Saturday, 15 June 2013 11:40

‹የፍቅር› አልባሳት በካሬቢያን የፋሽን ሳምንት ተደነቀ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ2013 የካሬብያን የፋሽን ሳምንት በኢትዮጵያዊቷ ዲዛይነር ፍቅርተ አዲስ የቀረቡ ዘመናዊ ፋሽን ያላቸው የአገር ባህል አልባሳት ተደነቁ፡፡ ዲዛይነር ፍቅርተ ባህሏን መሰረት አድርጋ እጅግ ውብና በየትኛውም ወቅት ሊለበሱ የሚችሉ አልባሳትን የፋሽን ዲዛይኖችን በማቅረብ ዘመን የማይሽራት ሴት መሆኗን አስመስክራለች በሚል “ዘ ጃማይካ ኦብዘርቨር” አድንቋታል፡፡ መቶ በመቶ በኢትዮጵያ በበቀለ ጥጥና ፈትል የተሰሩት የፍቅርተ የአገር ባህል አልባሳት በፋሽን ሳምንቱ ልዩ ትኩረት እንዳገኙም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡ የፍቅርተ አዲስ የፋሽን ዲዛይኖች በካሬቢያን የፋሽን ሳምንት የአፍሪካ አልባሳት ላገኙት ተቀባይነት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የገለፀው ደግሞ ሌላው የጃማይካ ጋዜጣ “ዘግሊነር” ነው፡፡ የፋሽን ሳምንቱ ባለፈው ሳምንት በጃማይካዋ ከተማ ኪንግስተን የተካሄደ ሲሆን ከመላው ካረቤያን፤ ከመካከለኛው አሜሪካ፤ከሰሜን አሜሪካ፤ ከዚምባቡዌ እና ከኢትዮጵያ የተወከሉ ታዋቂ ዲዛይነሮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

ከዲዛይነሯ ፍቅርተ አዲስ ጋር ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ማፊም አልባሳቷን እንዳቀረበች ያመለከቱት ዘገባዎቹ አልባሳቶቻቸው በቆንጆዋ ሱፕር ሞዴል ዮርዳኖስ ማራኪ አቀራረብ ታዳሚውን እንደማረኩ ገልፀዋል፡፡ በ2009 እኤአ ከላይ ‹የፍቅር› በሚል መጠርያ የራሷን የፋሽን ብራንድ የመሰረተችው ወጣቷ ዲዛይነር ፍቅርተ ላለፉት ሶስት አመታት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሃብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ዊክ ከመሳተፏም በላይ አምና እና ካችአምና በኒውዮርክ ከተማ በተደረገው አፍሪካ ፋሽን ዊክም የፋሽን ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ ፍቅርተ የፋሽን ዲዛይን ፍላጎት ያደረባት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ ሲሆን ሙያው ለፈጠራ በሚሰጠው ነፃነት ሁልጊዜም ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች፡፡

ኢትዮጵያዊ ባህልን መሰረት በማድረግ የፋሽን ውጤቶቿን በዓለም የፋሽን መድረክ ተወዳዳሪ የማድረግ አላማ እንዳላት በኦፊሴላዊ ድረገጿ አስታውቃለች፡፡ ‹የፍቅር› በመባል የሚታወቁት የፍቅርተ የልብስ ፋሽኖች በማንኛውም ወቅት መለበስ የሚችሉ፤ ዘመናዊነት እና ባህላዊነትን ያጣመሩ እና ተፈጥሯዊ መስህብ እንዳላቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡ በዴቨሎፕመንት ሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ ያላት ፍቅርተ፣ የህፃናት ስነልቦና አማካሪ ሆና ብትሰራም አሁን የፋሽን ዲዛይን ሙያ የሙሉ ጊዜ ስራዋ ሆኗል፡፡

Read 2435 times