡ እሷን የመሰሉ ህሙማን የሚታከሙበት ሆስፒታል ከአዲስ አበባ መኖሩን የነገሯት ሰዎች ሥፍራውን በአግባቡ ጠቁመዋት ኖሮ አዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል መጥታ ህክምና ጀመረች፡፡ ከህመሟ ተፈውሣ ወደ አገሯ ስትመለስ ቤተሰቦቿ ማመን ተሳናቸው፡፡ እንደ ልቧ ወዲያ ወዲህ እያለችና እየሰራች ኑሮዋን ትገፋው ጀመር፡፡

የኑሮ ውጣ ውረዱና እንግልቱ እንደ እሷ ላለ ጉዳተኛ ከባድ ነበረና ሕመሙ ድጋሚ አገረሸባት፡፡ ጐንደር ፌስቱላ ማዕከል ገብታ በድጋሚ ህክምናው ተደርጐላት አሁን ከበሽታዋ ድናለች፡፡ የተለያዩ ከባድ ጉልበትን የማይጠይቁ ሥራዎችን እየሰራች ኑሮዋን ትደጉማለች፡፡ ገነት አድማሱ፣ ታልፊያለሽ ማሙዬና አዛቡ ዋጋው እንደ እነ ወ/ሮ ነገሥ መስፍንና እንደ ፍርኑስ መንጌ ሁሉ በወሊድ ምክንያት የፌስቱላ ችግር ያጋጠማቸውና በማዕከሉ ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ህሙማን ናቸው፡፡ በ13 ዓመት ዕድሜዋ ተደፍራ በማርገዟ ሣቢያ ቤተሰቦቿ ከቤት አባረዋት ያለ ማንም እገዛና ድጋፍ ለብቻዋ በጫካ ውስጥ ከአምስት አሰቃቂ የምጥ ቀናት በኋላ ህይወት የሌለው ልጅ ተገላግላ የፌስቱላ ችግር ያጋጠማት ሴት ተመሳሳይ ታሪክም የፌስቱላ ችግር አሰቃቂው እውነታ ነው፡፡ በ60 ዓመት ዕድሜያቸው ለፌስቱላ ችግር የተጋለጡት የሞጣ ወረዳም ወ/ሮ የተመኝ መርሻም የፌስቱላ ችግር ዕድሜን የማይለይና በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር መሆኑን አመላካች ናቸው፡፡ ለኪንታሮት ህመም መድሃኒት ነው በሚል የባህል አዋቂ ነኝ ካለ ግለሰብ በሲሪንጅ የተወጉትና ምንነቱን የማያውቁት ነገር ወ/ሮ የተመኝን ለፌስቱላ ችግር ዳርጐአቸዋል፡፡

ዕድሜና ችግር ያደከመው ሰውነታቸው፣ በሽታውን ለመቋቋም አቅም ነስቷቸዋል፡፡ በማዕከሉ ህክምና ለማግኘት ከመጡ ሰነባብተዋል፡፡ ማዕከሉ እንደዚህ ላሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ የፌስቱላ ተጠቂዎች ከሚሰጠው ህክምና በተጨማሪ የምርምርና የስልጠና ማዕከል በመሆንም ያገለግላል፡፡ ፌስቱላ ሁለት በተፈጥሮአቸው ውስጣቸው ክፍት የሆኑ የሰውነታችን ክፍሎችን የሚለያየው አካል በጉዳት ሲበሣና ሁለቱን ክፍተቶች ሲያቀላቅል የሚከሰት የጤና ችግር ነው፡፡ በሽንት ፊኛና በሰገራ መውጫ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች በሚደርስ ጉዳት ሣቢያ ሁለቱን የሰውነት ክፍሎች የሚለያየው ስስ አካል ሲበሣ ወይም ሲቀደድ የፌስቱላ ችግር ተፈጠረ ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት ጉዳቱ የደረሰባት ሴት ሽንቷንም ሆነ ሠገራዋን ለመቆጣጠር ሣትችል ትቀርና ለከፋ የአካልና የሥነ ልቡና ጉዳት ትዳረጋለች፡፡ ችግሩ በወቅቱ ህክምና ካላገኘ ጉዳት የደረሰበት የሰውነት ክፍል ኢንፌክሽን ይፈጥርና ህመምተኛዋ መዳን ለማይችል ጉዳት ወይንም ለሞት ልትዳረግ ትችላለች፡፡ የፌስቱላ ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በሴቶች ላይ ሲሆን እጅግ ጥቂት የሚባሉ ወንዶች በሠገራ መውጫቸው ላይ በሚደርስ ጉዳት ሣቢያ ለፌስቱላ ችግር የሚዳረጉበት አጋጣሚ አለ፡፡

የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስቷ ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል እንደሚናገሩት፤ ፌስቱላ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም በአገራችን በብዛት የሚታየውና የብዙ ሴቶች ችግር የሆነው በወሊድ ምክንያት የሚከሰተው የፌስቱላ አይነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያለ ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት በማድረግ፣ በቀዶ ህክምና ወቅት በፊኛ ላይ ጉዳት ሲደርስና በተፈጥሮ ማህፀን ዝግ ሲሆን የፌስቱላ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ምክንያት የሚከሰተው የፌስቱላ ችግር “ዩሮ ጄኔታል ፌስቱላ” በአብዛኛው ዕድሜያቸው ለወሊድ ብቁ ባልሆኑ ሴቶችና ማህፀናቸው ጠባባ በሆኑ ሴቶች ላይ የሚከሰት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በምጥ ወቅት የፅንሱ አቀማመጥና አመጣጥ የተዛባ ከሆነና ልጁ ትልቅ ሲሆን በእናቲቱ ማህፀን ላይ የመተርተር ችግር ከመፍጠሩም በላይ በፊንጢጣ ላይ ጉዳት በማድረስ ለፌስቱላ ችግር ያጋልጣል፡፡ የአንዲት ሴት ምጥ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እናቲቱ ፅንሱን መገላገል ካልቻለች ልጁ ማህፀኗን ይጫነዋል፡፡

ይህም በፊኛዋና በሠገራ መውጫዋ ላይ ጫና በመፍጠር በቀላሉ እንዲጐዳና የደም ዝውውሩ እንዲቋረጥ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ወቅት ተጐጂዋ እርዳታ ካላገኘች በሽንት ፊኛዋና በፊንጢጣዋ አካባቢ ያሉት ህዋሳቶቿ ይበሰብሱና ቀዳዳ ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ ጊዜም ተጐጂዋ ሽንቷንም ሆነ ሠገራዋን መቆጣጠር ይሣናታል፡፡ ችግሩ መጥፎ ጠረንን የሚፈጥር በመሆኑ ታማሚዋ ከሰው ትገለላለች፡፡ ይህ ደግሞ በሥነ ልቦና ላይ ችግር በመፍጠር ተጐጂዋን ለከፋ ጉዳት እንደሚያጋልጣት ዶክተር አምባዬ ይናገራሉ፡፡ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ኃላፊ፣ የአለም አቀፍ ፌስቱላ ማሰልጠኛ ማዕከል የፕሮጀክት አስተባባሪና የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙላት አደፍርስ እንደሚገልፁት፤ በማዕከሉ በሙያው በሰለጠኑ ሐኪሞች በሚደረገው ህክምና 90 በመቶ የሚሆኑት የችግሩ ተጠቂዎች ከበሽታቸዉ ይድናሉ፡፡ ህክምናው ለችግሩ መፍትሔ ለማስገኘት ያስችላል፤ ሆኖም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት መኖር፣ የወር አበባ አለማየትና፣ መውለድ አለመቻል ህሙማኑን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ወደ ማዕከሉ ለህክምና የሚመጡ አብዛኛዎቹ ሴቶች በቤተሰቦቻቸው የተገለሉ በመሆናቸው ህክምናቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ማድረጉ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህ ሴቶች ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትና ራስን ማስቻል ማዕከሉ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ማዕከሉ የተቋቋመው የፌስቱላ ችግር በስፋት በሚታይበት በአማራው ክልል አካባቢ መሆኑ የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሴቶች ህክምናውን በአፋጣኝ ለማግኘት እንዲችሉ ዶ/ር ሙላት ይናገራሉ፡፡ በጐንደር ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ያሉት ጤና ጣቢያዎች የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሴቶችን ወደ ማዕከሉ በመላክ የህክም እርዳታ ለማግኘት እንዲችሉ እንደሚያደርጉም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ጤና ጣቢያዎች መካከል በማክሰኚት ወረዳ የሚገኘው የጤና ጣቢያ በበዓሉ ተሣታፊዎች ተጐብኝቷል፡፡ በዚሁ ወቅም UNFPA Ethiopia የተባለው ድርጅት የልብስ ማጠቢያ ማሽን ለማዕከሉ በእርዳታ አበርክቷል፡፡ ማዕከሉ ለህሙማኑ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ይሰራል፡፡

ሙያተኞችን ማሰልጠንና ማብቃትም በማዕከሉ ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ሴቶች በወሊድ ወቅት ለሚያጋጥም የፌስቱላ ችግር የሚጋለጡ ሲሆን በየዓመቱም 100ሺ የሚደርሱ ሴቶች የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በአገራችን በየአመቱ ዘጠኝ ሺህ ሴቶች የፌስቱላ ችግር የሚያጋጥማቸው ሲሆን ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ለችግራቸው መፍትሔ ያገኙት ግን 1200 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍና መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት ህብረተሰቡን ማስተማርና ያለ ዕድሜ የሚደረግ ጋብቻን ማስቀረት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር መሆን እንዳለበት የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ያለ ዕድሜ ጋብቻ መዘዙ እጅግ የከፋ ነውና፡፡

Read 5317 times